በሙሉጌታ ሞላ
የዚህ አጭር ጽሑፍ ዓላማ ስለኮሮና በሽታ ምንነት በጥቂቱ በተለይም የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት መወሰድ ስላለባቸው ነገሮች የቀረበ የግል ምልከታ ነው፡፡ ይህንን ጽሑፍ በአስተያየት መስጫው ላይ በመግባት ሐሳብ በመስጠትና ለሌላ ውይይት የሚሆኑ ነጥቦችን በመጠቆም ብናዳብረው መልካም ነው፡፡
ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምን ማለት ነው?
መንስዔያቸው የታወቀ/ያልታወቀ ከእንስሳ ወደ ሰው ብሎም ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍ በአገር/በዓለም ላይ ተሠራጭቶ በከፍተኛ ሁኔታ ሰዎችን ሊያጠቁ የሚችሉ በሽታዎችን ያጠቃልላል፡፡ እነዚህ በሽታዎች በጣም ገዳይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የበሽታው ባህሪ፣ ሥርጭት፣ መንስዔ፣ መተላለፊያ መንገዶችና መከላከያ መንገዶች በጊዜው ማወቅ አዳጋች ስለሆነ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡
ስለዚህ የበሽታውን ሥርጭት ለመቆጣጠር በየአካባቢያችን ያሉትን የጤና ክትትልና ምርመራ ሥርዓትን ማሳደግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በዓለም ላይ ለሚፈጠር ከፍተኛ የበሽታ ሥርጭት በብዛት ሊያጠቃና ሊጎዳ የሚችለው ታዳጊ አገሮችን ነው፡፡ ምንም እንኳን ያደጉ አገሮች ዕርዳታ ቢያደርጉም በሽታው በእነሱ ላይ ችግር የሚያስከትል ከሆነ ‘የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች’ የሚለው ነገር እነርሱ ጋር አይሠራም፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ ያለውን የኮሮና በሽታ ብናይ፣ ጣሊያን በዚህ ወቅት ኢትዮጵያን የምታግዝበት ምንም ምክንያት አይኖራትም፡፡ ማንኛውም የቅርብ ወዳጅ ቢሆን ቤቱን ዘግቶ የራሱን ችግር ለመፍታት ይሞክራል እንጂ ቤቱን እሳት እያጋየው የሌላን ለማጥፋት አይጓዝም፡፡ እናም በዚህ አስደንጋጭ ጊዜ ማንም እንደማይደርስልን አስበን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ተግቢ ነው፡፡
ማንኛውም ወረርሽኝ ዕጣ ፈንታው ጣራ ላይ ከደረሰ በኋላ (ከፍተኛ ሞት፣ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ማኅበራዊ ምስቅልቅል አስከትሎ) ነገሮች ወደ ቀደመ ሁኔታቸው ይመለሳሉ (ወይም በሽታው ይቀንሳል/ይጠፋል)፡፡
ምክንያቱም፦
ሀ) በሽታው በብዛት ከተሠራጨና ጉዳት ካደረሰ በኋላ ማኅበረሰባዊ የበሽታ የመቋቋም አቅም (Herd Immunity) ይፈጥራል፡፡
ለ) በሽተኞች ከሞቱ የመሠራጨት አቅሙ በእጅጉ ይቀንሳል፡፡
ሐ) ማኅበረሰባዊ በሽታን የመከላከል መንገዶችን ስንጠቀም (ለምሳሌ፡ ስለ ኮሮና፣ ራስን የማገገሚያ ቦታ በማስቀመጥ፣ እጅ ለእጅ ባለመጨባበጥ፣ ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ባለመገኘት፣ ንጽህናን መጠበቅ) በሽታው ይጠፋል፡፡
መ) በዚህ መካከል በሽታው መድኃኒት ይገኝለታል፡፡ ስለዚህ እኛ የምናደርገው ቅድመ መከላከልና ሕክምና ዋናው ዓላማ በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሲባል ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በአገራችን ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡
የኮሮና በሽታ ሥርጭት በጥቂቱ
የኮሮናን አስከፊነትና አሰቃቂነት ለማወቅ በሽታው በስፋትና በጥልቀት የተሠራጨባቸውን ቦታዎች ማየትና መገንዘብ ጠቃሚ ነው፡፡
በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ድረ ገጽ እንደተዘገበው (ይህ ጽሑፍ እስከተጠናቀረበት ዓርብ ምሽት አንድ ሰዓት ድረስ)፣ በሽታው በዓለም ላይ 25,251 ሰዎች ለሞት፟ ሲዳርግ፣ 558,502 ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ ያገገሙት 127,615 ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች 16 ደርሷል፡፡
ይህን መረጃ ከኢትዮጵያ አንፃር ብናየው ማለት በአንድ ኢትዮጵያዊ ቤት በአማካይ ከአራት እስከ አምስት ሰው ቢኖር፣ አንድ ሰው ተያዘ ማለት በአንድ የአውቶቡስ ጉዞ እንበልና ሦስት ሰው ቢያስተላልፍ ይህ ሰው በአንድ ጊዜ የራሱን ቤተሰብ ጨምሮ የ20 እና ከዚያ በላይ ሰው ሕይወት አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ ከዚያ በኋላ በሽታው በፍጥነት ያድጋል ማለት ነው፡፡
ስለ በሽታው አስከፊነትና ስለሚያስከትለው ጉዳት በየብዙኃን መገናኛው ስለሚነገር፣ እዚህ ላይ ገታ አድርገን አንዳንድ የመፍትሔ ሐሳቦችን እጠቁማለሁ፡፡
በመንግሥት በኩል መወሰድ ያለባቸው
ሀ. የተወሰኑ ሆስፒታሎችን ለኮሮና ታካሚዎች ብቻ ማድረግ፡፡ ይህ ማለት በአንድ የኦክስጂን ማሽን ላይ ከአራት እስከ አምስት ሰው ተኝቶ በሚታከምባት አገር፣ በሽታው ከመከሰቱ በፊት ለበሽታው ተዘጋጅተናል ማለት ለውስጥ አዋቂዎች (ጤና ባለሙያዎች) እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው፡፡ አንድ የሙቀት መለኪያ የሌላቸው መኝታ ክፍሎች በእያንዳንዱ ሆስፒታል ብዙ ናቸው፡፡ አቅምን አውቆ በቂ ዝግጅትና ዕርዳታ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡እውነታውን ማውጣት በአገር ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ስለምናውቅ ቁጥሩን ንገሩን ሳይሆን መፍትሔው ላይ እንበርታ ለማለት ነው፡፡
ለ. በእነዚህ ሆስፒታሎች ላይ የሙያ ስብጥሩን (diversity of expertise) ማስተካከል፡፡በአንድ ቡድን ውስጥ የሐኪም፣ ነርስ፣ ኢፒዲሞሎጂስት፣ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ፣ ላብራቶሪና ተያያዥነት ያላቸው ሙያተኞች ቡድን ማዘጋጀት፡፡
ሐ. አላስፈላጊ ስብሰባዎችን መከልከል፣ አስገዳጅ ከሆነም ከ100 ሰው በላይ አለመሰብሰብ፡፡ ሲሰበሰቡም በ1.5 ሜትር ርቀት ማድረግ፡፡
መ. የበሽታውን ሁኔታ አሳንሶ (underestimate) አለመረዳትና ስለ በሽታው የተዛቡ ትርክቶችን (flawed narratives) ለምሳሌ፦ በሽታው በኃጢአት መብዛት እንደሚመጣ፣ወጣቶችንና ሕፃናትን እንደማያጠቃ፣ ነጮችን ብቻ እንደሚያጠቃና በእነሱ የመጣ በሽታ ተድርጎ የሚነገሩ ንግግሮችን ማስተካከል፡፡
ሠ. በደካማ የጤና ሥርዓት ማለትም መመርመሪያ፣ መታከሚያ፣ የባለሙያ እጥረትና ዝቅተኛ የጤና ግንዛቤ (health literacy) ያለበት አገር ላይ እንደመሆናችን፣ በሽታውን በቀላሉ እንቆጣጠራለን ብሎ አጉል መመካት (overconfidence) አያስፈልግም፡፡
ረ. ኅብረተሰቡ የሚሰጠውን ምክር ካልሰማ አስተማሪ ቅጣት መቅጣት፡፡ ለምሳሌ፦በበሽታው ተጠርጥሮ ያመለጠ፣ ሆን ብሎ ያስተላለፈ፣ ራስን ማግለል (self-isolation) ያላደረገ ሰው ላይ አስተማሪ ቅጣት ማስተላለፍ፡፡
ሰ. መንግሥት ብቻውን ይወጣዋል ብዬ ስለማላምን ከባለሀብቶች ጋር በመወያየት አስፈላጊውን ዕርዳታንና ቀድሞ በሕክምና ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ማሟላት፡፡
ሸ. የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚወስነው ውሳኔ እንደ አንድ ግለሰብና የጤና ባለሙያ አስተያየት መስጠት ከባድ ቢሆንም ከአገር ምልክትነት አንፃር እስካሁን እየሠራ ያለው ነገር ጥሩ ነው፡፡ ተወደደም ተጠላም ከበሽታ ማምለጥ አስቸጋሪ ስለሆነ አማራጩ አስፈላጊውን ጥንቃቄና መፍትሔ ላይ ማተኮር የተሻለ ነው፡፡ በአገር ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲ በኩል እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት በረራዎችን እንደየ አስፈላጊነቱ ቢቀጥል መልካም ነው፡፡ ሆኖም ግን አየር መንገዱ ለወደፊቱ ትልቅ ሆስፒታልና የምርምር ማዕከል ከፍቶ በሰማይ ላይ ያለውን ተሞክሮ ወደ ምድር ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡
ቀ. የበሽታ ሥርጭቱ እየከፋ ከሄደ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል መዘዋወርን መከልከል፡፡
በ. የኢትዮ ቴሌኮም የጀመረውን መልካም ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ማገዝ፡፡
ተ. በሽታው እየከፋ ሲመጣ በተለይም የተለያዩ ማኅበራዊ ሁነቶች ለምሳሌ፦ ሠርግ፣ ሐዘን፣ ልደትና መሰል ጉዳዮች ኅብረተሰቡ እንዳይሳተፍ መንግሥት ጠንከር ያለ ትዕዛዝ ማስተላለፍ፡፡
ጤና ባለሙያዎች መወሰድ የሚገባቸው
ሀ. የእናንተን የሥነ ምግባርና ሞራላዊ ዕሴቶች የሚፈትን በሽታ እንደሆነ ብገነዘብም፣ ቅድሚያ መሰጠት ላለበት ታካሚ ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ነው፡፡ የሚመለከታቸው ውሳኔ ሰጪ አካላት የቅድሚያ አስጣጥ መመርያዎችን ማዘጋጅት፡፡ ይህም ፍትሐዊ የሆነ የሕክምና ቁሳቁስ ሥርጭት (distributive justice) እና የሕክምና አሰጣጥ ላይ የሚያስከትለውን ችግር ከመከላከል አንፃር የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጤና ባለሙያዎች ላይ የሞራል ምስቅልቅሎች (ethical dilemma) እና የጥፋተኝነት ስሜት (guilty feeling) እንዳይኖር ያግዛል፡፡ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች የራሳችሁንና የቤተሰቦቻችሁን ጤና መጠበቅ ለምሳሌ የበሽታው ሥርጭት እስኪቀንስ ድረስ፣ ራስን ማግለል ብንችል መልካም ነው፡፡
ለ. ታካሚው ከሆስፒታል አገግሞ (ተሽሎት) ቢወጣም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መምከር ተገቢ ነው፡፡
ሐ. በተቻለን አቅም በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች የዓለም ጤና ድርጅት፣ የጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት የሚያወጡትን መረጃ በፍጥነት ማሠራጨት፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ኢንስቲትዩት የበሽታውን ሥርጭትና መጠን በዕድሜና ጾታ ያለበትን ደረጃ ከየክልሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገርና በማሰባሰብ አስፈላጊውን መረጃ በየጊዜውና በፍጥነት ማድረስ፡፡
መ. የድንገተኛ ክፍሎችን በተቻለ መጠን ባለን አቅም ማጠናከር፣ ይህ ማለት የማኅበረሰቡንና የመንግሥትን ዕርዳታ በመጠየቅ ማሳካት ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡
በሃይማኖት አባቶችች፣ ማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ፖለቲከኞችና አርቲስቶች
ሀ. ቤተ እምነቶች ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ተራርቆ መኖርን (social distancing) እንዲሁም በግል አምልኮ እንዲያድርጉ ለምእመኑ አስፈላጊውን ዕርምጃና መልዕክት በየጊዜው እንዲያስተላልፉ ቢደረግ መልካም ነው፡፡
ለ. የማኅበርሰብ አንቂዎች ጊዜን፣ ሁኔታን፣ ችሎታና ሙያን እያገናዘብን ብናወራ መልካም ነው፡፡ ከልክ ያለፈ ቀልድና ቧልት ማኅበረሰባዊ ቀውስ ስለሚያስከትል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ሐ. ፖለቲከኞች ግብር ከፋይ ዜጋ ካጣችሁ የእናንተ የኢኮኖሚ፣ የጤና፣ የፖለቲካና የማኅበረሰባዊ ፖሊሲዎች ከንቱ ናቸውና በስምምነት ስብሰባዎች ብታቆሙ መልካም ነው፡፡
መ. የግል ባለሀብቶች እንደነዚህ ዓይነት ውስብስብ የጤና ችግሮች ሲከሰቱ ማኅበረሰባዊ ኃላፊነታችሁን (corporate social responsibility) መወጣት አለባችሁ፡፡
ሠ. አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ስለ በሽታው ቅድመ መከላከያና መተላለፊያ መንገዶች በኪነ ጥበባዊ መንገዶች ብታስተምሩ መልካም ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በግል ተነሳሽነት አንዳንድ ታዋቂ ግለሰቦች እያደረጋችሁት ያላችሁት አስተዋጽኦ እያመሰገንን ተጠናክሮ ቢቀጥል ሠናይ ነው፡፡
በማኅበረሰቡ የሚጠበቅበት
ሀ. ስለበሽታው የማያውቁትን መጠየቅ እንጂ በመሰለኝና ደሳለኝ ወይም በግብዝነት እኔን ወይም እኛን አይዘንም ብሎ በሳይንስ የተረጋገጡ (scientific evidence) ጉዳዮችን ወደ ጎን ቸላ ብሎ በአሉባልታዎች (conspiracy theories) እንዲሁም የሐሰት ወሬዎች (fake news) መጠመድ አደገኛ አካሄድ ስለሆነ ከወዲሁ መቅረፍ ይኖርብናል፡፡
ለ. ማኅበረሰባዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር የበሽታው ምልክቶች የታዩበት ግለሰብ ራሱን በለይቶ ማቆያ (quarantine) ውስጥ በማድረግ ወደ ሌሎች እንዳይዛመት ማድረግ፣ ሆነ ብሎ በሽታው እያለበት ራሱን የማይገልጽን ሰው ለሚመለከታቸው አካላት መጠቆም (social dobbing) አስፈላጊ ነው፡፡
ሐ. ታማሚን በመንከባከብ፣ በማስታመምና ከሞተም በኋላ ባሉ ሥርዓቶች የሚመለክታቸው አካላት ትዕዛዝና አቅጣጫን መከተል መተግበር ተገቢ ነው፡፡
መ. ስለበሽታው ከመጠን በላይ አለመደናገጥ በተለይም የስግብግብነት ግዥ (panic buying) አለማድረግ፣ አንዳችን ለአንዳችን መተዛዘን ብሎም ከመጠን በላይ ሸቀጦችን በቤት ውስጥ አለማከማቸት (hoard) ይጠበቅብናል፡፡
ሠ. ወደ ገበያ፣ ባንክ፣ መዝናኛ ቦታዎችና የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ስንሄድ ቤተሰብ አለማስከተል፡፡ የተሰብሳቢ ቁጥርን መቀነስ ብቻ ሳይሆን አደጋንም ከመቀነስ አኳያ የጎላ አስታዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
ረ. ወጣቶች በየአካባቢያችሁ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ በቡድን ተድራጅታችሁ እገዛ ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች (vulnerable groups) ተገቢውን እንክብካቤና እገዛ ብታደርጉ እንዲሁም በውጭ አገር ዜጎች ላይ ቀለምን መሠረት ያደረገ ጥቃት (racial attack) እንዳይደርስ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማድረግ አለባችሁ፡፡
“ታሞ ከመማቀቅ አስቅድሞ መጠንቀቅ!!!”
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡