Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበኮሮና ቫይረስ ለዕልቂት ከመዳረጋችን በፊት ስለበሽታው ያለንን የተዛባ አመለካከት ማስተካከል ግድ ይለናል!

በኮሮና ቫይረስ ለዕልቂት ከመዳረጋችን በፊት ስለበሽታው ያለንን የተዛባ አመለካከት ማስተካከል ግድ ይለናል!

ቀን:

በሀብታሙ ግርማ 

የኮሮና ቫረስ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለ አሥር ቀናት አለፉ፡፡ በእነዚህ ቀናት በሥራ ምክንያት በተዘዋወርኩባቸው ድሬዳዋ፣ ሐረርና ጅግጅጋ ከተሞች ሕዝቡ ስለበሽታው ያለውን አመለካከት ለመታዘብ ዕድሉ ነበረኝ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ የሚለው በሽታውን ከጸሎት በቀር ምድራዊ በሆነ ነገር መጠንቀቅ አይቻልም ነው፣ ስለሆነም የፈጣሪ ቁጣ ነው፡፡  ለአንዳንዶቹ ደግሞ ከበሽታው ማምለጥ የማይቻልበት ምክንያት አብዛኛው ሕዝብ የቀን ገቢ ያለው በመሆኑ፣ ኢኮኖሚያችን አንድ ቀን እንኳ ቤት እንድንውል አይፈቅድም የሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያ የአምላክ የቃል ኪዳን አገር ስለሆነች በሽታው እኛን አይመለከተንም የሚሉም በርካታ ናቸው፡፡

በእኔ እምነት ሁሉም ፍጥረት ሰውም ሆነ እንስሳ፣ ኢትዮጵያዊም ሆነ የሌላው አገር ዜጋ ሁሉ የፈጣሪ ልጆች ናቸው፡፡ ፈጣሪ በሽታን ለአንድ ሕዝብ ሰጥቶ ለሌላው አይከለክልም፡፡ በእስልምናም ሆነ በክርስትና እምነት አስተምህሮዎች መሠረት የሰው ልጅ በሕገ ልቡናው (Free Will) ይኖር ዘንድ ይገደዳል፡፡ ሰው ሁሉ በህሊናውና በአዕምሮው ተመርቶ ክፉና ደጉን እንዲለይ፣ የሕይወት ምርጫውንም ኃላፊነት ወስዶ እንዲንቀሳቀስ ሃይማኖቶች ያስተምራሉ፡፡ በመሆኑም ነፍስ ያወቀ ሰው ሁሉ የዕለት ተግባራቱን የሚያከናውነው በምርጫው እንደ መሆኑ፣ ድርጊቶቹ ለሚያመጡት ውጤቶችም ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ በሽታውን የፈጣሪ ቁጣ አድርጎ በተስፋ መቁረጥ እጅ አጣጥፎ መጠበቁ አግባብ አይደለም፡፡ ስለሆነም ወደ ፈጣሪ እጅን መዘርጋቱ መሠረታዊ መሆኑ ሳይዘነጋ፣ ነገር ግን አዕምሯችንን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ሁላችንም እንደ እምነታችን ጸሎት ማድረጉ ወሳኝ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ቸል ብሎ ጸሎት ማድረጉ፣ አንዱን ይዞ አንዱን ጥሎ ዓይነት ነው፡፡ ከሕዝቡ ከሚነሱ ጉዳዮች አንዱ የሆነው ደካማ ኢኮኖሚያችን ለቫይረሱ ሥርጭት የራሱ አስተዋጽኦ ሊኖረው የሚችልበት ዕድል ሰፊ የመሆኑን ጉዳይ እኔም የምቀበለው ነው፡፡ ቀደም ብሎ እንደ ተጠቀሰው ኢትዮጵያዊያን እንደ ቤተሰብም ሆነ እንደ አገር የዕለት ኑሮ ነው ያለን። ሥራችንን ትተን ቤት መቀመጥ አይቻልም። አገሪቱ ያላት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ15 ቀናት እንኳ አይበቃም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከዕለት ጉርስ ያለፈ ለክፉ ቀን የሚመነዝረው ተቀማጭ ገንዘብ የለውም፡፡ በመሆኑም ከሥራው ተስተጓጉሎ ቤቱ ተቀምጦ ሊውል አይችልም፡፡ አለበለዚያ ከኮሮና ቫይረስ በላይ በረሃብ ማለቅ ነው የሚሆነው፡፡

ነገር ግን አያድርስና በሽታው ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ሰው ቤቱ እንዲቆይ ሊገደድ የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ በዚህ ወቅት ኢኮኖሚ የሚባል ነገር ጉዳይ አይሆንም፡፡ በዚህ አስከፊ ወቅት አስታማሚ ቀርቶ ቀባሪም እንደማይኖር ከሰሞኑ የጣሊያን ተሞክሮ መማር ይገባል፡፡ ጣሊያን በዓለም ምርጥ የኅብረተሰብ የጤና ሥርዓት ከዘረጉ አገሮች ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡ አገሪቱ ለዜጎቿ ተደራሽ ባደረገችው አስተማማኝ የሥርዓተ ምግብ ዝግጅቷ ትታወቃለች፡፡ ታዲያ ኮሮና እንዴት ይህችን አገር እንዲያ በጥቂት ሳምንታት ሊያፍረከርካት ቻለ? የዚህ መልሱ ለኢትዮጵያዊያን የማስጠንቀቂያ ደውል ነው።

ከተለያዩ የሚዲያ ምንጮች እንደ ተረዳሁት ኮሮና ቫይረስ በጣሊያን ከባድ ዕልቂት ያስከተለው ሕዝቡ ስለበሽታው የተዛባ አመለካከት ስለነበረው ነው። ዛሬ በሽታው ከአገሪቱ ቁጥጥር ውጭ ሊሆን የቻለው በሕዝቡ ቸልተኝነት እንደሆነ በጣሊያን የሚኖር የቅርብ ጓደኛዬም ነግሮኛል፡፡ በጣሊያን ኮሮና ቫይረስ ከገባ ወራት ቢቆጠርም ሕዝቡ የተለመደ ዓይነት የኑሮ ዘይቤን ተከትሎ በመቆየቱ በሽታው ሥር ሰዶ ቆይቷል። በሽታው በባህሪው ለ14 ቀናት ራሱን ደብቆ ስለሚያቆይና በምርመራም ቶሎ ስለማይታወቅ፣ ዛሬ ጣሊያንን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የታየ የሞት መዓት አውርዶባታል፡፡ አገሪቱ የተዳከመውን ኢኮኖሚዋ በበሽታው እንዳይጎዳ በማሰብ በሽታው አስከፊ ደረጃ ሳይደርስ ለመቆጣጠር አልቻለችም፡፡

የአገሪቱ ዜጎችም ኢኮኖሚ ጫና ስላለባቸው የተለመደ ሥራቸውን ማከናወናቸውን አላቆሙም፡፡ በእርግጥ በእኛው አገርም እንዲሁ ከሥራ ቀርቶ ቤት መዋል ጫናው ከባድ እንደሆነ እኔም የምኖረው በመሆኑ አይጠፋኝም፡፡ ነገር ግን በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት እንደ መኖራችን የኑሮ ዘይቤያችንን ማስተካከል አለብን፡፡ ይህን ማድረጋችን መጠነኛ የኢኮኖሚ ጫና ሊያሳድርብን ቢችልም ሙሉ ለሙሉ ከሥራችን አያስተጋጉለንም፡፡ አብዛኛው እንዲያውም ጥንቃቄ ከማድረግ ጋር እንጂ ከኢኮኖሚ ጋር አይያያዝም፡፡ በሽታው አስከፊ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ የኑሯችን መርህ መቃኘት ያለበት በሦስቱ የ‹‹መ››ጎች ማለትም መጸለይ፣ መታጠብ፣ መራራቅ መሆን አለበት፡፡

ኢትዮጵያዊን ይህንን ማድረጋችን ምንም ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌላ ወጪ የለውም፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭት ለመግታት ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀው ማስተዋልና ጥንቃቄ ብቻ ነው!

ከአዘጋጁ-፡ ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፊ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...