Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኮሮና ቫይረስና አነታራኪው የቁጥሮች ፖለቲካ

ኮሮና ቫይረስና አነታራኪው የቁጥሮች ፖለቲካ

ቀን:

በያሬድ ንጉሤ

መንግሥትን ለፖለቲካ ፍጆታ የማይውሉ ጉዳዮችን ፖለቲካዊ አንድምታ በማላበስ የሚያሙት አሉ፡፡  ሚስጥር መሆን የሌለባቸውንም ጉዳዮች በመደበቅ በነቢብ የግልጽነት ደጋፊ ቢመስልም፣ በገቢር ግን የድብቅነት አባዜ የሚስተዋልበት እንደሆነም ተደጋግሞ ይነሳል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ተደጋግመው የፖለቲካ ጥል ሲሆኑ ከሚታዩት ጉዳዮች መካከል የቁጥር ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ በተለያዩ ግጭቶች የሞቱ፣ ጉዳትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸው ዜጎች ሲኖሩ በመንግሥት፣ በመብት ተሟጋች ድርጅቶችና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሰጡ ቁጥሮች ልዩነታቸው ሰፊ የሚሆኑባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም፡፡ ይህም አንድን አባባል ያስታውሰናል፡፡ ‹‹ስለራስህ ለመናገር ባልደፈርክና በሰነፍክ ቁጥር ክፍተቱን አሉባልታዎች ይሞሉታል፤›› የሚል ነው፡፡ ሚስጥር የማይሆኑ ጉዳዮችን ሚስጥር የሚያደርግ፣ ወትሮም ቢሆን ሚስጥር ምን እንደሆነ በቅጡ ያልተረዳ ሊሆንም ይችላል፡፡

በቀድሞው ኢሕአዴግ በአሁኑ ብልፅግና ፓርቲ ውስጥም በቁጥር ጉዳይ ያለው አተካሮ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የቁጥር ጦርነቱ የሚጀምረው በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በተለያዩ የሥልጣን እርከኖች በበቂ ሁኔታ አልተወከልንም የሚሉ ብሔሮችና የተለያዩ ቡድኖች፣ በተለያዩ ምክንያቶች ቅሬታቸውን ሲያነሱ የሚደመጡበትን ጊዜያት ጨምሮ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በቅርቡ ለአዳዲስ የመንግሥት ሹማምንት የፖለቲካ ሥልጣን ሲሰጥ የትግራይ ብሔር ተወካዮች በፌዴራል የመንግሥት ሥልጣናት ላይ በበቂ ሁኔታ አልተወከሉም የሚለው ክርክር በፓርላማ እንዲነሳ የሆነውም፣ ለረዥም ጊዜያት በገዥው ፓርቲ ውስጥ ያለውን የቁጥር ፖለቲካና ሥልጣንን በብሔር ውክልናና ኮታ ማከፋፈል የሚያመጣውን ንትርክ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል፡፡

አሁን በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ራሱን እንዳከሰመ የሚነገርለት የቀድሞው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)ም የፌዴራል ወሳኝ የሚባሉ ሹመቶችን በራሱ አባላት በመተካትና የሥልጣን ቅርምት በማድረግ፣ ‹‹የፖለቲካ ተረኝነት›› አዙሪት ውስጥ እንደገባ ሲታማ ባጅቷል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር፣  ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ፣ የመከላከያና ደኅንነት ተቋማትና መሰል ተቋማት የኦዴፓ ሥልጣን ቅርምት ማሳያዎች እንደሆኑ የሚናገሩ የፖለቲካ ተንታኞችና ጸሐፊያን ተበራክተዋል፡፡

እነዚህን ማስረጃዎች ስናይ በወንበርና ብሔር ስብጥርም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት በሚደረጉ ቁጥርን ሆን ብሎ የማብዛት፣ የመቀራመትና የማሳነስ ሁኔታዎችን ለሚከታተል ከቁጥሮቹ ጀርባ የሚቀመር አንዳች የፖለቲካዊ ብላ ተበላ ቁማር እንዳለ ልብ ይሏል፡፡

የሕዝብ ቁጥር ብዛትም አንዱ የፖለቲካ መሣሪያ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በ1999 ዓ.ም. በተደረገው የአገር አቀፍ ሕዝብና ቤቶች ቆጠራም፣ ሕዝባቸው ጥቂት ተደርጎ እንደተቆጠረና የተዛባ እንደሆነ በመናገር ቅሬታ ያቀረቡ ብሔሮች እንዳሉ በወቅቱ ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡

ሌላው የቁጥር ቅሬታ የሚቀርብበት ጉዳይ ደግሞ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ አናሳ መሆን ነው፡፡ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እስከ ቅርብ ጊዜያት ባሉት ወቅቶች፣ ገዥው ፓርቲ ውስጥ ለይስሙላ የሚጠቀስና ለፖለቲካ ፍጆታ የዋለ ጉዳይ ተደርጎ ሲወሰድ ቆይቷል፡፡  በተቃውሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥም የሴቶች ወደ አመራርነት ለመምጣት ድፍረት እንደ ሌላቸውም ይነገራል፡፡ ከዚህ ቀደም በፖለቲካ አመራርነት ከተሳተፉት ሴቶች ውስጥ በእስር ቤትና በተለያዩ ግፊቶች ከፖለቲካው ዓለም ራሳቸውን እንዲያርቁ የተደረጉ ሴቶች፣ ምናልባትም ምክንያት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ግምት አለ፡፡

አሁን የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እየተሻሻለ እንደመጣ ሲጠቀስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የካቢኔያቸውን 50 በመቶ በሴቶች ማዋቀራቸውም እንደ መልካም ጅማሮ ተቆጥሮላቸዋል፡፡

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም በቅርቡ ይፋ ባደረገው ዓለም አቀፍ የፆታ ልዩነት ጥናት (Global Gender Gap Report 2020) እንደሚያሳየው፣ በሥርዓተ ፆታ መካከል ያሉ ልዩነቶችን በመቀነስ ከዓለም 153 አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ 70.5 በመቶ ውጤት ያገኘች ሲሆን፣ ደረጃዋም 82ኛ ላይ ሠፍሯል፡፡  ከዚህ አኳያ ከተሻሻሉ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ስፔን፣ ማሊ፣ አልባኒያና ሜክሲኮ 34.5 በመቶ በማስመዝገብ በሥርዓተ ፆታ መካከል ያሉ ልዩነቶችን በመቀነስ በዓለም ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገባቸው ተረጋግጧል፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን የሴቶች ውሳኔ የመስጠት አቅም እንዳልተሻሻለም ይነገራል፡፡ ፖለቲካ ማለት ውሳኔ የመስጠት ሒደትና ችሎታ እስከሆነ ድረስ፣ የቁጥር ተሳትፎ ስላደገ ብቻ የፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው አደገ ማለት እንደሚያዳግት ዕሙን ነው፡፡

የምጣኔ ሀብት ዕድገት መጠንም ሁልጊዜ እንዳከራከረ ነው፡፡ አንዱ አከራካሪነቱ የሚያመዝነው ዕድገቱ ለአብዛኛው ሰው በሚገባውና እያንዳንዱ ኪስ በገባው መጠን የሚጠቀስ ሳይሆን፣ በግርድፉ በቁጥር የሚነገር መሆኑ ጥቂት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ብቻ የሚረዱት፣ አብዛኛው ሕዝብ ደግሞ የማይረዳው እንዲሆንና ከብዙዎችም የፍትሐዊነት ተጠቃሚነትና ተዓማኒነት ጥያቄዎች የሚነሳበት ብሎም ጥቂቶችን ብቻ የጠቀመ  ተደርጎ እንዲወሰድ እንዳደረገው የሚስማሙበት አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ሁለት አኃዝ ዕድገት ተመዝግቧል፣ ቁጥሮቹም እውነትነት ያላቸውና በተጨባጭ ማስረጃዎች የተደገፉ ማሳያዎች የሚቀርቡበት እንደሆነ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩት እንዳሉም ሳይዘነጋ ነው፡፡

ዓለምን ያስጨነቀውና በቅርቡም ኢትዮጵያ የገባው የኮሮና ቫይረስም  ከጠንካራ ቅድመ መከላከልና መፍትሔን ከማበጀት ይልቅ፣ የተጠቁትን ሰዎች ቁጥርን በየቀኑ ቀስ እያሉ ቁጥራቸው እየጨመረ እንደሆነ ለመናገር የተደረገው ጥረት የተስተዋለበት ሆኗል፡፡ በእርግጥስ ቫይረሱ ቻይናንና ሌሎች አገሮችን ሲፈትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቫይረሱ መነሻ እንደሆነች ወደተነገረላት ቻይና የሚያደርገውን በረራ ባላቆመበት፣ መንግሥትም አይመጣምን ትቶ ይመጣልን አጥብቆ ይዞ ጠንካራ ቁጥጥር በድንበርና በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንዳልተደረገ፣ በውጭ አገሮች ቆይተው የመጡ ኢትዮጵያውያን ጭምር ለቀድሞ መከላከል ሥራዎች ሲባል በለይቶ ማቆያ ቀድሞውኑ እንዲቆዩ ባልተደረገበት ሁናቴ ውስጥ፣ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ እንደሚችል እየታወቀ ከመጀመርያው ክትትል ባለማድረጉ ደካማነቱን አሳይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በየአካባቢው በደንብ ቢፈተሽ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል የሚል ይዘት ያለው ንግግር ማድረጋቸውና ቁጥሩ ከፍ ሊል እንደሚችልና ፍንጭ መስጠታቸው፣ ዓለምን ሲያስጨንቅ የከረመው ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ በሃያዎቹ የሚገመቱ ሰዎች ብቻ ናቸው ወይ በቫይረሱ የተያዙት የሚል ጥያቄን ማጫሩ አይቀርም፡፡

በቫይረሱ እንደተያዘ የተነገረለት አንድ ጃፓናዊ ቢያንስ በኢትዮጵያ በነበረው ቆይታ አሥር ሰዎችን አግኝቶ ቢሆንና እነዚያ ያገኛቸው ሰዎችም እያንዳንዳቸው አሥር ሰዎችን ቢያገኙና ንክኪ ቢኖራቸው ብለን ብናስብ፣ የቫይረሱ ሥርጭት እንዲህ እያለ በመቶዎች አልፎም ተርፎም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሊያጠቃ እንደሚችል ለማስላት የሒሳብ ሊቅ መሆንን ወይም ጠንቋይ መቀለብን አያሻም፡፡ በአናቱም የኢትዮጵያውያን አኗኗር መጠጋጋት፣ መጨባበጥና ማኅበራዊ ሕይወት የበዛበት እንደ መሆኑ መጠን ለበሽታው መስፋፋት ምቹ መደላድል እንደሚፈጥር ዕሙን ነው፡፡ በዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቅርቡ በሰጡት መግለጫም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ጥቆማ መስጠታቸውም ነጥባችንን ለማጠናከር ልናነሳው እንችላለን፡፡

በምጣኔ ሀብት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ብሎም በሕክምና ደረጃቸው ጠንካራ የሆኑ አገሮች ሳይቀሩ በቫይረሱ በተዳከሙበት ሁኔታ፣ ውስጥ ሆነው በበሽታው የተያዙና የሞቱ ወገኖቻቸውን ቁጥር በማይደብቁበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ቁጥሩን ትክክለኛውን ቁጥር ባለመናገር ምን የሚታጨድ ፖለቲካ ትርፍ እንደሚኖር መናገር ይከብዳል፡፡ ምናልባትም የገዥው ፓርቲ ነባር ቆጥሮችን የመደበቅና እውነታውን ለማፈን የመሞከር አባዜ ካልሆነ በቀር፡፡

የቀድሞው ኢሕአዴግ የአሁኑ ብልፅግና ፓርቲ በብዙ መንገዶች መረጃዎችን በመደበቅ ይታወቃል፡፡ ይኼ ሚስጥራዊነት ድርጅቱ ቀድሞ ከተቃኘበትና ለዓመታት ካራመደው የኮሙዩኒዝም ግራ ርዕዮተ ዓለምና ‹‹ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት››  ባህሪ የመነጨም ሊሆን እንደሚችል ሊገመት ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ሰጎን አንገትን አሸዋ ውስጥ በመደበቅ እየመጣ ያለውን ችግር ከመጋፈጥና መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ፣ ከእውነታው ለመሸሽ ከሚደረግ ትንቅንቅ የመጣ እንደሆነ የጸሐፊው እምነት ነው፡፡

ዳረል ሃፍ የተባሉት ምሁር ‹‹How to Lie with Statistics›› በሚለው መጽሐፋቸው መረጃን በማብሰል (Data Cooking) ይሉታል ባለሙያዎቹ በማጋነን፣ በማቃለል (ቁጥሮችን በመቀነስ) ሰዎችን ግራ ማጋባትና ስሜታቸውን መግዛት እንደሚቻል አስነብበዋል፡፡ ሰዎች በባህሪያቸው ከአመክንዮ ይልቅ ስሜታዊነት የተጫናቸው እንደሆኑ የሥነ ልቦና ጠበብት በጥናት ማረጋገጣቸውም ብዙኃኑ (The Crowd) አጥብቆ ጠያቂና ሞጋች ሳይሆን፣ በተቀደደለት ቦይ የሚፈስ ውኃ መሆኑንም ያነሳሉ፡፡ መንግሥትም ከዚህ እውነታ ተነስቶ መረጃዎችን የመቀሸብ ሥራን ሊሠራ የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም፡፡

የዓለምን ምጣኔ ሀብት እያቃወሰና የሰዎችን እንቅስቃሴና ሥራዎችን እያዘጋ ቤት ውስጥ እንዲውሉ ያደረገው የኖቭል ኮሮና ቫይረስ ወይም ኮቪድ-19፣ በአገራችንም ከመሠረታዊ የምግብና ፍጆታ ሸቀጦች እስከ የፊት መሸፈኛ ጭምብልና ጓንት፣ እጅ ንፅህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) የዋጋ ንረትን አንብሯል፡፡

የመጀመርያው የቫይረሱ ተጠቂ የሆኑት ጃፓናዊ መረጃ ይፋ ከተደረገ አንስቶ የሳኒታይዘር፣ የጓንትና የፊት መሸፈኛ ጭምብል ዋጋ ሰማይ ሲነካ ዓይተናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ምርቶቹን ለመግዛት የሚታየው ሠልፍና ድብድብ ከባድ ነበር፡፡  ከአሥር እስከ ሃያ ብር ይሸጥ የነበረው የፊት መሸፈኛ እስከ 500 ብር፣ ከ40 እስከ 50 ብር የሚሸጡ ሳኒታይዘሮች ከ150 እስከ 300 ብር ሲሸጡ መመልከት ግርምትና ድንጋጤን አያይዞ ይፈጥራል፡፡ በዚህም ሁለት ጉዳዮችን ታዝበናል፡፡ አንድም የሸማቹ ፍላጎት ከፍተኛ በመሆኑ ያላግባብ ዋጋዎች ተቆልለዋል፡፡ ሕዝቡ በውድ ዋጋ ምርቶቹን አልገዛም ቢል ዋጋቸው ላይጨምር እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ ይቻላል፡፡ አንድም የዋጋ ጭማሪ ያደረጉት ነጋዴዎች ከሰብዓዊነት ያፈነገጡና በሰዎች ችግር ትርፋቸውን ለማጋበስ የሚሯሯጡ ስግብግቦች እንደሆኑም በግላጭ ታይቷል፡፡ እዚህ ላይ ግን መንግሥት ሳኒታይዘሮችን በከነማ መድኃኒት ቤቶች በኩል ለማከፋፈል ያደረገውን የሚደነቅ ጥረት ማድነቅ ግድ ይለናል፡፡ ሸማቹ ደግሞ ለብዙ ቤተሰቦች የሚበቃ የእጅ ማፅጃዎችን በነፍስ ወከፍና በብዛት ለራሱ ብቻ ሲወስድ መታየቱም ለሌሎች አለማሰብና ርህራሔ የራቀው መሆኑን እዚህ ላይ ይጠቀሳል፡፡

ለቫይረሱ መከላከያ ተብሎ አምስት ቢሊዮን ብር በተመደበ ማግሥት፣ ለአፍሪካ ኮሮናን ለመከላከል ለምታደረገው ጥረት የ150 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቡድን 20 አገሮች  በጻፉት ደብዳቤ መጠየቃቸው፣ ችግሩ በኢትዮጵያም ምን ያህል ችግር ሊፈጥር እንደሚችልና ሥጋቱ ከፍተኛ እንደሆነ ከላይ ያነሳነውን አመክንዮ ያጠናክርልናል፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የኢትዮጵያን ድንበሮችን ከመዝጋትና ከውጭ አገሮች የሚመጡ ተጓዦችን በለይቶ ማቆያ እስከማቆየት የደረሰ ዕርምጃ ቢወስድም ቅሉ፣ በቅድመ መከላከል ላይ ጠንክሮ ቢሠራ ከዚህ የበለጠም መልካም ሥራ ተሠርቶ የተሻለና ጉዳቶችን የቀነሰ መፍትሔዎችን ይዞልን ይመጣ ነበር፡፡

ኮሮና ቫይረስ በቻይና ሁቤይ ግዛት በምትገኘው ውሃን ከተማ መገኘቱ ከተነገረ በኋላ ከ180 በላይ አገሮች ዓለም አገሮች የተዛመተ ሲሆን፣ ይህ ጽሁፍ ለኅትመት እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ከ800 ሺሕ በላይ ዜጎች በቫይረሱ ታመዋል፡፡ ከ37 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደ ቅጠል ረግፈው መሞታቸውንና ከ165 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ማገገማቸውን የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያሳያል፡፡

በምጣኔ ሀብታቸውና በሕክምና ቴክኖሎጂ ደረጃቸው ከፍተኛ የሚባል ደረጃ የተቆናጠጡ አገሮች ዜጎች ራሳቸው እንደ ቅጠል በበሽታው ሲፈግፉ ሲታይ፣ በሽታው ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያልተበገረ በጣም ከባድ የሚባል እንደሆነ በገሃድ አስታውቆናል፡፡ ጠንካራ የሕክምና መከላከያ ያላት ኃያሏ አሜሪካ ሳትቀር ከደቡብ ኮሪያና ከቻይና የበሽታውን መከላከያ ቁሰቆሶችን ዕርዳታ መጠየቋ የኮቪድ-19 አሳሳቢነትና ተቀያያሪ፣ እንዲሁም አስቸጋሪ ባህሪያት በቴክኖሎጂ አቅም ያደራጁትን አገሮች ሳይቀር ብርክ ያስያዘ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]> ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...