እጅግ በጣም ዘመናዊ የሕክምና ተቋማት፣ ዘመኑ ያፈራቸው የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች፣ ከፍተኛ ሥልጠና ያላቸው በጣም በርካታ የጤና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የተሟላ የሳይንስና የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው የበለፀጉ አገሮች ሊቋቋሙት የተሳናቸውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት መከላከል የሚቻለው ለጥንቃቄ በምንሰጠው ትኩረት ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ የሚገኝበትን አቅምና ደረጃ በመገንዘብ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት፣ የጥንቃቄ መመርያዎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማክበር የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡ በግድየለሽነት እየተፈጸሙ ያሉ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች የቫይረሱን ሥርጭት በማስፋፋት፣ በአገሪቱም ላይም ሆነ በጤናው ዘርፍ ላይ ታይቶና ተሰምቶ የማያውቅ ቀውስ ላለመፍጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ፡፡ የተለያዩ እምነቶችን የሚከተሉ ምዕመናን በሃይማኖት መሪዎች የሚሰጡ ምክሮችንና ማሳሰቢያዎችን በአንክሮ ያዳምጡ፡፡ ኮሮና ቫይረስን መከላከል የሚቻለው በተቻለ መጠን እንቅስቃሴን በመገደብ፣ ሰዎች የሚበዙባቸው ሥፍራዎች ባለመገኘት፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና በመታጠብ ወይም በፀረ ተዋህስያን በማፅዳት እንደሆነ በሚመለከታቸው የጤና አካላት እየተነገረ ነው፡፡ ማሳሰቢያውን ተግባራዊ ማድረግ የግድ ነው፡፡ በመንግሥት የሚሰጡ መመርያዎችንም ማክበር ይገባል፡፡ መመርያ ጥሶ ተሰባስቦ የአምልኮ ሥርዓት መፈጸም፣ መጠጥ ቤቶች መገኘት፣ በጫት መቃሚያዎችና በሺሻ ማጨሻዎች መታደምና በየመንደሩ መሰባሰብ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ጦሱ የሚተርፈው ለአገርና ለሕዝብ ነው፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ግዳቸውን እየተወጡ ያሉ የጤና ባለሙያዎቻችን ላይ ጫና ላለመፍጠር፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የድርሻን መወጣት ይገባል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥትም ሆነ በሚመለከታቸው የጤና አካላት እየተሰጡ ያሉ ማሳሰቢያዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን ወደ ጎን በማለት፣ በሕዝብ ደኅንነትና ጤና ላይ አደጋ የጋረጡ ወገኖችን በሕግ አደብ ማስገዛት ይገባል፡፡ ሰዎችን በመሰብሰብ መንፈሳዊ አገልግሎት እንሰጣለን የሚሉ፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን የሚያሠራጩ፣ የጥንቃቄ ማሳሰቢያዎችን በማጣጣል ለቫይረሱ ሥርጭት የሚረዱ ቅስቀሳዎችን የሚያካሂዱ፣ ትንቢት ተናጋሪ ነን በማለት የሚያጭበረብሩ፣ የጥንቃቄ መመርያዎችን በመጣስ ያልተገቡ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ፣ አጋጣሚውን በመጠቀም ዝርፊያ የሚያከናውኑ፣ ምርቶችን የሚደብቁ፣ በተጋነነ ዋጋ የሚሸጡና በአጠቃላይ ቀውስ ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት በፍጥነት ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል፡፡ ከአገርና ከሕዝብ ደኅንነት የሚቀድም የለም፡፡ ባለፀጋ አገሮች የቫይረሱን ሥርጭት መግታት አቅቷቸው የዕርዳታ ያለህ ብለው እጃቸውን ወደ ቻይና በዘረጉበት በዚህ አስደንጋጭ ወቅት፣ ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እርስ በርስ ተደጋግፈው በብልኃት የመጣውን ውርጅብኝ ማሳለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ አለመፈለግ ወይም አለመቻል አደጋውን የከፋ ያደርገዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ ዓይነት መረጃዎች ይለቀቃሉ፡፡ ከእነዚህ መረጃዎች አብዛኞቹ ማስረጃ የሌላቸው አሉባልታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሐሰተኛ መረጃዎች በሚያማልሉ ርዕሶችና እውነት በሚመስሉ ሁነቶችና ዳታዎች ስለሚታጀቡ የብዙዎችን ቀልብ ይስባሉ፡፡ በማኅበራዊ ትስስር ገጾችና በዩቲዩቦች አማካይነት በርካታ ተከታዮች ባፈሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደሚሠራጩ ይታወቃል፡፡ ባለቤቶቹ ደግሞ በርካታ ተከታዮችን በማፍራት ከፍተኛ ገቢ ስለሚያገኙ ውዥንብሮችን ይረጫሉ፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ከእኔና ከመንግሥታቶቻችሁ መመርያዎችና ማሳሰቢያዎች ውጪ ማንንም አትስሙ እያለ እያስጠነቀቀ፣ አሁንም ብዙዎች የእነዚህ ጨካኝ ነጋዴዎች ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ምንጫቸው ያልተረጋገጠ ግርድፍ መረጃዎችን እንደ ወረዱ መቀበል፣ የጥንቃቄ ማሳሰቢያዎችን ችላ ማለትና ኮሮና ቫይረስ አይደርስብንም ማለት ድረስ ያለው አጉል ድፍረት የሐሰተኛ መረጃዎች ውጤት ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እኮ ይህንን ቫይረስ እናሸንፈዋለን ብለው የሚፎክሩ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች፣ በዚህ ወቅት ዓለምን ብርክ ባስያዘው ቫይረስ በከፍተኛ ደረጃ ለተጎዱ አገሮች መፍትሔ መስጠት ነበረባቸው፡፡ እነሱ ዋናው ዓላማቸው ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም ስለሆነ አዎንታዊ አስተዋፅኦ የላቸውም፡፡ ብለን ነበር በማለት ከማጭበርበር የዘለለ ፋይዳም የላቸውም፡፡ ለዚህ ነው ከእንዲህ ዓይነቶቹ በመራቅ፣ ቫይረሱን በፅናት ለመመከት ጥንቃቄን በማስቀደም በቁርጠኝነት መነሳት የሚያስፈልገው፡፡
እርግጥ ነው በዚህ አሳሳቢ ጊዜ መጨነቅና መፍራት ይኖራል፡፡ ነገር ግን ጭንቀትና ፍራቻ መፍትሔ አይሆኑም፡፡ መፍትሔው ለጥንቃቄ ትልቅ ትኩረት መስጠት ነው፡፡ ከተሞችንና ገጠሮችን ሳይለይ ኮሮና ቫይረስ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በከተሞች የቫይረሱን ሥርጭት መግታት ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ገጠሮች ውስጥ ገብቶ አርሶ አደሮችን ካጠቃ ከባድ ቀውስ ይፈጠራል፡፡ የአገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን አርሶ አደር ከዚህ ወረርሽኝ መታደግ ለነገ መባል የለበትም፡፡ ቫይረሱ በኢትዮጵያ ጉዳት እንዳያደርስ ምክረ ሐሳብ አለን የሚሉ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎችም፣ በቀጥታ መንግሥትን በመቅረብ ያነጋግሩ፡፡ በእርግጠኝነት ጠቃሚ ሐሳብ አለን የሚሉ ከሆነ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሳይሆን፣ በቀጥታ ወይም በአድራሻቸው የመንግሥትን የሚመለከታቸው አካላት ያግኙ፡፡ መንግሥትም በሩን ከፍቶ ይቀበላቸው፡፡ በሚደረጉ የሐሳብ ልውውጦች መሠረት ወደ ተግባራዊ ዕርምጃ የሚያስገቡ አሠራሮችን ይከተሉ፡፡ ከዚህ ወጪ ለሐሜትና ለአሉባልታ መጣደፍ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ውጤታቸው በምርምር ያልተረጋገጡ መፈወሻዎችም ሆኑ የመከላከል አቅም የሚሰጡ ነገሮች ተገኙ ብሎ መለለፈፍም ተገቢ አይደለም፡፡ በመንግሥት ውሳኔ ሰጪነትም ሆነ በባለሙያነት የተሠለፉ ወገኖች፣ በተቻለ መጠን ከመላምቶችና ካልተረጋገጡ ነገሮች ራሳቸውን ያርቁ፡፡ ለጥንቃቄ ዕርምጃዎች ብቻ ትኩረት ይስጡ፡፡ ኮሮና ቫይረስን ለማሸነፍ መቅደም ያለበት ጥንቃቄ ብቻ ነው፡፡
መንግሥት በሕግ የተሰጠው ኃላፊነት የአገርን ደኅንነትና የሕዝብን ጤንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ለአገር ደኅንነትና ለሕዝብ ጤንነት ጠንቅ የሆኑ ድርጊቶችን በሕጋዊ መንገድ መከላከል ግዴታውም ነው፡፡ ሕገወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ሁነኛው መሣሪያ ሕግ ብቻ ነው፡፡ ዜጎችም ሕጋዊ መሆን ያለባቸው ሕገወጥነትን ለመከላከል ነው፡፡ ሕግ አስከባሪ አካላት ሁልጊዜም ሕጉን ብቻ ተከትለው መሥራት ሲኖርባቸው፣ ዜጎችም የመተባበር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ትዕግሥትን የሚፈታተኑ ድርጊቶች ቢኖሩም፣ በመሣሪያ መግደልም ሆነ ማቁሰል፣ እንዲሁም አካላዊ ጥቃት ማድረስና ያልተገቡ ድርጊቶችን መፈጸም አይገባም፡፡ ሕግ አስከባሪዎች ማድረግ ያለባቸው ተጠርጣሪን ሕግ ፊት ማቅረብ ብቻ ነው፡፡ የሕግ መርህ ‹‹ማንም ሰው እስኪፈረድበት ድረስ ንፁህ እንደሆነ ይገመታል፤›› ይላልና፡፡ በሌላ በኩል ማንኛውም ዜጋ መንቀሳቀስ ያለበት ሕግን ምርኩዝ በማድረግ ነው፡፡ አሁንም በመንግሥት የወጣውን መመርያ መጋፋት ሕገወጥነት መሆኑን በመገንዘብ፣ ካልተገቡ ድርጊቶች ራስን ማራቅ የግድ ነው፡፡ ለራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለቤተ ዘመድና ለጓደኞች፣ እንዲሁም ለመላው ማኅበረሰብ ሰብዓዊነትን በተግባር ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ሰብዓዊነት የጎደላቸው ድርጊቶችን በመተባበር መግታት የግድ ነው፡፡ በዚህ አሳሳቢ ወቅት አካላዊ ርቀትን እየጠበቁ በመተባበር ሰብዓዊ ተግባራትን ማከናወን ይቻላል፡፡ ጥንቃቄን በማስቀደም ሕዝብንና አገርን ከቫይረሱ ሥርጭት መታደግም ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለጥንቃቄ ትልቅ ቦታ ከሰጠን ተባብረን የማናሸንፈው ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ለመተባበር ግን ጥንቃቄ ይቅደም፡፡ ኮሮና ቫይረስን በብቃት ለመከላከል ከጥንቃቄ የበለጠ አማራጭ የለም!