Tuesday, December 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊኢሰመጉ በለይቶ ማቆይ ሥፍራ አስቸጋሪ ሁኔታ መታዘቡን አስታወቀ

  ኢሰመጉ በለይቶ ማቆይ ሥፍራ አስቸጋሪ ሁኔታ መታዘቡን አስታወቀ

  ቀን:

  ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከውጭ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ መንገደኞች ተለይተው ከሚቆዩባቸው ሥፍራዎች መካከል አንዱ በሆነው ግዮን ሆቴል ምልከታ ማድረጉን የገለጸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)፣ ችግሩን በብቃት ለመቋቋም አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን መታዘቡን አስታወቀ፡፡

  ኢሰመጉ ይህን ትዝብቱን ያስታወቀው ሐሙስ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ‹‹የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ሰብዓዊ መብቶችን በማይጥስ መልኩ መሆን ይገባዋል፤›› በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ አማካይነት ነው፡፡

  መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ሥፍራ እንዲቀመጡ መወሰኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ለዚህም ዓላማ በመጀመሪያ ስካይላይትና ግዮን ሆቴሎች  ቢለዩም ከመንገደኞች ቁጥር መጨመር የተነሳ ሌሎች ሆቴሎችም እንደማቆያነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

  በዚህም መሠረት ለማቆያነት ከተለዩት ሆቴሎች አንዱ የሆነውን ግዮን ሆቴልን መጎብኘቱን የገለጸው ኢሰመጉ፣ በሥፍራው በአስቸኳይ መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮችን መታዘቡን አስታውቋል፡፡

  በጉብኝቱ ወቅት በዋነኛነት የታዘባቸው ነገሮች ደግሞ በግዮን ሆቴል የሚገኙት መንገደኞች 163 ቢሆኑም፣ በሥፍራው የተመደቡት የጤና ባለሙያዎች ግን ሦስት ብቻ መሆናቸውን፣ ለመንገደኞቹም ሆነ በሥፍራው ለሚገኙ የሆቴሉ ሠራተኞችና የሕግ አስከባሪዎች ከቫይረሱ አስፈላጊ የመከላከያ ቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ አለመቅረቡን፣ እንዲሁም ሌሎች የጤና ችግሮች ያሉባቸው መንገደኞች በቂ የሕክምና ተስማሚ ምግብ በማያገኙበት ሁኔታ ላይ መሆናቸውን ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡

  ከዚህ በተጨማሪም፣ መንገደኞቹ ከተነሱባቸው አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ከመነሳታቸው በፊት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሱ ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚወሰዱ፣ በራሳቸው ወጪ በሆቴል እንደሚቆዩ በቂ መረጃ ስለማይሰጣቸው፣ እንዲሁም የሆቴል ወጪ ከአቅማቸው በላይ ስለሚሆንባቸው ከለይቶ ማቆያ ሥፍራዎች የማምለጥ ሙከራዎች መደረጋቸውን የተመለከቱ መረጃዎች እንደ ደረሱት ኢሰመጉ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

  ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን መንግሥት እየወሰደ ያለውን የመከላከል ዕርምጃ የሚያበረታታ መሆኑን በመጥቀስ፣ የሕዝብ ደኅንነትን የበለጠ ለመጠበቅ ይቻል ዘንድ ግን ‹‹በሥራቸው ምክንያት ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጫ ለሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች፣ የሕግ አስከባሪዎችና የሆቴል ሠራተኞች የመከላከያ ቁሳቁስ በበቂ ሁኔታ እንዲቀርቡ፣ ሌሎች የጤና ችግሮች ያለባቸው መንገዶች አስቸኳይ ሕክምና የሚያገኙበት መንገድ እንዲመቻችና ለመንገደኞች ከመነሻቸው በቂ መረጃ መስጠት፣ አገር ውስጥ ከገቡም በኋላ በሚመርጡት ለይቶ ማቆያ እንዲያርፉ የሚረግበት፣ አቅም ለሌላቸው መንገደኞችም መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግበት ሥርዓት ይዘርጋ፤›› የሚሉ የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦችን ኢሰመጉ አቅርቧል፡፡

  የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ በሚገኝባቸው አካባቢዎች አገልግሎቱን በማስጀመር፣ የዜጎች ስለቫይረሱ ሥርጭት መረጃ የማግኘት መብት እንዲያከብር ኢሰመጉ መንግሥትን አሳስቧል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...