ዓርብ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተገለጹት ተጨማሪ አራት ሰዎች መካከል አንዱ መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባልደረባ በመሆናቸው፣ የኅብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽነርን ጨምሮ ሌሎች ንክኪ የነበራቸው የኅብረቱ ሠራተኞች ራሳቸውን በማግለያ እንዲያቆዩ ተደረገ።
በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ አራት ሰዎች መካከል አንዱ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር መሐመት ሙሳ ፋቂ የቅርብ የሥራ ባልደረባ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፣ ኮሚሽነሩም ይህንኑ አስታውቀው በቫይረሱ መያዝ አለመያዛቸው እስኪታወቅ ድረስ ራሳቸውን ማግለላቸውን በትዊተር ገጻቸው ይፋ አድርገዋል።
የጤና ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸው ከተረጋገጠው አራት ሰዎች መካከል አንዱ የ72 ዓመት ሞሪሸሳዊ እንደሆኑ መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ከኮንጎ ብራዛቪል ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸው አስታውቋል።
ሪፖርተር ከአፍሪካ ኅብረት ምንጮቹ ማረጋገጥ እንደቻለው ግለሰቡ የኅብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ የቅርብ ረዳት ነው። ግለሰቡ የቫይረሱን ምልክቶች በማስተዋላቸው መጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረጋቸውን፣ የሕክምና ተቋሙም ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሪፖርት በማድረጉ የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎላቸው በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል።
በዚህም ምክንያት ከግለሰቡ ጋር ግንኙነት የነበራቸው የኅብረቱ ሠራተኞች ወደ ማግለያ እንዲገቡ እየተደረገ ነው። ሪፖርተር ከኅብረቱ ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው የአፍሪካ ኅብረት የጤና ማዕከል ሦስት ባልደረቦች ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል። ከኅብረቱ ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ በተጨማሪም በእሳቸው ጽሕፈት ቤት የሚሠሩ ሁለት ባልደረቦች፣ ራሳቸውን እንዲያገሉ መደረጉን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በመሆኑም እስከ ዓርብ አመሻሽ ድረስ የኅብረቱ ኮሚሽነርን ጨምሮ ስድስት የኅብረቱ ሠራተኞች ተለይተው እንዲቆዩ ተደርጓል። የኅብረቱ ሠራተኞች ወደ መንግሥት መለያ ማዕከል ሳይሆን፣ በራሳቸው ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደተደረገና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ክትትል እያደረገላቸው እንደሆነም ማወቅ ተችሏል።
ሪፖርተር ያገኘው የኅብረቱ የውስጥ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው እስካሁን ከተለዩት የኅብረቱ ሠራተኞች በተጨማሪ ሌሎች ግንኙነት የነበራቸው ሰዎችን የመለየት ሥራ በመከናወን ላይ በመሆኑ፣ ንክኪ የነበራቸው ሠራተኞች ኅብረቱ የቫይረሱ ሥርጭትን ለመከላከል ባወጣው የውስጥ መመርያ መሠረት ሪፖርት እንዲያደርጉና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት እንዲተባበሩ አሳስቧል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የማሳወቅ ኃላፊነት የኢትዮጵያ መንግሥት በመሆኑ፣ የኅብረቱ ሠራተኞችም ይህንኑ እንዲያከብሩ አስታውቋል። የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በቫይረሱ ከተያዘው የኅብረቱ ሠራተኛ ጋር ንክኪ የነበራቸው ኢትዮጵያውያን መኖራቸውን ለማረጋገጥ እየሠራ መሆኑ ታውቋል።
ባለፈው ዓርብ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠው ግለሰቦች መካከል አንዱ በአዳማ ከተማ የሚኖሩ የ61 ዓመት ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ኢንስቲትዩቱ ያወጣው መግለጫ ያመለክታል። ከእኝህ ግለሰብ የተገኘው መረጃ የውጭ የጉዞ ታሪክ እንደሌላቸው፣ ነገር ግን በሥራ ባህሪያቸው ምክንያት ከአንድ የውጭ አገር ዜጋ ጋር ግንኙነት እንደነበራቸው ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
ግለሰቡ መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. የሕመም ስሜት ሲሰማቸው ራሳቸውን አግልለው እንደቆዩና መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ወደ ጤና ተቋም የሄዱ ሲሆን፣ ተቋሙም ሪፖርት ባደረገው መሠረት በላቦራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዛቸው እንደተረጋገጠ ተገልጿል፡፡ በአሁኑ ወቅት ታማሚው በለይቶ ማከሚያ ውስጥ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ፣ ከእሳቸው ጋር ግንኙነት የነበራቸው 24 ሰዎች ራሳቸውን አግልለው ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
ሌላኛዋ በቫይረሱ መያዟ የተረጋገጠው የ28 ዓመት ኢትዮጵያዊት ስትሆን፣ የመጨረሻ ጉዞዋም መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም. እስራኤል ደርሳ የተመለሰች መሆኗን መግለጫው አስታውቋል። ከታማሚዋ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሰባት ሰዎች በክትትል ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነሱ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሌሎች ሰዎችን ማጣራት እየተከናወነ እንደሆነ መግለጫው ያመለክታል።
በተጨማሪም የ24 ዓመት ኢትዮጵያዊት በቫይረሱ መያዟን ዓርብ ዕለት የወጣው መግለጫ ያመለከተ ሲሆን፣ ግለሰቧ ምንም ዓይነት የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ እንደሌላት፣ ነገር ግን የበሽታው ምልክት ከታየባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራት መሆኑን ለማወቅ የማጣራት ሥራ ላይ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው አስታውቋል።
ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከታወቀ አንስቶ በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካይነት 718 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎባቸው 16 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ይፋ ተደርጓል፡፡