Friday, December 8, 2023

ኮቪድ 19 በደሃ አገሮች ላይ የሚያሳድረው የኢኮኖሚ ውድቀት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኮሮና ቫይረስን (ኮቪድ 19) ቀድሞ ከመከላከል እስከ አክሞ ማዳን ድረስ ያለው ሒደት የሰው ባህሪን ከመግታት የሚጀምር መሆኑ በሽታውን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ሒደት አዳጋች አድርጎታል፡፡ ዓለምንም ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡

የቫይረሱ ሥርጭት ፍጥነት ከዚህ ቀደም ከነበሩ የጉንፋን ዓይነቶች የተለየና በሽታውም አዲስ መሆኑ ቀድሞውንም የጤና ሥርዓታቸው እዚህ ግባ ለማይባሉት ደሃ አገሮች ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ የበለፀጉትንም አንበርክኳል፡፡

በዓለም በቴክኖሎጂ ምጥቀታቸውም ሆነ በኢኮኖሚያቸው ጎምቱ የተባሉ አገሮች፣ ዛሬ ላይ ለኮሮና ቫይረስ እጅ ሰጥተዋል፡፡ አሜሪካ ቫይረሱ በቻይና ሲከሰት ትኩረት አለመስጠቷና መዘናጋቷ ዛሬ ላይ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡

በኢኮኖሚ የመጠቀችው ቻይና በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ በሽታውን ስትቆጣጠር አውሮፓና ሌሎች አገሮች ግን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎችን እያስመዘገቡ ነው፡፡ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ሪሶርስ ሴንተር፣ ማክሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ 1:30 ላይ እንዳስታወቀው፣ በዓለም በኮሮና ቫይረስ ሰበብ የሞቱት 39,545 ሰዎች ሲሆኑ፣ በቫይረሱ የተጠቁት ደግሞ 809,608  ናቸው፡፡

ኮቪድ 19 በደሃ አገሮች ላይ የሚያሳድረው የኢኮኖሚ ውድቀት

 

በሽታውን ለመቆጣጠር ከሚያስችሉ መንገዶች አንዱ ቤት ውስጥ መቀመጥ መሆኑ የዓለምን ኢኮኖሚ ማናጋቱ አይቀሬ ነው፡፡ የበርካታ ኢንዱስትሪዎች መዘጋት፣ የእንቅስቃሴ መገታትና የበሽታው አስጊነት በራሱ የሚፈጥረው ጫና በሕዝብ ላይ የሚያሳድረው የሥነ ልቦና ቀውስም ከባድ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ደግሞ፣ ኮቪድ 19 በጤናው ዘርፍ ላይ የሚያሳድረው ጫና መዘዝ፣ በሽታው በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላም የሚቀጥል መሆኑን ነው፡፡ ያደጉት አገሮች ኢኮኖሚያቸው በጥቂት ጊዜያት እንዲያገግም የሚያስችል አቅም ሲኖራቸው፣ በማደግ ላይ ያሉትና ደሃ አገሮች ግን የኢኮኖሚ ውድቀት ያጋጥማቸዋል፡፡ ቫይረሱን ለመግታት በሚደረጉት ርብርብም ኢኮኖሚያቸው ያሽመደምዳል፡፡

የአፍሪካ ብቻ ቢታይ፣ ቫይረሱን ለመግታት ሲባል በሁሉም የሥራ ዘርፍ ከተሰማሩ ሠራተኞች ከግማሽ በላይ ያህሉ ሥራ አጥ ይሆናሉ፡፡ 220 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢም ይታጣል፡፡ ኮሮና ቫይረስ በደሃ አገሮች ላይ ጥሎ የሚያልፈው ጠባሳም በምንም መስፈርት ከሌሎች የሚነጻጸር አይሆንም፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ)፣ ደሃ አገሮች ባላቸው ጥቂት ሀብት ተጠቅመው ቫይረሱን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት፣ ከሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ለማገገም ዓመታት ይወስድባቸዋል ብሏል፡፡

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫም፣ ደሃ አገሮች ቫይረሱን ለመግታት በሚደረግ ርብርብ 220 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ያጣሉ፡፡ የዩኤንዲፒ አስተዳዳሪ አሻም ስቴነር እንደሚሉት፣ በዓለም በበርካቶቹ አገሮች ቫይረሱ ጥሎት የሚሄደው ጠባሳ ጥልቅ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድጋፍ ካላደረገም ባለፉት ሁለት አሠርታት በዓለም የታዩ ዕድገቶች ወደኋላ የሚመለሱ ሲሆን፣ ይህም አንድ ትውልድን እንደማጣት ይቆጠራል፡፡

በገቢ ላይ የሚፈጠረው ቀውስ በማኅበረሰቡ ትምህርት፣ ሰብዓዊ መብትና ምግብ ዋስትና ላይ ከባድ አደጋ ይጥላል፡፡ በደሃ አገሮች የሚገኙ ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ከአቅማቸው በላይ የሚጥለቀለቁ በመሆኑ፣ ቫይረሱ እንዲሠራጭ ያደርጋል፡፡ በደሃ አገሮች ከሚገኙ ሕዝቦች 75 በመቶ ያህሉ ውኃና ሳሙና የማያገኙ መሆናቸው፣ በሽታው እንዲዛመትና አገሮቹም ኢኮኖሚያቸው እንዲወድቅ ምክንያት ነው፡፡

በዩኤንዲፒ የኤችአይቪ ኤድስ፣ የጤናና የልማት ቡድን ዳይሬክተር ማንዲፕ ዲሊዋል፣ ምንም እንኳን የተጠናከረ የጤና ሥርዓት ያላቸው አገሮች ጭምር በኮሮና ወረርሽኝ እየተፈተኑ ቢሆንም፣ የጤና ሥርዓታቸው ባልተጠናከረ አገሮች ሊፈጥር የሚችለው ቀውስ የላቀ ነው፡፡

ኮቪድ 19 በደሃ አገሮች ላይ የሚያሳድረው የኢኮኖሚ ውድቀት

 

በመሆኑም በደሃ፣ በማደግ ላይ ባሉና ኢኮኖሚያቸው እያደገ በሚገኙ አገሮች መሠረተ ልማት ባልተሟላላቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ፣ ለእስረኞችና ለስደተኞች ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ አገሮች ከፍተኛ ወንጀል የሠሩትን ሳይጨምር ለቀሪዎቹ ይቅርታ እያደረጉ ሲሆን፣ ስደተኞች ላይ የሚሠራው ሥራ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃም ፈታኝ ሆኗል፡፡

ከቀያቸው ተፈናቅለው እዛው አገራቸው በሚገኙ ከተሞች የቀን ሥራ የሚሠሩ የችግሩ ሰለባ እየሆኑ ነው፡፡ በህንድ ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ ተዘዋውረው የሚሠሩ ሰዎች፣ ሥራዎች በመዘጋታቸው ሳቢያ ለችግር ተጋልጠዋል፡፡ ዕርዳታ ሰጪዎችም ቢያንስ በቀን አንዴ በልተው እንዲያድሩ የምግብ ማከፋፈል ሥራ ጀምረዋል፡፡ ይህ ግን ሁሉን የሚያዳርስ አልሆነም፡፡

የኢኮኖሚ ጫናው በህንድ ብቻ ሳይሆን በአሜሪካም ታይቷል፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ ምግብ ያገኙ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርት በመዘጋቱ እንዳይራቡ ሲባልም፣ ትምህርት ቤቶች በየተማሪዎች ቤት በመዘዋወር ምግብ ማከፋፈልን ተያይዘውታል፡፡

በኢኮኖሚው ላደጉ አገሮች ይህ ቢቻልም፣ ለደሃ አገሮች ግን ቤት ቁጭ ያሉትን ተማሪዎችም ሆነ አቅም የሌላቸውን ቤተሰቦች መመገብ ከባድ ነው፡፡

ህንድ ከሕዝቧ ግማሽ ያህሉ ከድህነት ወለል በታች የሚኖር ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሰዎችን ከእንቅስቃሴ መገደብ የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ ችላ የሚባልም አይደለም፡፡ በህንድ የተስተዋለው ችግር በአፍሪካም ሊከሰት እንደሚችል አልጀዚራ ያነጋገራቸው በዩኤንዲፒ የአፍሪካ ቢሮ ዳይሬክተር አሁዋና ዚኮንዋ ይገልጻሉ፡፡

ለአብነትም የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የወሰዱት ዕርምጃ፣ ከኬንያ ሠራተኞች ውስጥ በኢመደበኛ የተሰማሩትን 83.6 በመቶ ያህል ሠራተኞች አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡

በአፍሪካ በኢቦላ ቫይረስ በተጠቁና ከበሽታው ለመውጣት በሚጥሩ አገሮች ላይ ያለው የገንዘብ ቀውስም ቀላል አይደለም፡፡ በአፍሪካ አሁን ላይ ኮሮና ቫይረስ ያደረሰው ጉዳት ከሌሎች ሲነጻጸር ትንሽ ቢሆንም፣ ወደፊት የሚከሰተው የከፋ ሊሆን ይችላል የሚል ግምትም ተጥሏል፡፡

በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ያለው ቀውስና ግጭት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከኢቦላ ወረርሽኝ ጋር ግብ ግብ ይዛለች፡፡ ሌሎች አገሮች በአንበጣና በሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች እየተጎዱ ነው፡፡ ታንዛኒያ በቅርቡ በጎርፉ ተመትታለች፡፡

በአፍሪካ በርካቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ላይ ተመሥርተው ይኖራሉ፡፡ አሁን ኮሮና ቫይረስን ለመግታት በተጣሉ የመዘዋወር ገደቦች ምክንያት፣ የምግብ ዕርዳታዎች አይደርሱም፡፡ ዚኮንዋ እንደሚሉት፣ የጤና ባለሙያዎችም ቢሆኑ የመከላከያ ቁሳቁስ ካላገኙ ለሥራ አይመጡም፡፡ ይህና ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች ባሉባት አፍሪካ ኮሮና ቫይረስን መከላከሉ ቀላል አይሆንም፡፡

በሽታውን ለመከላከል በሌሎች አገሮች እየተወሰዱና በአፍሪካም በአንዳንድ አካባቢዎች በከፊል እየተተገበረ የሚገኘው የ‹‹ቤት ውስጥ ቁጭ በሉ›› ገደብ፣ ዕለት ከዕለት እየሠሩ ለሚመገቡና በድህነት ውስጥ ለሚኖሩ አፍሪካውያን አዋጭ አማራጭ አይደለም፡፡

በአፍሪካ በርካቶች ውኃና ሳሙና የላቸውም፡፡ ቤት ተቀምጠው የሚጠብቁት ነገር የለም፡፡ ምግብ የለም፡፡ ገቢ የሚያገኙት የቀን ሠርተው በቀን ነው፡፡

ይህንን ችግር ለመቅረፍ የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በማደግ ላይ ላሉና ደሃ አገሮች የብድር እፎይታ ጊዜ የመስጠትን አስፈላጊነት አስምረውበታል፡፡ ልገሳና ተጨማሪ ብድር ከመስጠት በተጨማሪም፣ አበዳሪዎች ለደሃ አገሮች የብድር እፎይታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ደሃ አገሮችን መርዳት የሚቻለውም ብድራቸውን በማንሳትና የእፎይታ ጊዜ በመስጠት ነው፡፡ በተለይ ብድር ወስደው ለመመለስ ያቃታቸውና ቫይረሱ ከመከሰቱ በፊትም የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ያሉትን አገሮች መታደግ ወሳኝ መሆኑን የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ ተናግረዋል፡፡

ዩኤንዲፒ በአሁኑ ሰዓት ቻይና፣ ዩክሬን፣ ኢራን፣ ኤርትራ፣ ናይጄሪያና ቬትናምን ጨምሮ የሌሎች አገሮችን የጤና ሥርዓት እየደገፈ ነው፡፡ 100 አገሮችን ለመርዳትም 500 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው አስታውቋል፡፡ ይህ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለሚሠራው ሥራ ያግዛል፡፡ ሆኖም በአኅጉሪቷ የተረጋገጠውን የኢኮኖሚ ቀውስ ለመታደግ የሚያስችል አይደለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -