Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እጅ አንሰጥም!

ሰላም! ሰላም! እህ? እንዴት ነው ጃል? ‹ማግኘት ያበጃጃል ማጣት ያገረጅፋል› አትሉም እንዴ? ሁሉም ነገር በማግኘትና በማጣት መረብ ላይ የተዘረጋ በመሆኑ እኮ ነው፣ መወጣጠር በዝቶ ዓለም ለመፈንዳት ቋፍ ላይ ያለችው። በአንድ በኩል ሲታጨድ በሌላው መበተን እየተለመደ ነው ዓለም መስማማት አቅቶት እርስ በርስ ሲጓተት የረቂቅ ህዋስ ሰለባ እየሆነ ያለው። እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ባልማርም ይኼ እንደማይጠፋኝ በእርግጠኝነት እናገራለሁ፡፡ ‹‹አፈር ናችሁና ወደ አፈር ትመለሳላችሁ›› ስንባል ራሱ በመገኘትና በመታጣት ንድፈ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ መሆኑንም እረዳለሁ። ‹‹ማግኘትም አልከፋ ማጣቱም አልከፋ፣ እኔን የጨነቀኝ መኖር ነው በተስፋ፤›› ብሎ አንድ ደላላ ወዳጄ አንጎራጎረ። ‹‹ምነው ትዝታ ውስጥ የገባህ ትመስላለህ?›› ብለው፣ ‹‹እንዴት ቢሆን ነው ማግኘትና ማጣት ጥግ ድረስ እየሄዱ የማይበላ የተስፋ ዳቦ ሲያሳዩን የሚኖሩት?›› ብሎ መልሶ ጠየቀኝ። መጠያየቅ ከጀመርንማ አንላቀቅም!

እኔ ትዝታን በተመለከተ ከዘፈን ጀምሮ ብዙ ትውስታዎች አሉኝ፡፡ ሁሌም የማረሳው ግን፣ ‹‹ሰው ማርጀቱን የሚያውቀው በተስፋ መኖር ትቶ በትዝታ መኖር ሲጀምር ነው፤›› የሚለውን ዘመን ተሻጋሪ ጥቅስ ነው፡፡ ‹‹ትዝታሽ ዘወትር ወደኔ እየመጣ ዕፎይ የሚልበት ሕይወቴ ጊዜ አጣ. . .›› ማለት ስጀምር ማንጠግቦሽ ወጣትነቷ እየታሰባት ነው መሰል በንዴት፣ ‹‹በቃህ!›› ስትለኝ እደነግጣለሁ፡፡ ማን ማርጀትን በዋዛ ይቀበላል? ወገብ ሲንቀጠቀጥ እግር መራመድ ሲያቅተው ይታያችሁ፡፡ ለዚህ መስሎኝ በስተርጅና ፖለቲከኞቻችን እንደ ሠፈር ጎረምሳ ይዋጣልን እያሉ የሚውረገረጉት፡፡ አሁን ደግሞ ከፈንጣጣ፣ ከትክትክ፣ ከኮሌራ፣ ከልጅነት ልምሻ፣ ከኤችአይቪ/ኤድስና ከበርካታ የዚያ ዘመን ወረርሽኞች በቅጡ ሳንገላገል እንደ ሱፐር ሶኒክ ጄት የሚወነጨፍ ኮሮና የሚሉት ሲመጣብን፣ ለወሬ ነጋሪ እንዳያስቀረን ብሠጋ ይፈረድብኛል ወይ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ፡፡ አጠገቤ ያሉትን ስጠይቃቸው ወይ የምለው አይገባቸውም፣ ወይም ሁሉንም ነገር ለላይኛው ጌታ ሰጥተው ባላየ ባልሰማ ያልፉኛል፡፡ አሁንማ እሱው ይሁነን እንጂ አካሄዳችን ያስፈራል፡፡ ደፈር እንበል እንጂ!

በቀደም ተራራቅ በሚለው የወቅቱ ሕግ መሠረት ቫይረሱን ትተን ቀስ እያልን የተለመደውን የፖለቲካ ጨዋታ ከጓደኛዬ ጋር አነሳነን። ያለ ውጤት እንደ መረብ ኳስ ጨዋታ ኳሱን አየር ላይ ስንቀባበለው 2012 ዓ.ም. ሊጋመስ ነው። ሕዝባዊ አጀንዳ በሰነቁና ድንፋታ በታጠቁ ፖለቲከኞች ምክንያት የአገራችን ችግር እየባሰበት ከርሞ አሁን ደግሞ ሌላ ሰይፍ ተመዞብናል። ምን ታደርጉታላችሁ? ካልጎደለ ስለማይሞላ ካልሞላም ስለማይጎድል፣ ሚዛኑን ለማስጠበቅ መባዘናችንን ግን አልተውነውም። ይኼን የተፈጥሮ ሕግ ጨዋታ ሚዛን በቅጡ ለመምራት፣ ጠማማውን ፖለቲካ ለጊዜው ወደጎን ብለን በተነሳብን የጋራ ጠላት ላይ ብንበረታ፣ እንኳንስ ግብፅን የመሰለ ነውጠኛ ዓለምን እያሸበረ ያለውን ኮሮና አደብ ባስገዛን ነበር። ‹‹አሁን አሁንማ ኮሮናን ጭምር የፖለቲካ መቆመሪያ ለማድረግ የሚፈልጉ መዥገሮች እንደ ማፊያ አገር ማመሳቸው የሚቆም አይመስለኝም፤›› አለኝ ጓደኛዬ። ‹‹ምን ያድርጉ ብላችሁ ነው ለነገሩ? እኛስ ከግዴታ ይልቅ መብትን ጠንቅቀን የምናውቀውን ያህል መቼ ዘመትንባቸው? ከጭቆና ተገላገልን ስንል ለባሰ ጭቆና ለመዳረግ የተነሱ አውሬዎችን መታገስ የለብንም. . .›› አለኝ ወዳጄ እየተብሰለሰለ፡፡ ምን ያድርግ ጨንቆት እኮ ነው!

 እግረ መንገዴን አንድ ያጋጠመኝን ጉዳይ ላጫውታችሁ። በአንዱ ዕለት ማለዳ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከቤቱ ወጥቶ ወደ ሥራ ሲጣደፍ አገኘኝ። ደህና አደርክ ሳይለኝ የለበጣ ሳቅ እየሳቀ፣ ‹‹አንበርብር እንደ ተዳከመ ቡድን በገዛ ሜዳዬ ነጥብ የመጣል አባዜ አስቸገረኝ እኮ!›› አለኝ ሁለት እጁን በኪሱ ከቶ አንገቱን እየነቀነቀ። በነገራችን ላይ የባሻዬ ልጅ ቀንደኛ የእግር ኳስ ተመልካች ነበር። ሊቨርፑልን እንደሚደግፍ ራሱን ቢደግፍ ይኼኔ የት በደረሰ ነበር ያስብላችሁ ነበር፡፡ ‹‹ምነው ሰላም አላደርክም? እንዴት አደርክ ማለት አይቀድምም?›› ስለው፣ ‹‹ደመወዝ በወር ኑሮ በዕለት ሆኖ መፈናፈኛ አጥተን እንዴት ሰላምታ ይቅደም?›› አለኝ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እጁን ተስሞ የሚፈለግ ልዩ ባለሙያ እንደሆነ ባውቅም የገቢው ነገር ዘወትር ሲያሸማቅቀው አያለሁ። ‹‹ደመወዜ ከማነሱ ቀኑ እንደ ምጥ መርዘሙ ነው የሚገርመኝ፤›› አለኝ፡፡ ‹‹እንዴት?›› ብዬ ስጠይቀው፣ ‹‹ቀኑ እንዴት እንደሚከንፍ፣ የደመወዝ ቀን ግን እንዴት ሰውን እንደሚያንቆራጥጠው አታይም? ከታክሲ ጥበቃና ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ዳኝነት ጥበቃ በተጨማሪ የመጣልንን ለውጥ መጠበቅ አቅቶን እየተናጀስን የደመወዝ ቀን ጥበቃ ሲጨመር አይጣል ነው፤›› አለኝ ጭንቅ ብሎት። ‹‹አይዞህ ማጣትም ቢሆን ከልኩ አያልፍም፤›› አልኩና 1‚000 ብር አውጥቼ ደመወዝ ስትቀበል ትሰጠኛለህ በሚል ሸጎጥኩለት። ጥሩ አይደል? ታዲያ ወገን ለወገኑ መቼ ነው የሚደርሰው? ተግባር የማያውቅ ባዶ የተስፋ ቃል መስማት አልሰለቻችሁም? በትንሽ በትልቁ ተጋግዘን አገር እናቀናለን ስንል የሥልጣን ጥም ያቃጠላቸው አስመሳይ ፖለቲከኞች ሲያወናብዱን ይነደኛል፡፡ ወይ ነዶ!

‹‹ኧረ ኩሉን ማን ኩሏታል. . .›› የሚባልበት ወርኃ ሚያዝያ ተቃርቦ አሁን እንኳ ለሠርግና ለፍቺ ጊዜ መምረጥ ቀርቷል፡፡ ጊዜው ነዋ፡፡ ለፖለቲከኛም ቢሆን፡፡ አንድ የሠፈራችን የተከበሩ ሀብታም ልጃቸውን ለመዳር ሽር ጉድ እያሉ እንደሆነ ሳላጫውታችሁ የቀረሁ አይመስለኝም። የሠፈሩ ሰው ታዲያ እኝህን ሰው እጅግ ፈርቷቸው ሰነበተ። ስለራሳቸው አዳዲስ የወጡ መረጃዎችን የሚሰጡ ጥቃቅንና አነስተኛ ምላሶች ሠፈሩ ውስጥ በረከቱ። ሁሉም የየግሉን ኤፍኤም ጣቢያ የጀመረ መስሎን ነበር። የሚዲያ ነገር ሲነሳ ፌስቡክን አለማስታወስ ነውር ይመስለኛል። በዚሁ ፌስቡክ ስለአገር የምንሰማው ያው ተቀላቅሎ መሆኑ አያከራክረንም። መፈክሩም ‹‹ምርጥ ምርጡን ለሕዝባችን›› የሚል ነው ተብሎ በአንዳንድ ስላቅ ቀማሪዎች ይታማል። ‹‹ጆሮ ለባላቤቱ ባዳ ነው›› እንዲሉ ፖለቲከኞቻችንም የሕዝብ አስተያየት ሲያዳምጡ ‹‹ምርጥ ምርጡን›› ነው። ‹‹እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር በአርበኞች ጊዜ ቀረ፤›› ሲሉ የሰነበቱት አዛውንቱ ባሻዬ ናቸው። ባሻዬ አልቀረም የሚሉት አንድ ነገር ብቻ እንደሆነ ነግረውኛል። እርሱንም ‹‹ና ወዲህ!›› ብለው በጆሮዬ፣ ‹‹አንበርብር ዛሬም ትናንትም ያለውና የነበረው ስለራሳችን እውነቱን ስንሰማ እንደ ወባ ታማሚ የሚያንዘረዝረን ነገር ነው፤›› ነበር ያሉኝ። ታዲያ እኔም በጆሯችሁ ነው ሹክ ያልኳችሁ እሺ? በዘመነ ኮሮና ቫይረስ አንበርብር ተናገረ ቢባል በፍጹም እንዳታምኑ፡፡ ወሬኛ ሁሉ እንጀራው የሚጋገረው ፌስቡክ ላይ መሰለ እኮ!

 የሠፈራችን ትልቁ ባለሀብት በነዋሪዎች ላይ የለቀቁትን ከራስ ይዞታና ከቀበሌ ቤት የማፈናቀል የማሸበር ስሜት አልቃይዳ እንኳ ሊፈጥረው የሚችለው አልነበረም። ሰውዬው በመንደራችን፣ ‹‹የቴረሪዝምን ቲዮሪ በደንብ ሊያስተዋውቁ የቻሉ፤›› ተብለዋል። ‹‹እንዳሻቸውና በአሻቸው ጊዜ የሰሙትን ገልብጠው የማውራት ሱስ ያለባቸው ይኼንን በተመለከተ ሊያስቡበት የሚገባ ነገር አለ። አገር በሥራ እንጂ በነውጠኛ ወሬ አታድግም የሚለውን ደግሞ አድሮ ቃሪያ ለሆኑት ፖለቲከኛ ተብዬዎችና አክቲቪስት ነን ባዮች በሉልን፤›› አለኝ አንድ በጉልበቱ ለፍቶ አዳሪ ወጣት ኮስተር ብሎ። ምንም እንኳ ደላላ እንጂ የፖለቲከኞች ተወካይ ባልሆንም፣ ‹‹እኔ ምን አገባኝ?›› ሳልል በጥሞና አዳመጥኩት። ባለሀብቱ፣ ‹‹ልጄ መዳር ያለባት የዳኸችበትና የሮጠችበት እዚህ መሬት ላይ ነው። ምንም እንኳ ዛሬ ሞልቶኝ በሾፌር ገብታ ስትወጣ ዓይኗን ለማየት ባትችሉም፣ እኔ እንደ እናንተ ሳለሁ (ደሃ ሳለሁ ለማለት ነው) ከእኩዮቿ ልጆቻችሁ ጋር አፈር ፈጭታ አድጋለች፤›› አሉ ተባለ። ‹‹እናስ?›› ተብሎ ሲጠየቅ ለከተማው አስተዳደር አካባቢውን ለማልማት እንዲሰጣቸው ማመልከቻ አስገቡ ማለትን የሰሙ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ይመካከሩ ጀመረላችሁ። ‹‹ወጪና ጉልበት ቆጣቢ በሆነው ፌስቡክ ካልሆነ ለጊዜው ሰላማዊ ሠልፉ አልተፈቀደም፤›› ያለው ሰው ባይታወቅም፣ በዚሁ አንድምታ አዛውንቶች ሳይቀሩ ኢንተርኔት ካፌውን አጨናንቀው ሰነበቱ። ያውም ኮሮና ቫይረስን እንከላከል ተብሎ ዘመቻ በተጀመረበት ወቅት፡፡ ዘንድሮ ገላጋይ ያጣ ተደባዳቢ መስለናል እኮ!

እንግዲህ እኔ ይኼን ሁሉ በሩጫዬ መካከል በትዝብት እከታተልላችኋለሁ። ግማሹ፣ ‹‹የዘንድሮ ባለሀብት የተነሳበትን ለመርሳት የሚቀድመው የለም፤›› ሲል ሌላው ይቀበልና፣ ‹‹አገር የሚጠቅም ስንት ዓይነት ፋብሪካ መትከል እየቻለ ከተማ የሚበጠብጠውን ማን ያርቅልን?›› ሲል እሰማዋለሁ። ባሻዬ በበኩላቸው፣ ‹‹አሁን እሱ ሕንፃ ልገነባ ነው ብሎ ቤታችንን አፍርሶ ሲያበቃ፣ እዚህ ዳስ ጥሎ ሠርግ ሊደግስ ነው ያሰበው። ብልጥ ለብልጥ ዓይን ፍጥጥ አለ ያገሬ ሰው። አይ የተነሱበትን አለማወቅ! ትናንትን እንደ መርሳት የመሰለ ክፉ በሽታ የለም። አናውቅም እንዴ እንዴት እንዴት ብሎ ሀብቱን እንዳጋበሰው. . . ለመሆኑ ዓለም በዚህ ቀሳፊ ቫይረስ አቅሉን ስቶ እሱ የት ሆኖ ሊበላው ነው. . .››  እያሉ በዕድሜ እኩያቸው ስለሆኑት ባለሀብት ብዙ ሚስጥሮች ሲዘከዝኩልኝ ሰነበቱ። ሰው ከሰነበተ የማይሰማውና የማያሰማው የለም። በመጠላለፍ ሕግ አንዱ ሲያመልጥ ሌላው ወዳቂ ነው። እንደምታዩት ዛሬ ይኼ የጨዋታ ሕግ ኮሮና አጨናንቆት የሰው ልጅ በድንጋጤ እንደ ሰጎን አንገቱን አሸዋ ውስጥ ለመቅበር የሚፈልግ ይመስላል። ጤናማ ፉክክር የዕድገት አንቀሳቃሽ እንደሆነ በእኔም ሕይወትና ሙያ ስለማስተውለው እጅግ እደግፈዋለሁ። ሆኖም የትናንት ታሪካቸውን እየረሱ ለወገን ባዕዳን የሚሆኑትን ሳይ ልቤ ይቆስላል። ለአገር ዕድገትና ብልፅግና መረዳዳት፣ መተጋገዝና መተሳሰብ ሲገባን ለመበላላት መሯሯጥ ያስከፋል። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ይኼ ነው አንዱ የሥርዓተ አልበኝነት ጦስ፤›› የሚለኝ ነገር ከቶውንም ባይገባኝም፣ በከፊል ግን የተወላገደው የዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ለዚህ ያለውን አስተዋጽኦ አላጣውም። አሥር ሳንቲሞች ተጠራቅመው ሚሊዮኖችን እንዴት እንደሚታደጉ ማስረዳት እንደሚቻል አላውቅም። ‹‹ዋናው ጠላታችን የክፋት የጀርባ አጥንት የሆነው ራስ ወዳድነት ነው፤›› ብለው የሚነግሩን እስኪወለዱ እንጠብቅ ይሆን? ደጅ መጥናት አይታክተን መጥኔ!  

መቼ ዕለት በጥድፊያዬ መሀል ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ደወለችልኝ። ምን ገጥሟት ይሆን እያልኩ በጥድፊያ ስልኬን አነሳሁት። እንደ እኔ ስልካችሁ መጥራቱ በመቻሉ ብቻ ፈጠን ብላችሁ ማንሳት ይኖርባችኋል። ‹‹እንዴት?›› እንደማትሉ ተስፋ አደርጋለሁ። ምክንያቱም የአገራችን ዘርፈ ብዙ ችግር እንደ አዲስ የሚወራ አይደለምና ነው። ‹‹ሎተሪ ቢደርሰኝ ከሚሰማኝ የደስታ ስሜት እኩል ሲደወልልኝና የደወልኩት ስልክ ሲጠራ እደሰታለሁ፤›› ያለኝ ደላላው ጓደኛዬ ነው። እውነቱን ነው የደላላ ስልክ ካልሰራ ገቢ የለም፡፡ ‹‹ኖ መኒ ኖ ፈኒ›› ሆነ ማለት ነው፡፡ ልክ ስልኩን አንስቼ ሳነጋግራት፣ ‹‹በእጮኝነት ዘመናችን ታደርገው እንደነበረው ሲኒማ ቤት ይዘኸኝ ሂድ፤›› አለችኝ። ወይ ማንጠግቦሽ? አካላዊ ርቀታችሁን ጠብቁ ተብሎ እየተለፈፈ ጭራሽ ሲኒማ ቤት? እኔም ተዘናግታ ይሆን እንዴ ብዬ የጤና ሚኒስቴርን ማሳሰቢያ ደጋግሜ አስረዳኋት። ዛሬ እርጅና እየመጣ ጉልበት እንደ ልጅነት አልሆን ሲልና ማስታወስ ሲቸግር ሰው ነንና ግራ ይገባናል። በአጉል አምሮት ውስጥ ደግሞ መሳቀቅ አለ። እናማ ማሳሰቢያው ሲደጋገምባት በድንጋጤ ውስጥ ሆና ይቅርታ አለችኝ። የዘመኑ ወረርሽኝ አቅል አሳጥቶን ይሆን እንዴ ስንከለከል የሚብስብን? አንዳንዴ እኮ ጭንቀት ሲበዛ ማሰብና ማስተዋልን የሚጋርድ ይመስለኛል፡፡ ለዚህም ይሆን እንዴ የእኛ ሰው በግራ እያሳየ በቀኝ እየታጠፈ የሚያሳቅቀን ለማለት እፈልግና የምተወው? እንተወው እንጂ ብዙ ያነጋግራል!

አዕምሮዬ በአንድ በኩል በማንጠግቦሽ ሰሞነኛ የመዘንጋት አመል፣ በሌላ በኩል ለማሻሻጥ እየሮጥኩለት በነበረው አምስት ዓመት የሠራ ባለተጎታች ቦቴ ምክንያት ተወጥሮ ነበር። በዚህ መሀል ከኋላዬ ‹‹አንበርብር!›› የሚል ድምፅ ብሰማ ወዲያው ዞርኩ። በቅርቡ ከወንድሙ ጋር ተጋግዞ ሬስቶራንት የከፈተ የቀድሞ ደላላ ወዳጄ ድምፅ ነበር። ቤቱን አይቼለት ስለማላውቅ እግረ መንገዴን ጎራ እንድል ፈልጎ ስለሥራው እያጫወተኝ ሳለ ድንገት የመገረም ፈገግታ አሳይቶኝ፣ ‹‹‹ጤና ተቆጣጣሪዎች መጥተው መፀዳጃ ቤቱን ለማየት ገብተው ፅዱና ደረጃውን ያሟላ መሆኑን ዓይተው ሲያበቁ፣ ‹ይኼንን ባለ ሳህን መቀመጫ አንስተህ የመሬቱን ነው ማድረግ ያለብህ፤› አይሉኝ መሰለህ? ለምን? ስላቸው ‹አዲስ የወጣ መመርያ ነው። በሁሉም ላይ ተግባራዊ እናደርገዋለን› አሉኝ። እኔም ደሜ ፈልቶ መመርያው የወጣው ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ነው? ስላቸው እርስ በርሳቸው ይተያዩ ጀመር። እኔምለው አንበርብር ደንብና መመርያ የሚያወጣው በደመነፍስ ነው እንዴ?›› በማለት አስደመመኝ። የአንዳንዱ መመርያ ‹‹ላም በሌለበት ኩበት ለቀማ›› የአንዳንዱ ደግሞ ‹‹ልፋ ያለው ገለባ ይወቃል›› ዓይነት ሲሆን ስናይ አግራሞታችን ያይላል፡፡ ‹‹ግራ ተጋብተው ግራ የሚያጋቡ ባይበዙ እኮ የጀመርነው የሁለት ዓመት የዴሞክራሲ ጉዞ ለምሥራቅ አፍሪካ ይተርፍ ነበር፤›› ያለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ድንቄም ዴሞክራሲ!  

በሉ እንሰነባበት። በለስ ቀንቶኝ ቦቴውን አሻሽጬ ጠቀም ያለ ገንዘብ ቆጠርኩ። ያሻሻጥኩለት ሰው የዕድሜውን ግማሽ ነዳጅ ሲያመላልስ ቢኖርም፣ ነዳጅ መፈለግ እንጂ በበቂ መጠን ማግኘት ያቃተን ምስኪኖች ስለሆንን ቅር እንዳይልህ ብሎ ያሰበልኝ ኮሚሽን ከበቂ በላይ ሆኖብኛል። አባባሉ የብዙዎቻችንን ምኞት ይወክል ይሆን ብዬ መብሰልሰሌ ግን አልቀረም። ይኼንን ጥያቄ የተለመደችው ግሮሰሪያችን ቀዝቃዛ ቢራችንን እየተጎነጨን እንዳንጫወት ግሮሰሪያችንም ተዘግታለች፡፡ ‹‹በድርቅና በረሃብ ምክንያት የጠቆረው ስማችን ወደ ዴሞክራሲ መንገድ ስጀምር በግጭት መነሳት ጀምሯል፡፡ አሁን የቀረን አንድ ነገር ብቻ ነው፤›› አለኝ የባሻዬ ልጅ፡፡ ቀና ብዬ፣ ‹‹ምንድነው እሱ?›› በማለት ጥያቄ አቀረብኩለት፡፡ ‹‹በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የታጀበ ብሔራዊ አንድነት፡፡ ከጥላቻና ከንቀት የተላቀቀ መከባበር፡፡ ሁሉም በእኩልነትና በባለቤትነት ስሜት የሚኖርባትን ዴሞክራሲያዊት አገር ዕውን ማድረግ፡፡ ከዚያ ዜጎች በአገራቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲራመዱ ምኅዳሩን ማመቻቸት፡፡ ዋናው አንገትን አንዴ ቀና ማድረግ ነው። ከዚያ በኋላ ጉዞው አባጣ ጎርባጣ የሌለበት ሜዳ ነው፤›› ብሎኝ ሲያበቃ በማንጠግቦሽ ቡና ቺርስ ተባባልን። እስቲ ፖለቲከኞችም ቂም በቀላቸውን ትተው ቺርስ ይባባሉ፡፡ የተወጠረው አየር ተንፈስ ብሎ እኛም ንፁህ አየር እንማግ፡፡  ስለዚህ የተኳረፋችሁ፣ ጀርባ ለጀርባ የተሰጣጣችሁ፣ በአሉባልታና በሐሜት የተለያያችሁ፣ በጠመንጃ አገር ለማፍረስ የምትባዝኑና ባልበሰለ አስተሳሰብ ታሪክ የምታዛቡ ተቀራረቡና ቺርስ ተባባሉ፡፡ ብትፈልጉ በውኃ፣ በወይን፣ በፈለጋችሁት፡፡ እናንተንም ቺርስ ብያለሁ! ከማቀርቀር ቀና እንበል! ሥጋት የፈጠረብንን ኮሮናን ተባብረን አጥቅተን እንደምስሰው! እጅ አንሰጥም እንበል! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት