በአቃቂ ቃሊቲ የተሰበረው ውኃ ማስተላለፊያ መስመር ጥገና ተጠናቀቀ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽ በኢትዮጵያ መከሰቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ አንስቶ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች የውኃ አቅርቦት ችግር ይፈጠራል የሚል ሥጋት ቢኖርም፣ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ግን እስካሁን ችግር የሆነበት የኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት እንጂ የውኃ ምርት እንዳልሆነ አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሰርካለም ጌታቸው ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ባለሥልጣኑ በቀን የሚያመርተው የውኃ መጠን 574 ሺሕ ሜትር ኩብ ነው፡፡ በፊትም ይኸው ነው፣ አሁንም ይኸው ነው፡፡ የከተማው ፍላጎት ግን አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩብ ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ ማምረት የሚችለው ግን የተጠቀሰውን ያህል ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ውኃ ለነዋሪዎች እየደረሰ ያለው በፈረቃ መሆኑን ጠቁመው በተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ ኃይል ስለሚጠፋ ባለሥልጣኑ ባሉት 28 ቦቴ ተሽከርካሪዎች ለደንበኞቹ ውኃ እንደሚያከፋፍል ገልጸዋል፡፡
ፍላጎትና ምርቱ ካለመጣጣሙም በተጨማሪ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ደግሞ ችግሩን እንደሚያባብሰው አስረድተዋል፡፡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የውኃ ፍጆታ ቢኖርም፣ ባለሥልጣኑ የሚያመርተው የውኃ መጠን ግን ያው መሆኑንና ተጨማሪ ወይም ከነበረው የቀነሰ የውኃ ሥርጭት የለም ብለዋል፡፡ ምንም እንኳን ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሆኑ ከ90 በላይ ዲዝል ጄኔሬተሮች ቢኖሩም በቂ አለመሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን ባልታወቀ ምክንያት የአቃቂ ቃሊቲ የከርሰ ምድር ውኃ ማስተላለፊያ መስመር መሰበሩ የተገለጸ ቢሆንም፣ ሙሉ በሙሉ ተጠግኖ ማለቁን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡ በጥገና ወቅት በመስመሩ ላይ የገባውን አፈርና አላስፈላጊ ነገሮችን በማፅዳት ላይ መሆናቸውንና በአጭር ቀናት ውስጥ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አስታውቀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋትን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ እንደገለጹት፣ ለአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ራሱን የቻለ መስመር አለ፡፡ ነገር ግን መስመሩ ከኮተቤ ተነስቶ ለገዳዲን አልፎ እስከ ሰንዳፋ ስለሚሄድ፣ በመሀል ላይ በዛፎች መውደቅ ወይም ሌላ ችግር ሲያጋጥመው ኃይል የመቋረጥ ችግር ደጋግሞ እንደሚያጋጥም፣ ጥገና እስከሚደረግም ችግር እንደሚፈጠር አስረድተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት ለውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ብቻ የሚሆን መስመር መዘርጋት ቢያስፈልግም፣ ባለሥልጣኑ ክፍያ ባለመፈጸሙ ችግሩ ሊቀጥል እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡ በቅርቡም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡