Monday, March 4, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ብሔራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄና መረጋጋት ያስፈልጋል!

በብሔራዊ ደረጃ የተጀመረውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መከላከል አጠናክሮ ለመቀጠል፣ ከፍተኛ ጥንቃቄና መረጋጋት የሚያስፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነን፡፡ በዚህ አሳሳቢ ጊዜ የሚያስፈልገው ፍራቻን በማስወገድ ለተግባራዊ ዕርምጃ መዘጋጀት ብቻ ነው፡፡ በመንግሥትም ሆነ በሚመለከታቸው የጤና ዘርፍ አካላት የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችንና ማስጠንቀቂያዎችን ሳያዛንፉ ተግባራዊ ማድረግ፣ ምንጫቸው የማይታወቅ መረጃዎችንና መላምቶችን እንደወረዱ አለመቀበል፣ ለቫይረሱ መስፋፋት አመቺ የሆኑ ድርጊቶችን ከመፈጸም መቆጠብ፣ የቫይረሱ ምልክቶች የሚታዩባቸውንና የሚያጠራጥሩ ሰዎችን በፍጥነት ወደ ሕክምና ተቋማት እንዲሄዱ ማድረግ፣ ፈቃደኛ ካልሆኑም ለሚመለከታቸው አካላት ወዲያውኑ ሪፖርት ማድረግና ለጥንቃቄ የሚረዱ ማናቸውንም ዕርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆን ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ አሁን በመላው ዓለም በቫይረሱ በተያዙና በሟቾች ቁጥር ላይ በመንተራስ ከሚሰጡ ትንተናዎች በተጨማሪ፣ ከቫይረሱ ጥቃት ያገገሙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውንም ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ በቫይረሱ ላለመጠቃትና ላለመሞት ደግሞ ለጥንቃቄ ትልቅ ትኩረት መሰጠት ሲኖርበት፣ በኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ የተጀመረውን ጥረት በባለቤትነት ስሜት ማገዝ ከተቻለ ደግሞ የተጠቁትን አክሞ ማዳን እንደሚቻል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም ብሔራዊ ቀውስ እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያዊያን አገር ችግር ውስጥ ስትገባ ተባብረው ችግሩን የመመከት አኩሪ ታሪክ እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ታሪክ ወራሪዎችን ከመመከት ጀምሮ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን እስከ መመከት ድረስ ስለሆነ አሁን ደግሞ ድንበርንም ሆነ ዜግነትን፣ እምነትንም ሆነ ማንነትን፣ ማኅበራዊ አመጣጥንም ሆነ ርዕዮተ ዓለምን የማይመርጥ ቫይረስ ዓለምን እያተራመሰ አደጋ ጋርጦ ችላ ማለትም ሆነ አለመጠንቀቅ ኪሳራው ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ መንግሥት ከወዲሁ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ አቅም በፈቀደ መጠን የመከላከል ብቃትን ለማሳደግ ሕዝቡን በማስተባበር ሀብት ለማሰባሰብ ሲጥር፣ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እንዲገኝ ላይ ታች ሲል፣ ጡረታ ለወጡ የሕክምና ባለሙያዎችና በትምህርት ላይ ለሚገኙ ዕጩ የጤና ባለሙያዎች ጥሪ ሲያቀርብ፣ የለይቶ መከላከያ ማዕከላትንና ማገገሚያዎችን ሲያዘጋጅ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውሶችን ከወዲሁ ለመከላከል ወሳኝ የተባሉ ዕርምጃዎችን ሲወስድ፣ እያንዳንዱ ዜጋ የሚፈለግበትን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ መረጋጋትና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ቫይረሱ ሊያደርስ የሚችለውን ጥቃት ከወዲሁ ለመመከት ነው፡፡ ክፍተቶችና ችላ ባይነቶች ሲያጋጥሙ በመተባበር ለማረም ነው፡፡ የመረጃ ሥርጭቱ ፈጣን፣ ግልጽና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ተመሳሳይ ግንዛቤ ሲኖር በመተባበር ለመንቀሳቀስ ቀላል ይሆናል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን አደጋው የከፋ ነው፡፡

በብዙ ቦታዎች ለማስተዋል እንደተቻለው የጥንቃቄ ዕርምጃዎች በሚፈለገው መጠን አይደሉም፡፡ በተለይ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ትልልቅ ከተሞች የሚታየው ጥንቃቄ አልባ እንቅስቃሴ አስፈሪ ከሆነ፣ ለመረጃ ራቅ ያሉ ገጠራማ ሥፍራዎች ውስጥ ጥንቃቄው በምን ደረጃ እንደሚገኝ ለመገመት አያዳግትም፡፡ በተለይ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሬዲዮ ጣቢያዎችና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች እዚህ ችግር ላይ በትኩረት መሥራት ትተው፣ የታዋቂ ባለሀብቶችንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ልገሳና የታይታ ክንውኖች ላይ ቢያተኩሩ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ሕዝብ ግማሽ ያህሉ ንፁህ የመጠጥ ውኃ ማግኘት እንደማይችልና እጁን በሳሙና ለመታጠብ ብርቁ መሆኑን፣ ሰሞኑን በፋይናንሻል ታይምስ መጽሔት ላይ ባቀረቡት ጽሑፍ በማስታወቅ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ዕርዳታ መማፀናቸው አይዘነጋም፡፡ እንዲህ ዓይነት የከፋ ችግር ያለበት አገር ውስጥ ኮሮና ቫይረስ አደጋ ደቅኖ የሚዲያው አብዛኛው የአየር ሰዓት ለጥንቃቄ ካልዋለ ለምን ሊውል ነው? ቫይረሱ በአካላዊ ንክኪና በመቀራረብ እንደሚተላለፍ እየተነገረ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት በዓለም የጤና ድርጅት ከፍተኛ ማሳሰቢያና ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ፣ ኢትዮጵያ ውስጥም በሚመለከታቸው የጤናው ዘርፍ አካላትና በመንግሥት አማካይነት አደራ እየተባለ መጠንቀቅ አዳጋች ከሆነ ብሔራዊ የመከላከል ጥረቱ ይዳከማል፡፡ በተዳከመና ተስፋ በቆረጠ አቅም እንኳንስ ይህንን አደገኛ ወረርሽኝ የተለመዱ በሽታዎችንም ለመከላከል አይቻልም፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ውስጥ የሚታዩት መዘናጋቶችንና ችላ ባይነቶችን በተደጋጋሚ ትምህርት በማስወገድ፣ ለማኅበራዊ መስተጋብር በሚሰጠው ትልቅ ቦታ ምክንያት የሚፈጠረውን ውዥንብር ባላሰለሰ ጥረት በማስተካከል ብሔራዊ ጥረቱን በቁርጠኝነት ማጠናከር የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ የሚበልጥ አገራዊ ተልዕኮ የለም፡፡

ሌለው ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ አሁን ያለንበት ወቅት ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑን ነው፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባያወጣም፣ የተዛቡ መረጃዎችን በማሠራጨትና የተከለከሉ ድርጊቶችን በመፈጸም ቀውስ ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው፡፡ ብሔራዊ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ በመክተት የቫይረሱን ሥርጭት የመከላከል አቅም መፈታተን በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን አጋጣሚ ለፖለቲካ ባላንጣነት ነጥብ ማስቆጠሪያነትም ሆነ ሒሳብ ማወራረጃነት መጠቀም ከሕግም ከሞራልም አንፃር ትክክል አይሆንም፡፡ የአገሪቱ ፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ከባድ ጊዜ መተጋገዝንና ለጋራ ዓላማ አንድ ላይ መቆምን በመለማመድ፣ ለሠለጠነና ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የመንግሥትን ድንጋጌዎች በመጣስ የጫት፣ የመጠጥና የጭፈራ ቤቶችን በተለመደው መንገድ የገቢ ማግኘት ማድረግ፣ በእነዚህ ሥፍራዎች በመገኘት ለአደጋ የሚዳርጉ ድርጊቶችን መፈጸም፣ መሠረታዊ ሸቀጦችን መደበቅና ከዋጋቸው በላይ አንሮ ለመሸጥ መሞከር፣ በምግብ እህሎች ውስጥ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅሎ ማቅረብና በሚዛን ማጭበርበር የተወገዙ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ብሔራዊ የመከላከል አቅምን ለማጎልበት የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍ ሲገባ፣ በአጠቃላይ በሕዝብ ደኅንነትና ጤና ላይ አደጋ የሚፈጥሩ ድርጊቶች ላይ ማተኮር ለራስም ለአገርም አይጠቅምም፡፡ በማስተዋል፣ በእርጋታና በጥንቃቄ ይህንን ክፉ ጊዜ ለመሻገር ኅብረት መፍጠር ብልህነት ነው፡፡ የሚያዋጣውም ይኸው ነው፡፡

ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ በመወሰኑ ወደ ቤተሰቦቻቸው የተመለሱ ተማሪዎችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን መጨናነቅ ለመቀነስ ቤታቸው እንዲቆዩ የተደረጉ ሠራተኞችን፣ እንዲሁም በጎ ፈቃደኞችን በማንቀሳቀስ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩትን ጥንቃቄ አልባ ንክኪዎችንና መተፋፈጎችን በአስቸኳይ ማስቆም ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ ውስጥ የሚለቀቁ መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ሐሰተኛ መረጃዎችን በትክክለኛና በወቅታዊ መረጃዎች በመመከት፣ ጥንቃቄ ላይ ብቻ ከፍተኛ ትኩረት እንዲደረግ በቁርጠኝነት መሥራት የግድ ይላል፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልሎች በአስፈጻሚነትና በፈጻሚነት ያሉ ሹማምንትንና ሠራተኞችን ተልዕኮ አፈጻጸም በመከታተል ክፍተቶችን መድፈን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኃላፊነት ሲሆን፣ ዜጎችም የሚያስተውሏቸውን ችግሮች በግልጽ መናገር አለባቸው፡፡ አሁን የሚያዋጣው በዕውቀትና በእውነት ላይ የተመሠረተ የመረጃ ፍሰት ነው፡፡ የሐሰት ሪፖርት በማቅረብ መደናገር የሚፈጥሩ የመንግሥት ሹማምንትም ሆኑ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ሽብር የሚነዙ ግለሰቦችና የተደራጁ ኃይሎች፣ የአገርና የሕዝብ ጉዳይ በሚያሳስባቸው ሀቀኛ ዜጎች መጋለጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በከፍተኛ ሥነ ምግባርና ኃላፊነት ሙያዊ ግዴታቸውን በመወጣት፣ በቫይረሱ የተጠቁ ወገኖችን ሕይወት ለማትረፍ የሚረባረቡ ባለሙያዎችን አርዓያነት በመከተል አገርን ከተደቀነው አደጋ በብቃት ለመከላከል ማናቸውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ ብሔራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄና መረጋጋት እንደሚያስፈልግ መገንዘብም እንዲሁ!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...