Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመድረክ ለሕዝብ ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጥ መንግሥትን ጠየቀ

መድረክ ለሕዝብ ደኅንነት ቅድሚያ እንዲሰጥ መንግሥትን ጠየቀ

ቀን:

ዓለም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የፖለቲካና የአመለካከት ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ቫይረሱን ለመከላከል በአንድነት እየተንቀሳቀሰ ባለበት ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም በፖለቲካ ምክንያት በተለያዩ ሥፍራዎች የታሰሩ ዜጎችን በመፍታት ሁሉንም ዜጎች አስተባብሮ ቫይረሱን በመከላከሉ ሥራ ላይ እንዲሰማራ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ  አንድነት መድረክ (መድረክ) ጥሪ አቀረበ፡፡

ፓርቲው ይህን ጥሪ ለመንግሥት ያስተላለፈው ማክሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ‹‹ከፖለቲካ ትርፍ ይልቅ ለአገራዊና ሕዝባዊ ጥቅሞች ቅድሚያ ይሰጥ›› በሚል ርዕስ፣ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የአገሪቱን ሁለንተናዊና አሳሳቢ ችግሮችን ለመፍታት ይቻል ዘንድ በሰጥቶ መቀበል መርህ ተቀራርቦ መሥራታቸው አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፣ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ የትግል ጥሪም አቅርቧል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጥሮና በሰው (መንግሥት) ሠራሽ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ስትናጥ የቆየችና አሁንም በመናጥ ላይ ነች ያለው መድረክ፣ ‹‹ችግሮችን ለመፍታት በየጊዜው በነበሩት አምባገነን መንግሥታት የተወሰዱት ዕርምጃዎች መንግሥታቱንና ጥቅሞቻቸውን ማዕከል ያደረጉ እንጂ፣ የአገሪቱንና የሕዝቡን ችግር በመፍታት ላይ ያነጣጠሩ ስላልነበሩ ለሕዝቡ ሲያስገኙ የነበሩት ውጤቶች አነስተኛ እንደነበሩ እንገነዘባለን፤›› ብሏል፡፡ በተለያዩ ዘመናት የነበሩ መንግሥታት የሕዝቡን መሠረታዊ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማርዘም ይሠሩ ነበር በማለት ወቅሷል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ብልፅግና ፓርቲ በቅርቡ የገቢ ማሰባሰቢያ አድርጎ ሰበሰብኩ ያለውን ገንዘብ፣ ከፓርቲው ይልቅ ለተፈጠረው ችግር መጠቀሚያነት ሊያውለው እንደሚገባ መድረክ አሳስቧል፡፡

‹‹የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልገው የገንዘብ፣ የባለሙያና የተቋማት እጥረት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እየታወቀ ያለውን አገራዊ ሀብት ገዥው ፓርቲ የራሱን አቅም ለማጎልበት መሰብሰብ መጀመሩ ስህተት ነው፤›› በማለት መድረክ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡

በዚህ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹ምርጫው መቼና እንዴት ይካሄድ በሚለው ጉዳይ ላይ በቂ ስምምነት ባለመኖሩ፣ የምርጫው ውጤት ተዓማኒነትን ጥርጣሬ ውስጥ ይከተዋል፤›› በማለት ሥጋቱን ገልጿል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ከፓርቲው ዕውቅና ውጪ ከመንግሥት ሠራተኞች መሀል መሆኑን በመቃወም፣ ምርጫ አስፈጻሚዎች ከዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ከተማሪዎች እንዲውጣጡ ጠይቋል፡፡

መድረክ የአራት ፓርቲዎች ስብስብ ነው፡፡ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን)፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ሉዓላዊነት (አረና)፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የመድረክ አባላት ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...