Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት መኖር ያለበት ጥንቃቄ አናሳ መሆን አሳሳቢ ሆኗል

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት መኖር ያለበት ጥንቃቄ አናሳ መሆን አሳሳቢ ሆኗል

ቀን:

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረጉ ጥረቶች በበርካታ ሥፍራዎች በሚፈለገው መጠን አለመሆናቸው የጤና ባለሙያዎችን፣ የመንግሥት አካላትንና ሌሎችንም እያሳሰበ ነው፡፡

የቫይረሱ አደገኛነትና ጅምላ ጨራሽነት በብዙዎች ዘንድ ተዘንግቶ ወይም በችላ ባይነት ታልፎ፣ በብዙ ሥፍራዎች ሰዎች አሁንም መሰባሰባቸውና የተለመደውን ተግባር ማከናወናቸው አደጋ መደቀኑ እየተነገረ ነው፡፡

በመንግሥትና በጤናው ዘርፍ አካላት የወጡት መመርያዎች ተግባራዊ ባለመደረጋቸው በቤተ እምነቶች አሁንም ርቀታቸውን ሳይጠብቁ ተጨናንቀው በብዛት መገኘታቸው፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚደረገውን ጥረት መና እንዳያስቀረው እየተጠየቀ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እስከ ዓርብ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 16 መሆኑ ይፋ ቢደረግም፣ እንዲሁም መንግሥትና የሚመለከታቸው የጤና አካላት ሥርጭቱ እንዳይስፋፋ ብሔራዊ መርሐ ግብር ነድፈው የዝግጅቱን ሥራ እያከናወኑ ቢሆንም የጥንቃቄ ግንዛቤው ግን አርኪ አለመሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሥጋት የገባቸው ሰዎች የሚስማሙት ብዙዎች ዘንድ የግንዛቤ ችግር እንዳለ፣ ከዚህም ባለፈ ፈጣሪ ስለሚጠብቃቸው ብዙም እንደማይጨነቁ የሚናገሩ ቁጥራቸው ቀላል እንዳልሆነ፣ እንዲሁም ወረርሽኙ የሚያጠቃው የፈጣሪን ትዕዛዝ የማያከብሩትን እንደሆነ የሚናገሩም እንዳሉ ነው፡፡ በሌላ በኩል ማኅበረሰቡ ውስጥ ለዘመናት በቆየው መስተጋብር ምክንያት ቅርርቦችንና መነካካቶችን በቀላሉ መግታት ስለማይቻል፣ ጠንካራ የሚዲያ ዘመቻ አስፈላጊነትንም አውስተዋል፡፡

ከቤተ እምነቶች በተጨማሪ የመንግሥትን ክልከላዎች በመጋፋት በጫት መቃሚያ ቤቶች፣ በመጠጥና በጭፈራ ቤቶች፣ እንዲሁም በተለያዩ መዝናኛዎች ለአካላዊ ንክኪ የሚያጋልጡ ቅርርቦች አሁንም በብዛት እየተስዋሉ ናቸው፡፡  

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአዲስ አበባ ከተማ አደረግኩት ባሉት ምልከታ ያዩት እንዳስደነገጣቸው ተናግረዋል፡፡ የመከላከል ዕርምጃዎችንና መመርያዎችን በመተግበር ገና ብዙ እንደሚቀር አስታውቀው፣ ‹‹የሚጠጋን ቫይረስ የለም ሲሉ የነበሩ ያሉበትን እያየን አንዘናጋ፣ ምርመራ በብዛት ባለመደረጉ ትክለኛውን ሁኔታ አላየንምና በአገር ደረጃ ተቀናጅተን መዘጋጀት አለብን፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ሌላው ቀርቶ ትምህርት ቤቶች የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት ሲባል ቢዘጉም፣ ተማሪዎች እየተሰባሰቡ ኳስ መጫወታቸውና የእጅ ንክኪ ያላቸው ተግባራት ውስጥ መጠመዳቸው የችግሩን ግዝፈት ያሳያል ተብሏል፡፡

በተወሰኑ ሥፍራዎች ርቀትን በመጠበቅና ባለመተፋፈግ የትራንስፖርት አገልግሎት የመጠቀም እንቅስቃሴ ቢታይም፣ በብዙ ቦታዎች ሰዎች እንደ ወትሮው በአንድ ሥፍራ ተፋፍገው እየታዩ መሆኑ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ መንግሥት በፍጥነት ዕርምጃ በመውሰድ አሁን ያለውን አስደንጋጭ ሁኔታ እንዲለውጥ እየተጠየቀ ነው፡፡

ምንም እንኳ አስቸኳይ ጊዜ በማወጅ ሕዝቡን ለተወሰነ ጊዜ ከቤቱ እንዳይወጣ ማድረግ የራሱ የሆነ ጉዳት የሚያስከትል ቢሆንም፣ ለሁለት ሳምንት ያህል ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ በመገደብ ሊመጣ ከሚችለው መዓት አገሪቱን መከላከል ይገባል የሚሉ አሉ፡፡

የሕዝቡን የዘመናት የተለመደ አኗኗር፣ እምነት፣ አመጋገብ፣ ማኅበራዊ ግንኙነቶችና ልማዳዊ ጉዳዮች በቀላሉ ለመለወጥ የሚደረገው ጥረት የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ከሚደረገው አጣዳፊ ርብርብ ጋር አብሮ ማስኬድ ስለማይቻል ጨከን ማለት ይገባል ሲሉም ያክላሉ፡፡ ይህ የማይቻል ከሆነ ደግሞ በጎ ፈቃደኞችን በፍጥነት በማሰማራት የማስተማር ሥራውን ማጠናከር ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡ በሌላ በኩል ከዚህ ይልቅ አሁንም መንግሥትና የጤና አካላት ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ ቢያተኩሩ ይመረጣል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡

በቤተ እምነቶች አካባቢ ያለውን መጨናነቅ ከተቻለ ከእምነት መሪዎች ጋር በመነጋገር በቶሎ መፍትሔ መፈለግ፣ ካልሆነ ደግሞ ከሕዝብ ደኅንነትና ጤና ስለማይበልጥ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌን ማስከበር እንደሚያስፈልግ ምክረ ሐሳብ ቀርቧል፡፡

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ያለው ሁኔታ ይህንን ያህል አሳስቦ የፌዴራል ፖሊስ ሳይቀር ዕርምጃ እወስዳለሁ ብሎ እያስጠነቀቀ፣ በገጠርና በገጠር ቀመስ ከተሞች ውስጥ የግንዛቤ ጉድለቱም ሆነ ችላ ባይነቱ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አድመድ (ዶ/ር) ቫይረሱን ለመከላከል ከተቋቋመው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ብሔራዊ ኮሚቴ ጋር በኢንተርኔት አማካይነት ውይይት ካደረጉ በኋላ ዓርብ መጋቢት 18 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት ተጨማሪ ዕርምጃዎችን መውሰዱን አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት ትምህርት ቤቶች ለተጨማሪ 15 ቀናት መዘጋታቸውን፣ ዜጎች አሁንም ከንክኪ ነፃ ሆነው ርቀታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው፣ ሃይማኖታዊ መሰባሰቦችን ለማስቆም መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢኖረውም ሕጋዊ ዕርምጃዎች ከመወሰዳቸው በፊት ዜጎች ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እንደገና ጥሪ መቅረቡን፣ ለብሔራዊ የድጋፍ ኮሚቴ ሕዝቡ የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያበረክት አሳስበዋል፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል ሲባል አስፈላጊ ዕቃዎችና ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ የመቀጠልና ባንኮች በቫይረሱ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር ዕፎይታና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊዮን ብር ለግል ባንኮች እንደሚሰጥ፣ የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋቸውና ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ ዕቃዎችንና ግብዓቶችን ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች ባንኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስተናግዱ እንደሚደረግም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

በፋይናንስ አገልግሎት የተነሳ ገጽ ለገጽ መገናኘትና የብር ንክኪን ለመቀነስ እንዲቻል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል አማካይነት የሚደረግ ክፍያና ገንዘብ የማስተላለፍ ጣሪያውን ከፍ እንደሚል፣ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ በሚቀርብ አበባ ላይ የጣለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት እንዲነሳ መደረጉን፣ ኩባንያዎች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸው ለማስቻል የገቢዎች ሚኒስቴር የተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ሒደቱን በተለየ ሁኔታ እንዲያፋጥን እንደሚደረግ፣ በወረርሽኙ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን የሸቀጦች እጥረትና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...