የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፍጥነት የመዛመቱና ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በዓለም የሚገኙ ሰዎችን በማዳረስ በሺዎች የሚቆጠሩትን ለሞት አብቅቷል፡፡ አሁንም በመዛመት ላይ ይገኛል፡፡ የወረርሽኙ አስፈሪ ሥርጭት ግን የሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፍ አልፎ ኢኮኖሚያዊ ጥቃቱም ከሚገመተው በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡ አብዛኞቹን የበለፀጉ አገሮችን እያመሰ የሚገኘው ኮሮና፣ ወደ አፍሪካና ሌሎች ድሆች ሕዝቦች የሚያደርገው ጉዞ እያየለ ሲመጣ ሊያደርስ የሚችለው ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡
ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዓለም አቀፋዊ ትስስር ያላቸው በመሆናቸው የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት እየተመታና እየታመሰ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፣ በርካታ አገሮችን አስቸኳይ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ፣ የንግድ ዘርፍ ድጋፍ እንዲሁም ሌሎች የማገገሚያ ዕርምጃዎች ከወዲሁ እየተዘረጉ ነው፡፡ አሜሪካ የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመከላከልና ኢኮኖሚዋን ለመታደግ የ2.2 ትሪሊዮን ዶላር የአደጋ ጊዜ በጀት አፅድቃለች፡፡ ሌሎችም በርካታ አገሮች ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያም ከጥቂት ሳምንታት በፊት በጊዜያዊነት 300 ሚሊዮን ብር መድባ ነበር፡፡ ይህ ለበሽታው መከላከያነት የተመደበው ገንዘብ ብዙም ሳይቆይ ወደ 500 ሚሊዮን ብር እንዲያድግ ቢወሰንም፣ የበሽታው አያያዝና ወደ ኢትዮጵያ ያቀናው ዱካው ቀስ በቀስ እየጠነከረ በመምጣቱ ሳቢያ፣ ኢኮኖሚውም ከወዲሁ አጣብቂኝ ውስጥ የመግባቱ ጉዳይ የማያጠያይቅ ሆኖ በመገኘቱ በድጋሚ አምስት ቢሊዮን ብር በጀት እንዲመደብ ተደርጎ ነበር፡፡ ወረርሽኙ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየደቆሰ መሆኑ ከየዘርፉ ከተገኙ መረጃዎች የተገነዘው መንግሥት፣ በባንኮች በኩል ለግሉ ዘርፍ ድጋፍ የሚውል ከፍተኛ ገንዘብ ለመመደብ ተገዷል፡፡
ዓርብ፣ መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ኢኮኖሚውን ከመደገፍ አኳያ የተላፈው ውሳኔም ይህንን ያመላከተ ነበር፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተገለጸው የመንግሥት ውሳኔ፣ እየተስፋፋ ካለው ችግር አንፃር የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ሊገጥማቸው ለሚችለውና እየገጠማቸው የሚገኘው ችግር ዕፎይታ ሊሰጣቸው የሚችል ድጋፍ በባንኮች በኩል እንዲያገኙ ለማስቻል የተላለፈ ነበር፡፡ የግል ባንኮች ለንግድ ተቋማትና አምራቾች የብድር መክፈያ የማራዘሚያና የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጡ መደረጉ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 15 ቢሊዮን ብር ለግል ባንኮች እንዲያቀርብ ሲወሰን፣ ይህም ከብድርና ከብድር አመላለስ ጋር ያለውን ክፍተት በተወሰነ ደረጃ ለመቅረፍ እንደሚያውሉት የሚጠበቅ ነው፡፡
እንዲህ ያለው ውሳኔ በመልካም የሚታይ ቢሆንም ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ከሚታሰበው አንፃር ግን በቂ ላይሆን ቢችልም፣ በዚህ መጀመሩ ትልቅ ነገር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ውሳኔ የተደረሰባቸው ቀናት ታይተው ተጨማሪ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ካሉ ውሳኔ ይሰጥባቸዋል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ኢኮኖሚውን በተመለከተ ከተላለፉ ውሳኔዎች መካከል አምስት ቢሊዮን ብር ከገንዘብ ሚኒስቴር ተመድቦ ለተለያዩ ዕቃዎችና አቅርቦቶች ግዥ የሚውል ነው፡፡ ይህንን ገንዘብ የግል ባንኮች እንዲያውሉ የሚጠበቀው ደንበኞቻቸው ያለባቸውን የገንዘብ ችግር ተገንዝበው የብድር ዕፎይታን በመስጠት የመክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙላቸው፣ ወለድ ከማስከፈል፣ ኮሚሽን ከመጠየቅና ከመሰል የባንክ አገልግሎቶች የሚሰበስቡትን ክፍያ ለጊዜው እንዲገቱ ለማድረግና የገንዘብ አቅርቦት ችግር እንዲቃለል ለማስቻል፣ በዚህም ሳቢያ ኢኮኖሚው እንዲረጋጋ ታስቦ የተወሰደ ዕርምጃ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች፣ ለግል ባንኮች እንዲውል የተወሰነው 15 ቢሊዮን ብር፣ ከዚህ ቀደም በ27 በመቶ የቦንድ ግዥ አማካይነት ብሔራዊ ባንክ እጅ ተሰባስቦ ከሚገኘው ገንዘብ ላይ ለባንኮች እንደሚከፋፈል የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ በቅርቡ በኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር በኩል የግል ባንኮች ካለባቸው የገንዘብ አቅርቦት ችግር በመነሳት ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው፡፡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለባንኮች ተመላሽ ይደረግ የነበረው ገንዘብ በኮሮና ምክንያት ቀድሞ እንዲደርሳቸው እንዲደረግ ተወስኖላቸዋል፡፡ ባንኮች ንግድ በተቀዛቀዘበት ወቅትና የዓለም ኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት ይህን ያህል ገንዘብ ማግኘታቸው እንደሚጠቅማቸው ኃላፊው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ከኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ባሻገር፣ ለኮሮና ቫይረስ መከላከያ ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡና ለዚህ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ባንኮች ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያቀርቡም ታዘዋል፡፡
በፋይናንስ አገልግሎት ሒደት ወቅት የገንዘብ ሽክርክሪትና ንክኪን ለመቀነስ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል አማካይነት የሚደረገውን የክፍያና የገንዘብ የማስተላለፊያ ጣሪያ ከፍ እንዲያደርግ ተወስኗል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ አሁን ካለው ችግር አንፃር በሞባይል፣ በኢንተርኔትና በሌሎችም የኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች አማካይነት የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ እንደየባንኮቹ አቅምና ፍላጎት ገደብ ነበረበት፡፡ የጥሬ ገንዘብ ንክኪን ለማስቀረት ባንኮች ገደቡን በማንሳት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለምሳሌ በኢንተርኔት አማካይነት ለሚፈጸም የገንዘብ ዝውውር፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚፈቅደው መጠን 100 ሺሕ ብር ሲሆን፣ አሁን ግን ይህንን ከፍ በማድረግ የገንዘብ ዝውውሩን ያለንክኪ እንዲከናወን የማድረግ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል ተብሏል፡፡ በወኪል ባንክ አግልግሎት አማካይነት ማንቀሳቀስ የሚቻለው የገንዘብ መጠን 25 ሺሕ ብር ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ የዚህንም ጣሪያ ያነሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረበው ሌላው ውሳኔ፣ ባለፈው ሳምንት ከኢትዮጵያ አበባ አምራቾችና ላኪዎች በኩል ለመንግሥት በቀረቡ የድጋፍ ጥያቄዎች ላይ አፋጣኝ ምላሽ የተሰጠበት ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው የአበባ ምርት ላይ አስቀምጦት የነበረውን ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ለጊዜው እንዲነሳ ተወስኗል፡፡ አበባ ላኪዎች አሁን ካለው ዓለም አቀፍ የአበባ ገበያ መንኮታኮት በመነሳት ባለፈው ሳምንት ካቀረቧቸው ጥያቄዎች ውስጥ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ እንዲነሳላቸው ያቀረቡት አንደኛው ጥያቄያቸው ነበር፡፡
ይኸውም በዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ መመርያ መሠረት፣ አንድ ኪሎ አበባ ከ3.87 ዶላር በታች መሸጥ እንደማይቻል ተደንግጎ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ኩባንያዎች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸውም፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ያስቀመጠው የተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ሒደት በተለየ አሠራር እንዲፋጠንላቸው እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
ከዚህ ባሻገር በኮንትሮባንድ መልክ የሚወጡ ዕቃዎች በተለይም ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ ገቢ የሚደረግበት መንገድ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡
በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የተላለፈው ውሳኔ የብዙዎችን ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ተጨማሪ ዕርምጃዎች ካስፈለጉ ይህ ዕርምጃ ከወዲሁ አሳታፊ በሆነ መንገድ መወሰድ አለበት ብለዋል፡፡
አንድ የባንክ ባለሙያ እንደገለጹት፣ አገር ማዳን ሥራ ውስጥ የሚገኘው መንግሥት ያስተላለፈው ውሳኔ ተገቢና ከዚህም በላይ የሚጠበቅ የማነቃቂያና የድጋፍ ዕርምጃ ነው ብለውታል፡፡ ኢኮኖሚው ችግር ውስጥ በመሆኑ ባንኮችም በዚህ ወቅት ግባቸው ትርፍ ሳይሆን፣ ቢዝነሱ የበለጠ የማይጎዳበት አሠራር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ቢያንስ ለሁለት ወይም ለሦስት ወራት የሚቆይ የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ ላይ ቅናሽ የማድረግ ዕርምጃና መሰል አካሄዶችን ሊተገብሩ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡
የብድር ወለድ ማስከፈያ ምጣኔ ላይም ቅናሽ ማድረግ ካስፈለገ ይህንኑ ዕርምጃ በመተግበር የኢኮኖሚ ቀውስ እንዳይከሰት አስተዋጽኦ በማድረግ ባንኮችም የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ ከመንግሥትም ተጨማሪ ዕርምጃዎች እንደሚጠበቁና ከሥር ከሥር ክትትል በማድረግ የማረጋጊያና የማነቃቂያ ሥራዎችን በመሥራት ኢኮኖሚው ከመሥመር እንዳይወጣ መሥራት እንደሚገባ አክዋል፡፡
እንደ ኬንያ ያሉ አገሮች በተመሳሳይ ችግር ቫት ቀንሰዋል፣ ኮርፖሬት ታክስን አውርደዋል፡፡ የሠራተኛ ታክስም እንዲቀንስ አድርገዋል፡፡ ይህ ኢኮኖሚውን ለመጥቀም ከሆነ እዚህም ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ይኼ መሆኑ የመንግሥትን ገቢ ሊቀንስ የሚችልም ቢሆንም ያለንበት ወቅት ሁሉም ወገን የሚጎዳውን እየተጎዳ የተሻለ አገራዊ ጠቀሜታ እንዲኖር ተባብሮና ተደጋግፎ መሥራት የግድ በመሆኑው ብለዋል፡፡
መንግሥትም ለዚህ ዓይነት ጉዳይ ባቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ የፋይናንስ ዘርፉን ባለሙያዎች አሳትፎ የተሻለ አማራጭ እንዲኖር ዕድል መስጠት እንዳለበትም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡