Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አዲስ ተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚ ተሰይመዋል

በኢትዮጵያ የመጀመርያ የሆነውን የጠለፋ መድን ኩባንያ በመመሥረት ሒደትና በኋላም የኩባንያው የመጀመርያ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ የወንድወሰን ኢተፋ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት አቶ ወንድወሰን ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ የተገደዱበት ምክንያት ግልጽ ባይሆንም፣ ኃላፊነታቸውን በፈቃደኝነት ለመልቀቅ ለኩባንያው ቦርድ ደብዳቤ አስገብተዋል ተብሏል፡፡

ቦርዱም የአቶ የወንድወሰን ጥያቄ በመቀበል በምትካቸው አዲስ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሾሙ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበርን በተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ የተሰየሙት ወ/ሮ መሠረት ጥላሁን ናቸው፡፡

ወ/ሮ መሠረት ይህንን ኃላፊነት እስኪረከቡ ድረስ የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ የኦፕሬሽን ዲፓርትመንት ማናጀር ሆነው እየሠሩ ቆይተዋል፡፡ ኃላፊነቱም በኩባንያው ውስጥ ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ቀጥሎ ሁለተኛ የኃላፊነት ቦታ በመሆን ይጠቀሳል፡፡ ወ/ሮ መሠረት በኢኮኖሚክስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪና በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ በማገልገል ልምድ አላቸው፡፡ ወደ ጠለፋ መድን ኩባንያው ከመቀላቀላቸው በፊት የንብ ኢንሹራንስ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡

ተሰናባቹ አቶ የወንድወሰን በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ውስጥ አገልግለዋል፡፡ በተለይ የጠለፋ መድን ኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ከመሰየማቸው በፊት የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን ለሰባት ዓመታት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት መርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን ኩባንያ የጠለፋ መድን ሥራዎችን ለመሥራት የተቋቋመ ብቸኛው ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው በአክሲዮን የተቋቋመ ሲሆን ሰባት ባንኮች፣ 17ቱም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ 78 ግለሰቦችና አንድ የሠራተኛ ማኅበር ባለአክሲዮን የሆኑበት ነው፡፡ ትልቁ የአክሲዮን ድርሻም የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው፡፡

ኩባንያው በ2011 የሒሳብ ዓመት የተከፈለ ካፒታሉ 758.8 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ይህ ኩባንያ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በውጭ ምንዛሪ ወደ ውጭ የሚላከውን ለጠለፋ መድን አገልግሎት የሚከፈለውን ወጪ ለማዳንና የጠለፋ መድን አገልግሎትን በአገር ውስጥ ለመስጠት ነው፡፡

ኩባንያው አገልግሎት ከጀመረ ሦስት ዓመታትን የተሻገረ ሲሆን፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለውጭ የጠለፋ መድን ሰጪዎች ይከፍሉ የነበረውን 60 ሚሊዮን ዶላር የካሣ ክፍያ እንዳዳነ እንዲሁም ከታክስ በፊት 144.5 ሚሊዮን ብር እንዳተረፈ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች