Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቧን የውኃ አሞላል በተመለከተ የያዘችውን አቋም ይፋ አደረገች

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቧን የውኃ አሞላል በተመለከተ የያዘችውን አቋም ይፋ አደረገች

ቀን:

ወደ ግድቡ የሚመጣው ውኃ 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ከሆነ የሁለተኛው ዙር ሙሌት ጅማሮ ሊተላለፍ ይችላል

በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷ በምንም ዓይነት ምክንያት እንደማይጣስ አስታውቃለች

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በውኃ ለመሙላት የምትከተላቸውን ምዕራፎችና የአሞላል ሒደቶች የተመለከተ አቋሟን ይፋ አደረገች።

- Advertisement -

በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተዘጋጀውና ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው ይፋ ያደረጉት ሰነድ እንደሚያመለክተው በዘንድሮ ክረምት የመጀመርያው ዙር የመጀመርያ ምዕራፍ ሙሌት እንደሚከናወንና በዚህም 4.9 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሚያዝ ይገልጻል።

 የመጀመርያው ዙር ሙሌት ሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ በቀጣዩ ክረምት ማለትም በ2013 ዓ.ም. የዝናብ ወቅት ለሁለት ወይም ሦስት ወራት እንደሚከናወንና 13.5 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃም በዚህ ወቅት እንዲሞላ ተደርጎ፣ የመጀመርያው ዙር ሙሌት እንደሚጠናቀቅ ከሰነዱ ለመረዳት ተችሏል።

 በዚህ ዙር የሚደረገው የውኃ ሙሌት በአጠቃለይ 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ በግድቡ እንዲጠራቀምና የመጀመርያዎቹ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ፣ እንዲሁም ሌሎቹ ተርባይኖች ላይ የኃይል ማመንጨት ሙከራ ለማድረግ እንደሚያስችል ሰነዱ ይገልጻል።

ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌትም በተመመሳሳይ በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ እንደሚከናወን፣ ይህም በግድቡ የሚጠራቀመው የውኃ መጠን 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ እስከሚደርስ መሆኑን ሰነዱ ያብራራል።

በግድቡ የሚጠራቀመው ውኃ 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ሲደርስ ግድቡ የታቀደውን የኃይል ማመንጨት ተግባር ማከናወን እንደሚችል፣ ይህንንም ከሁለት እስከ አምስት ዓመታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ ለመፈጸም ማቀዷን ያስረዳል።

በግድቡ የሚጠራቀመው አጠቃላይ የውኃ መጠን 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ እንደሆነ የሚገልጸው ሰነዱ፣ በሁለተኛው ዙር እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ከተሞላ በኋላ ቀሪው የውኃ መጠን በማንኛውም የዝናብ ወቅት እንዲሞላ እንደሚደረግ ተመልክቷል።

የመጀመርያው ዙር ሙሌት በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ሁለተኛው ዙር በምዕራፎች የተከፋፈለ የውኋ ሙሌት በ2014 ዓ.ም. ክረምት ወቅት እንደሚጀምርም ሰነዱ ያስረዳል። ሁለተኛው ዙር ሙሌት በሚጀመርበት ወቅት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ ብቻ ከሆነ፣ ሁለተኛው ዙር ሙሌት ወደ ቀጣዩ ክረምት እንዲተላለፍ እንደሚደረግ ሰነዱ ያመለክታል።

በሁሉም ምዕራፍ የሙሌት ሒደቶች በሚከናወንበት ወቅት ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ ደግሞ፣ የመጣው ውኃ ሳይያዝ በተርባይን ውስጥ ኃይል አመንጭቶ እንዲያልፍ እንደሚደረግ በሰነዱ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ይኼንን የውኃ አሞላል ሒደት የቀረፀችው የታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳያደርስ በመጠንቀቅ መሆኑን የሚያመለክተው ሰነዱ፣ ኢትዮጵያ ራስ ወዳድና ለሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ግድ የሌላት ቢሆን ኖሮ፣ 49.3 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚሆነውን የውኃ መጠን በሦስት ዓመታት ውስጥ መሙላት የምትችል መሆኑን ይገልጻል።

በግብፅ መንግሥት በኩል የተያዘው አቋምና በግብፅ ሚዲያዎች የተያዘው ዘመቻ የኢትዮጵያን በውኃዋ የመጠቀም መብት የሚክድ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ አባል ባልሆነችበት የቅኝ ግዛት ውል ለመጫን ያለመ እንደሆነም አስታውቋል። ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷ በምንም ዓይነት ምክንያት የማይጣስ እንደሆነ የሚገልጸው ሰነዱ፣ የህዳሴ ግድቡና በዓባይ ውኃ የመጠቀም ጉዳይ ለኢትዮጵያ ሞትና ሽረት መሆኑንም አመልክቷል።

 የህዳሴ ግድቡ የወኃ አሞላል ቴክኒካዊ መረጃዎችን በማምታታት ጉዳዩን ፖለቲካዊ በማድረግ ኢትዮጵያን መጠምዘዝ፣ መቼም ቢሆን ሊሳካ የማይችል ጥረት እንደሆነም ያመለክታል።

ሚኒስቴሩ ይፋ ባደረገው የውኃ አሞላል ምዕራፎችና የሙሌት ሥርዓቶች መሠረት 18.4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውኃ በግድቡ ከተያዘ በኋላ፣ ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብና ከዚያ በታች ከሆነ ወሳኙ ሁለተኛው ዙር የውኃ ሙሌት እንደማይጀመር መገለጹ ተገቢ እንዳልሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል።

በተጨማሪ ወደ ግድቡ የሚመጣው የውኃ መጠን ለቀጣይ ተከታታይ ዓመታት 31 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ቢሆን ሁለተኛው ዙር ሙሌት መቼና እንዴት ሊከናወን እንደሚችል አለመገለጹ፣ ለተቀናቃኝ ወገን የውዝግብ በር እንደሚከፍትና ግድቡ ከግማሽ በታች በሆነ አቅሙ እንዲሠራ ወይም ቀድሞ የያዘውን ውኃ ጨርሶ ኃይል ማመንጨትም የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...