Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የያገባናል ኢትዮጵያ ጉዞ

ሰዎች ከራሳቸው የሕይወት ልምድ ተነስተው ክፍተቶቻቸው የሌሎች ሰዎች ክፍተት እንዳይሆን ይጥራሉ፡፡ ጥረታቸው ይሰምር ዘንድ ማኅበራትና ሌሎች መሰብሰቢያ ቡድኖችን በመመሥረት ችግሮችንና ክፍተቶችን እንዳይኖር ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ያገባናል ኢትዮጵያ ማኅበር የተለያዩ ሐሳብና የኋላ ታሪክን ያላቸው ሰዎች ስብስብ ነው፡፡ ማኅበሩ እያንዳንዱ አባል የነበረበትን ችግር የተለያዩና የመጡበት  የቤተሰብ ኑሮ ለየቅል ቢሆንም የየራሳቸው ችግር ማኅበር እንዲመሠርቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ያገባናል ኢትዮጵያ ማኅበር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ ተማሪዎችና ሠራተኞች የማበረታታትና በአዕምሮ የማጎልበት ምክር በመለገስ ለተማሪዎች ግንዛቤ እያስጨበጠ ቆይቷል፡፡ ስለ በጎ አድራጎት ማኅበሩና በሥሩ ስላሉት እንቅስቃሴዎች ሔለን ተስፋዬ የበጎ አድራጎት ማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅን ወ/ሮ መስተዋት ስሜን አጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ያገባናል ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበር መቼ ተመሠረተ?

ወ/ሮ መስተዋት፡– ያገባናል ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበር የተመሠረተው ሐምሌ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ማኅበሩ ያገባናል ኢትዮጵያ ከመባሉ ቀደም ብሎ ያገባናል ፀረ ኤድስ ማኅበር ከዚያ በፊት ደግሞ ሴና የሚባል የኪነ ጥበብ ቡድን ነበር፡፡ በፀረ ኤድስ ማኅበር ሳለን ብዙ እንቅስቃሴዎችን ስንሠራ ቆይተናል፡፡ በይበልጥ የተፈተንበት የሴተኛ አዳሪዎች ፈተናዎቻቸውን በጥልቀት ለመገንዘብ የቻልንበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ሴቶች የነበረባቸው ችግር ወደ አሁኑ ማኅበር ድልድይ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሴቶቹ ችግራቸው ምንድን ነበረ? በምን መልኩ ነበር ድልድይ የሆናችሁ?

ወ/ሮ መስተዋት፡– እኛ ስንሠራ አብዛኛዎቹ ሴቶች ዩኒቨርሲቲ እየተማሩ ያቋረጡ፣ አንዳንዶች ደግሞ 11ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ትምህርታቸውን መከታተል ያልቻሉ ናቸው፡፡ ትልቁ ችግራቸው የነበረው ቤተሰቦቻቸው ቤት እያሉ አዲስ ዕቃ ሲገዙ ከየት አመጣሽ ብሎ የሚጠጥቅ የለም፡፡ ቤተሰብ በተለይም የወጣት ሴት ልጆቹን እንቅስቃሴ መከታተልና መነጋገር በሌለበት ችግሩ ይበልጥ ጎልቶ እንደሚታይ በሥራዎቻችን ለማየት ችለናል፡፡ ሴቶችን የሚያባባብሉ፣ በገንዘብና በተለያዩ ብልጭልጭ ነገሮች የሚታለሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ከፀረ ኤድስ ማኅበር ወደ ያገባናል ኢትዮጵያ ማኅበራት የተሸጋገረው፡፡ ምክንያቱም ትልቁ ችግር የሚጀመረው ሴቶች ለአቅመ ሔዋን (አፍላ ጊዜ) ሲደርሱ ጓደኞቻቸው በሚያደርጉት ነገር መሳብ ሲጀምሩ ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ችግሮቻቸውን ለቤተሰብ ከመንገር ይልቅ በራሳቸው መንገድ መፍታት የጀመሩ ጊዜ ነው ትልቅ ጥፋት፡፡ እነሱ ችግሮችን ፈታሁ ብለው ያመኑበት መንገድ እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን ስለደረሰንበት ነው ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ሥራችንን የጀመርነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ፀረ ኤድስ ማኅበር እያለ ከማን ጋር ነበር የምትሠሩት? ማኅበሩ ምን ዓይነት ነገሮችን አከናውኗል?

ወ/ሮ መስተዋት፡– በዚያን ጊዜ በዋነኛነት ከዲኬቲ ኢትዮጵያና ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር እንሠራ ነበር፡፡ ኮንዶሞችን ለሴተኛ አዳሪዎች ከማድረስና ግንዛቤ መስጠት ባሻገር ዲኬቲ ኢትዮጵያ ያንግ ማርኬት (Young Market) በሚል ፕሮግራም በመሳተፍ ለራሳችን ገቢ ማግኘት፣ ከዚያም ለማኅበሩም መዋጮ ማሰባሰብ ጀመርን፡፡ በዚህ መልኩ ነበር ፀረ ኤድስ ማኅበር ውስጥ ስንሠራ የቆየነው፡፡ የሴቶቹ ችግር እጅግ ብዙ ነው፡፡ ቤተሰብ የሚያስተዳድሩ፣ ልጅን የሚያስተምሩ ብዙ ናቸው፡፡ በሱስ የተጠመዱ ከዚያ መውጣት ቢፈልጉም እንደየገቡበት ሰንሰለት በቀላሉ የሚበጠስ አለመሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ለዚያም ነው ምንጩን ወደ ማድረቅ የገባነው፡፡ ምንጩ ያለው ቤተሰብ ላይ፣ ትምህርት ቤቶች በተለይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ስለሆነ ወደ እዚህኛው ማኅበር ተሸጋግረናል፡፡ የተሸጋገርነው በእውነቱ እነሱ ጋር መሥራት ከእኛ በላይ የሚደሰት አለ ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም በጣም በቅርበት ነበር የምናወራው ብዙ ዓላማና ግብ ያላቸው ሴቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡-  በበጎ አድራጎት ማኅበሩ የተሰባሰባችሁት ምን ያህል ናችሁ? ማን ነው የሚደግፋችሁ?

ወ/ሮ መስተዋት፡– በፊት ቁጥራቸው አነስተኛ ነበር፡፡ ነገር ግን ዓላማው የገባቸውና ኃላፊነት የተሰማቸው እየገቡ አሁን ላይ ከ160 በላይ ሆነናል፡፡ አሁን ላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር መሥራት ጀምረናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ችግሩን በቅርበት ስለሚያውቁት አብረን መሥራት ጀምረናል፡፡ እንደ ጅማሮ እጅግ ጥሩ ለውጥ እያመጣን ነው፡፡ በተለይም ወላይታ ዩኒቨርሲቲ ላይ የነበረን ሥራ የሚናፈቅና በተማሪዎቹም እጅግ የተወደደ ነው፡፡ ምክንያቱም በችግሮቻቸው ዙርያ በቅርበት ከሚፈልጉት ሰዎች ጋር እንዲወያዩና እንዲመካከሩ አግዘናልና፡፡

ሪፖርተር፡- ከወላይታ ዩኒቨርሲቲ ውጪ የት ሠርታችኋል ውጤቱስ?

ወ/ሮ መስተዋት፡– ሐሳቡን የጀመርነው ቤተሰቡን የሚወድ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በመጀመርያ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ መሠራት አለበት ብለን ነው፡፡ የጀመርነው ከኮተቤ ሲሆን ከዚያም ወላይታ ሶዶ ቀጠልን፡፡ ከወላይታ ሶዶ ፈቃድ ለመጠየቅ ከአንድ ወር በላይ ጊዜ ፈጅቶብናል፡፡ ከዚያም ከ13,000 በላይ ተማሪዎች በተሰበሰቡት ያዘጋጀነው ፕሮግራም የተዋጠ ነበር፡፡ በጋምቤላ፣ ኮተቤ፣ ጅግጅጋ፣ አርሲ ልክ እንደ ወላይታ ዓይነት ዝግጅት አዘጋጅተን ጥሩ ውጤት አይተንበታል፡፡ ተማሪው የሚያወያየውንና የውስጡን የሚናገርበት መድረክ ይፈልጋል፡፡ ይህን እኛ በተገኘንበት ወቅት ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ከእነዚህ ተቋማት በኋላ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ጥያቄ አቅርበውልን ሥራዎቻችንን ይዘን ለመሄድ ተዘጋጅተናል፡፡ ነገር ግን አሁን በዓለም የተከሰተው ወረርሽኝ ገታ አድርጎናል እንጂ ብዙ ሥራዎችን ለመሥራት ዝግጅታችንን አጠናቀን እየተጠባበቅን ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በሄዳችሁበት የትምህርት ተቋማት የነበረው ምላሽ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ መስተዋት፡– በሄድንባቸው ተቋማት ጥሩ የሆነ ምላሽ አግኝተናል፡፡ ከዚያ በላይ የነበረው ቅርርቦሽ ይበል ለሚቀጥለው ምን ማድረግ እንዳለብን አስገንዝቦናል፡፡ በተለይ ከእህቶቻችን ጋር የነበረን ቅርርብ ይበልጥ ጥሩ ነበር፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምም ችግሩን ስላመነበት በጋራ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ይኼ ጅማሮ ነው እንጂ ፍጻሜ አይደለምና እየተሻሻለና እየጎለበት የሚመጣ ይሆናል፡፡ በሁሉም ጊዜ በምናደርገው ሥራ ችግሮቻችንን እየለየንና እያሻሻልን እንገኛለን፡፡ በዓለም ተከስቶ ያለው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭቱ ሲገታ ሥራችንን በይፋ ይቀጥላል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የአልኮል የመስጠት ሥራ ለመሥራት ዝግጅቶቻችንን አጠናቀናል፡፡ እንደ ማኅበር ችግሩ ስለሚመለከተን በተቻለው ነገር ሁሉ ለመሥራት ዝግጁ ሆነናል፡፡

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች