Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተነቃቅቶ የነበረው የአበባ ወጪ ንግድ በኮሮና ቫይረስ ጦስ እስከ 80 በመቶ ተዳክሟል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የሠራተኞች ደመወዝን ጨምሮ የብድር ማራዘሚያ እንዲሰጣቸው ላኪዎች ጠይቀዋል

የአበባ ምርት ከዋና ዋና የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በወጪ ንግድ አፈጻጸሙ በዓመት በአማካይ ከ270 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ሲያስገኝ የቆየ ዘርፍ ለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  

የ2012 ግማሽ ዓመት የዘርፉን የወጪ ንግድ አፈጻጸም የተመለከተው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በስድስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ገቢ ካስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች መካከል አበባ በሁለተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችልበትን ውጤት አሳይቶ ነበር፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳው፣ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ከተገኘው 1.33 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ውስጥ አበባ 225.26 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ድርሻውን ይዟል፡፡ ከዚህ ቀደም ከአበባ ንግድ ይህን ያህል የውጭ ምንዛሪ ገቢ ተገኝቶ እንደማይታወቅ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ቀደም በዓመት ውስጥ ያስገኝ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዘንድሮ በግማሽ ዓመት ውስጥ ያስገኘው ተቀራራቢ መሆን የቻለበት ውጤት የተመዘገበበትም ነው፡፡

የዘንድሮውን የአበባ የወጪ ንግድ ለየት የሚያደርገው በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ያስገኛል ተብሎ ከታቀደውም በላይ በማስገኘቱ ጭምር ነው፡፡ በሚኒስቴሩ መረጃ መሠረት ከአበባ የወጪ ንግድ እንደሚገኝ የታቀደው 123.13 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡

ይሁንና አፈጻጸሙ 225.26 ሚሊዮን ዶላር በመሆኑ ከቡና በመከተል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ በግማሽ ዓመቱ ከቡና ወጪ ንግድ የተገኘው 365 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ከአበባ ንግድ የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በዓመቱ መጨረሻ እንደሚገኝ ለሚጠበቀው የገቢ መጠን ትልቅ ተስፋ ሰጥቶ ነበር፡፡ የበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የወጪ ንግድ ከፍ እንደሚያደርግ ጭምር ተስፋ የተጣለበት የአበባው ዘርፍ፣ ይህንን ተስፋ የሚያጨልም ክስተት ለማስተናገድ ተገዷል፡፡

 እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የነበረው የአበባ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ እንደ ግማሽ ዓመቱ አካሄድ ሊቀጥል እንደማይችል፣ እንደውም የከፋ ችግር ውስጥ እንደሚገባ ገሃድ እየወጣ የታየው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአውሮፓ መስፋፋቱን ተከትሎ ነው፡፡ የአውሮፓ አገሮች ድንበራቸውን ተራ በተራ መዝጋት ሲጀምሩ የአበባ ገበያውም እየጠወለገ መጣ፡፡

በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የአገሪቱ የአበባ ወጪ ንግድ በከፍተኛ መጠን ቀንሷል፡፡ የኢትዮጵያ የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ እንደገለጹት፣ የአበባ የወጪ ንግድ ከ70 እስከ 80 በመቶ ቀንሷል፡፡ እስከ 30 በመቶ የሚገመተው ገበያም ቢሆን ዋጋው በእጅጉ ስለቀነሰ ከአበባ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል፡፡ ይህም ዓለምን የወረረው የኮሮና ወረርሽኝ የአበባ ገበያን ጨምሮ የዓለም እንቅስቃሴዎችን በማስቆሙ  ነው፡፡ የአውሮፓ ድንበሮች ተዘግተዋል፡፡ ሰዎች ከቤታቸው እንዳይወጡና እንዳይንቀሳቀሱ በሕግ ተከልክለዋል፡፡ በበርካታ አገሮች አስቸኳይ አዋጅ ታውጇል፡፡  

በዚህ ሳቢያም የአበባ መሸጫ መደብሮች እንደ ሌሎች የንግድና የአገልግሎት ተቋማት ሁሉ ተዘግተዋል፡፡ ይህም ሆኖ የተወሰነ አበባ ከዚህ እየተላከ በተወሰኑ ሱፐርማርኬቶች ብቻ ለገበያ እየቀረበ ይገኛል፡፡ ይሁንና መጠኑ ውስን ነው ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ከጥቂት ቀናት ወዲህ በርካታ የአውሮፓ አገሮች ድንበሮቻቸውን በመዝጋታቸው ሳቢያ እንቅስቃሴው ተዳክሟል ብለዋል፡፡ የአበባ የጨረታ ንግድ ማዕከል ከሆነችው ኔዘርላንድስ እየተነሳ ወደተለያዩ አገሮች ይሠራጭ የነበረው የአበባ ምርት እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተቋርጧል፡፡

ይህ ሁኔታ የኢትዮጵያን የአበባ ወጪ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው ይገኛል፡፡ አበባ በቶሎ የሚበላሽ በመሆኑ አከማችቶ ማቆየት አይቻልም ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ በሚሊዮን ዶላር የሚገመት የአበባ ምርት እየተጣለ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹እዚህ የሚመረተው አብዛኛው አበባ እየተጣለ ነው፡፡ ወደ ውጭ የሚወጣው ጥቂት አበባም እዚያ ደርሶ ሲጣል ይታያል፡፡ በሌላ አነጋገር ለማዳበሪያነት እየተጣለ ነው ማለት ይቻላል፤›› በማለት አቶ ቴዎድሮስ ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡

የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ እያስከተለ ያለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ ከወዲሁ እየታየ ሲሆን፣ የአበባ ምርት ላይ ጫናው ጎልቶ እየታየ መጥቷል፡፡ ከጫና በላይ የዘርፉን ህልውና እየተፈታተነ እንደመጣ እየተነገረ ነው፡፡ በአበባ አምራችነት የተሰማሩና በዘርፉ የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው አንድ ባለሀብት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ የአበባ ምርት ችግር ውስጥ የተዘፈቀበት ሌላው ትኩሳት ገበያው መበላሸቱ ሳያንስ፣ ወደፊት በገበያው ለመቆየት  ለአበባ የሚደረገው እንክብካቤ ሳይቋረጥ መካሄድ እንዳለበት የሚያስገድድ ጠባይ ያለው በመሆኑ ነው፡፡

የአበባው የውጭ ገበያ በመስተጓጎሉ፣ በየዕለቱ ለገበያ መቅረብ የሚጠበቅባቸው የደረሱ አበባዎች መቆረጥ አለባቸው፡፡ አበቦቹ ሊሸጡ ወይም ሊነሱ ባለመቻላቸው አልሚዎቹ እየቆረጡ ለመጣል ይገደዳሉ አለያም ለማዳበሪያነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ ይህ ከፍተኛ ወጪ ከመጠየቁም ባሻገር፣ የአበባ ገበያ ስለሌለ ብቻ የአበባው እርሻ ሥራ ማቆም አይችልም ያሉት እኚህ አስተያየት ሰጭ፣ ይህንን ግዴታ በኪሣራ እየተወጡ መጪውን ጊዜ መጠባበቅ ፈታኙ ችግር ሆኖ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ፡፡ እስከመቼ የበሽታው ዳፋ በዘርፉ ላይ ችግር ሆኖ እንደሚቆይ አለመታወቁም ሌላው አሳሳቢ ፈተና ነው፡፡

‹‹የአበባውን እርሻ ካቆምከው መልሰህ ለማልማት የሚጠይቀው ኢንቨስትመንት ከፍተኛ በመሆኑ፣ ያለውን አበባ ሌላ ጊዜ እንደሚደረግለት እየተንከባከብክ ማቆየቱ ግድ ይላል፡፡ ይህንን በማድረግ ለማትሸጠው አበባ መደበኛ ሥራውን እየሠራህ ትቀጥላለህ፡፡ ሠራተኞችም ይኖራሉ፡፡ ለእርሻው የሚያስፈልጉት ግብዓቶች ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ ገበያ ከማጣት በላይ ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቅ ነው፤›› በማለት የችግሩን ስፋት ይገልጹታል፡፡

የኢትዮጵያ የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበርም ዘርፉ ትልቅ ችግር ውስጥ እንደወደቀ ይጠቅሳል፡፡ ‹‹የአበባ እርሻው መልማት አለበት፡፡ አሁን የተከሰተው ሊያልፍ ይችላል፤›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ሌሎች አበባ አምራች አገሮች ቀውሱን ለመሻገር የወሰዷቸው ዕርምጃዎች እየታዩ እንደሚገኙ ይጠቅሳሉ፡፡ የኔዘርላንድስ፣ የኢኳዶርና የኬንያ መንግሥታት የወሰዱትን ዓይነት ዕርምጃ መንግሥትም እንዲያጤነው መደረጉን ይገልጻሉ፡፡ እነዚህ አገሮች ለዘርፉ ሠራተኞች ደመወዝ ለመክፈል እየተንቀሰቀሱ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያም ይህን እንድታጤነው ማኅበሩ ጠይቋል፡፡

ማኅበሩ ለመንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ አምራቾች የሦስት ወራት የሠራተኞች ደመወዝ በመንግሥት እንዲሸፈንላቸው፣ የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው፣ የሥራ ማስኬጃ እንዲለቀቅላቸው፣ ምልልሱ ያነሰም ቢሆን እንኳ  የአየር ካርጎ ጭነት አገልግሎት እንዳይቋረጥባቸው፣ የቫት ተመላሽ ሒሳብ እንዲለቀቅላቸውና የታክስ ክፍያ ለጊዜው እንዲቋረጥላቸው ከመጠየቃቸውም ባሻገር፣ የሠራተኛ ቅነሳ ለማድረግ ቢገደዱ እንኳ ከሠራተኛ አሠሪ አዋጅ የተገናኘው ሕግ ተፈጻሚ እንዳይደረግባቸው አመልክተዋል፡፡   

በኢትዮጵያ የአበባ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከ50 ሺሕ በላይ ሠራተኞች የሚተዳደሩ ሲሆን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፉ ሲታከልበት፣ ከ150 ሺሕ በላይ ሠራተኞች እንዳቀፈ ይነገራል፡፡ ይህ በመሆኑም የሠራተኛ ቅነሳ እንዳይከሰት የሚያግዙ አማራጮች ቀርበዋል፡፡ የአጭር ጊዜ ፋይናንስ አቅርቦት ተመቻችቶ ሠራተኛው ሳይቀነስ በሥራ ገበታው ላይ እንዲቆይ የሚችልበት ዕድል እንዲመቻች ማኅበሩ ጠይቋል፡፡ ማኅበሩ በብድር መክፈያ ላይ ያቀረበው የይራዘምልን ጥያቄ ከባንኮች መልካም ምላሽ እንዳስገኘለት አስታውቋል፡፡

ብድሩ የሚከፈልበት ጊዜ ሲራዘም አብሮ የወለድ ክፍያው መገታት እንዳለበት ይህ ካልሆነ ግን ኩባንያዎቹ መክፈል የማይችሉበት አደጋ እንደሚከሰትና ህልውናቸው እንደሚያከትም ማኅበሩ ሥጋቱን ገልጿል፡፡ ኢንዱስትሪው ከገባበት አጣብቂኝ ቢያንሠራራ እንኳ ያለባቸውን የባንክ ዕዳ በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ መክፍል ስለማይችሉ የብድር መክፈያ ጊዜው ላይ እፎይታ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አበክሮ ይጠይቃል፡፡ 

የሥራ ማስኬጃን በሚመለከት በቀረበው ማብራሪያ እንደተገለጸው፣ አልሚዎች ምርት ሸጠው የሚያገኙት ገቢ ስለሌ ለሥራ ማስኬጃ የሚያውሉት ገንዘብ የላቸውም፡፡ በመሆኑም ሥራው እንዳይቋረጥ ለማገዝ የሥራ ማስኬጃ እንዲያገኙ መንግሥት እንዲያመቻች ጠይቀዋል፡፡ ይህ መደረጉ ከገበያ እንዳይወጡ ጭምር የሚያግዝና ዘርፉ እንዳይጎዳ ከማሰብ አኳያ የሚደረግ ድጋፍ በመሆኑ ጥያቄው እንደቀረበ ተጠቅሷል፡፡

ማኅበሩ አፅንኦት የሰጠበት ሌላው ጉዳይ፣ በአበባ አላላክ ላይ የሚተገበረውን አሠራር ነው፡፡ አበባ ላኪዎች ምርት ሲልኩ ለአንድ ኪሎ ግራም አበባ ማስገባት የሚጠበቅባቸው ገንዘብ 3.86 ዶላር እንደሆነ የሚደግግ ሕግ ወጥቶ እስካሁን ሲሠራበት ቢቆይም፣ ከወቅቱ የአበባ ገበያ መዳከምና ከዋጋ መውደቅ አኳያ ለአንድ ኪሎ አበባ 3.86 ዶላር ገቢ ማምጣት አዳጋች እንደሆነ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ይህንን ሕግ ማስተካከል እንደሚኖርበት በመግለጽ ጥያቄ ማቅረቡን ከማኅበሩ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ችግሩ በዚሁ ተራዝሞ ከቀጠለ፣ የአበባው ዘርፍ ሌለው ፈታኝ ጉዳይ የሚያስተዳድራቸውን በርካታ ሠራተኞችን በምን አግባብ ይዞ ሊቀጥል ይችላል የሚለው ነው፡፡ ሠራተኛ ለመቀነስ የሚያስገድድ ሁኔታ ከመጣ አልሚዎቹ ለሠራተኞቻቸው በሕጉ መሠረት የሦስትና የአራት ወራት ደመወዝ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡

ይህን ማድረግ ዘርፉ ከሚያስተዳድራቸው ሠራተኞች ብዛት አኳያ የማይቻል በመሆኑ አብዛኞቹን ኩባንያዎች ከዘርፉ እንደሚያስወጣቸውና ኪሣራ እስከማወጅ ሊያደርሳቸው እንደሚችል ከወዲሁ ሥጋት ገብቷቸዋል ያለው ማኅበሩ፣ መንግሥት የዘርፉ ተዋናዮች የገቡበትን አጣብቂኝ ተመልክቶ ምላሽ እንዲሰጥ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡ የማኅበሩ ደብዳቤ ለመንግሥት ከተላከ ሳምንት ማስቆጠሩንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች