Sunday, April 14, 2024

‹‹ኮሮና ቫይረስ የሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት የሚታይበት ጊዜ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ፌዴራል ፖሊስ የመንግሥትን ውሳኔዎች እንዲያስከብር ጥብቅ ትዕዛዝ ተሰጠ

ኮሮና ቫይረስ የሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ሳምንታት ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት የሚታይበት ጊዜ ነው ሲሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አስታወቁ፡፡

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ከተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ ጋር ማክሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢንተርኔት ባደረጉት ውይይት በኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ ትልቁ ፈታኝ ሁኔታ አካላዊ ርቀትን ተግባራዊ ለማድረግ አለመቻሉ ነው ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ይህንን የሚኒስትሮች ስብሰባ ከመሩ በኋላ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በተለይ በገበያ ሥፍራዎችና በትራንስፖርት መገልገያዎች ውስጥ ሁሉም ሰው አካላዊ ርቀቱን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ባለፉት 15 ቀናት የነበረው የቫይረሱ ሁኔታ ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ በሚገቡ መንገደኞች ላይ ተወስኖ የቆየ እንደነበር ይታወሳል፡፡ መንግሥት የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ማኅበረሰቡ በበቂ ሁኔታ እየተገበራቸው ባለመሆኑ፣ ከፍተኛ የሆነ የጥንቃቄ ጉድለት ይታያል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ማኅበረሰባዊና አካላዊ መራራቅን ማኅበረሰቡ እንዲተገብር መንግሥት ውሳኔ ቢያሳልፍም፣ በተለይ በአምልኮ አካባቢዎች ይህ ውሳኔ እየተተገበረ አለመሆኑን መንግሥት በዋናነት መገምገሙንና ከሃይማኖት ተቋማትም ጋር በጉዳዩ ላይ መወያየቱ ታውቋል፡፡

በተጨማሪም ይኸው ተመሳሳይ ችግር በገበያ ሥፍራዎችና በትራንስፖርት አገልግሎቶች በስፋት መስተዋሉ ተገምግሟል። ይህንን ችግርና ማኅበራዊ መዘናጋት ለማረም በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ግንዛቤ ለማስጨበጥና ማኅበረሰቡን ለማንቃት በጎዳናዎች ላይ ጭምር በመዘዋወር መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ጥረት ቢደረግም፣ የታየው ውጤት ግን አነስተኛ እንደሆነ ተገምግሟል፡፡

ማኅበረሰቡ ስለቫይረሱ ያለው መረጃ በአመዛኙ ጥሩ እንደሆነ ነገር ግን በቂ ግንዛቤና መረጃው ያለውን ልሂቅ ጨምሮ በተለያዩ ማኅበረሰብ ክፍሎች የጥንቃቄ ዕርምጃዎችን በመፈጸም ረገድ ከፍተኛ ዳተኝነት መስተዋሉን በግምገማው መነሳቱን ለማወቅ ተችሏል።

አንዱ በፈጸመው ስህተት ወይም መዘናጋት ጉዳት የሚደርሰው በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ላይ በመሆኑ፣ መንግሥት ግንዛቤ ከማስጨበጥ ተግባሩ በላይ ውሳኔዎቹ በሕግ አስከባሪዎች ተፈጻሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚባው በግምገማው መረዳቱን ምንጮች አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት የፌዴራል ፖሊስ በመንግሥት የተላለፉ ውሳኔዎችን እንዲያስከብር ሲወስን፣ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮችም ትዕዛዙ እንዲደርሳቸው መደረጉ ተጠቁሟል። ይህንንም መሠረት በማድረግ ያለመተባበር ችግሮች እንዳይከሰቱ የፌዴራል ፖሊስ አመራሮች ከሃይማኖት ተቋማት ጋር መምከራቸውንና ሙሉ መግባባት መፍጠራቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ፌዴራል ፖሊስ በተለይ ለቫይረሱ ሥርጭት በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ በሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ሥምሪት እንደሚያደርግ፣ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችና ድንበሮች ላይም ተመሳሳይ ሥምሪት ሰሞኑን እንደሚያደርግ ተሰምቷል።

ከዚሁ ጎን ለጎንም በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ዜጎችን ከፍተኛ ሥጋት ወዳለባቸው አገሮች አታለው እየወሰዱ በሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች ላይም ጠንካራ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ታውቋል። እስካሁን ባለው የቫይረሱ ሥርጭት ከአዲስ አበባ ውጪ በኦሮሚያ (አዳማ) እና በአማራ ክልል (በባህር ዳር) መገኘቱን የመንግሥት መረጃ ያመለክታል።

ይህ በዚህ እንዳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማክሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት፣ ከቁሳቁስ በተጨማሪ ከሕዝቡ የተሰበሰበው 150 ሚሊዮን ብር መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ ይህንን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ የተቻለው ብሔራዊ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ በተመሠረተ በአምስት ቀናት ውስጥ መሆኑን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -