Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትብርቱ ችግርን የሚያሸንፈው የበረታ መንግሥት ነው!

ብርቱ ችግርን የሚያሸንፈው የበረታ መንግሥት ነው!

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ሕገ መንግሥቱ የሕዝብ ጤንነትን ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝብ ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ብሎ ከሚጠራው አደጋ ጋር ዓለምም አገርም ጦርነት ገጥመዋል፡፡ በመላው ዓለም እየገሰገሰና ሁሉንም እያዳረሰ የሚገኘው ይህ በሽታ የሕዝብ ጤና ጥበቃ ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ ጭምር ሆኗል፡፡ የደረሰውም እየደረሰ ያለውም ዕልቂት ከሩቅ ብቻ ሳይሆን አገርም እያሳጣና መደበኛ ሕይወትን እያሠጋ ነው፡፡ በመላው ዓለም ከሁለት ቢሊዮን ሕዝብ በላይ በየአገሩ በየቤትህ ክተት፣ ከቤትህ አትውጣ ተብሎ ታዟል፡፡ የህንድ ሕዝብ ብቻውን 1.3 ቢሊዮን ነው፡፡

ኢትዮጵያም ውስጥ ከመጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ በተወሰዱ ዕርምጃዎችና በተሰጡ ትዕዛዞች ከ39 ሺሕ በላይ የአንደኛና 3,300 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ከ28 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎቻቸው ትምህርት ቤቶች ለሚያጋልጡት ንክኪና መሰባሰብ ተጠበቁ ተብለው በየቤትና በየመንደራቸው ተበትነዋል፡፡ ስምንት መቶ ሺሕ ነው የሚባለው የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪም መጀመርያ ከዩኒቨርሲቲው/ከየካምፓሱ እንዳይወጣ ታዝዞ፣ አሥራ አምስት ቀን ባልሞላው የተለወጠ ትዕዛዝ መሠረት ደግሞ ወደ ቀዬው ተመለሰ፡፡ የአገር የየብስ በሮች በሙሉ ከተወሰኑ በስተቀሮች ውጪ ተዘግተዋል፡፡ በረራዎች በእጅጉ ተቀንሰዋል፡፡ ለገቢ መንገደኞች ለዜጋም፣ ዜጋ ላልሆነም የ14 ቀን ኳራንቲን ታዟል፡፡ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች እያንዳንዱ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በሚወስነው መሠረት ቤቱ የሚቀረው መሥሪያ ቤቱ መገኘት ካለበት ተለይቶ፣ የተመላላሽ ሠራተኛው ቁጥር እንዲቀንስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወስኗል፡፡ የክልል መንግሥታትም የተለያዩ የክልከላ ዕርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማትም ምዕመናቸውን ባለአድራሻ ያደረገ ትዕዛዝም ምክርም ሰጥተዋል፡፡

ፈርዶብን ጦርነቱን የምንዋጋው ለወገን ጦር በሚያመች ዱር ገደል፣ ጋራ ሸንተረር፣ ወዘተ ሆነን አይደለም፡፡ የሕዝብ ጤና ጥበቃ መሠረተ ልማቶችን ተደጋግሞ እንደተነገረው እንደገና ሲወስን፣ ሲያፈርስ፣ ሲገነባ በመኖሩ ማፍረስ መደረትን እየደጋገሙና እየመላለሰ ከሚያመጣ አዙሪት አልተላቀቀም፡፡ ዛሬም ድረስ ዘላቂ ዲዛይን እንዲያገኝ ማድረግ አልተቻለም፡፡ የእያንዳንዱ ዘርፍ ሆነ የሁሉም የተቋም ግንባታችን (የሕዝብ ጤና ጥበቃውንም ጨምሮ) ያልተዋከበም፣ ዘገምተኛም ያልሆነ፣  ቅልጥፍናንና ልቅም አድርጎ መሥራትን ያገናኘ፣ እዚህም እዚያም ለጠፍ እያደረጉ መተውን ያስቀረና የሥራ ባህልን መሠረት ያስያዘ መሆን አልቻለም፡፡ ዛሬ ሲተላለፉ የምንሰማቸው ትዕዛዞች መመርያዎች፣ ዛሬ የምንገኝበት ሁኔታ እንዲህ ያለውን ግርግር፣ ቅብጥርጥርና ሽርጉድ ውስጥ ብቻ ገብቶ የቀረ መሆኑ ከዚህ የመነጨ ነው፡፡

በዚህ ላይና ከዚህ ጋር ተያይዞም ጭምር የልማት ዕጦታችንና ከቅርብ ጊዜ ማለትም ከሃያና ከሰላሳ ዓመት ወዲህ ደግሞ በዓለም ‹‹አንደኛ›› እየተባለ የተወተወተለት ልማት የዕለት ሕይወታችንን፣ የቀን ተቀን የባህርይ አረማመዳችንን ሊነካ አለመቻሉ አንዱ ከባድና ግዙፍ ችግራችን ነው፡፡ ‹‹የጣት ውኃ›› ማለት ዛሬም የዕለት ተዕለት ቋንቋ መሆኑ ባልቀረበት፣ የሚወርድ የቧንቧ ውኃ እንኳን በየጓዳ ጎድጓዳው ሁሉ ሊገባ፣ በገባበትምና ወርኃዊ ቢል በሚከፈልበት ቤት እንኳን በደረቀበት አገር ‹‹እጅ መታጠብ››ን የባህርይ ለውጥ አድርጎ ማምጣት፣ እንደሚባለው በጎመን በደለሉት ሆድና ጉልበት አቀበት መውጣት ነው፡፡

የግል ንፅህና ጉድለት ለአገራችን አዲስ አይደለም፡፡ ዛሬም አለ፡፡ የመንደር ዕርድ የዛሬውን አያድርገውና የኑሮ ውድነት ሳያሸንፈንና ሳይከለክለን በፊት በየዓመት በዓሉ በሽ በሽ ነበር፡፡ ክረምትና ጎርፍም ከኢሕአዴግ በኋላም ቀጥለዋል፡፡ ኮሌራን አተት ማለት የመጣው፣ አተት ተብሎ ኮሌራ መሆኑ የተረሳው፣ ኮሌራ ግን ከዓመት ዓመት በአዲስ አበባም ጭምር የሚያስጨንቅ ሥጋት የሆነው፣ ዛሬም ትናንትም በ‹‹ልማቱ›› ዘመን ጭምር ነው፡፡ የጤናማ ውኃ እጥረት፣ የደረቅና የፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ችግሮች ባሉበት አገር እንዴት አድርገን እንደኖርን እንቆቅልሻችን ነው፡፡ ገፍ እስረኛ የሚታጎርባቸውና ‹‹ማረሚያ ቤቶች›› ብለው አለቆቻችንና ሚዲያውም ጭምር ያለ ኃፍረት በሚጠሯቸው ተቋማት፣ ስደተኛም የረሃብ ተጠቂም በሚከማቹባቸው ቦታዎች ከተባሉት ችግሮችና ከትፍፍግ ኑሮ ጋር ኮሮናም ባይመጣ የኮሌራ ሥጋት አብሮን ይኖራል፡፡ በዓለም ደረጃ ያሸበረውን፣ የታላላቅ ሀብታምና ግዙፍ ኢኮኖሚዎችን እንኳን ያርበተበተውንና መሽመድመድ ሥጋት ውስጥ የከተተውን የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ጦርነት እየተዋጋን ያለነው፣ በዚህና በመሳሰሉት ችግሮችና የከፋ ነገሮች ውስጥ ሆነን ነው፡፡

እዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነንም ቢሆን ይህንን ዕልቂት መከላከል አለብን፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 93(1) በንዑስ አንቀጽ (ሀ) ‹‹የሕዝብ ጤንነትን…›› በንዑስ አንቀጽ (ለ) ‹‹የሕዝብን ደኅንነት…›› አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ የሚለው ይህንን ነው፡፡ ከኮሮና የበለጠ ሌላ አደጋ ዓለም አይታም ሰምታም አታውቅም፡፡ አሁን በደረስንበትና በምንገኝበት የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ‹‹በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል›› አደጋ የለም፡፡ የተለመደ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ጨርሶ የሌለን መሆኑንም ኮሮና አጋልጦ አሳይቶናል፡፡ በዚህ ምክንያት መንግሥት የአመራር ሚናውን በድል ለመወጣት ይችል ዘንድ፣ ሁሉም ተባብሮና ተረባርቦ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ዕርምጃ እንዲወስድ መጠየቅና ለሚወሰደውም ዕርምጃ ወጥና ፍቱን መሆን ግዴታችንንና ግዳጃችንን መወጣት፣ ሐሳባችንን መሰንዘር፣ ምክራችንን መስጠት አለብን፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለማቆም፣ እንዲሁም በበሽታው ለተጠቁትና ለተነኩት ሁሉ አስፈላጊውን እንክብካቤ ለመስጠት፣ ከዚህም ሁሉ በፊት አሁን ከገባንበት ዝርክርክ ግርግር ያልተለየው፣ የደመነፍስ፣ ከድንገተኛና የብልጭታ ስሜት የመነጨ፣ የተዘበራረቀና እርስ በርሱ የተቃረነ፣ እርስ በርሱም የሚጠፋ ዝግጅትና ዕርምጃ ለመወጣት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን ሊኖረው፣ አቻ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ዕርምጃ ሊወስድ፣ በዚያው ልክም ይህንኑ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን መሸከም የሚችል ኃላፊነት፣ ተጠያቂነትና ጨዋነት ይኖረው ዘንድ የሕዝብና የሚዲያ ዓይንና ጆሮ (ከተመሳሳይ አጣማጅ አቻ ኃላፊነትና ጨዋነት ጋር) ሊከታተለው ይገባል፡፡

ይህ ሁሉ ደግሞ የመንግሥትን በዕውቀትና በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ዝግጅትና አመራር ይጠይቃል፡፡ ከዚህም ጋር ከእሱም በማይተናነስ ሁኔታ ግዙፍ የሰውም፣ የገንዘብም የማኅበራዊ ሀብት እንደገናና መልሶ መደልደልን አስፈላጊ ያደርጋል፡፡ መንግሥት የሚቆጣጠረውን ይህንን ምላሽ የሚመራውና መነሻ መሠረት የሆነው የአገር ጉዳይ፣ የአገር ጥቅም፣ ከማናቸውም ጉዳይ በላይ ነው የሚለው መርህ ነው፡፡ ኮሮና የመኖር ወይም ያለ መኖር የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ ሁሉንም የአገርና የሕዝብ፣ የሕዝብ ውስጥ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችንና አጀንዳዎችን የሚያስገብር ጉዳይ ነው የሚለው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የትኛውም የፓርቲ ፖለቲካ፣ የጊዜያዊ ድጋፍ ሩጫ፣ ወዘተ ሥሌት በሽታውን የመከላከል ውሳኔያችንና ዕርምጃችንን ሊገድብ፣ ሊያጎሳቁል፣ ሊያልኮሰክስ ወይም ሊገታ አይገባውም፡፡

ከዚህ አኳያና በዚህም መሠረት የመንግሥት ትኩረትና የሕዝብ ዕይታና የሁሉም ርብርብ፣ ከሌሎች መካከል የሚከተሉትን ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ ጭምር የሆኑ ነጥቦችን እንዲያካትት እናሳስባለን፡፡

ጦርነቱን የመመከትና ኮሮና ቫይረስን የመዋጋት ጉዳይ በዓለም የጤና ድርጅት አጠቃላይ መርህና መሠረታዊ ዕቅድና ስትራቴጂ ላይ መመሥረት አለበት፡፡ ይህንን የምናደርገው ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት አባል ስለሆነች ወይም ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ትክክል ስለሆነ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በሽታውን፣ ወረርሽኙን የመከላከልና ጦርነቱን የመዋጋት ሥራችን የዕውር ድንብርና የእንቧይ ካብ ከንቱ ልፋት እንዳይሆን፣ ምርመራ ዋናውና ቅድሚያው የአገርና የሕዝብ ጤና ጥበቃ የዘመቻም ሆነ የመደበኛ ሥራችን ቁልፍ ነገር መሆን አለበት፡፡ በበሽታው የተያዘውን ካልተያዘው በምርመራ መለየት ካልተቻለ፣ በበሽታ የተያዘውን ሰው ከሌሎች መለየት (ለይቶ ማቆየት)፣ እንዲሁም የእሱን የግንኙነት ዱካና ሰንሰለት ተከታትሎ መመርመር ካልተቻለ ይህ ሁሉ በዕውር ድንብር ላይ ከተመሠረተ የአገር ትኩስ ዓላማ የለሽነት ይሆናል፡፡

በዚህ ምክንያት  ምርመራን አሁን ከሚገኝበት ለማንም ከማይገባ፣ ሚስጥረ ሥላሴ ከመሰለ የምርመራ አሠራራችን መውጣት አለበት፡፡ ምርመራን በሽታውን በመከላከልና ጦርነቱን በማሸነፍ ማዕዘን አኳያ ግልጽና ያንኑ ያህል ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ግንባር ቀደም ተግባር የሚቆጠብ/የምንቆጥበው ገንዘብ የለም፡፡ ከዚህም በላይ ምርመራው፣ መለየቱ፣ የልየታ ክፍሎች ዝግጅቱ፣ ለመከላከያ ልብሶች፣ ለኦክስጅን መሣሪያ ዋጋ፣ ለሌሎችም አስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች፣ እንዲሁም ለአዳዲስ ጊዜያዊ ሆስፒታል ግንባታዎች ማመቻቸቶች ነባሮችን ለዚህ አገልግሎት ምቹ የማድረግ መሰናዶዎች ግዙፍ ወጪ ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም ጥያቄው ምናልባትም ይህንን ያህል ገንዘብ ከየት እናመጣለን እንጂ፣ ይህንን ያህል ገንዘብማ ለዚህ አናወጣም አይደለም፡፡ አገር ሲወረር መልካው ሲናጋ ችግራችን መሣሪያውን የሚሸጥልን ማጣት እንጂ፣ ለመሣሪያው የሚወጣውንም ገንዘብ ለመከስከስ ከመሳሳት የመጣ አይደለም፡፡ ይህ ጦርነት ይህ ወረራ ከየትኛውም ጦርነት የበለጠ አገር ከመውረር መልካውን ከማናጋት የከፋ በሕዝብ ላይ በሕዝብ ህልውና ላይ የተቃጣ፣ የሁላችንም የመኖር ወይም ያለ መኖር ጉዳይ ነው፡፡ ሀብታችንን፣ በጀታችንን እንደገና ማደላደል የሚያስፈልገን፣ የመንግሥትንም የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን ተገቢና የግድ አስፈላጊ የሚያደርገው ይኸው ጉደይ ነው፡፡ መንግሥትም ባሳለፍነው ሳምንት እስከ ረቡዕ ድረስ ከወሰዳቸው ብጭቅጫቂና ምስቅልቅል ዕርምጃዎች የሚድነው፣ እንዲህ ያለ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ሲገባ ነው፡፡

ይህ የምርመራ ነገር እንኳንስ በእኛ አገር በኢኮኖሚያቸው ዓለምን በሚመሩና  በሚያስፈራሩ፣ በመላው ዓለምም በሚፈሩ አገሮች ጭምር ብዥታና የተድበሰበሰ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ይህ እነሱም ጋር እውነታና አስቸጋሪ የመሆኑ ጉዳይ ግን እኛ አገር የመደገሙን ጥፋት ይቅርታ የሚያሰጥ አይደለም፡፡ ባለን አቅም ጉዳዩን ግልጽ፣ ዓላማውን ደግሞ ጦርነቱን ለማሸነፍ ግብ አነጣጥረን መሥራት አለብን፡፡ እዚህ ላይ የባለሙያዎች ጩኸት፣ ንግግር፣ ትምህርትና መግለጫ ሲበዛ አስፈላጊ ነው፡፡ ስንቱ ጉድ በሚሰማበት በኢትዮጵያ አየር ሞገድ ውስጥ ስንትና ስንት የኢትዮጵያ የሕክምና፣ የጤና ጥበቃ፣ የመድኃኒት ባለሙያዎች ማኅበራት ድምፅ ሲጠፋና የት አለ ሲባል መሰማት አለበት፡፡ የዚህን የምርመራ (Testing) ጉዳይ ለማጠቃለል ተደራሽና ሁለንተናዊ የሆነ የምርመራ ሥርዓት የመዘርጋት ጉዳይ የጠራና ሁሉም የሚያውቀው ጦርነቱን በማሸነፍ ላይ ያነጣጠረ ሆኖ፣ የሕዝብ ንቃትና ግንዛቤ መሆን አለበት፡፡ ‹‹ምን ይዞ ጉዞ?›› ብሎ ሁሉም መሰናዶ መጀመር ያለበት እዚህ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የበሽታው ቁጥር አሥራ ሁለት ገባ፣ ቁጥሩም እየጨመረ ነው ማለትን እውነትና ተዓማኒ የሚያደርገውን ምርመራ በሽታውን የመከላከል የጥበብ መጀመርያ ስናደርግ ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ ነፃና በተቻለ መጠን ከፍተኛ ጥራት ያለው ሕክምናና መስተንግዶ ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት የመግታት ጉዳይ በሁሉም ዘርፍ፣ በተለይም መንግሥት በሚሰጠው አገልግሎት ግንባር በገንዘብ የሚገዛ፣ ገንዘብ ያለው ብቻ የሚያገኘው አገልግሎት መሆን የለበትም፡፡ መብት ነው፡፡ ረቡዕ መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የተፈጠረውን የኤርፖርት ‹‹ግርግር›› እና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አሁንም በለውጡና በሽግግሩ ወቅት አልቀር ብሎ ያስቸገረ የመንግሥትን ዳፍንታም ‹‹እኔ ብቻ ልክ›› ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ ባይነትና ድንቁርና ነው፡፡ የኳራንቲን ወጪ ኃላፊ ልክ እንደ የዓቃቤ ሕግ ወጪ፣ የእስር ቤት ወጪ የመንግሥት ወጪ ነው፡፡ የሕዝብ ጤና ጥበቃ አገልግሎት ለግለሰብ ባለ ገንዘቦች የሚቸርቸር ሸቀጥ አይደለም፡፡ በዕለቱ የተፈጠረው ግርግር መነሻ ግን ይህ ብቻ ሳይሆን፣ መንግሥትን ከቫይረሱ ይልቅ እየተፈታተነው ያለው ዝርክርክነትና በዕውቀት አስቀድሞ በማሳወቅ ላይ ያልተመሠረተ የዘፈቀደ አሠራር ነው፡፡ ደግነቱ ቫይረሱ ገብቶ የትግል አንድነታችንን ስላያያዘው እንጂ (ያዝልቅልን የሚባል ፀጋ ነው) ከዚያ በፊት ቢሆን ኖሮ ስንትና ስንት ቄንጠኛ የአፀፋ ፕሮፓጋንዳ የሚሠራበት ቅሌትና ጥፋት በሆነ ነበር፡፡

ሌሎችም በመንግሥት የሥልጣን አካላት የአስተዳደር መሥሪያ ቤቶችና በኃላፊዎቻቸው ጊዜያዊ መልካም ፈቃድና በጎ ምኞት ላይ ሳይሆን በሕግ ላይ የተመሠረቱ፣ በሕግ መደንገግ ያለባቸው፣ የባለሙያዎችን፣ የባለጉዳዮችን፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላትን ነፃ ምክርና አስተያየት እንዲሁም አቋም ያካተቱ ዝርዝር ጉዳዮች ብዙ ናቸው፡፡ ከተራውና ከምስኪኑ ፀጉር አስተካካይ እስከ ባለ አምስት ኮከብ ያሉ ሆቴሎችንና የመዝናኛና የመስተንግዶ ተቋማትን  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዘግቶ፣ ወይም በገበያቸው ላይ ክልከላ አውጆ ረሃብተኛውንና የማይጠረቃውን የመንግሥት የገቢ ግብር መሥሪያ ቤት ባህርይና አሠራር ባለበት ቀጥል ማለት አይቻልም፡፡ ሕመምተኞችን እንከባከባለን ማለት የመንግሥትም ሆነ የግል ዘርፉን የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ በተለይም የሕመም ፈቃድ ሕግ፣ እንዳለ ትቶ የሚሞከር ሥራ አይደለም፡፡

የእስረኞች አያያዝ መብት ፖለቲካው ሲከፈት፣ ፈታ ሲልና ተላላፊ በሽታ በእኛ ላይ ሲሠለጥን ብቻ ደንግጠን የምናየው፣ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አደራ ብቻ አይደለም፡፡ የታጎሩ እስረኞች የሚገኙባቸው ተቋማት የመስተንግዶ አቅም እንደ አገር የሕዝብ ትራንስፖርት ማጓጓዣዎች እንኳን (በተግባር ግን እንደሚጣሰው) የሕግ ገደብ የለውም፡፡ እስረኞች እንኳንስ ገና ያልተፈረደባቸው ይቅርና ፍርደኞችም ቢሆኑ ከገቡ በኋላ የተቆለፉበት ቤት መክፈቻ ቁልፍ ተወርውሮ የሚጣልባቸው ‹‹የምድር እርኩሳን›› አይደሉም፡፡ ይህን የኢትዮጵያ የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱ ድቅድቅ ጨለማ የሆነውን ገመናችንን ማረምና ከእሱም ጥፋታችን መመለስና መራቅ ያለብን የአገር የአስቸኳይ ጊዜ አጀንዳ ሲመጣ አይደለም፡፡

አሁን የገባንበት የሚያስገምትና አፀፋዊ ፕሮፖጋንዳ መሠረት የሚቻልበት ነውር ውስጥ የገባነው የዘወትር ግዴታችንን ባለማክበራችን፣ 25 ዓመት የሞላውን የሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት መብቶችና ነፃነቶች ላይ ደንታ ቢስ በመሆናችና ነው፡፡ ጭራሹንም ከእነሱ ጋር ባለመተዋወቃችን ነው፡፡ መያዝና ማሰር የወንጀል የፍትሕ ሥርዓቱ ‹‹የጥበብ መጀመርያ›› አይደለም፡፡

ከዚህ በላይ የተገለጹት በተለይም የመንግሥትን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ሥልጣን የሚመለከቱ ጉዳዮች፣ በሕግና በየዘርፍ ዘርፋቸው በዝርዝር መደንገግ አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የአንቀጽ 93 የሕዝብ ጤንነትን ወይም የሕዝብ ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት ድንጋጌ በገዛ ራሱ ተቀባብሎ የሚጠብቅና ተፈጻሚ የሚሆን አይደለም፡፡ ሕግ ማውጣትን ይጠይቃል፡፡ የዚህ ባለቤት ይህን የመሰለ የአስቸኳይ ጊዜ ሥልጣን እፈልጋለሁ፣ ያስፈልገኛል የሚለው በእርግጥም የሚያስፈልገው የአገሪቱ ከፍተኛ አስተዳደራዊና አስፈጻሚ አካል ማለትም መስተዳድሩ ነው፡፡ መስተዳድሩ ይህን ማድረግ የሚችለውና የሚፈቀደው ግን በመግለጫና በተብላችኋል ማስታወቂያ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን ያጋጠማት ፈተናና አዲስ ነገር ዓለምን፣ ዋና ዋና አንደኛ፣ ሁለተኛ እየተባባሉ የተፈረጁትንም ጭምር አጋጥሟልና በዚህ ረገድ ጉልበታችንን፣ አቅማችንንና ዕውቀታችንን አሰባስበን እንደ ኮሎኒያሊስቶች ጦርነት ጊዜ፣ እንደ ረሃቡ ጊዜ መረባረብ አለብን፡፡ ዛሬ ደግሞ ከምንጊዜውም የበለጠ ፖለቲካዊ ሁኔታ አለ፡፡ በለውጡ ውስጥ ሳይቀር እንደ እባብ ካብ ለካብ የሚተያዩት የፖለቲካ ኃይሎች ከሞላ ጎደል በዚህ በሽታ ዙሪያ አንድ ላይ በገጠሙበት ወቅት፣ መንግሥት ጊዜ ማባከን የለበትም፡፡ አስቸኳዩንና ድንገተኛውን የከፋ ጊዜ ግዳጅ በሚመጥንና ኃላፊነትና ተጠያቂነት በሚገዛው የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ ይወጣው፡፡ ደግሞም አገር የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ የግድ መግባት ያለበት፣ ወደፊት ግን በአስቸኳይ መወሰድ ያለባቸውን ዕርምጃዎች በሕግ ለማወጅ ብቻ ሳይሆን እስካሁን በተበጣጠሰ መልክ የተወሰዱ ዕርምጃዎችንም መውሰድ እችላለሁ ማለት የሚቻለው፣ የዚህ ዓይነት ሥልጣን አስቀድሞ በሕግ ሲያገኝ ነው፡፡ እናም ችግሩ ሲበረታ፣ ችግሩን አሸንፈውና ድል አድርገው የሚወጡት የበረቱት ናቸው፡፡ ይህን ብርታት ከጨዋነት ጋር ለመቀዳጀት ደግሞ ተገቢውን ሥልጣን በሕግ ማግኘትና መወሰን ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...