አዲስ አበባ የበርካታ ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ብትሆንም፣ ዓለም አቀፍ ከተማነትን የሚመጥን ውበትም ሆነ መሠረተ ልማት አልተሟላላትም፡፡ ከተማዋን ውብ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ደረጃዋን የጠበቀች እንደሚያደርጓት ተስፋ ቢጣልም፣ ከዚሁ ጎን ለጎን የከተማዋ ሕዝብ መብዛትና መጨናነቅ እክል ሆኖባታል፡፡ ሥራ አጥነቱም የከተማዋ ችግር ሆኖ ይጠቀሳል፡፡
የንግድ ማዕከል ጭምር የሆነችው አዲስ አበባ ከአስመጪ እስከ ላኪው፣ ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ነጋዴ የከተመባትም ናት፡፡ በከተማዋ በንግዱ እንቅስቃሴ ዘርፍ አዎንታዊም አሉታዊም ገፅታ ካላቸው አንዱ የጉሊት ንግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በከተማዋ የነበረው የጉሊት ንግድ፣ የነዋሪውም ሆነ የሥራ አጡ ቁጥር እንደ ዛሬው ልቅ የወጣ ስላልነበር፣ በሚታወቁ መደበኛ ገበያ ውስጥና በአንዳንድ ሰፈሮች ለጉሊት ንግድ ተብለው በተለመዱ ሥፍራዎች ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ዛሬ ተቀይሯል፡፡
በአዲስ አበባ ክፍት ተብለው የተገኙ ሥፍራዎች ፆም ማደር የለባቸውም የተባለ ይመስል፣ የከተማዋን ውበት በሚያጎድፍ መልኩ ጉሊት ሆነዋል፣ እየሆኑም ነው፡፡ ካለው ሥራ አጥነትና ድህነት አንፃር ይህን ማድረግና፣ በዚህ ሲጠናከሩ ወደ ሌላ ማሸጋገር የሚሉ ሐሳቦች በከተማ አስተዳደሩ ቢስነዝሩም፣ እንደዚህ ዓይነት አሠራሮች በተለይ ባልተሟላ የጤና ሥርዓት ላይ መደመራቸው ሥጋት ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ወደ አጥሩ መጠጋት እንኳን ክልክል የነበረው ጦር ኃይሎች የሚገኘው የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ከፊል አጥር ሳይቀር ተሸንቅሮ መነገጃ ሥፍራ ሆኗል፡፡
እግረኛ መሄጃ አጥቶ አስፋልት እስኪወጣ ድረስ መነገጃ የሆነው ዘነበወርቅ አደባባይ አካባቢ የሚገኘው መሸጫ ቦታ፣ ካዛንችስ፣ ፒያሳ፣ አዲሱ ገበያ፣ ገርጂ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም አጥርን ተከትሎ ያለው ሥፍራና በየአካባቢው እየተቀለሱ ያሉ ጉሊቶች ከአካባቢና ግል ግፅህና አንፃር ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሥፍራዎች ናቸው፡፡
ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ ተብሎ ለጊዜው በእንዲህ ዓይነት ሥፍራዎች ላይ ለሥራ አጦች ሥራ ለመፍጠር የተዘየደው መላ ነዋሪውን ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍለው የታሰበበት አይመስልም፡፡
በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች በተለይ ከፍተኛ የተሽከርካሪና የእግረኛ እንቅስቃሴ የሚያስተናግዱትን መገናኛና ሜክሲኮን ጨምሮ ሕገወጥ ናቸው ወይስ አይደሉም? ብሎ ለመደምደም በሚያስቸግር ሁኔታ በሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት የእግረኛውን መንገድ ዘግተው የሚነግዱ በርካቶችን ያየ፣ ይህ ሁሉ የጎዳና ላይ ነጋዴ የት ይፀዳዳል ብሎ መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡
የቀደሙ የንግድ ሥፍራዎች ያለባቸው የአካባቢ ንፅህና ችግር ባልተቀረፈበት ሁኔታ በቅርቡ የተሰጡ ጉልቶችንም ሆነ የጎዳና ላይ ንግዶችን ለቃኘ፣ በየአካባቢያቸው ካለ ክፍት ሥፍራ በስተቀር ለነሱ ታስቦ የተሠራ መፀዳጃ አለመኖሩን መታዘብ ይቻላል፡፡
ዓለም አቀፍ ሥጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ቀድሞ ከመከሰቱ በፊት አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) እንዲሁም ኮሌራ እየተፈራረቁ ለሚጎበኟት ኢዲስ አበባ፣ ከፍተኛው የጤና እክሏ የሚመዘዘው ከግልና አካባቢ ንፅህና ጉድለት ቢሆንም፣ ይህንን ፈር የሚያስዝ ሥርዓት ሲዘረጋ ብሎም ሲተገበር አይስተዋልም፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሳሙኤል ዘመንፈስ ቅዱስ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ሁሉም ፖሊሲዎች የጤና ጉዳይን ያካተቱና ታሳቢ ያደረጉ መሆን አለባቸው (Health in all Policies) ቢባልም፣ ይህ ወደመሬት ወርዶ ሲተገበር አይስተዋልም፡፡
እንደ አገርም ሆነ እንደ ከተማ በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ እክል ወይም የበሽታ መነሻ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ባለመሠራቱም፣ የጤናው ዘርፍ ባለው ውስን አቅም የታመሙትን ከማከምና እንዳይታመሙ ከማስተማር የዘለለ እየሠራም አይደለም፡፡
እንደ ዶ/ር ሳሙኤል፣ አሁን ባለው አቅም ጤና ዘርፉ ሊሠራ የሚችለው፣ ማስተማርና ማከም ላይ ቢሆንም፣ ለጤናው ዘርፍ ማነቆ የሆኑ ችግሮች ላይ አስተያየት ከመስጠት አልተቆጠበም፡፡ ሆኖም የግልና አካባቢ ንፅህናን በመጠበቅ ብቻ ሊወገዱ የሚችሉትን በሽታዎች መቋቋም አልተቻለም፡፡
የሠለጠኑት አገሮች ተላላፊ በሽታዎችን ተቆጣጥረውና አጥፍተው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ እየሠሩ ሲገኙ፣ ኢትዮጵያና አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች በድህነት ሽፋን ተላላፊ የሆኑትን በሽታዎች ሳይቋቋሙ፣ ተላላፊ ያልሆኑት በሽታዎች ተጨማሪ ሸክም ሆነውባቸዋል፡፡
ለአብነት ያህል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየመንገዱ የተቀለሱ ጉሊቶች ከአካባቢና ግል ንፅህና ውጪ መሆናቸው ተነሳ እንጂ፣ በከተማዋ የመፀዳጃ ቤትና የውኃ ችግር ከማኅበረሰቡ ግዴለሽነት ጋር ተዳምሮ ለተላላፊ በሽታዎች መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡
ዶ/ር ሳሙኤል እንደሚሉትም፣ በከተማው በመኖሪያ ቤቶችና በጎዳና ብቻ ሳይሆን፣ በጤና ጣቢያዎች ላይ የሚከሰት የውኃ መቆራረጥ ፈተና ነው፡፡ ውኃ ማዳረስ፣ የአካባቢ ግል ንፅህና ሊያስጠብቁ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ማሟላት ባልቻለች ከተማ ውስጥ የሕክምና ባለሙያውም ሆነ የጤናው ዘርፍ የታመሙትን ከማከም ውጪ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል በመጠቆም፣ ካለፉ ስህተቶች በመማር በቀጣይ በሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ የጤናውን ዘርፍ በማካተት በዓለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመቋቋም መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዓለም ሥጋት የሆነውና የየትኛውም አገር ኢኮኖሚ ሊመክተው ያልቻለው ኮሮና ቫይረስ ደግሞ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥጋትና መከራ የሚያስከትል እንደሆነ ሳይጠቅሱም አላለፉም፡፡
ኮሌራንና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎችን ለመቋቋም ያልቻለው የጤና ሥርዓት፣ ያደጉትን አገሮች ያንበረከከውን ኮሮናን ይሸከማል የሚል አመኔታም ሆነ መላምት እንደማይሠራም ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ሳሙኤል ‹‹ሰዎች አርፈው ቤት መቀመጥ አለባቸው›› የሚለውን አፅንኦት ይሰጡታል፡፡ መንግሥት ተማሪዎች ቤት እንዲቀመጡ፣ ሠራተኞች ከሥራ እንዲቀሩ ያደረገው ለመዝናናት ወይም ሌላ የግል ጉዳይ እንዲፈጸም አይደለም፡፡ ይልቁንም ሰዎች ለራሳቸውም ለወገናቸውም ችግር እንዳይሆኑ ለማስቻል ነው፡፡
በኢትዮጵያ በተለይ ኮሮናን አስመልክቶ የጤናው ዘርፍ ላይ ተስፋ መደረግ የለበትም፡፡ ድንገት በሽታው ቢስፋፋ ኢትዮጵያ የመሸከም አቅም የላትም፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕሙማንን ማስተናገድ የሚያስችል የሕክምና ቁሳቁስም ሆነ ባለሙያ ማግኘትም አይቻልም፡፡
‹‹አሁን ያለው አቅም አንድ ነው፣ ሰው አርፎ ቤቱ መቀመጥና በሽታውን ለመግታት መተባበር›› የሚሉት ዶ/ር ሳሙኤል፣ በዕድሜያቸን አይተን የማናውቀው በሽታ ሲከሰት መዘናጋት ዋጋ የሚያስከፍል ሊሆን እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኅብረተሰቡ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚተላለፉ መመርያዎችን ምን ያህል እየተገበረ እንደሆነ ለመታዘብ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. አደባባይ የወጡት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ምልከታቸውን በትዊተር ገጻቸው አንፀባርቀዋል።
“ዛሬ በአዲስ አበባ ተዘዋውሬ ነበር፣ መመርያዎችን በመተግበር ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ የሚጠጋን ቫይረስ የለም ሲሉ የነበሩ ያሉበትን እያየን አንዘናጋ፣ ምርመራ በብዛት ባለመደረጉ ትክለኛውን ሁኔታ አላየንምና በአገር ደረጃ ተቀናጅተን መዘጋጀት አለብን፤” ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ በሽታዎችን ከኢትዮጵያ ለምን ማጥፋት አልተቻለም? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው የሚሉት ዶ/ር ሳሙኤል፣ ለሁሉም ምክንያቱ ከሚገጥሙ ችግሮች ተምሮ መፍትሔ አለማበጀት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡
በኢትዮጵያ ኮሌራ፣ አተትና ሌሎች በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ ሲከሰቱ፣ በወቅቱ በዕርዳታ ድርጅት በሚገኝ አቅም በሽታውን ከማከም፣ ከተገኘም የውኃ አቅርቦትን ለማሻሻል ከመሥራት ባለፈ የሁልጊዜ ሥራ ተደርጎ አለመቀጠሉ ኢትዮጵያን የተላላፊ በሽታ መናኸሪያ እንድትሆን አድርጓታል፡፡
በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ የጤናው ዘርፍ ያልተሻሻለው ከስህተትና ከተሞክሮ ባለመማር በቀጣይነት ባለመሥራት ነው፡፡ የትኛውም በሽታ ተከሰተ ሲባል በዕርዳታና በድጋፍ ችግሩ ያልፋል፣ የሞተው ይሞታል፣ የሚድነው ይድናል፡፡ ይህ ከዚህ ቀደም የነበረ አሉታዊ አካሄድ ግን ኮሮና ቫይረስ ላይ የሚሠራ አይደለም፡፡
ኮሮና ቫይረስ የግልና አካባቢ ንፅህናን አጥብቆ የሚፈልግ ብቻ ሳይሆን፣ ቤት መቀመጥን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይህ ግን እየተተገበረ አይደለም፡፡ የገበያ ቦታዎች መርካቶም ሆነ አትክልት ተራ እንደቀድሟቸው ናቸው፡፡ ምናልባት ጓንት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ያደረጉ የተወሰኑ ሰዎችን ማየት ይቻል እንደሆን እንጂ፣ ግፊያው ንክኪው እንዳለ ነው፡፡
ከበሽታው አስከፊነትና የሥርጭት ፍጥነት አንፃር የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት የሚቋቋመው ባለመሆኑ ሰዎች ቤት መቀመጥን ቀዳሚ መፍትሔ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ዶ/ር ሳሙኤል የሚመክሩትም ይህንኑ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የአገሪቱ የጤና ሥርዓት ኮሮናን ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የነበሩ ተላላፊ በሽታዎችን መሸከም ያልቻለ መሆኑን ተገንዝቦ፣ በመንግሥት በኩል የሚሰጡ መመርያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ “ቫይረሱን ለመከላከል የሚወጡ መመርያዎችን መተግበር የእኛም ፋንታ ነው፣ የጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ አንዘናጋ፣ በጣሙን አደራ፤” ሲሉም በትዊተር ገጻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።