በአሰፋ ጉያ
ከብርሃን ፍጥነት በልጦ፣ ከምሥራቅ ምዕራብ ተወናጭፎ
ከሁዋን ትንሽ መንደር ከቻይና ተነስቶ፣ ከአውሮፓ ጉያ በገሐድ ተወትፎ ቀጠፋቸው’ ኮ አጅር የጣልያንና የስፔን ልጆች አስተቃቅፎ፡፡
ኮሎምቦስ በማዕበል ካገኛት፣ ከሞገደኛው የትራምፕ አገር፣
በአሜሪካ ተባዝቶ
በመላው ዓለም ዳንከረበት ግዛተ- ኃይሉን አስፋፍቶ፡፡
‹ሀ!› ብሎ ሆ! እያለ ኮሮና ቫይረስ
በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ፡፡
ዘር ማንዘርን፣ ዕድሜና ፆታን ሳይለይ ሕዝብ ዓለምን
ያለርህራሄ ፈጃጅቶ
በሐዘን ማቅ ጀብኖ እንባ በእንባ አራጭቶ
ቀባሪና ተቀባሪን ሩቅ ለሩቅ አለያይቶ
በየመንደሩ በየቤቱ፣ በየክፍሉ በየጓዳው ከታቶ፣
አውራ ጎዳናዎችን፣ ጉራንጉር መንደሮችን ሳይቀር አራቁቶ
ኮሮና ነግሷል በዓለም -ሞትን ይጋልባል ሺሕ በሺሕ አባዝቶ፡፡
ኮሮና መንጠቆዎቹን ከጉሮሮና ከመንጋጋ አወሳስቶ
ንፋስ እንዳይገባ- እንዳይወጣ ትንፋሽ አሳቶ
ተራቋል በመዘረር ኃያሉን ከደካማው አቆራኝቶ፡፡
ኮሮና- በደማቅ የዘውድ ውብ አበቦች ተበጅቶ
በትንፋሽ- በንክኪ ተበዛዝቶ
ኢኮኖሚውን በአፍ-ጢሙ ደፍቶ
ሃይማኖትን- ከሳይንስ አስማምቶ
ጀግናው! ኮሮና ነግሷል በዓለም ላይ እጅግ ተስፋፍቶ፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን እንበል እንዴ?
እንደ ባህላችን ‹ዋ!?›
ወይስ? በፀሎትና ምህላ . . .
ወይስ? እንደቀድሞው እጅ እንንሳ?
ወገኔ!
ወደ ውስጣችን ጠልቀን እንዝለቅ
እንደው፣ በዚህ ዘመን ዓይናችን እያየ
ዳግም በደቃቁ- ተስቦ እንለቅ?
ማሰብ መተባበር ካልቻልን
ታዲያ ምኑ ላይ ነው ሰው መሆን?
ለደቂቃን እጅ ከሰጠን
ፈጣሪም ይንቀናል አቦ’ ለምን ፈጠርኳቸው ብሎን፡፡
እንዴት በኢምንት- ተስቦ እንበለጥ
እንዴት እንደ ዓይጥ በየጉድጉዱ ተደብቀን እንቀጥቀጥ፡፡
ወገኔ!
እንደትናንቱ በቀይ ሽንኩርት፣ በቀበርቾ
በነጭ ሽንኩርት፣ በፌጦ ተበጃጅቶ
ከሥራ ስሮች- ከቅጠላ ቅጠሎች ተወቅቶ
በሀገር ባህል ይነቀል ይሆን? ኮሮና ከአካላችን ተነጫጭቶ፡፡
ሳንነካካ፣ ሳንበካከል በምልክት እንነጋገር የሩቅ ቅርብ ሆነን
የእጆቻችንን፣ የልባችንን ንጽህና ጠብቀን
የከፋ ቢሆንም በንፋስ ፍጥነት መርዙን ቢረጭብን
እንደ ባህላችን በደፈጣ እንግጠመው ፈጥነን
‹ፐ!. . . ፖ!!!› እንበል ቀድመን፣ ተሽቀዳድመን፡፡
ሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም.
ከጠዋቱ 3፡00
አዲስ አበባ