ከመቼውም ጊዜ በላይ አስቸጋሪና አደገኛ ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ የዓለም ቀውስ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ መላ የታጣለት አስከፊው በሽታ ለአራት ወራት ቀስ እያለና እያሰለሰ የዘረጋው ወጥመድ ለኢትዮጵያም ለተቀረው አፍሪካም ሳንካ ሆኖባቸው 46 ያህሉን እያስጨነቃቸው ይገኛል፡፡ በጠቅላላው ከ140 በላይ አገሮችን አዳርሷል፡፡ የዓለማችን ኃያላንና ሀብታም አገሮች ለኮሮና ተንበርክከዋል፡፡
ወረርሽኙ የአገሮችን ገበና አደባባይ አውጥቶታል፡፡ አንዳንዶች የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በዕርዳታ የተሰጡ ቁሳቁሶችን ጠልፈው ሲያስቀሩ ወይም በስርቆት ሲያስቀሩ መታየታቸው ተዘግቧል፡፡ መነሻና መድረሻው ያልታወቀው ይህ በሽታ፣ መሪውን ከተራው፣ ባለሀብቱን ከድሃው የማይለይ አብረክርክ አስከንዴ ሆኗል፡፡ የዓለም የሥልጣኔ ጥበብና መራቀቅ ለበሽታው መገታት አልፈየዱም፡፡ እንደምንሰማው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበሽታው ተለክፈው ሌሎችን እንዳይበክሉ ተገልለው ይገኛሉ፡፡ እሳቸው ብቻም ሳይሆኑ ባለሟሎቻቸውም ክፉ ዕጣው ደርሷቸዋል፡፡ ታላላቅ የጥበብ ሰዎችም በበሽታው መያዛቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡ ዓለም ለዚህ ዓይነቱ የጭንቅ ጊዜ የሚሆን መላ የጠፋት መስላለች፡፡ በየቦታው የዕርዳታ ጥሪዎች ይስተጋባሉ፡፡ የአልጋ፣ የኦክስጂን፣ የአየር ማቀዝቀዣ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የተህዋስያን መከላከያ ቁሳቁሶች እጥረት የዓለም አገሮች ራስ ምታት ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም ከፍተኛ የታማሚዎችን ቁጥር የያዘችው አሜሪካ ታላላቅ ከተሞቿ በእነዚህ ችግሮች መላወሻ አጥተዋል፡፡ አሳዛኟ ጣልያን የሺዎች ዜጎቿን ህልፈት፣ የብዙዎች ሺዎቿን የአልጋ ቁራኛነት ትቋቋምበት አቅም አጥታ በሐዘን የተቆራመደች የሙታን መንደር መስላለች፡፡ ታላላቆቹ የዓለም ውብ ከተሞች የሞት ጥላ ያጠላባቸው፣ ነዋሪዎቻቸው መቅሰፍት በደጃቸው የሚያንዣብብባቸው ታዳኞች ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያም የዚህ ክፉ ዕጣ ተካፋይ ሆናለች፡፡ በጎዳናዎቿ የሚርመሰመሰው ሕዝቧ በቤቱ እንዲከተት እያስጠነቀቀች ትገኛለች፡፡ ትምህርት ቤቶቿ ለአንድ ወር እንዲዘጉ አስጠንቅቃለች፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ ግድ ካልሆነ በቀር በሥራ ገበታው እንዳይገኝ አውጃለች፡፡ ቤቱ እንዲከተት አስጠንቅቃለች፡፡ በዓለም የወረደው ማዕበል የኢትዮጵያን ድንኳኖችም እየዞራቸው ይገኛል፡፡
በየደቂቃው የሚሰማው የወረርሽኙ መስፋፋት ያርዳል፡፡ ኢትዮጵያም የወረርሽኙ ሥጋት ፋታ አሳጥቷታል፡፡ ሰቀቀኑም በየዕለቱ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የመንግሥት ተከታታይ ዕርምጃዎችም ይህንኑ ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን ፈተና ምን ያህል እንደሚከብዳቸው እንዴት እንደሚወጡት መገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ ምኞታችን ከከፋ ሁሉ ይሰውረን ነው፡፡ ክፉውን ያርቅልን ቢሆንም፣ አያያዛችን ግን እንደምንሰማውና እንደምናየው አስፈሪው ሰቆቃ ያሳቀቀን አንመስልም፡፡ ከቀን ቀን የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ‹‹ብልህ ከሰው ይማራል›› የሚለውን ብሒል በተግባር የምንተገብርበት ወቅት አሁን ነውና መዘጋጀቱ በሕይወት ለመቆየታችን ዋስትና ይሆናል፡፡
አደጋውን ለመቀነስ ጊዜ ተሰጥቶናል፡፡ በሌሎች የሚደርሰውን ዓይተናል፡፡ ስለዚህ ተባብሮ፣ ተደማምጦና ተቻችሎ ከመራመድ ውጪ ተስፋችን የተመናመነ ነው፡፡ አደጋውን ለመቀነስ በየአቅጣጫው ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡ ውጤት የሚኖራቸው ግን ዜጎች የመጣባቸውን አደገኛ ፈተና ተገንዝበው ሲተባበሩ ብቻ ነው፡፡
ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ እንዲተገበሩ በተከታታይ የተደረጉ ጥሪዎች፣ የተላለፉ መልዕክቶች በትዕዛዝ መልክ የወረዱ መመርያዎች ምን ያህል ተተግብረዋል? ተብሎ ሲታይ ግን ብዙዎች ችግሩ በቅጡ የገባቸው አለመሆኑን ነው፡፡ ነገ እየታየን አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ የሚደረግ የራስ ጥንቃቄ ተደምሮ ሊያስገኝ የሚችለውን ውጤት አልተገነዘቡም፡፡ ተጠንቀቁ ራሳችሁን ጠብቁ የሚለው ወሳኝ መልዕክት ወደ ውስጥ አልገባም፡፡
ለሳምንታት ተቆጥቦ ረዥሙን ጊዜ እንድንጠቀምበት እየቻልን አይደለም፡፡ ስዘሊህ እስካሁን ባልተገበርናቸው መከላከያ ዘዴዎች የምንከፍለው ብዙ ሊሆን መቻሉን ሳንዘነጋ ከዚህም በኋላ ላለው እስካልበረታን የገጠመንን መከራ ለማለፍ በብዙ ልንፈተን እንችላለን፡፡ ይህም ቢሆን ግን አሁንም ተባብሮና ተደጋግፎ ይህንን ችግር ለማለፍ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መተባበር የሚመጣውንም ችግር ለመቀነስ የእያንዳንዳችን አስተዋጽኦ የግድ ይላል፡፡ በሌላ አነጋገር አገር ጦርነት ላይ ነችና ሁላችንም በተጠንቀቅና በጥንቃቄ ዘብ መቆም አለብን ማለት ነው፡፡ ይህ ጦርነት ግን እንደቀድሞ ታሪካችን በሽለላና በፉከራ ከየአቅጣጫው ተሰባስበን በጦር መሣሪያ የምንመልሰው አይደለም፡፡ የአሁኑ ጠላት ይለያል፡፡ አደብ ገዝቶ መቀመጥን ይጠይቃል፡፡ ለጥንቃቄ ከባለሙያዎች የሚሰጠንን መተግበር ነው፡፡ ፉከራና ሽለላ አሁን ላለንበት ጦርነት አይሆንም፡፡ ችግር ቢመጣ ችግሩን ለመቅረፍ ወይም ጥፋቱን ለመቀነስ ያለስስት ድጋፍ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ አንዳንዴ እንደሚሆነው በአንድ ሰው መስዋዕትነት ሌላው የሚረማመድበት ዕድል የለም፡፡ ነግዶ ማትረፍ፣ ወልዶ መሳም፣ አስተምሮ ማስመረቅና ለፍቶና ጥሮ የዕለት ጉርስን ለመሸፈን ከታሰበ ይችን ጊዜ በትንሽ መስዋዕትነት ለማለፍ የሚያስችል ቅን ልቦና ሊኖረን ይገባል፡፡ አሁን ምርመራ ይጀመር ሲባል ከዚህ የከፋ ቁጥር ከመጣ የሚቀጥለውንም ሕይወት ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ቀውሱን የአዕምሮ ጭንቀቱንና ሥጋቱን ካከልንበት ደግሞ በቶሎ መንቃትን ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ መንግሥት ሌሎቹን ነገሮች ለጊዜው ተወት በማድረግ በሽታው እንዳይዘን በሚደረግ የመካለከልና የመዘጋጀት ሥራ ላይ ይጠመድ፡፡ ሕዝብም ራሱን ይጠብቅ፡፡ ከተዝረከረከ አሠራር ራሱን አፅድቶ ይጓዝ፡፡ የአገር መሪነት የሚለካው እንዲህ ባለው ወቅት በመሆኑ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፖለቲካ አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አንዳንድ እያየን ያለናቸው አነጋገሮችም በመልካም የሚወሰዱ ሲሆን፣ ከዚህ የበለጠም ይጠበቅባቸዋል፡፡
በተለይ የቫይረሱ ወረርሽኝ ሁሉንም ነገር የሚነካካ በመሆኑ ከኢኮኖሚ አንፃር መንግሥት እየወሰደ ያለው አንዳንድ ዕርምጃዎች በመልካም የሚታዩ ናቸው፡፡ ጦርነቱ የሕዝብ ሕይወትን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚውንም ባለአቅም መደገፍና አማራጭ ፖሊሲዎችን በጊዜያዊነት መተግበር ጭምር በመሆኑ አሁንም ችግሮች እየታዩ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ እንዳይሰፋ ውሳኔዎች ማሳለፍ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ የብድር ዕርዳታን ለመስጠት የግል ባንኮች እንዲያገኙ ይደረጋል የተባለው የ15 ቢሊዮን ብር አቅርቦት አንዱ ነው፡፡ ከታክስ ጋር በተያዘም መሆን የሚገባቸውን እያጠኑ መከወን የግድ ነው፡፡
ከሁሉም በላይ የዜጎች ኃላፊነት ከማንም ሊስተካከል አችልም፡፡ ሕዝብ ይጠንቀቅ፡፡ የአንዱ በቫይረሱ መያዝ ለእሱ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎችም ዕልቂት ሰበብ ነውና አፍጥጦ የመጣብንን ችግር ለመወጣት የእያንዳንዳችንን ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ይህ ከሆነና አንዱ ለሌላው ካሰበ ችግራችንን እንወጣዋለን፡፡ ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ የተጀመረው የድጋፍ ሥራ ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ሥጋቱን የሚቀንስ ነውና ከመቼውም ጊዜ በላይ እንተባበር፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲሉ የከረሙ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸው የት ነው ያሉት? አይመለከታቸው ይሆን? ብቻ ትዝብት ነው፡፡ ከመቶ በላይ ፓርቲዎች ባሉባት አገር ውስጥ፣ የሰደድ እሳት ሊፋፋምብን ሲያደባ ድምፃቸው መጥፋቱ ያስተዛዝባል፡፡ አንዳንዶቹን ተቃዋሚዎችና አክቲቪስቶች ማመስገኑም ተገቢ ነው፡፡