Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከ100 ያላነሱ ኩባንያዎች ሠራተኞችን ለመቀነስ ማቀዳቸው ሥጋት ፈጥሯል

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሦስትዮሽ ስምምነት ሠራተኞችን በሥራ ላይ ለማቆየት ስምምነት ተደርጓል

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በሥሩ ከ750 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን በአባልነት ያቀፉ ዘጠኝ ፌዴሬሽኖችን ያካተተ አንጋፋ ለሠራተኞች የመብት የቆመ ተቋም ነው፡፡

የኮንፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ኢሠማኮ በርካታ ችግሮች ሲያጋጥሙት ቆይቷል፡፡ ለሠራተኛው መብት የሚንቀሳቀሰው ይህ ኮንፌዴሬሽን፣ በዘመኑ ከገጠሙት ሁሉ የበረታ ችግር ከፊቱ ተደቅኖበታል፡፡ አቶ ካሳሁን እንደሚሉት፣ በኃላፊነት ዘመናቸው እንዳሁኑ ያለ የሠራተኛውን ህልውና የሚፈታተን ሥጋት ገጥሟቸው አያውቅም፡፡ ኮንፌዴሬሽኑን ያሳሰበውና እሳቸውንም ዕረፍት የነሳቸው ጉዳይ የወቅቱ የዓለም አደጋ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነው፡፡ ይህ አደገኛ በሽታ በሺዎች ዜጎች ላይ ከፍተኛ የህልውና ሥጋት በመደቀኑ፣ ከሥራ የመፈናቀል አደጋን በሠራተኛው ላይ አንሰራፍቷል፡፡

የወረርሽኙ ጫና በንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ የታየ ሲሆን፣ ከ100 በላይ ድርጅቶችም ሠራተኞቻቸውን ለማሰናበት፣ ለመቀነስ፣ ወይም ያለደመወዝ የግዳጅ ዕረፍት ለማስወጣት ማቀዳቸውን በመግለጽ ለሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ይህን ጉዳይ የተመለከተው ኢሠማኮ፣ የመጣውን አደጋ በመፍራትና ችግሩን ለማለፍ ይረዳል ባለው ሐሳብ ላይ የሦስትዮሽ ፕሮቶኮል መፈራረሙ አስፈልጎታል፡፡ ይህንኑ አደጋ መንግሥትም በመመልከቱ፣ ከንግድና ከአምራች ዘርፉ ተዋናዮች ጋር በመነጋገር ሠራተኞችን ከሥራ ከማሰናበት ይልቅ፣ ባሉበት የሥራ ዘርፍ ደመወዝ እየከፈሉ እንዲያቆዩ የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው አስታውቋል፡፡ ሠራተኞች ደመወዛቸውን እያገኙ እንዲቀጥሉ የሚያስችል የሥራ ቦታ ምላሽ መስጫ ሦስትዮሽ የስምምነት ፕሮቶኮል፣ በመንግሥት፣ በአሠሪውና በሠራተኛው ወኪሎች አማካይነት በሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲተገበር ስምምነት ተደርጓል፡፡

የስምምነት ሰነዱ ቀውስ የገጠማቸው ተቋማት እንዲተገብሩት ይደረጋል ተብሏል፡፡ የቫይረሱ ወረርሽኝ እየፈጠረ ያለው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሆነ የሚገልጹት አቶ ካሳሁን፣ በተለይ በአበባና በሆቴል መስክ የሚታየው ተፅዕኖ የተባባሰ በመሆኑ የሠራተኛውን ሥጋት ከፍተኛ አድርጎታል፡፡ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረተውና ለወጪ ንግድ የሚቀርበው ምርትን መላክ አልተቻለም፡፡ አገሮች ድንበሮቻቸውን ዘጋግተው በመቀመጣቸው ንግድ ማካሄድ ፈታኝ ሆኗል፡፡ በመሆኑም ወቅታዊ ሁኔታውን በመመልከት፣ ሦስትዮሽ የስምምነት ፕሮቶኮል እንዲተገበር ማድረግ ወትሮውንም ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ገቢ የሚተዳደረው ሠራተኛ ደመወዙ ሳይቋረጥበት ለተወሰነ ጊዜ እየተከፈለው እንዲቆይ ያስችላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ፕሮቶኮሉ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃ መውሰድ የሚቻልበትን ሥልት እንዲያካትት ታስቦ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎበታል ተብሏል፡፡ የወረርሽኙ አዝማሚያ እየታየ ውሳኔና አቅጣጫ መስጠት የሚቻልበትን መንገድ ያካተተ ስለመሆኑ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመለከታል፡፡ ፕሮቶኮሉ በምን አግባብ ተፈጻሚ ይደረጋል ለሚለው፣ ዝርዝር መመርያ ተዘጋጅቶ በመጪዎቹ ሁለት ቀናት ውስጥ ወጥቶ ለሚመለከታቸው እንደሚሠራጭ ይጠበቃል፡፡

በዚህ ፈታኝ ወቅት ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸውን ያለምንም እንቅስቃሴና የሥራ ሒደት ይዘው እንዲቆዩ ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ መንግሥት ድጋፍ ለማድረግ የገባውን ቃል ተግባራዊ ካደረገ፣ የሠራተኛውን ሥጋት መቀነስ እንደሚቻል አቶ ካሳሁን ይገልጻሉ፡፡ ሠራተኛውም በዚህ ጊዜ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞቹ ቀርተውበት ደመወዙን እያገኘ ለወራት ባለው ሁኔታ ውስጥ እንዲቆይ ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት አስታውቀው፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሠራተኛ እንዲሁ መበተን ስለማይቻል፣ ሁሉም በርብርብና በመተባበር ሊሠሩ እንደሚገባ አቶ ካሳሁን ሳያሳስቡ አላለፉም፡፡

ኩባንያዎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከዘርፍ ዘርፍ እንደሚለያይ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፣ ሰሞኑን ከመንግሥት እንደተሰማው ለአበባና ለሆቴል ዘርፍ ከመንግሥት ይደረጋል የተባለው የብድር ዕዳ የመክፈያ ጊዜ ማራዘሚያና ተመሳሳይ ዕርምጃዎች ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ይሁንና አሁንም አንዳንድ ተቋማት ሠራተኞችን እንቀንሳለን የሚሉ ስላሉ በዚህ ፕሮቶኮል እንዲታቀፉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ለዚህም እንደ አዲስ አበባ ሒልተንና ኢትዮጵያ ቆዳ አክሲዮን ማኅበር ያሉ ድርጅቶች ሠራተኛ እንቀንሳለን ማለታቸውን የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ እንዲህ ያለው ጉዳይ በፕሮቶኮሉ መዳኘት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

ወረርሽኙ እያስከተለ ያለው ጉዳት እንደ የተቋማቱ የሥራ ዘርፍ ቢለያይም፣ አበባ አምራቾች፣ ሆቴሎችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾች ላይ ጎልቶ የታየ ችግር ሆኗል፡፡

‹‹አበባ አምራች ምርቱን እየጣለ ነው፡፡ ጉዞዎች በመስተጓጎላቸው የሆቴል ዘርፉ በእጅጉ ተጎድቷል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ምርቶቻቸው ለመላክ የሚያስችላቸው ሁኔታ የለም፤›› በማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው አዝማሚያም ጉዳታቸው ከፍተኛ እንዲሆን ማድረጉን የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ ድርጅቶቹ ኪሳራ ውስጥ እንደሚወድቁ በግልጽ እየታየ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት ችግሩን ተረድቶ ለእነዚህ ዘርፎች ዕገዛ የሚያደርግ በመሆኑ፣ ኩባንያዎቹም በዚያው ልክ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚባቸው አሳስበዋል፡፡

ችግሩ በአገርና በዓለም ላይ የመጣ በመሆኑ፣ ከሠራተኛው ወገንም የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ለጊዜው ሳያነሳ መደበኛ ደመወዙን ብቻ እያገኘ እንዲቆይ ራሱን ማሳመን አለበት ተብሏል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝና ተፅዕኖዎቹ እስከመቼ ይቆያል የሚለውን መመለስ አዳጋች ቢሆንም፣ በስድስት ወራት ውስጥ ሁኔታው እየታየ በመመካከር የፕሮቶኮሉ አፈጻጸም እንዴት ይተግበር የሚለው ላይ እየተነጋገሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚጠይቅ አቶ ካሳሁን ያስረዳሉ፡፡

ከአበባና ከሆቴል ዘርፍ ባሻገር በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ አምራቾችን የሚጠቅሱት አቶ ካሳሁን፣ በተለይ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው የወረርሽኙ ዳፋ ካረፈባቸው መካከል በጉልህ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ዘርፍ በመቶ ሺዎች የሚጠሩ ዜጎች ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በጠቅላላው በሆርቲካልቸርና በሌሎች የወጪ ንግድ ምርቶች መስክ የተሠማሩ የኮሮና ተፅዕኖ ሰለባዎች ሆነዋል፡፡

ይህ ፕሮቶኮል ኩባንያዎች ሠራተኛ ለመቀነስ በተነሱበት ወቅት የወጣ እንደመሆኑ፣ ፕሮቶኮሉ የሚመለከታቸውም በቀውሱ ጉዳት የደረሰባቸውና ሊደርስባቸው እንደሚችል የሚገመቱት ሲሆኑ፣ ቀውሱ የማይነካቸው አምራቾችና ሌሎችም ፕሮቶኮሉን መተግበር አይጠበቅባቸውም ወይም ሠራተኛ ለማሰናበት የሚያስገድዳቸው ሁኔታ ውስጥ ስለማይሆኑ በነባር አሠራራቸው ይቀጥላሉ፡፡

በፕሮቶኮሉ መሠረት ሠራተኞች የደመወዝ ጭማሪና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ለአንድ ዓመት አይጠይቁም፡፡ ችግር ያልገጠማቸው ዘርፎች ግን ባለው ሕግ ይቀጥላሉ፡፡ እስካሁን ችግር ሳይኖርባቸው የሚሠሩና ተጨማሪ ሥራ እንዳገኙ ከተጠቀሱት ውስጥ የስኳር ኢንዱስትሪው አንዱ ነው፡፡

በሥራ ዘመናቸው ከባድ ከሚሏቸው ወቅቶች የኮሮና ቀውስ ትልቁ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ካሳሁን፣ ‹‹ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በ2008 የዓለም የፋይናንስ ቀውስ ተከስቶ ነበር፡፡ ከዚህም በፊት የኢኮኖሚ ቀውስ ነበር፡፡ ይኼኛው ግን ይለያል፤›› ብለዋል፡፡ ምክንያቱም የኢኮኖሚ ጉዳት ብቻ ሳይሆን፣ የሰው ልጅን ጥፋት እያስፋፋ በመምጣቱ ነው ይላሉ፡፡

መንግሥት፣ የሠራተኛ ማኅበራት፣ ኅብረተሰቡ፣ አሠሪዎች፣ በአጠቃላይ ሁሉም ባለድርሻ ለብቻቸው የማይወጡት ባላጋራ በመምጣቱ አብሮ ላለመጥፋት በጋራ መሥራት እንደሚገባ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች