Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርይድረስ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች

ይድረስ ለኢትዮጵያ የፖለቲካ መሪዎች

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ                  

እንደሚታወቀው ፖለቲከኞች ለአገርና ለወገን አርቆ አሳቢዎች፣ የልማት አርበኞች፣ የፍትሕ ተሟጋቾችና የነፃነት መሪዎች ለመሆን ቀደምት ሚና ያላቸው፣ ከራስ ይበልጥ ለአገርና ለወገን የሚሠሩና ግለኝነትን አስወግደው አገር ወይ ሞት የሚሉ መሆናቸውን የምንገነዘብ፣ ለመምራትም ሆነ ቀርበን ለማነጋገር አቅሙ የሌለን ዜጎች የምናውቀው ሀቅ ነው (ማን ቢያቀርበን?)፡፡ ታዲያ ዛሬ ዛሬ  የምናየው ለየት ባለ መንገድ ታሪክ ታሪክነቱን ለውጦ የግል ፍላጎትን፣ ለራስ ባይነትንና እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል መሰል ጉዳዮችን እያየን ነው። ምንድነው ይህንን ጉድ ያፈላብን? ብለን ስንጠይቅ የቴክኖሎጂ ግስጋሴ፣ የዓለም መቀራረብና የመሳሰሉት ራስ ወዳድነትን ፈጥረው የሰው ልጆች የሰውነትን ባህሪ ትተው ወደ አውሬነት ተለውጠዋል፡፡

አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ከመባባል ይልቅ ወደ ራስ ወደድናትና ግለኝነት በመዛወሩ የሰው የሕይወት ዋጋ ተሽቆልቁሎ ወርዶ፣ ያለ ገላጋይና መያዣ ገመድ ሳይኖረው ኤላ ውስጥ ገባና አረፈው። ለመሆኑ አዲሱ ወጣት ወገኔ ኤላ ምን እንደሆነ ያውቅ ይሆን? ኤላ ማለት የዛሬውን አያድርገውና ከ10 እና 20 ሜትር በማያንስ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውኃ ተስቦ የሚወጣበት ጉድጓድ ማለት ነው። ወገኔ ወጣቱ እወቀው፡፡ ታዲያ ከጉድጓድ ምን ይሆን የሚያድነን ብለን ስንጠይቅ፣ ወገጎኖቼ ለፖለቲካ የበላይነትን የምትሯሯጡ ቀዝ ቀዝ ብላችሁ ስለወገን ስለአገር እንድታስቡ ለማሳሰብ ነው። በሠለጠኑት አገሮች ሰዎች ለፖለቲካ የሚሯሯጡት ራሳቸውን ችለው፣ ካሁን ወዲያ ለራሴ ሳይሆን ለወገኔ ብለው ቆርጠ ሲነሱ ነው። እኛ አገር ግን የራስ ማሳደጊያ፣ መበልፀጊያ፣ መታወቂያና ራስን ቀና አድርጎ ከሁሉ በላይ ነኝ ለማለት ነው። እንዲያውም ሮጦ ያልጠገበ፣ ገና ያሻቸውን ያላገኙ ፈሪኃ ፈጣሪን የማመዛዘን አቅም ያላጎለበቱ፣ ኑሮን ገና ለመጀመር የሚሯሯጡትንና ለማገናዘብ ጊዘ ያላገኙ የየክፍሉ አለቃ በማድረግ የሚደረገው ሩጫ እንዳያዋርደን። 

- Advertisement -

አገራችን የተፈጥሮ ሀብት ሞልቶ ተርፎ እያለ ወጣቱ የሚሠራውን አጥቶ በየመንገዱ ስንገላወ፣ ወጣት እናት ልጇን አዝላ በየመንገዱ ስትለምንና የነገን ተተኪ ወጣት ከማስተማር ይልቅ፣ የልመና ቋት አያያዝ ስታስተምር የእኔ ማግኘት ከማፈር የተሻለ የሚሰጠኝ ኩራትም ሆነ አለኝታነት ከንቱ በመሆኑ እጅግ አዝናለሁ። ትናንትና ከእኛ በታች የነበሩ እንደ እነ ኮሪያ ያሉ አልፎላቸው በኢንዱስትሪ ተራቀው፣ ከራሳቸው   አብቅለውና አልምተው ሳይሆን የሌላውን ወስደውና አሻሽለው ሲራቀቁና ሲመኩበት እናያለን፡፡ ሁሉም ነገር ያላት ኢትዮጵያ ሁሌ ተመፅዋች መሆን ካላሳፈረን ምን ያሳፍረን ይሆን? ወይስ የኃፍረት ይሉኝታችን ጨርሶ ጠፍቶ ይሆን? ልንኩራራ የምንችለው በግል ማግኘት ሳይሆን፣ የጋራ ሲሆን ለፍተው ባልሠሩት ቤት ከሚንቀባረሩ ዛሬ ሁላችንም ተባብረንና አብረን ባነስተኛ ኑሮ እየኖርን አገራችንን ስናስቀደም ብቻ ነው ውጤት የምናመጣው።

ሹማምንት በተሸከርካሪ ወንበር ከመሽቀርቀር፣ በሚሊዮን ብሮች በተገዛ ላንድክሩዘር ከመኩራራትና በትንሹ አስፈላጊውን ተጠቅመውበት ለወገናቸውና ላለአራቸው አለሁላችሁ ቢሉ እንጂ፣ የሻምፓኝና የብሉ ሌብል ብርጭቆ ቢያጋጩ ዋጋ የለውምና ብትነቁ የተሻለ ያስከብራችኋል። በረሃማዎቹ አገሮች እነ እስራኤል ከራሳቸው ተርፈው ለእኛ አበዳሪ ለመሆን ሲቃጣቸው፣ እኛ የተማሩ መሪዎች እንደ ጉንዳን በፈሉበት ዘመን ለልማት ሳይሆን ለመታያ መሯሯጥ ያሳፍራል። እ.ኤ.አ. ከ1945 በኋላ ነፃነቷን ያገችው እስራኤል ጥላን ስትሄድ እኛ ባለንበት ስንረግጥ መታየቱ ካላሳፈረን ምን ያሳፍረን ይሆን? ልብ እንግዛ! መሪዎቻችንም ሹመት የዘለዓለም እንዳልሆነ ተገንዝባችሁ ወረድ ብላችሁ ከወገናችሁ ጋር ተነጋገሩ፣ መንገድም ፈልጉ፣ አፈላልጉም። ያኔ ነው መሪነታችሁ እንዳለፉት ታላላቅ መሪዎች እንደ እነ አፄ ምኒልክ፣ እንደ ፃድቁ ዮሐንስ የምትመሠገኑት። ጊዜያዊ ሁኔታ አያታልላችሁ፣ ልቦና ግዙ! በስብሰባ፤ሬዲዮና በጋዜጣ ብቻ አገር አይለማምና ልፍለፋዬን ተረዱልንኝ!

እንዲያው ለምሳሌ ራሳቸውን አሳልፈው ለወገንና ለአገር የሰጡትን ላንሳና ተከቱልኝ። ታላቁ 16ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት አብርሃም ሊንከንን ምሳሌ ልሰጣችሁ ወደድሁኝ።አብረሃም ሊንከን የደሃ ገበሬ ልጅ ነበር፡፡ አካባቢውም ያን ያህል የሀብታም ስላልነበረ ከአንድ ቦታ ወደ አንዱ በመፈናቀል በመጉላላት ይንከራተት ነበር። ታዲያ ሊንከንም የረባ ትምህርት ሳይማር ከወላጅ ጋር አብሮ ስንከራተት ትንሽ ማንበብ ብቻ ይችል ነበር፡፡ ታዲያ ወላጆቹ ከኢንዲያና ወደ ኢሎኖይስ ሄዱ፡፡ በሄዱበት ቦታ ሁሉ ሊንከን ቀልደኛና ተውዳጅ፣ ረዘም ያለ ለግላጋ ወጣትተ ሁሉንም አክባሪና አስታዋይ ነበር። ሊንከን ትንሽ ሥራ አንዲት ሱቅ ውስጥ አገኘ፡፡ በደስታ ተውጦ በመሥራት ላይ እያለ ያም በዛ ተብሎ ሳያስበው ተዘጋ፡፡

ተስፋ የማይቆርጠው ሊንን ለመሐንዲሶች ሰርቬይ ለማድረግ ሥልጠና ወስዶ ተቀጠረና በመሥራት ላይ እያለ አንድ ቀን ቀናነቱን ያየ ጓደኛው ለምን ጠበቃ አትሆንም አለው። በዚያን ዘመን ጠበቃ መሆን እንደ ዛሬው ከባድና ብዙ የሚጠይቅ አልነበረምና አጅሬ ሊንከን መጻሕፍትን ተውሶ ማጥናት ጀመረ፡፡ ሕጉንም ጠንቅቆ ተረዳና ወዲያውኑ ጠበቃ ሆነ። ቀጠለና የስቴቱ ምክር ቤት አባል ሆነ። ወዲያውኑ በስቴቱ ሕግ ምክር ቤት ታስቦ የማይታወቅ ሐሳብ አቀረበ። ሐሳቡም እንደሚከተለው ነበር። በዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ የሚገኙትን ባሪያዎች ሁሉ፣ መንግሥት ለባሪያዎቹ ባለቤቶች ገንዝብ ከፍሎ ይግዛቸው የሚል ነበር። ምክንያቱም ጌቶቹ ገንዘብ ካልተከፈላቸው ስለማይለቋቸው፣ መንግሥት ከፍሎ ካስለቀቃቸው በኋላ መንግሥት ነፃ እንድለቃቸው ነበር። ይሁን እንጂ ሊንከን በሁሉም ጥርስ ውስጥ ገባና ሁለተኛ የመመረጥ ዕድሉን አጣ። ከዚያ ወደ መጣበት ኢሎኖይስ ተመለሰ፡፡ ሊንከን አይመረጥ እንጂ የባሪያ ነፃ የመውጣት ጉዳይ አንዴ ተቀጣጥሏልና በነበረበት ቀጠለ።                                                               

ሊንከንም ለጊዜው ጥብቅናውን ለትንሽ ጊዜም ቢሆን እየሠራ ከፖለቲካውም ሳይርቅ ቆይቶ፣ ይበልጥ ተጠናከረና እንዲያውም ድሆችን ለመርዳት አቅም እያጎለበተ ቀጠለ፡፡ ምክንያቱም ድህነት ምን እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ድህነት ለማጥፋትም ተያያዘው (እኛ የደሃ ልጅ እንዲያውም እንዳይታወቅበት ይሸሻል)፡፡ እ.ኤ.አ. በ1858 ትጉህነቱንና ለወገን አሳቢነቱን የተመለከቱት የኢሎኖይስ ሪፐብሊካን                                                          ፓርቲ ሊንከንን ለፓርቲው እንዲወዳደር አጥብቀው ጠየቀው (እንዲያውም የማስገደድ ያህል)፡፡ ለማንኛውም ተወዳዳሪውን ዝነኛውን ስቴፈን ዳግላስን ማሸነፍ ባይችልም፣ በተደረገው የይፋ ክርክር ሊንከን በእጥፍ በልጦ በመገኘቱ ለቀጣዩ ምርጫ ያንን የውክልናውን ዕድል ባያገኝም፣ ሪፐብሊካን ፓርቲ ሊንከንን ለአገሪቱ መሪነት (ፕሬዚዳንትነት) አቅርቦት መራራ የሆነ ውድድር አሸንፎ ግማሽ ዴሞክራቶችና መላው ሪፐብሊካን መርጠውት እ.ኤ.ኤ በ1861 አሸንፎ የአሜሪካን 16ኛ ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ።  ‹‹ማንም ሰው የተፈጠረው በእግዜብሔር ፊት በነፃነትና በእኩልነት ነው፤›› በማለት ትግሉን አቃንቷል።

ውድ አንባቢያን የአብርሃም ሊንከንን ታሪክ ለማፀባረቅ ፈልጌ አይደለም፡፡ አንድ የፖለቲካ መሪ ለራሱ ሳይሆን ለሚመራው ሕዝብ አልፎም ለዓለም ማሰብ እንዳለበት፣ የራሱን ጥቅም ጨርሶ መርሳትና ለመጪው ትውልድ መልካም ድልድይ ሠርቶ ማለፍን ለማመላከት ነው። የራሳችንን ሰዎች ረሳህ እንዳትሉኝ ረስቼያቸው ሳይሆን፣ ለቀባሪው ማርዳት እንዳይሆንብኝ። ውሎ ይደር እንጂ ዛሬ ሁላችንም የምንኖርባትን፣ ባንኖርባትም መሆን የምንፈልጋትን አሜሪካ መስመር አስይዘው ክፉም ይሁን ደግ ትምህርት፣ ከዘመናዊ ሥልጣኔያቸው ዓለም በሙሉ የተማረበትና የነቃበት ሁኔታ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ መሪዎች የሚያመላክቱት መንገድ ለራስ ሳይሆን ለወገንና ለገር መሆኑን ማገናዘብ ይገባል። ዛሬ በአገራችን የሚታየው ከምኔው ተሾሜ በልቼ ልሙት ዓይነት ሁኔታ ጨርሶ እንዳያጠፋን በእጅጉ እፈራለሁ። በሁኑ ዘመን የሚካሄደው የሹመት ሩጫ፣ የቁንጅና ውድድር ይመስላልና መሠረቱን ባይለቅ የተሻለ ነው፡፡ ከሰፊው ሕዝብ ጋር ለመመካከርና አዎንታን ማግኘት ቢሞከር እንዲሁ መልካም ነው።

ታናሽ ታላቁን የማያከብርበት አለቃና ምንዝር መቀመጫ የተነጣጥቁበትና ሥርዓት የጠፋበት ሁኔታ እየታየ ነው። ወታደሩ መለዮውን ጥሎ አለቃውና ምንዝሩ የማይታወቅበት፣ አቤት የሚባልበት ቢሮ ወይም የበላይ የጠፋበት ዘመን እየታየ ነው። የሚገርመው ነገር በምዕራብም ሆነ በምሥራቅ አገሮች ሥነ ሥርዓት እጅግ ከቁምነገር ገብቶ የሚታይበት ሁኔታ ነው ያለው። ታዲያ በአዲሱ በእነ ኢሕአዴግ ዘመን ምን ተፈጠረና ነው ሥርዓተ አልባኝነት የሰፈነው? የፖሊስ አለቃው ሲቪል ይሁን ወይም ነጭ ለባሽ ያልለየበት፣ ቋንቋችን የተከላለሰበት፣ የቅኝ ግዛት አንለው አልተገዛን፣ ነፃ ነን እንዳንል ቋንቋችን ተንቆ ያገር መሪዎቻችን በፈረንጁ ቋንቋ ተጠምደው እያየን ነው። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አሳምረው ፈረንሣይኛውንና እንግሊዝኛውን ያቀላጥፉ ነበር፡፡

ግን አንድም ቀን በይፋ ከመንግሥታት ጋር በሚነጋገሩበት ጊዜ በገራቸው ቋንቋ እንጂ በሰው ቋንቋ ተናግረው አያውቁም (ኦፊሴል ቋንቋ)፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር መሪ ባለመሆናቸውና የሚኒስትሮች ሰብሳቢ ስለሆኑ የውጭ ሰዎችን በእየ ቋንቋቸው ያናግሩ ነበር። ልብ በሉ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተ ወልድ ፈረንሣይንና እንግሊዝኛን እንደ ራሳቸው ቋንቋ ተናጋሪ ነበሩ፡፡ የሚገርመው ግብፅ ብዙ ቅኝ ገዥዎች የተቀያየሩባት አገር ብትሆንም፣ ከእኛ በተሻለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ቀድማን ተክና ለምኒልክ ትምህርት ቤትን በአስተማሪነት በቀደምትነት ኢትዮጵያ የመጣች አገር ነበረች። ከገማል አብዱል ናስር ጀምሮ እስካሁን ባሉት መሪዎቿ እንግሊዝኛን በስብሰባ ላይ በየትኛውም አገር ተጠቅመውበት አያውቁም፣ ሱዳንም እንዲሁ። ታዲያ የችኛዎቹ ምነው ለባርነት ቅድሚያ ሰጡ? አገራቸው በቅኝ ለብዙ ዓመታት የተገዙ ቋንቋቸውን የረሱ ቢጠቀሙበት ምንም ችግር የለውም። ቋንቋ መግባቢያ ነው ቢባልም የአገርም ኩራት ነውና አንርሳ!

እንዲያውም ቀደምቷ ኢትዮጵያ የተጠናከረና መሠረት የያዘ ባህል የነበራት፣ የ980 ዓመት ዕድሜ ያላትን እንግሊዝን በሺዎች ዓመታት የቀደመች አገራችን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የዘመኑ መሪዎቻችን ቋንቋችንን ንቀዋል። በልማት ያልቀደምንበት ምክንያቱ የዓለም ዓይን ያረፈባትን ኢትዮጵያን ከጠላት ለመከላከል በተደረገው ትግል መሆኑን መገንዘብ ያሻናል። አሁን ደግሞ ሙሉ ነፃነታችንን በያዝንበት ዘመን በራሳችን ተማምነን ባለመልማታችንና ወደኋላ በመቅረታችን ተቆጭተን ወደፊት መራመድ ሲገባን፣ እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ መጎታታችንን ወጣቱ ትውልድ በቅናት መንፈስ ተነሳስቶ ያሳለፍነውን የከረመ ዕዳችንን ማወራረድ ይጠበቅበታል፡፡ ነገር ግን በቁጭት ከመነሳሳትና ለሥራ ከመሯሯጥ ይልቅ በከንቱ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚል አጉል ፉክክር ተይዞ ፍሬያማ ላለመሆን እየተሽቀዳደመ ነው። ይህ በአጭር ተቀጭቶ ሁሉም በኅብረት ለልማት ለመነሳትና ወደፊት ለመራመድ መሽቀዳደም ቢጀምር፣ እንደተለመደው አፍሪካን ጨምረን ለመልማት የምንችልበትን መንገድ መቀየስ አለብን።

በዘርና በሃይማኖት መከፋፈሉ ጉዳት እንጂ የሚያመጣው ጥቅም የለምና እናስብበት። ከየሰው አገር ቃርመን ባመጣናት ፉት ቢሉ ጭልጥ የምትሆን ሚሊዮን ዶላር ይዘን መጥተን ወገኖቻችንን ባናወናብድ የተሻለ ይሆናል። ለአገር የምናስብ ከሆነ ወገኖቻችን ስንቱ በልቶ ያድራ?ል የስንቱስ ልጅ ነው በዕድሜው ትምህርት ቤት ገብቶ አስፈላጊውን ትምህርት የሚማረው? ይህንን ለሟሟላት ነው የመጀመርያው የማያወላዳ ሥራችን መሆን ያለበት።  በሉ አንፈራራ እናንተም ጠይቁኝ እኔም ልጠየቅ። ‹‹ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም›› ይባላል፡፡ ወቀሳዬ አንዳንድ የተፈጥሮ ስጦታ ያላቸው የእነ ዓብይ ዓይነቶችን አይጨምርም፡፡ በወጣቱ ላይ ያቀረብኩት አስተያየት የተፈጥሮ ስጦታ ካላቸው መካከል አንዱ ከሚባሉት ውስጥ ሊሆን ይችላልና።                                                        

 ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...