አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከ4,000 በላይ መዝናኛ ቤቶችን አዘጋ
ፌዴራል ፖሊስ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ኢንስቲትዩት ለሕዝቡ ከሚያስተላልፉት መረጃ ውጪ፣ ማኅበረሰቡን የሚያደናግር መረጃ በሚያስተላልፉ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ዕርምጃ መውሰድ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል እንዳሻው ጣሰው ለመገናኛ ብዙኃን እንዳስታወቁት መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና ወረርሽኙ ፈጣንና ገዳይ መሆኑን የተረዱ ወገኖች እያስተላለፉ የሚገኙትን መልዕክትና መመርያ ተግባራዊ በማያደርጉ ላይ ዕርምጃ መውሰድ ተጀምሯል፡፡
መንግሥት ዜጎችን የመጠበቅ ግዴታም ስላለበት የሚያወጣውን መመርያ ተግባራዊ ማድረግ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ በሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ከቻሉ ዋጋ መቀነስ ወይም ባለበት ሁኔታ ለኅብረተሰቡ መሸጥ ሲገባቸው፣ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው ከአምስት ሺሕ በላይ በሚሆኑት ላይ ዕርምጃ መወሰዱን አስታውቀዋል፡፡
ለሕግ በማቅረብም የእስራት ቅጣትና የንግድ ፈቃዳቸውን እስከ ማሰረዝ የሚደርስ ዕርምጃ ሊወስድባቸው እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡
ሌላውም የኅብረተሰብ ክፍል ዓለምን እያዳረሰ ያለውን ወረርሽኝ ለመከላከል አድርግ የተባለውን ማለትም ርቀትን ጠብቆ መቆምና መቀመጥ፣ እጅን መታጠብ፣ በቤት ውስጥ መቆየትና የመሳሰሉትን ማድረግ ተገቢና ግዴታም መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሕዝብን ለሥጋትና ለፍርኃት የሚዳርጉ ሐሰተኛ መረጃዎችን እየለቀቁ በመሆናቸው፣ ለጊዜው ተደጋጋሚ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩትን በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን ተናግረው፣ በቀጣይም ዕርምጃው እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ድርጊታቸውም እንዲታቀቡ አስጠንቅቀዋል፡፡
ዓለም አንድ ሆኖና ተባብሮ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለማጥፋት እየሠራ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የራስን ፍላጎት ለማራመድና ድብቅ አጀንዳን ለማስፈጸም እኩይ ተግባር ለመፈጸም መሯሯጥ እንደማያዋጣና መንግሥት የሚወስደውም ዕርምጃ የከፋ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል፡፡ የመንግሥትን መመርያ በመከተል ትብብር እያደረጉ የሚገኙትን ወገኖችንም አመሥግነዋል፡፡
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ኅብረተሰቡን ለመታደግ ከ4,000 በላይ የመጠጥና መዝናኛ ቤቶች እንዲዘጉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ለመገናኛ ብዙኃን እንደገለጹት፣ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመግታት በርካታ ጭፈራ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች፣ ጫት ማስቃሚያ፣ አረቄና ጠጅ ቤቶች፣ ፑልና ቪዲዮ ቤቶች፣ ግሮሰሪዎች፣ መኝታ ቤቶችና ሌሎች ተዘግተዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን በሦስት ቀናት ብቻ ከ4,000 በላይ ማዘጋት መቻሉንና ይህም የመንግሥትን መመርያ ተከትሎ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡