Sunday, March 26, 2023

ለኮሮና ቫይረስ የተጠየቀው ዓለም አቀፍ ትብብርና የኢትዮጵያ ዝግጅት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ኮሮና ቫይረስ ዜግነትም ሆነ ዘር፣ እምነትም ሆነ ምንም ግዱ አይደለም፡፡ ፋታ ሳይሰጥ ሁሉንም ያጠቃል፡፡ ለዚህም ነው ሰብዓዊ ፍጡራን በሙሉ ተባብረን ቫይረሱን ማስቆም ያለብን፤›› ያሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ መሣሪያ አንግበው የሚዋጉ ባላንጣዎች ሳይቀሩ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው፣ ቫይረሱን በጋራ እንዲዋጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዓለም ላይ ዕልቂት ይዞ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ከዓለም ላይ እንዲጠፋ ከተፈለገ፣ የአገሮች ተናጠል ጥረት የትም እንደማይደርስ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ማኅበራዊ አመጣጥ፣ ወዘተ የማይለየው ኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፋዊ ትብብር እንደሚያስፈልገው ጥያቄዎች እየጎረፉ ነው፡፡ ከተለየዩ አቅጣጫዎች የሚሰሙ ድምፆችም ይህንን እያስገነዘቡ ነው፡፡ አገሮች ብሔራዊ ጥረቶቻቸውን ከማቀላጠፍ ጎን ለጎን ለዓለም አቀፍ ትብብሮች ትኩረት ካልሰጡ፣ ቫይረሱን ለመግታት የሚደረገው ጥረት ከንቱ እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ በሰው ልጆች ላይ መቅሰፍት ይዞ የመጣውን ኮሮና ቫይረስ አገሮች በጋራ እንዲከላኩ ጥሪ አቅርበው፣ ይህንን መቅሰፍት ለመከላከል በዓለም ተጋላጭ ለሆኑ ደሃ አገሮች የሚውል ተመድ የሁለት ቢሊዮን ዶላር በጀት መመደቡን አስታውቀዋል፡፡ ይህ ወቅትም ቫይረሱን በጋራ ለመመከት ትኩረት የሚደረግበት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን የከፋ ጊዜ ለማለፍ ያለው አማራጭ የጋራ ጥረትን ማስተባበር እንደሆነም አክለዋል፡፡ 

‹‹በአፍሪካ የከፋ ጊዜ እንዳይመጣ ጥንቃቄ››  ይደረግ ሲል በቅርቡ የዓለም ጤና ድርጅት ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ በአፍሪካ በተነፃፃሪ የቫይረሱ ሥርጭት መጠነኛ ቢመስልም፣ በየቀኑ ቁጥሩ እያሻቀበ መሆኑ ሥጋት እየፈጠረ ነው፡፡ ከቻይና ቀጥሎ አውሮፓና አሜሪካን የወረረው ኮሮና፣ ቀጣዩ በትሩ የሚያርፈው አፍሪካ ላይ ሊሆን ይችላል የሚለው ግምት ብዙዎችን እያስማማ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ኮሮና ቫይረስን አፍሪካ ውስጥ ካላሸነፍነው ተመልሶ ሁላችንንም ይወረናል›› በማለት ይህንን ወረርሽኝ የሀብታም አገሮች ጊዜያዊ አሸናፊነት ሳይሆን የሚያቆመው ዓለም አቀፋዊ ድል ብቻ ነው ሲሉ፣ ሰሞኑን በፋይናንሻል ታይም ላይ ባስነበቡት ጽሑፍ ያስገነዘቡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በኢኮኖሚ የፈረጠሙት አገሮች በቫይረሱ ምክንያት ጉዳት ለገጠመው ኢኮኖሚያቸው ማነቃቂያ የሚሆኑ መርሐ ግብሮች ማዘጋጀታቸውን ገልጸው፣ በአንፃሩ የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ አቅም እንደሌላቸው አስታውቀዋል፡፡ የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር አጋጣሚውን በመጠቀም የአፍሪካንና የሌሎች ታዳጊ አገሮች ድምፅ መሆን መጀመራቸውን በሚያሳየው ጽሑፋቸው፣ ቫይረሱን አፍሪካ ውስጥ ማሸነፍ ካልተቻለ በተቀረው ዓለም ላይ እንደሚከለበስ አስጠንቅቀዋል፡፡

ድንበር የማይገድበውና ለድንበር ደንታ የሌለውን ኮሮና ቫይረስ በመቀናጀት ካልሆነ አገሮች በተናጠል በሚያደርጉት ጥረት መመከት እንደማይቻል ጠቁመው፣ በዓለም ዙሪያ አሁን እየተደረገ ያለው ያልተቀናጀ እንቅስቃሴ አርቆ ማየት የጎደለው፣ ዘላቂነት የሌለውና ውጤት አልባ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ይህንን የማይታይና ጨካኝ ጠላት ድል እንመታዋለን፡፡ ድል መምታት የምንችለው ግን በዓለም አቀፍ የተቀናጀ አመራር ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ውጪ የመጨረሻዋና ብቸኛዋ ባትሆንም አፍሪካ ምናልባት ከባድ ተጎጂ ትሆናለች፡፡ ለዚህም ሲባል እስከ መጨረሻው ድረስ አንድ ላይ መሥራት አለብን፤›› ሲሉ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እየሩሳሌም በሚገኘው ሒብሩ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ዲፓርትመንት መምህርና ተመራማሪ ዩቫል ኖህ ሐሪሪ (ፕሮፌሰር) በታይም መጽሔት በቅርቡ ባስነበቡት መጣጥፍ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ዓለም ከባድ ጊዜ ውስጥ ለመሆኗ ማመላከቻው የሰው ዘር በትውልዶች ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ እንደተጋረጠበት፣ በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት የዓለም መንግሥታትና ሕዝቦች የሚደርሱበት ውሳኔ የዓለምን ቅርፅ ሊለውጥ እንደሚችል ኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ በተነተኑበት ጽሑፍ አስረድተዋል፡፡

አሁን ሰብዓዊ ፍጡራን በኮረና ቫይረስ ምክንያት ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ ያለ መተማመን ፅኑ ቀውስ እንደገጠማቸው ገልጸዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለማሸነፍ የሚቻለው የእርስ በርስ መተማመን መፍጠር፣ ሳይንሳዊ ሙከራዎችን ማመን፣ በመንግሥታት የሚሰጡ መመርያዎችን ዜጎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርባቸውና አገሮችም እርስ በርስ በመተማመን ጥረቶቻቸውን ማስተባበር እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ እያንዳንዱ አገር በተናጠል የሚያደርገው መፍጨርጨር የትም እንደማያደርሰው መግባባት በመፍጠር በሰው ኃይል፣ በማቴሪያልና በመረጃ ልውውጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ መተባባር ብቻ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት እንደሚያስችል አሳስበዋል፡፡

የኮረና ቫይረስ ሥርጭት በጣም ፈጣን ሆኖ በአውሮፓ ጣሊያንና ስፔን እጅ መስጠት ደረጃ ላይ ሲያደርሳቸው፣ በአሜሪካ ግማሹን ያህል የቫይረሱ ተጠቂዎች የያዘችው የኒውዮርክ ከተማ ከተማ ከንቲባ ቢል ዲ ቢላሲዮ፣ የመድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ ዕቃዎች አቅርቦት ከቫይረሱ ሥርጭት አንፃር የመጋቢት ወርን እንደማያልፍ አስጠንቅቀዋል፡፡ በአሜሪካ የቫይረሱ የስበት ማዕከል የሆነችው ኒውዮርክ ከንቲባዋ በጭንቀት ውስጥ ሆነው ይህንን ሲናገሩ የችግሩን መክፋት አመላካች ሆኖ ተወስዷል፡፡ ሌላው ቀርቶ እንኳንስ የጋራ ጥረቶችን ማስተባበር የሐሳብ መከፋፈል እንዳለ ከከንቲባው አንደበት ተሰምቷል፡፡

ከንቲባው ለኒውዮርክ ነዋሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት ለተራዘመና ከባድ ትግል ለሚጠይቀው የኮረና ቫይረስ ፍልሚያ እንዲዘጋጁ አስታውቀው፣ በቅርቡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚያዝያ ወር አጋማሽ ወደ ተለመደው ተግባራችን እንመለሳለን ያሉትን አልቀበልም ብለዋል፡፡ ‹‹እውነቱን ለመናገር ይህ በቶሎ ይከናወናል ብለን አናምንም፡፡ ቢሆን ምኞቴ ነው፣ ነገር ግን መሆን አይችልም፡፡ ከአክብሮት ጋር ከፕሬዚዳንቱ ሐሳብ ጋር አልስማማም፤›› ብለው፣ ከኒውዮርክ ከተማና ከመላው አሜሪካ ሁኔታ አኳያ ትራምፕ ያሉት ነገር ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል፡፡ አሁን ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልገው በተቻለ መጠን በወራት ውስጥ ውጤት ለማግኘት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የዓለም ታላቋ ከተማ በእንብርክክ እየሄደች አቅሟ እየተሟጠጠ ቀኑ እየጨለመባት ሳለ፣ ሌሎች አቅም የሌላቸው አገሮች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲታሰብ አስደንጋጭ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ ታዳጊ አገሮች የጤና ተቋማት ምላሽ የመስጠት አቅም ደካማ መሆንና በበለፀጉት አገሮች ላይ ጥገኛ መሆን ሲታሰብ፣ አሁንም ከዓለም አቀፍ ትብብር ውጪ ኮሮና ቫይረስን መቋቋም እንደማይቻል የብዙዎች እምነት ነው፡፡ በአሊባባ መሥራችና ባለቤት ጃክ ማ ተበርክተው ለመላው አፍሪካ በኢትዮጵያ አማካይነት እየተሠራጩ ያሉት የመመርመሪያ ኪቶችና ተዛማጅ ቁሳቁሶች፣ የትብብርን አስፈላጊነት ማመላከቻ እየተደረጉ ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት በአፍሪካ የከፋው ጊዜ እንዳይመጣ ሲያሳስብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ቫይረሱን አፍሪካ ውስጥ ማሸነፍ ካልተቻለ ከባድ ጊዜ ከፊት እንዳለ ሲያስጠነቅቁና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ትብብርን ማቀናጀት የግድ ነው ሲሉ በዋዛ መታየት እንደሌለበት ግልጽ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች ታዳጊ አገሮች የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እጅ እያየች የምትኖር ደሃ አገር ስለሆነች፣ ለዓለም አቀፍ ትብብር ጥሪ ሲደረግ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ እንደማይገባ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየተነገረ ነው፡፡ በተለይ የቫይረሱ ሰለባ ላለመሆን መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች የሚተላለፉ መልዕክቶችን ተግባራዊ አለማድረግና በተለያዩ ንድፈ ሐሳባዊ የሴራ ትንተናዎች ግራ መጋባት ውስጥ መግባት አደጋ እንዳለው በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት ዓለምን እያዳረሰ ባለበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ መጠጋጋቶችና መተፋፈጎች አስደንጋጭ መሆናቸውን ችግሩ ያሳሰባቸው ወገኖች በሚዲያዎች አማካይነት እያሳሰቡ ነው፡፡ ተማሪዎች ትምህርት ለጊዜው ተቋርጦ ቤታቸው ሆነው እንዲያጠኑ እረፍት ቢወጡም፣ በመኖሪያ አካባቢያቸውና ርቀው በመሄድ ኳስ ሲጫወቱና ፑል ቤቶች ውስጥ በብዛት መገኘታቸው እንደሚያሳስብ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡ በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚታየው ጭንቅንቅም ከፍተኛ ሥጋት አጥልቷል፡፡ እነዚህ ችግሮች በበቂ ደረጃ መረጃው ኅብረተሰቡ ዘንድ አለመድረሱን ማመላከቻ ናቸው ሲሉ የሚያሳስቡ አሉ፡፡

ይህ ሥጋት ካሳሰባቸው መሀል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሰሞኑን በትዊተር ገጻቸው፣ ‹‹ዛሬ በአዲስ አበባ ተዘዋውሬ ነበር፡፡ መመርያዎችን ለመተግበር ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ የሚጠጋን ቫይረስ የለም ሲሉ የነበሩ ያሉበትን እያየን አንዘናጋ፡፡ ምርመራ በብዛት ባለመደረጉ ትክለኛውን ሁኔታ አላየንምና በአገር ደረጃ ተቀናጅተን መዘጋጀት አለብን፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡ የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመግታትና ለመከላከል መንግሥት ተጨማሪ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ የሕዝብን ጤንነትና ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚደረገው ሁሉ በዛ ሊባል አይችልም ብለዋል። ‹‹ቫይረሱን ለመከላከል የሚወጡ መመርያዎችን መተግበር የእኛም ፋንታ ነው፣ የጉዳዩ አሳሳቢነት ላይ አንዘናጋ፣ በጣሙን አደራ፤›› በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

በተለያዩ ሬዲዮ ጣቢያዎችና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመቅረብ አስተያየት የሰጡ ግለሰቦች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን መዘናጋትና የግንዛቤ ጉድለት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ለዘመናት ማኅበረሰቡ ውስጥ የነበሩ መስተጋብሮችን በቀላሉ መላቀቅ ስለማይቻል፣ የማስተማሩና የማስገንዘቡ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ይላሉ፡፡ አካላዊ ርቀትን በሁለት የትልቅ ሰው ዕርምጃዎች ማድረግና መሰባሰብን ለጊዜው ማስቆም የሚቻለው፣ ድርቅ ባለ መግለጫ ወይም በተወሳሰበ አገላለጽ ሳይሆን ሰዎች የሚወዷቸውን ልጆቻቸውን፣ የትዳር አጋሮቻቸውንና ወላጆቻቸውን በጥንቃቄ ጉድለት በቀላሉ ሊያጡ እንደሚችሉ በተጠና መንገድ በማስገንዘብ እንደሆነ የሚመክሩ አሉ፡፡ ሚዲያው የታዋቂ ሰዎችንና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን እጅ የማስታጠብና የተበታተነ ልግስና ለማስተጋባት የአየር ጊዜውን ማባከን እንደሌለበት፣ የእምነት መሪዎችንና በየዕውቀት ዘርፉ አሉ የሚባሉ ልሂቃንን በመጋበዝ ግንዛቤ ማስጨበጫው ላይ ማተኮር እንዳለበትም ያስገነዝባሉ፡፡ አቅም በሌለበት አገር ችግሩ ከሚገመተው በላይ ግዙፍ ነውና፡፡ የመረጃ ፍሰቱ ዘመኑን በሚመጥን ደረጃ መከናወን እንዳለበት ማሳሰቢያ እየቀረበ ነው፡፡

ይህንን በተመለከተ በፋይናንሻል ታይምስ መጽሔት ላይ ጽሑፋቸውን ያስነበቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ የኢትዮጵያን ተሞክሮ እንዲህ በማለት ገጸውታል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ግስጋሴ አድርጋለች፡፡ በኮረና ቫይረስ የተጋረጠውን አደጋ ለመከላከል ግን አልተዘጋጀችም፤›› ብለው፣ የጤና አገልግሎቶች ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑን፣ ንፁህ ውኃ ለማግኘት ብርቅ የሚሆንበት ግማሽ የሚሆነው የአገሬው ሕዝብ፣ እጅን በሳሙና ለመታጠብ እንኳ እንደማይቻለው በግልጽ አስፍረዋል፡፡

ሌላው ቀርቶ ምንም ወጪ የሌለበት አካላዊ ርቀት መጠበቅን (Social Distancing) ተግባራዊ ማድረግ እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡ የኢትዮጵያዊያን የኑሮ ዘይቤ ጥልቅ የሆነ ማኅበራዊ ትስስርን፣ በሰፊ ቤተሰባዊ ቁርኝት ክፉውንም ደጉንም በጋራ የመወጣት ባህልን፣ በአንድ ገበታ አብሮ መመገብን፣ ወዘተ አውስተዋል፡፡ ልማዳዊውና የዝናብ ጥገኛ የሆነው የአገሪቱ እርሻ በአየር በተለያዩ የአየር ፀባይ ዑደቶች አርሶ አደሮችን እንዲዘሩ፣ እንዲያርሙና እንዲሰበስቡ እንደሚያደርጋቸው፣ በዚህ መሀል የሚፈጠር መዛባት ወትሮም እንደ ነገሩ የሆነውን የምግብ ዋስትና ችግር ውስጥ እንደሚከተው አመልክተዋል፡፡ ሌሎች ተያያዥ ችግሮችን በማውሳት አሁን ትክክለኛው ሰብዓዊነትና አጋርነት በተግባር የሚታይበት፣ እንዲሁም ድጋፍ የሚደረግ ከሆነም ከዚህ የበለጠ ጊዜ እንደሌለ በማስገንዘብ ዓለም ለትብብር እጁን እንዲዘረጋ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን ጥሪ በመሪዋ አማካይነት እያቀረበች የውስጥ ጥረቷን ማጠናከር ይኖርባታል ሲሉ፣ የወቅቱ ሥጋት የሚያሳስባቸው ወገኖች ይናገራሉ፡፡ አሁንም በዓለም ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ጥንቃቄዎች በፍፁም ሳይዘነጉ እያንዳንዱ ዜጋ ተግባራዊ እንዲያደርጋቸው ሚዲያዎች አቅማቸውን በሙሉ መጠቀም እንዳለባቸው፣ የመንግሥት አመራሮችና መዋቅሮች የአመራር ሚናቸውን በከፍተኛ ትጋት ማከናወን እንደሚኖርባቸው፣ የእምነት ተቋማትና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አደረጃጀቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚህ ተግባር እንዲያውሉ፣ እንዲሁም ከሕዝቡ በተጨማሪ ባለሀብቶች የመንግሥትን ብሔራዊ ጥረት ለመደገፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚፈለግባቸው በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ጥሪ እየቀረበ ነው፡፡

በጥቁር አንበሳና በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታሎች የአንገት በላይ ሐኪም የሆኑት ዶ/ር አሰፋ ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት የሚያስመሠግንና ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አስችሏታል፡፡ ‹‹እየተከናወኑ ያሉት የጤና ጥበቃ እንቅስቃሴዎች የመንግሥትን ቁርጠኝነት የሚያበረታቱ ስለሆኑ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡ ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ የተቀናጀ ሥራና በሚኒስትሮች የተዋቀረ ግብር ኃይል አለ፡፡ የጤና ባለሙያዎች በመከላከልም ሆነ በማከም ግዴታቸውን በሚገባ እየተወጡ ናቸው፡፡ የመንግሥትም ሆኑ የግል ሆስፒታሎች እያደረጉዋቸው ያሉ እንቅስቃሴዎች እጅግ የሚበረታቱ ናቸው፤›› ያሉት ዶ/ር አሰፋ፣ በቂ በጀት መመደብና የትንፋሽ መርጃ መሣሪያዎችን በበቂ ሁኔታ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ቫይረሱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የዓለም ሳይንቲስቶች ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ እንደሆነና ተስፋ ሰጪ ሙከራዎች እንዳሉ፣ መረበሽና አላስፈላጊ ፍርኃት ወደ ሌላ አቅጣጫ ስለሚወስድ፣ ራስንና ሌሎችን በመጠበቅ መከላከሉ ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል፡፡

አገራዊው እንቅስቃሴ በተቀናጀ ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንደሚኖርባቸው፣ የጤና ባለሙያዎች በቂ ሥልጠና በየጊዜው እንዲሰጣቸው፣ በተለይ ከጉሮሮ ናሙና በመውሰድ የሚታወቅበትምርመራ መሣሪያ በበቂ ሁኔታ ለዚህ ተብሎ በተመደቡ ሆስፒታሎች መኖር እንደሚገባው፣ አሁን እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ እጅግ አበረታች እንደሆነ፣ የመንግሥት ቁርጠኝነትና የባለሙያዎች ትጋት መመሥገን እንደሚገባው በማስገንዘብ፣ ብሔራዊው የመከላከል ዝግጅት በሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ዶ/ር አሰፋ አሳስበዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲመለሱ፣ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ከእስር በይቅርታም ሆነ በምሕረት፣ እንዲሁም ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦች ከማኅበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ ለጥንቃቄ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እየተጠየቀ ነው፡፡ የተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰዳቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በጊዜያዊነት ከከተማ ወደ ከተማም ሆነ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን ዝውውር ማገዱን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም የመንግሥት ሠራተኞችን በተመለከተ ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች፣ ዕድሜያቸው ለጡረታ የተቃረቡና ለረጅም ጊዜ የቆየ የጤና ዕክል ያለባቸው ሰዎች በቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ መወሰኑን ገልጿል። በትልልቅ ገበያዎች ላይ ዕግድ ጥሏል፡፡ ሌሎች ተጨማሪ ዕርምጃዎችን መውሰዱንም አክሏል፡፡ ይህንን ዕርምጃ ብዙዎች በተደበላለቀ ስሜት በተለያዩ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ድምፆችን አሰምተዋል፡፡ ውሳኔውን የደገፉ እንዳሉ ሁሉ፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያልተናበበ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነው ያሉም አሉ፡፡ የመከላከል ሥራው ከብሔራዊ ጥረቱ ጋር መቀናጀት እንዳለበት ያሳሰቡም አሉ፡፡

ኢትዮጵያ ከመጪው ምርጫ በላይ፣ ካሉባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ባሻገር፣ በፖለቲከኞች መካከል ከሚስተዋለው የዘወትር ጭቅጭቅና ከፋይዳ ቢስ ሴራዎች በባሰ ግዙፍ አደጋ የደቀነው ኮሮና ቫይረስ ብዙዎችን እንቅልፍ ነስቷል፡፡ ዜግነት፣ ብሔር፣ እምነትና የተለያዩ ልዩነቶች ሳይገድቡት በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በዓለም ዙሪያ እየያዘና እየገደለ ያለው ይህ ቫይረስ፣ የተናጠል ሳይሆን የጋራ ክንድ እንደሚያስፈልገው ብዙዎችን እያስማማ ነው፡፡

ምንም እንኳ ለእንዲህ ዓይነቱ ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ የሚሉ እንደ ዶናልድ ትራምፕን የመሳሰሉ ብሔርተኞች (Nationalists) በተለያዩ የምዕራብና የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች እያቆጠቆጡ ቢሆኑም፣ በተከፋፈለ አቅምና ልብ ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ ማለፍ እንደማይቻል እየተነገረ ነው፡፡ ‹‹ማንኛውም አገር ብቻውን ኮሮና ቫይረስን መቆጣጠር ስለማይቻለው ዓለም አቀፋዊ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ የዓለም መሪዎች ግን ስለዚህ ዕቅድ እስካሁን አልተነጋገሩም፡፡ ምን እየጠበቁ ነው?›› ሲሉ የሒብሩ ዩኒቨርሲቲው ሐሪሪ (ፕሮፌሰር) አበክረው ጠይቀዋል፡፡  

እንደሳቸው ሁሉ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳስባቸው ስሜ አይገለጽ ያሉ አንድ አንጋፋ የሕክምና መምህርና ባለሙያ፣ ‹‹ካለን ውስን አቅምና ከኅብረተሰባችን የግንዛቤ ጉድለትና ቸልተኝነት በተጨማሪ የአገሪቱ መንግሥት ሹማምንት፣ ልሂቃን፣ ፖለቲከኞችና በተለያዩ ዘርፎች ውስጥ ያሉ ባለሙያዎች ተጨንቀውና ተጠበው በጋራ መምከር አለመቻላቸውና የጋራ የድርጊት መርሐ ግብር ለመንደፍ አለማሰባቸው ያሳስበኛል…›› ነው ያሉት፡፡ መንግሥት ሕዝቡን በማስተባበር ገንዘብ አሰባስቦ ብሔራዊ አቅም ለማጠናከር የሚያደርገው መልካም ጥረት፣ በብሔራዊ ደረጃ በምክክርና በጋራ ዕቅድ ቢታገዝ ዓለም አቀፉን ድጋፍ ለማግኘትም ሆነ ለማስተባበር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ሲሉም አክለዋል፡፡ ‹‹አሁን ወቅቱ ብሔራዊ የመከላከል ዝግጅትን በአንድ ዓላማ ሥር በመሠለፍ የምናስተባብርበት መሆን ስላለበት፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ መመካከርና ማቀድ አለብን፤›› ሲሉም አሳስበዋል፡፡ ይህ የእሳቸው ብቻ ሳይሆን የሌሎችም እንደሚሆን ይታሰባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -