Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገር‹‹አሁኑኑ ተኩስ ይቁም. . . !››

‹‹አሁኑኑ ተኩስ ይቁም. . . !››

ቀን:

በቁምላቸው አበበ ይማም

የቀድሞው የፖርቹጋል ጠቅላይ ሚኒስትር የዛሬው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ ሰሞኑን የጦርነቶች ሁሉ ጦርነት የሆነውን የኖቨል ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በተባበረና በፈረጠመ ክንድ መከላከል ይቻል ዘንድ ዓለም አቀፍ የተኮስ አቁም እንዲደረግ ለመላው ዓለም ጥሪ አድርገዋል፡፡ ተኩስ አቁሙ ያስፈለገው እውነተኛውንና የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት የሆነውንና ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዝነውን ትንቅንቅና የጨበጣ ፍልሚያ በድል ለመወጣት ነው፡፡ ሌሎች ጦርነቶች በገዥዎች ግትር አቋም፣ ሥውር ጥቅምና ፍላጎት በአገርና በሕዝብ ስም የሚካሄዱ የውክልና ጦርነቶች እንጂ፣ እውነተኛ ጦርነቶ አለመሆናቸውን ዋና ጸሐፊው በዘወርዋራ ነግረውናል፡፡

እውነተኛው ጦርነት በማንም ስህተት የማይቀሰቀስ እናት ተፈጥሮ የምታውጅብን እንደ መሬት መንቀጥቀጥ፣ ሱናሚ፣ ኃይለኛ ውሽንፍር፣ እሳተ ጎመራ፣ ከባድ አውሎ ንፋስና ወረርሽኝ ነው፡፡ ተኩስ አቁም ከጠብመንጃም ሆነ ከማንኛውም የጦር መሣሪያ አፈሙዝ የሚወጣ አረር ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ከመደበኛውም ሆነ ከማኅበራዊ ሚዲያው የሚተኮሰውን የፍርኃት፣ የጥላቻ፣ የልዩነት፣ የቂም፣ የደባ፣ የሴራ፣ የውዥንብር፣ የአሉባልታ፣ የሐሰት የመረጃ ወረርሽኝ (ኢንፎዴሚክ) እሩምታ ጭምር እንጂ፡፡ ወረርሽኙን ፖለቲካዊ ግዳይ መጣያ፣ ነጥብ ማስቆጠሪያ፣ መራጭ ማማለያ ለማድረግ የሚከወን ሥውር ወይም ይፋ ትንቅንቅና ግብግብንም ያካትታል፡፡

- Advertisement -

ጉቴሬዝ እነዚህን ሰው ሠራሽ ከፍ ሲልም ጊዜያዊና ሐሰተኛ ጦርነቶችን በተኩስ አቁም አቆይተን፣ ዋናውን በሰው ልጅ ህልውና ላይ የተደቀነውን ጦርነት በአንድነት እንፋለመው ሲሉ ነው ጥሪ ያስተላለፉት፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ 70 ዓመታት በላይ ዓለምን ዋልታና ማገር ሆነው ያቆሟትን፣ ገድግደው የያዟትን ሉዓላዊነት (ግሎባላይዜሽን) እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የቡድን 20 የቡድን ሰባት የእስያ፣ብሪክስ፣ ወዘተ. ተቋማት በሕዝበኝነት (ፖፑሊዝም) በተነጣይነት፣ በአክራሪ ብሔርተኝነት፣ አሜሪካ በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ ኢኮኖሚያዊ የበላይነትና የጦር ልዕለ ኃያልነት የተጎናፀፈችውን ዓለም አቀፍ የመሪነት እርካብ በቀኝ አክራሪውና አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ ‹‹አሜሪካ ትቅደም›› ስሁት ወለፈንድ መርህ ከሦስት ዓመታት ወዲህ በፈቃዷ ስለለቀቀች በዓለማችን የመሪነት ክፍተት ተፈጥሯል፡፡ ክፍተቱን በአየር ንብረትና በአካባቢ ጥበቃ፣ በኑክሌር የጦር መሣሪያ፣ በዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትና በዓለም አቀፍ ነፃ የንግድ ሥርዓት ስምምነቶች መክሸፍ ተመልክተናል፡፡

ዛሬ ደግሞ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት አስተባብሮ አቀናጅቶ የሚመራ ኃይል ባለመኖሩ፣ የተፈጠረው ክፍተት ዓለማችንን ውድ ዋጋ እያስከፈላት ነው፡፡ በባራክ ኦባማ ዘመን ሳርስ፣ ኢቦላንና ሌሎች ወረርሽኞችን ለመከላከል አሜሪካ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን፣ ምዕራባውያንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን አስተባብራ በመምራቷ በአጭር ጊዜ ውጤታማ መሆን ችላ ነበር፡፡ ዛሬ ዕድሜ ለትራምፕ አሜሪካ ወረርሽኙን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ጥረቱን ማስተባበር አይደለም፣ የየግዛቶቿን ጥረት በቅጡ ማቀናጀት ተስኗት ማጠፊያው አጥሯታል፡፡ ይህን መጣጥፍ እየጫርኩ በአሜሪካ ቻይናንና ጣሊያንን ቀድማ ከ140 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 2,100 በላይ ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ የወረርሽኙ ዋና መናኸሪያ ወይም ማዕከል በሆነችው ኒውዮርክ በየሦስት ቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ አሻቅቧል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያግዙ ቁሳቁሶችና መድኃኒቶች እጥረት በሁሉም ግዛቶች እየተስተዋለ ነው፡፡ እስከ ሰኞ ዕለት በዓለማችን ከ725 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የሞቱት ደግሞ ወደ ከ34 ሺሕ በላይ ናቸው፡፡

በአንድ ሳምንት ብቻ 3.2 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ወረርሽኙን ተከትሎ የሥራ ፈላጊ ሆነዋል፡፡ ሁሉን ነገርፖለቲካ መሣሪያ፣ የምርጫ መቀስቀሻ ማድረግ የሚቀናው ትራምፕ ወረርሽኙን ለመከላከል ያደረገው ጥረት ደካማ መሆኑ ሲተች፤ዴሞክራቶች በሩሲያ ላይ የሚደረገው ምርመራናልጣንን ያላግባብ የመጠቀም ክስ አልሳካ ቢላቸው፣ አሁን ደግሞ እ.ኤ.አ. 2020 ምርጫ እንዳላሸንፍ በኮሮና ቫይረስ ስም እየቀሰቀሱብኝ እንጂ ወረርሽኙስ እንዲህ የሚያሳስብ አይደለም በማለት ቢያቃልለውም፣ ዛሬ ዙሪያው ገደል ሆኖበታል፡፡ ቀኝ ዘመም ሚዲያዎችም በፎክስ ኒውስ ፊታውራሪነት ከእሱ ጋር ወረርሽኙን ሲያናንቁት እንዳል ኖሩ ዛሬ ተመልሰው ስለወረርሽኙ ዋና ለፋፊ ሆነዋል፡፡ በዓለማችን አሜሪካ በትራምፕ ስሁት አይዲኦሎጂ የተነሳ የመሪነት ሚናዋን መወጣት ባለመቻሏ፣ ቻይናም ከወረርሽኙ የዞረ ድምር በቅጡ ባለማገገሟ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል ዓለም አቀፍ ጥረት እያስተዋልን አይደለም፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል የተመሠረተው ፋና ወጊና አንድ ለእናቱ ትብብር፣ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አነሳሽነትና በአሊባባ የቻይና ቁጥር አንድ ቢሊየነር ጃክ ድጋፍ የተቋቋመው ግብረ ሰናይ ድርጅት ይጠቀሳል፡፡ በዚህ አርዓያነት ባለው ትብብር 100 ቶን የአፍንጫና የአፍ መሸፈኛና መከላከያ አልባሳት በኢትዮጵያ አጋፋሪነት ለአፍሪካ አገሮች እየተከፋፈለ ነው፡፡ ለዚህ ነው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋቂ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን፣ ‹‹በአኅጉሩ ወረርሽኙን ለመከላከል እየሰጡ ያለውን በሳል አመራርና ያሳዩትን ተነሳሽነት አደንቃለሁ፡፡ የዓብይ ጃክ ድርጅት (ፋውንዴሽን) ኮቪድ19 ለመከላከል የሚያግዙ የምርመራ መሣሪያዎችን፣ የአፍንጫና የአፍ መሸፈኛዎችንና የመከላከያ አልባሳትን ስለለገሰ አመሠግናለሁ፤›› ሲሉ የምሥጋና ደብዳቤ በመጻፍ ዕውቅና የሰጡት፡፡

በዚህ ፈታኝ ወቅት ወረርሽኙን ለመከላከል ከሚያስፈልገው ሀብት በላይ የተዋጣለት አመራር ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው በአሜሪካ፣ በጣሊያንናስፔን ወረርሽኙ እያስከተለ ያለው የከፋ ጉዳት አንዱ መንስዔ የመሪ እንደ ንስር አርቆ አለማየት፣ አቅላይነት፣ አቀናጅቶ የመምራት ልምሻ፣ ዳተኝነት፣ መወላወል፣ ወዘተ. ተደርጎየተወሰደ ነው፡፡ ኮቪድ19 እያጠቃ፣ እያሸበረ፣ ኑሮአችንን እያመሰቃቀለ፣ ነፃነታችን ተስፋችንን፣ ራዕያችንን እየሸራረፈ ማኅበራዊ መስተጋብራችንን በአዲስ እየበየነ ያለው፣ ያለ ልዩነት በሰው ልጅነታችን ነው፡፡

ልናስቆመውና ልንገታው የምንችለው እንደ ሰው በአንድነት ቆመን ስንመክተው ነው፡፡ ወረርሽኙ ቀኝ አክራሪ፣ ሦስተኛ አማራጭ፣ ግራ ዘመም፣ ለዘብተኛ፣ ሕዝበኛ፣ ሶሻሊስትና ካፒታሊስት አይለይም፣ አይመርጥም፡፡ ሊበራል፣ ኒዮ ሊበራል፣ ዴሞክራት፣ ሶሻል ዲሞክራት፣ ሪፐብሊካን እያለ በአይዲኦሎጂ አይከፋፍልም፡፡ ቀራጭ፣ ጸሐፍት፣ አይሁድ፣ ግሪክ፣ ግብፅ፣ እስራኤል፣ ሙሴ፣ ፈርኦን እያለ አያሠልፍም፡፡ ጥቁር፣ ነጭ፣ ቢጫ፣ ስፓኒክ፣ ነባር፣ መጤ በሚል መርጦ ለይቶ አያጠቃም፡፡ ከቆዳህ ቀለም ጉዳይ የለውም፡፡ ክርስቲያን፣ እስላም፣ ሺዓ፣ ሱኒ፣ ሒንዱ፣ ቡድሃ፣ ሽንዙ፣ ኮንፊሺየስ በማለት ከሃይማኖትህ ጋር ፀብ የለውም፡፡ ምዕራባውያን፣ አሜሪካ፣ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ፣ ቅብርጥሴ፣ ምናምን የሚል ዝርዝርም የለውም፡፡

የኖቨል ኮሮና ቫይረስ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ጋምቤላ፣ ጉምዝ፣ ወላይታ፣ ጌዴኦ፣ ሀድያ፣ ወዘተ. የሚል ፋይል የለውም፡፡ ኮቪድ19 ብልፅግና፣ ኢዜማ፣ አብን፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ አረና፣ ትህነግ፣ ፌዴራሊስት፣ አህዳዊ፣ ጎጠኛ፣ ትምክህተኛ፣ ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ ቁሞ ቀር፣ ተቸካይ፣ አጎንባሽ፣ ጨለምተኛ፣ ወዘተ. የሚል ጥቁር መዝገብ የለውም፡፡ ሴት፣ ወንድ፣ ብላቴና፣ ጎልማሳ፣ መበለት፣ ሽማግሌ፣ አሮጌ፣ ወዘተ. የሚል መደብም የለውም፡፡ ኮቪድ19 የሞት ፈረሱን ሽምጥ እየጋለበ፣ ጦሩን እየሰበቀ፣ ዘገሩን እየነቀነቀ ከቻይናዋ ውሀን ታኅሳስ መጨረሻ ላይ ተነስቶ ከአንታርቲካ ውጪ ሁሉን አኅጉራት ያዳረሰው ሕዝበ አዳምን ያለ ልዩነት በማርገፍ ነው፡፡

የመጣው በሁላችን በሰው ልጆች ላይ ነው፡፡ የጦር ዕቃችንንና ጥሩራችን ለብሰን፣ የራስ ቁራችንን ደፍተን የምንጋፈጠው ሰው በመሆን ነው፡፡ ከሰውነት ልዕልና ባለመጉደል፡፡ ውኃ ልካችንን በመጠበቅ፡፡ ትራምፕ ‹‹ቻይና ቫይረስ›› ያለው ጊዜ ስቷል፡፡ ከሰውነት ሙላት ጎድሏል፡፡ በዚህ ፈታኝ፣ ክፉ ቀን በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በጎጥ፣ በቀዬ ከተከፋፈልን ከኢትዮጵያዊነት ፅዋ ጎድለናል፡፡ ለኮቪድ19 እጅ ሰጥተናል፡፡ ይኼን ክፉ ቀን ተጋግዞ፣ እጅ ለእጅ ተያይዞ፣ አንተ ትብስ አንቺ ትብሸ ተባብሎ ማለፍ ሲገባን የሀብት ማካበቻ ካደረግነው ከሰውነት ተራ ወጥተናል፡፡ 20 ብር ይሸጥ የነበረን አፍንጫ የአፍ መከለያ 20 እጥፍ 400 ብር ሲሸጥ፣ 100 ብር ይሸጥ የነበረ ነጭ ሽንኩርት 250 ብር ሲልህ፣ ገና ክፉ ቀን መጥቷል ብሎ ትናንት ምሽት ያየኸውን ሸቀጣ ሸቀጥ ዛሬ ማለዳ መደርደሪያውን ባዶ አድርጎ ስታገኘው ሰውነቱን፣ ኢትዮጵያዊነቱን ብትጠራጠር አይፈረድብህም፡፡ ይፈረድበታል እንጂ፡፡ ከወዲህ እንደ ጋዜጠኛ ቤተልሔም ጥጋቡ ያሉ የሰውነት ልኬቶች በትርፍ ጊዜያቸው ጭምብል ሰፍተው በነፃ ውሰድ ሲሉህ፣ በዚህ በኩል ቤታቸውን ለቀው ለለይቶ ማቆያ ይዋል ብለው ሲሰጡ፣ ኦል ማርት ዋጋ ሳይጨምር ከማገልገል አልፎ 100 ሺሕ ብር ሲለግስ በወገንህ እንዳላፈርህ፣ እንዳልተሸማቀቅህ መልሰህ ትፅናናለህ፡፡

አንተ ዓይንህን ለአፈር ተባብለህ መሽገህ ገድበህ እየተጠባበቅህ እያለ ጃክ ውቅያኖስ ተሻግሮ ሲደርስልህ በራስህ ከማፈር ውጭ ምን አማራጭ አለህ፡፡ ተፀፅተህ በማንነቱ ያገለልከውን ወገንህን ለመደገፍ ብትነሳ ግን ትድናለህ፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ ተማፅኖ በአንድም በሌላ በኩል የሰውን ልጅ ወደ ሙላቱ ወደ ከፍታው የመመለስ የንዑድ ጥሪ አካል ነው፡፡ ‹‹የቫይረሱ አስከፊነት የጦርነትን ከንቱነት ያሳያል፡፡ ለዚህ ነው በመላው ዓለም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ የማደርገው፡፡ አፈሙዝን በመዘቅዘቅ፣ የባሩድ ሽታን በማስወገድ በአንድነት ወረርሽኙን መከላከል ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ‹‹የተኩስ አቁሙ በሶሪያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሊቢያ፣ በፍልስጤም፣ በዩክሬን፣ በየመን፣ በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ኮንጎ፣ በካሜሩን፣ በናይጀሪያያ፣ ወዘተ. የረድኤት ድርጅቶች ያለ ሥጋት ለሆስፒታሎች ለዜጎች ድጋፍ በማድረግ የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ያስችላቸዋል፡፡

ጉቴሬዝ ለሰው ልጆች ሁሉ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሣይኛ፣ በማንዳሪን፣ በዓረብኛ፣ በስፓኒሽ፣ በስዋሂሊ፣ ወዘተ. ባስተላለፉት ጥሪ ‹‹ዓለም ኮቪድ19 የተሰኘ የጋራ ጠላት ተነስቶባታል፡፡ ቫይረሱ ዜግነት፣ ጎሳ፣ ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉን ያጠቃል፡፡ ይሁንና ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች፣ ተፈናቃዮች፣ አረጋውያን፣ የተገለሉ ሰዎች ላይ ይበረታል፡፡ ጦርነት ባወደማቸው አገሮች ደግሞ የጤና ተቋማት ስለፈራረሱ የሕክምና ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ስለሌሉ የወረርሽኙ ጉዳት የከፋ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው በማስከተልም፣ ‹‹ተዋጊ ኃይሎች ጠብ ጫሪነትን አቁመው፣ አለመተማመንንና ለግጭት መፈላለግን ትተው፣ ተኩስንና የአየር ጥቃትን በማስቀረት ሕይወትን ለማዳን የሚያግዝ ዕርዳታ ለማድረስ መተላለፊያ መንገድ (ኮሪደር) ሊከፍቱ ይገባል፡፡ እግረ መንገድም ተቀራርቦ ለመነጋገር ለመወያየት መልካም አጋጣሚ መፍጠር ይቻላል፡፡ በግጭት ቀጣናዎች ለሚኖሩ ዜጎችም ተስፋን የሚያለመልሙና ቫይረሱን ለመከላከል የሚያግዙ ድጋፎች ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ተፃራሪ ኃይሎች ለትብብርና ለንግግር ዕድል ፈንታ በመስጠት በመሀላቸው ያለውን ልዩነት በማጥበብ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል ተጨማሪ አቅም መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁኑኑ በየትኛውም የዓለማችን ማዕዘናት የሚገኙ ግጭቶች ጦርነቶች ቆመው፣ ፊታችንን የሰው ልጅ የጋራ ጠላት ወደሆነው ኮቪድ19 ማዞር አለብን፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ማጠቃለያ

1911 ዓ.ም. በአገራችን በተከሰተው ስፓኒሽ ፍሉ (የኅዳር በሽታ) 40 ሺሕ ወገኖቻችን አልቀዋል፡፡ ከዚህ ከፍ ያሉ በፀና ታመው ድነዋል፡፡ እንደ የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ ያሉ የቁርጥ ቀን ሰዎች መኖር የወረርሽኙን ጉዳት በእጅጉ ቀንሶታል፡፡ የኔታ ለሕይወታቸው ሳይሰስቱ ጎሳና ሃይማኖት ሳይለዩ በሠፈራቸው በጉለሌ በየቤቱ እየዞሩ ለበሽተኞችና ለገመምተኞች እንጀራና ውኃ በማደል የብዙዎችን ሕይወት መታደጋቸውን  ሙሴ ሴደርኩይስት የተባሉ ስዊድናዊ ሚስዮናዊ አስተማሪ በየሠፈሩ እየዞሩ ለበሽተኞች እህልና ውኃ መድኃኒት በመስጠት ትሩፋት መሥራታቸውን ከጥቂት ቀናት በኋላ በዚሁ በሽታ ታመው ሞተው ጉለሌ መቀበራቸውን፣ ‹‹የሃያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ›› ደራሲ መርስዔ ሐዘን ልደ ቂርቆስ ሰንደው አቆይተውናል፡፡

ዛሬም በአገራችን የኮቪድ19 ወረርሽኝ ለመከላከል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ ቅንና ደጋግ ሰዎች ለሕይወታቸው ሳይሠጉ፣ ለሀብት ገንዘባቸው ሳይሰስቱ አርዓያነት ያለው ተግባር በማከናወን ባለፉት ሦስት ዓመታት ካሳለፍነው የጥላቻ፣ የልዩነተ፣ የቁርሾ የዞረ ድምር እንድናገግም ማስታገሻ ሆነውናል፡፡ በዜጋችን በአገራችን መልሰን ተስፋ እንድንሰንቅ ከወረርሽኙ አድማስ፣ ከአሜን ባሻገር እንድንመለከት ዓይናችንን ከፍተውልናል፡፡ ውለታቸውንም ትውልድ ሲዘክረው ይኖራል፡፡

ፈጣሪ አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
አሜን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...