Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ከ7,000 በላይ የንግድ መደብሮች መታሸጋቸውንና ነጋዴዎች መታሰራቸውን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኮሮና ቫይረስ ሰበብ ምርት በመደበቅ፣ በሕገወጥ መንገድ በማዘዋወርና ዋጋ በማናር የተሳተፉ ብሎም በወንጀል የተጠረጠሩ ነጋዴዎችን እንዳሰረና ከ7,300 ያላነሱ መደብሮችን እንዳሸገ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታዎቹ አቶ እሸቴ አስፋውና አቶ ተካ ገብረየሱስ በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልሎች ጭምር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዱ የንጽህና ቁሳቁሶችን ጨምሮ የምግብ ሸቀጦችን ሆነ ብለው በመደበቅና ከሚገባው በላይ ዋጋ በማናር ሲያግበሰብሱ የተደረሰባቸው ነጋዴዎች፣ ከዚህ ተግባር አልፈው ባዕዳን ነገሮችን በመቀየጥ፣ ምንም ጥቅም የማይሰጡ ውህዶችን እንደ ሳኒታይዘርና ሌሎችም መከላከያዎች እያስመሰሉ ሲሸጡ የተያዙ ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ 

የጥራትና ሬጉላቶሪ ዘርፍን የሚመሩት አቶ እሸቴ እንዳብራሩት፣ በአዲስ አበባ ከ1,400 በላይ ነጋዴዎች ዋጋ በማናርና ሸቀጦችን ሲደብቁ ተደርሶባቸው መደብሮቻቸው ታሽገውባቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ1,150 ያላነሱት ለሕግ መቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአማራ ክልል 1,800 መደብሮች ሲታሸጉ፣ 34 ነጋዴዎች ታስረዋል፡፡ በኦሮሚያም ከ1,792 ያላነሱ መደብሮች ሲታሸጉ፣ 30 ነጋዴዎች መታሠራቸው ተጠቅሷል፡፡ በደቡብ ክልል ከ1,000 በላይ መደብሮች ታሽገው ንግድ ፈቃዶቻቸው እንደተሰረዙባቸው ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡

በትግራይ 111፣ በአፋር 610፣ በቤንሻንጉል 213፣ በጋምቤላ 34፣ በድሬዳዋ 209፣ በሶማሌ 29፣ በሐረሪ 9 መደብሮች ሲታሸጉ፣ በአፋር 78 እና በሶማሌ 23 ነጋዴዎች መታሰራቸው ታውቋል፡፡

በአጠቃላይ ከ50 እስከ 100 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ አልፈው፣ የምርት ጥራት በማጓደላቸው፣ የሚዛን ቅናሽ በማድረጋቸው፣ ያለደረሰኝ በመሸጣቸውና ሐሰተኛ ደረሰኝ በመጠቀማቸው ብሎም ምርት በገፍ ደብቀው በመገኘታቸው ዕርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል አብዛኞቹ መደብሮች ዳግም እንዲከፈቱ መደረጋቸው ሲገለጽ፣ ይኸውም ነጋዴዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት ይቅርታ በመጠየቃቸውና ዳግም በእነዚህ መሰል ተግባራት እንደማይሰማሩ በፊርማቸው በማረጋገጣቸው ጭምር በማስጠንቀቂያ መከፈታቸውን አቶ እሸቴ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ እስካሁን ከነበረው ተግባራቸው ሳይማሩ በሕገወጥ የንግድ ተግባርና ሕገወጥነት ሥራ ውስጥ የሚገኙት ላይ ጫን ያለ የሕግ ማስከበር ዕርምጃ እንደሚወስድ የገለጹት አቶ እሸቴ፣ ‹‹ነጋዴ የሚኖረው ሸማች ሲኖር ነው፡፡ አሁን ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ትዝብት ላይ የሚወደቅበት ጊዜ ነው፤›› በማለት ከ2.2 ሚሊዮን ያላነሰ ቁጥር ካለው ነጋዴ ውስጥ ሥነ ምግባር የጎደላቸው አካላት ከድርጊታቸው ካልታቀቡ መንግሥት ጠንካራ ዕርምጃ እንደሚወስድባቸው አስጠንቅቀዋል፡፡

የምርት እጥረት የለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በተለይም መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች ከሚባሉት ውስጥ 650 ሺሕ ኩንታል ስንዴ፣ 40 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት እንዲሁም 300 ሺሕ ኩንታል ስኳርም እየገባ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡ ገበሬውም የጥራጥሬ፣ የእህል፣ የአትክትልና ሌሎችም ምርቶችን በአግባቡ እያቀረበና የምርት እጥረትም እንደሌለ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቋቋመው ግብረ ኃይል ተዟዙሮ መመልከቱን ገልጸዋል፡፡

የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የጨርቃ ጨርቅና ኬሚካል ዘርፉን የሚመሩት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ በበኩላቸው፣ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸውንና ከገበያም የታጡትን የሳኒታይዘር ምርቶች፣ የፊት መሸፈኛ ጭንብሎችና የእጅ ጓንቶችን እጥረት ለመቅረፍ የአገር ውስጥ አምራቾችን ያሳተፈ እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ከስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘ 750 ሺሕ ሊትር አልኮል (ቴክኒካል የሚባለው) ለ13 ፋብሪካዎች መሠራጨቱንና ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥም ከ200 ሺሕ ሊትር በላይ የሳኒታይዘር ምርት እንደ ኢፋርም ባሉ አምራቾች አማካይነት ተመርቶ ለሚመለከታቸው አካላት መከፋፈሉን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥም የምርት እጥረቱ እንደሚቀረፍ አረጋግጠዋል፡፡ ምንም እንኳ በስግብግነታቸው የኮሮና ወረርሽኝ ያደናገጠውን ሕዝብ ለመበዝበዝ የተሽቀዳደሙ ነጋዴዎችና አምራቾች የመታየታቸውን ያህል፣ ከምርታቸው እስከ 20 በመቶ ለተቸገሩ፣ ደራሽ ለሌላቸው የኅብረተሰቡ ክፍሎች እንደሚያውሉ የገለጹ አምራቾች፣ ለጋሾችና በጎ አድራጊ ነጋዴዎች መታየታቸውንም አቶ ተካ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች