እነሆ መንገድ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። በላብህ ወዝ ትበላለህ ሆኖ በለቅሶ የተቀላቀልናት ዓለም ላይ የኑሮ ትግሉን ተያይዘነዋል። የሕይወትን ትርጉም፣ የመኖርን ጣዕም አጣርተን ሳናውቅ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ነገን እንጓጓለን። መነሻውን ባልደረስንበት የጉጉት ሰቀቀን ጎዳናው ላይ ወዲያ ወዲህ እንመላለሳለን። ግራ የገባው፣ በከፊል የገባው የመሰለው፣ ምንም ያልገባው፣ የሚሄድበትን የማያውቀው፣ እግሩ እንደመራው የሚራመደው፣ መድረሻውን የወሰነው፣ እንኳን መድረሻ መነሻ የሌለው፣ ከዚያም ከዚህም እየተግተለተለ ይተራመሳል። ድሎት የናፈቀው የወገናችን ኑሮ ዛሬ ደግሞ ከአደገኛ ቫይረስ ጋር ትንቅንቅ ገጥሟል። የትናንቱ አሰልቺ እንግልት ዛሬም በደከመ ጉልበት ሊደገም ጎህ ቀዷል። ለአንዳንዱ ደግሞ ገና ሳይነጋ መሽቶበታል። አስቀድሞ የክስረት ሒሳቡን ላወራረደ የሰማይ ዓይን መግለጥና የምድር ዓይን መክደን ትርጉም አይኖራቸውም። ብቻ ጎዳናው የተሸናፊውም የአሸናፊውም መድረክ ስለሆነ፣ ይኼኛው ከዚያኛው እኩል ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ታክሲ ይጠብቃሉ። ርቀት ጠብቁ ቢባልም ሰሚ ያለ አይመስልም፡፡ ወይ አበሳችን!
አሁንም አሁንም አፍንጫውን የሚጎረጉረው ከሲታ ወያላ በታክሲዋ ዙሪያ እየተሽከረከረ ይቁነጠነጣል። አስቀድሞ እርሱ ራሱ በከፋፈታቸው መስኮቶች በኩል አንገቱን ያስገባና ተሳፈሪዎችን ይለክፋል። ‹‹እሺ እዚህ ጋ! አንችኛዋ ትንሽ ጠጋ በይ! እዚያ ጋ! ሄይ ጩጬ ተማሪዎች! ዋ! እስክሪብቶአችሁን ቦርሳችሁ ውስጥ ክተቱ። ነግሬያለሁ ወንበር ላይ ብትጽፉ! በተለይ ፖለቲካን በተመለከተ አንድ ነገር ጻፉና እናንተን አያድርገኝ። ይኼን ጊዜ ስንት ያልሠራችሁት የቤት ሥራ አለ!›› ይላል። ደግሞ በዋናው በር በኩል ዞሮ፣ ‹‹ገና በጠዋቱ እንዳንለካከፍ ሳንቲም አዘጋጁ። አዳሜ በብላክ ማርኬት እየዘረዘርሽ አገር ማራቆት ለምደሽ፣ እኔን ሳንቲም መልስ ብትሉኝ አልሰማችሁም፤›› ይላል። ታክሲው ውስጥ 20 ሰዎች ታጭቀው እሱም ሆነ እነሱ ምንም ሳይመስላቸው፣ ‹‹ዛሬ ቁርስ የበላኸው የፍየል ምላስ ነው እንዴ ፍሬንድ? ይልቅ ሞልቷል ሳበው በለው፤›› ይላል አንድ የቸኮለ ወጣት ተሳፋሪ፡፡ ይኼኔ ታክሲያችን መንቀሳቀስ ትጀምራለች። እኛም ምንም ሳይሰማን ጉዞ ጀምረናል፡፡ ጉዞ ከተባለ ለማለት ነው!
ደላላ፣ ነጋዴ፣ ሸማች፣ አሠሪ፣ ሥራ ፈላጊ፣ ወዘተ. በታክሲያችን ጣሪያ ሥር ታጭቀን ጉዞ ጀምረናል። መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየመች ወጣት፣ ‹‹ይኼ የፖለቲካ ፓርቲ ከመደገፍ ወይም ከመቃወም ጋር የተያያዘ አይደለም፤›› ስትል ፈዘዝ ብለን የነበርነው ተነቃቃን። ሁላችንም እርስ በርስ ተያይተን ወደ ልጅቷ አፈጠጥን። ልጅት ቀጥላለች፣ ‹‹ነገር ግን መስዋዕትነት ተከፍሎበታል የተባለውን ዴሞክራሲና ነፃነት እንዳሻቸው ሲፈነጩበት ማየት ከምንም በላይ ስለሚያም ነው። አሁንም ድሮም ሆነ ወደፊት ሥልጣንን ተገን በማድረግ የሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ጥቃቶችን በፅኑ እቃወማለሁ፤›› ብላ ስታበቃ እጇን ወደ ላይ ማንሳት ነበር የቀራት። ጨዋታዋ አብሯት ከተቀመጠ ጎልማሳ ጋር ኖሯል። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ተሳፋሪዎች በበኩላቸው፣ ‹ባላሰብነውና ባልጠበቅነው ሰላማዊ ሠልፍ ስንሳተፍ ሌላው ቢቀር ይህ ኮሮና ቫይረስ ሳይታዘበን ይቀራል ትላላችሁ? ኧረ አንድ በሏት. . .› ይባባላሉ። ‹‹ሰው ያለ ከልካይ የበላ የጠጣውን የሚለጥፍበት የፌስቡክ ግድግዳው አልበቃ ብሎት፣ ደግሞ ጎዳናውን በብሶት ‘ፖስት’ ካላተራመስኩት ይላል። መተሳሰብ እኮ ትተናል፤›› ስትል አንዲት ወይዘሮ የእንኑርበት መልዕክቷን ታስተላልፋለች። ያለንበት ሁኔታ ያሳሰባት አትመስልም!
ወያላው በበኩሉ፣ ‹‹ሰው ለበላው ቁርስ አያዝንም? ምናለበት ምሳ ሰዓት ሳይደርስ በነገር እየተነቋቆረ ለረሃብ ባይቸኩል?›› እያለ በማያገባው ሲገባ ሾፌሩ፣ ‹‹ስለሰው ስለሰው ቀድጄ ልልበሰው ብላለች ዘፋኟ። ይልቅ ወሬውን ትተህ ‘ስፖክዮውን’ አስተካክለው አይታየኝም፤ ‹‹ብሎ ኩም ያደርገዋል። ከወገቡ በላይ በመስኮት ሾልኮ ሲወጣ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ሁለት መምህራን ተሳፋሪዎች ስለቫይረሱ ያወራሉ። አላደርስ ብሎን ዜና ስንት አዳዲስ ሰዎች ተያዙ የሚለውን ለመስማት ጆሯችንን ወደ እነሱ ቀና ስናደርግ፣ ‹ኑሯችን ትላለህ ፖለቲካው፣ ትዝብታችን፣ ሐዘናችን ሳይቀር የቫይረሱ ወሬ ሸፍኖታል። ችግሮቻችን ሁሉ እንዳሉ ሆነው አሁን ደግሞ ይህ ሰይጣን ነገር ተከሰተ ሲባል ተስፋ ያስቆርጣል…› ሲባባሉ ስንሰማ ግን፣ የባከነ ሰዓት ላይ መድረሳችን ታወቀን። በስንቱ እንደ ምንባክን አልገባን አለ እኮ!
ወያላው ሒሳብ መሰብሰብ ጀምሯል። ጋቢና የተሰየሙትን ሴቶች ሾፌሩ እንዳትቀበል ስላለው ወያላው ተነጫንጯል። ‹‹በቃ አጠገቡ ሴት ከተቀመጠች እኮ በነፃ ‘አላስካ’ ደርሶ ይመለሳል! ምን አገባኝ እኔ?›› እያለ ለራሱ እያጉተመተመ መጨረሻ ወንበር ተደራርበው ወደ ተቀመጡት ታዳጊዎች ሲደርስ “ሒሳብ!” ብሎ ጮኸባቸው። ነገረ ሥራቸው ሁሉ ፈገግ የሚያሰኝ እነዚያ ታዳጊዎች የሞባይል ስልካቸውን እየጎረጎሩ ቀና ብለው እንኳ ሳያዩት ዝም አሉት። “ምድረ ጩጬ አትከፍሉም?” ወያላው ደገመላቸው። “ቆይ አንዴ! ‘ሪከርድ’ ልሰብር ስለሆነ ነው እሰጥሃለሁ፤›› ብሎ አንደኛው መለሰ። ወይዘሮዋ አፏን ሸፍና ሳቀች። አጠገቧ የተሰየመች ቀዘባ ደግሞ ፈገግ ብላ፣ ‹‹አይ ኢትዮጵያ አገሬ! በዱር በገደሉ ለነፃነትሽ የተዋደቁ አርበኞች ልጆችሽን ባየሽበት ዓይን፣ ዛሬ ‘የጌም’ አርበኞች ሲተኳቸው ስታይ ምን ትይ ይሆን?›› ብላ ወደ ሰማይ ቀና አለች። ሰማዩ ምን እንዳላት እንጃ!
መሀል መቀመጫ ያለ ጎልማሳ ዘወር ብሎ፣ ‹‹እነሱ ምን ያውቃሉ? እኛ ነን የጠቀምናቸው እየመሰለን በዚህ ዕድሜያቸው ሞባይል ገዝተን የምንሰጥ። ወላጆች ነን ልጆቻችንን እያበላሸናቸው ያለነው፤›› ብሎ ተነፈሰ። አኳኋናቸው ሁሉ ፈገግታን የሚያጭረው ታደጊ ተማሪዎችን ወይዘሮዋ ጎንበስ ብላ አለሳልሳ ጥያቄ መጠየቅ ጀመረች። “ማነው ስምህ?” ይነግራታል። “አንተስ?” ያም ይመልሳል። “ወንድማማቾች ናችሁ?” ስትላቸው፣ “መንታዎች ነን፤” ሁለቱም ተመሳሳይና እኩል ናቸው፡፡ “ስንተኛ ክፍል ናችሁ?” “አምስት!” ይመልሳሉ። ‹‹ወደፊት ስታድጉ ምን መሆን ነው የምትፈልጉት?›› ከማለቷ ሁለቱም ከሞባይል ስልኮቻቸው ዓይኖቻቸውን ነቀሉና “ባለሥልጣን!” አሉዋት። ለምን እንደምትስቅ አንዳንዴ እሷ ራሷ የገባት የማትመስለው ወይዘሮ፣ ይኼንን ስትሰማ ከጣራ በላይ ተንከትክታ “ሌላስ?” ብትላቸው “ጋንግስተር!” ብለዋት አረፉት። የባሰ አታምጣ ማለት አሁን ነው!
ጉዟችን ቀጥሏል። ታዳጊዎቹ ወንድማማቾች ሒሳባቸውን ከፍለው ወርደው ሲጓዙ በሩቁ ላያቸው ልዩ ስሜት ውስጥ ይከታሉ፡፡ ወልዶ ያልሳመን ያስተክዛሉ። ወያላው በእነሱ ምትክ ሌላ ሰው ያሳፍራል። አዲሱ ተሳፋሪ፣ ‹‹ስማ ገና እኮ አልተቀመጥኩም እኮ፡፡ ችግሩ ምንድነው ስል አይ አንተ ከሄድክ ስለማትመለስ ‘ኬዝህን’ አላመነበትም አትለኝም አስተርጓሚዋ። ኧረ ትንሽም ቢሆን ድርጅት አለኝ ይኼው የባንክ ወጪና ገቢዬ ብል ማን ይስማኝ? ለነገሩ እነሱ ምን አለባቸው ለኮቴ የሚቀበሉት ብቻ እኮ በዓመት የትናየት ሚሊዮን ብር መሰለህ? በትንሹ በአምስት ሺሕ ብር በቀን 100 ሰው ይገባል ብለህ አስላውማ! ማን መፅዋች ማን ተመፅዋች እንደሆነ እኮ ነው ግራ የሚገባህ። ግድ የለም ቆይ!›› እያለ በብስጭት በሞባይል ስልኩ ያወራል። “የአሜሪካ ‘ቪዛ’ ተከልክሎ እኮ ነው፤” አለኝ ይኼን ያህል ሰዓት ዝምታ ውጦት የተቀመጠ አጠገቤ የነበረ ተሳፋሪ። ተሳፋሪው ስልኩን ከመዝጋቱ ደግሞ ይባስ ብሎ ያም ያም ያፅናናው ጀመር። ‹‹በኮሮና ዘመን እሱም ቪዛ መጠየቁ ይገርማል፡፡ ይኼኔ እኮ እጁን በደንብ ሳይታጠብ ነው የሄደባቸው…›› እያለ የሚስቀው አጠገቤ የተቀመጠው ነው፡፡ ሳቅ አንተ ምን አለብህ!
“አይዞን ነገም ሌላ ቀን ነው፤” ሲል አንዷ ቆንጂት ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ይኼ ቫይረስ ሲጠፋ ተመልሰህ ሄደህ ሌላ መስኮት ላይ እንዲደርስህ አድርገህ ብትጠይቅ ይሰጡሃል። ተስፋ አለመቁረጥ ነው፡፡ ዋናው ለመሞከር አለመስነፍ ነው!›› ትለዋለች። ከወደፊት የተቀመጠ ስለቢዝነስ አብዝቶ የሚያወራ ተሳፋሪ በበኩሉ፣ ‹‹እኔም እንዳንተ ሆኜ ነበር። ምን አደረግኩ መሰለህ? አንድ የአውሮፓ አገር ‘ቪዛ’ ጠይቄ ከዚያ ላጥ አልኩና ዲሲ ገባሁ። ዋናው ተስፋ ሳትቆርጥ ወደፊት በሩን ማንኳኳት ነው። አንተ ደህና ሆነህ ጠብቅ እንጂ መሳካቱ አይቀርም፤›› ይለዋል። ሰውየው ከተከለከለው ‘ቪዛ’ ይልቅ የሚሰማቸው የማፅናኛ ቃላት ብዛት እንዳስደተው ያስታውቃል። ‹‹የእኛ ሰው ግን አሜሪካ ሲባል ምን ሆኖ ነው እንዲህ ጆሮው የሚቆመው…›› ይለኛል አጠገቤ ያለው ነገረኛ፡፡ እንጃ አባቴ!
ወደ መዳረሻችን ነን። ሾፌራችን ጋቢና ከተሰየሙት የሚያውቃቸው ሴቶች ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ መቆየቱ ወያላውን ክፉኛ አበሳጭቶታል። ጨዋታውን ለማቆርፈድ ይመስላል፣ “እባክህ ርቀተህን ጠብቅ በፈጠረህ?” ሲል ከወሬው ያደናቅፈዋል። ሾፌሩ ነገሩ ገብቶት፣ ‹‹አታስመስል እባክህ! ያረጀ ብር ያጨማለቀውን እጅህን ሳትታጠብ እየበላህበት እኔንማ አትመክረኝም፤›› ብሎ አጠገቡ ካሉት ጋር ተጠቃቅሶ ፈገግ አለ። ወያላው ሴራው እንዳልተሳካለት አውቆ ዝም ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹ምን ይሻለናል ዘንድሮ? ሰው ከመረዳዳትና ከመመካከር ይልቅ በነገር እየተወጋጋ ነው እንዴ ይህንን ክፉ ጊዜ የምናልፈው!›› ሲል ትዝብቱን ይወረውራል። ግራ ገብቶት እኮ ነው!
በጎልማሳው ትዝብት ዘና ብለን ሳንጨርስ ከየት መጣ ሳይባል ከኋላችን አንድ ‘አይሱዙ’ መጥቶ ተላትሟል። የታክሲያችን የኋላ መስታወት ሿ ብሎ መሬት ላይ ተበትኗል። ተሳፋሪዎች ‘ምን መዓት ነው?’ እየተባባሉ እርስ በርስ ይተያያሉ። ትንሽ ስንረጋጋ ተሽቀዳድመን ከታክሲያችን ወረድን። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች ማንኛቸውም አለመጎዳታቸው ቢያስደስተንም፣ የገጨንን መኪና አሽከርካሪ ጤንነትና ሕጋዊነት ለማጣራት ስንሰባሰብ ወጣቱ የአይሱዙው ሾፌር ጥምብዝ ብሎ ሰክሯል። የትራፊክ ፖሊስ ደርሶ መንጃ ፈቃድ ሲጠይቀው የቀበሌ መታወቂያ ካርዱን አውጥቶ ሰጠው። ለወሬ የተሰበሰበው መንገደኛ ይኼን ሲያይ በሳቅ ይንከተከታል። ድንጋጤው አመድ ያስመሰላት ወይዘሮ፣ ‹‹እኮ በዚህ አያያዝህ እንኳን ሰው ሆነህ ልትኖር ወግ ያለው ሞት ለመሞትም ዕድል የምታገኝ ይመስልሃል?›› ብላው እያማተበች ራቀች። “ለነገርና ለሞት ቸኩለን እንዴት ይሆናል?” ብላ ሁሉን አሳታፊ ጥያቄ የምትጠይቀው ደግሞ ቆንጂት ናት። ‹‹ሳይነጋ አይምሽባችሁ የተባለው ለካ ለእንዲህ ዓይነቶቹ ነው?›› ይላል ሌላው፡፡ በዚህ መሀል አንድ ከየት መጣ የተባለ ወፈፌ ብጤ፣ ‹‹መኪና ቢጋጭ ይሠራል፣ ሰው ቢጎዳ ነበር የሚያሳዝነው…›› ብሎ፣ ‹‹ለነገሩ አንዳንዱ እኮ ግዑዝ ነው፣ አሁን ደግሞ እያለ የሌለ የሚመስል እየበዛ ነው… በገዛ ንብረቱ ላይ እንደ ቅርጫ ዕጣ ብትጣጣሉ የማይገባው ግዑዝ እኮ ነው መንገዱን ሞልቶ በደመነፍስ የሚራመደው… እጅህን ታጠብ ሲባል ጀርባውን የሚሰጥ… የባለሙያ ምክር ስማ ሲባል ጆሮውን የሚደፍን… ርቀትህን ጠብቅ ሲባል የሚላተም… ደመነፍሳዊነት የተፀናወተው ብዙ ነው…›› እያለ ሲስቅ በዝምታ መንገዳችንን ቀጠልን፡፡ እውነቱን ነው ይህ ደመነፍስ የት ያደርሰን ይሆን! መልካም ጉዞ!