Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሕግ ማክበር አያከስርም!

ሰላም! ሰላም! እስኪ ጭንቀቱን ለማስወገድ ገራገሩን እናውራ፡፡ ገራገር ሰው ልቡ ንፁህ ነው እንዲሉ ወጋችንም ከክፉ ነገሮች ይፅዳ፡፡ ገራገሩን እያወራን እንንጠንቀቅ፣ ፅዳታችንን እንጠብቅ፣ ርቀታችንን እናስከብር፡፡ በቃ ይኸው ነው የሚሻለን፡፡ እንደምታዩት አገሩ ተለውጦ፣ የሕዝብ ቁጥር ጨምሮ፣ ከተማው ሰፍቶ፣ ትውልድ ተቀይሮና አስተሳሰብ ተዛንቆ እዚህ ደርሰናል። ማማር አለማማሩን ለባለሙያዎች እንተወው። ለእኛ በሚመቸንና በምናውቅበት ብሂል ለጨዋታ ስናመቻቸው፣ የአገሩ መለወጥና መስፋትን ተከትሎ ሕዝባችን በሦስት ምድቦች ተከፍሏል አሉ። ምንና ምን ማለት ጥሩ። አሉን መቼም ማን ነገረህ ብሎ ጥያቄ የለም። ዕድሜ ለአሉ አቀባባዮች።  ምድቦቹ ይኼንን ይመስላሉ። ከፊሉ ማለት ዓለም ከአገር ይሰፋል ባይ ሆኖ ሲሉ ሰምቶ ወይም መሠልጠን እንዲህ አንዲህ ያስቀባጥራል በሚል ወለፈንድ የሚመራ፣ የምር ገብቶት በፈረንጅም በአገርኛውም መቁጠሪያ እየተጠቀመ የአገርና የዓለምን ሁኔታ እየመዘነ ሚዛኑን የሚጠብቅ ዘመናዊ ሲባል ወጌ፣ ሥርዓቴና እምነቴ አንድና አንድ ብቻ ነው ባዩ ደግሞ ኋላቀር መባሉን ሰማሁ። እንግዲህ ዕውቀታችንና ምልከታችን እንዲህ ይመዘናል ማለት ነው!

ከዘመናዊ እስከ ኋላቀር ያለውን ርቀት መቼም የተጓዘ ያውቀዋል። እኛ ደግሞ ጥሎብን ከዕውቀቱ ጭቅጭቁ ይቀድምብናል። እንዴት ማለት ጥሩ። ትዝ ይለኛል አንድ ጊዜ አዛውንቱን ባሻዬን ከወለፈንዱ ምድብ አንዱ ያገኛቸውና የአውሮፓውያንን አዲስ ዓመት በማስመልከት፣ ‹‹እንኳን አደረስዎ ባሻዬ፤›› ይላቸዋል። ባሻዬ እንኳን እርጅና ይዟቸው ገና ያኔ በአፍላነታቸው በዱር በገደሉ አርበኛ ያደረጋቸው የአበው ልማድና ባህል እንከን የለውም ስለሚሉ፣ ‹‹ምናባህ ቆርጦህ ነው?›› ብለው ከዘራቸውን ማንሳት። አጅሬ ደንግጦ ሲፈረጥጥ ገና በእኩለ ቀን በአረቄ አቅሉን ስቶ የሚያሽከረክር ዠብራራ ለጥቂት ይስተዋል። ልብ በሉ እንግዲህ አሁንም እኮ ይኼ ሰቆቃ ተሸክሞ የመጣ ቫይረስ እንዲህ ዓይነቶቹን እኮ ነው ከመንገድ የሚያስቀራቸው የሚሉት፡፡ እጅህን ታጠብ ሲባል አሻፈረኝ የሚል፣ አልጨብጥህም ሲሉት የሚያኮርፍ፣ ተበተን ሲባል ባህሌ፣ ልማዴ፣ መብቴ ተጣሰ የሚል ዠብራራ እኮ ነው እንደወጣ የሚቀረው፡፡ ወይ ጉድ አሁንም ዘልዬ እዚያው ገባሁ እኮ፡፡ ጎበዝ አቅላችንን ሳትን እኮ!

ባሻዬን ሰሞኑን እንዲያው ከዚህ ሁሉ ከቤቴ ባልወጣስ ብለው ቤታቸው ዘግተው ተቀመጡ። መቼም የእንጀራ ጥያቄ ባይኖርብን በዚህ ነገሩ ሁሉ ግራ ግራ በሚጫወትበት ዘመን፣ አይደለም ከቤት መውጣት ወደ እናታችን ማህፀን ተመልሰን ብንገባ የምንመኝ ብዙ የምንሆን ይመስለኛ። እና ባሻዬም ቤት ተቀምጠው ሬዲዮናቸውን ሲከፍቱ የሰው ልጅ ሕይወት ቁጥር ሆኖ የተያዙ፣ የሞቱ፣ ያገገሙ ተብሎ ቁጥር ይደረደራል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለስታሊን ከዓመታት በፊት የተናገረው ትዝ አለኝ፡፡ የያኔዋ ሶቪየት ኅብረት የአሁኗ ሩሲያ መሪ የነበረው ጆሴፍ ስታሊን፣ ‹‹የአንድ ሰው ሞት ትራጄዲ ነው፣ የሚሊዮኖች ሞት ግን ስታትስቲክስ ነው፤›› ነበር ያለው፡፡ ይህንን ሲነግረኝ እውነት እላችኋለሁ ደንግጬ ነበር፡፡ ባሻዬ አሁን ሰው ቁጥር ሲሆን መሬቱ ከዳቸው። ‹‹ምነው ባሻዬ እስቲ ይረጋጉ?›› ብላቸው ሳይቸግረኝ፣ ‹‹በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ ሰብዓዊ ፍጡር ቀባሪ አጥቶ በሹም መቀበሩ ሳያንስ፣ ይህን ያህል እየተባለ ሲነገር ሰው መሆኔን ጠላሁ. . .›› ሲሉኝ ዝም አልኩ። እስኪ ይሁና!

ብቻ ከሚታየውና ከሚሰማው ሁሉ ውስጠ ሚስጥሩን መበለት የሚያቅተን  በዝተናል። እንዲያው ከሁሉ ከሁሉ የገረመኝ ለሚታየውና ለማይታየው ነገር የሚሰጠው  ክብደት፣ እያደር እንደ ኑሮ ኪሎ እየጨመረ መምጣቱ ነው። ማለት ስንቱ በሕይወት ባህር ውስጥ በሥውር የበደል ማዕበል ህልውናውን እየተነጠቀ እንዳለ እያወቅን፣ የምናወራውና የምናስወራው በዓይን የምናየውን ብቻ ሳይሆን መላምቱን ጭምር ነው። እውነቴን እኮ ነው። የህሊና ጉዳትንና የሞራል ስብራትን እውነት በአሁን ዘመን ማን ነው አክብዶ የሚያያቸው? ባለፈው ሰሞን ምን ሆነ መሰላችሁ? አንድ ደንበኛዬ የቶርኖ ማሽን ገዝቶ አስመጥቶ ለመሸጥ ያስባል። ወንድሙ በደህና ጊዜ አንገቱን ያስገባ ዓለም አቀፍ የቢዝነስ ሰው ስለሆነ የማስጫኑን ነገር በእሱ በኩል እጨርሳለሁ ብሎ ሙሉ እምነቱን ጥሎ፣ ከተማው ውስጥ አሉ የሚባሉትን ማሽኖች እየዞርን አብረን አየን። ማስመጣት ስላለበት ማሽን ዓይነትና ሞዴል በቂ መረጃ አሰባሰበን ስንጨርስ ገንዘቡ በወንድሙ የባንክ ቁጥር አስገብቶ መጠባበቅ ያዘ። ምን ያደርጋል ኮሮና በአቋራጭ መጥቶ እንዳልነበረ አደረገው፡፡ ለነገሩ እሱው የላይኛው ጌታ ይሁነን እንጂ ከዚህ የከፋስ አለ አይደለ እንዴ፡፡ ዋናው አለመክፋት ነው!

በጣም እኮ ነው የሚገርማችሁ ቀደም ብሎ ወንድምዬው ገንዘቡን አላየሁም አልሰማሁም ብሎ ክዶት አያርፍ መሰላችሁ? ቢባል ቢሠራ ፍንክች ያባ ቢላዋ ልጅ አለ አሉ። ውል የለ ማስረጃ የለ ሕግስ ምን ብሎ መሀል ይግባ? ይኼው ከትናንት ወዲያ የተለመደችዋ መደገፊያዬ ላይ ሆኜ አላፊ አግዳሚውን ሳስተውል መለ መላውን አብዶ ሲሮጥ አየሁት። ‹‹የማይታይ የማይታየውንማ ለፈጣሪ መተው ነው አንበርብር። እስኪ መጀመርያ ማየት የቻልነውን በደንብ እናፅዳው፤›› ያሉኝ ባሻዬ ናቸው ከአቅም በላይ ለሆነ ነገር ምን ማድረግ ይቻላል ሲሉ። ሳስበው ባሻዬ የተናገሩት በጣም እውነት ነው። አጠገባችን ዓይን ያወጣ ሌብነት፣ የሰብዓዊነት ክስረትና የፍትሕ መጓደል እያስመረሩን ችግራችንን አራግፈን ሳንጨርስ፣ ስለማይታዩት የህሊናና የሞራል ወንጀሎች ልናወራ እንደማንችል ገባኝ። በዚህ መሀል መዓት መጥቷልና፡፡ ታዲያ አንድ ወዳጃችን፣ ‹‹ይገርማል ለመጠጥ የሚሆን ውኃ በወጉ በቧንቧ ማግኘት የሚያቅተን በዚህ በከበደ ጊዜ በውኃ ዕጦት የኮሮና ሰለባ ብንሆን ምን ይባላል?›› ሲለን ስለኛ ‹አብስትራክት› የኑሮ ቋጠሮ ማንም ምንም ማለት እንደማይችል ገባኝ፡፡ ይኸው ነው!

ደግሞ የቱንም ያህል ያሰብነው ቢሳካ የወጠንነው ቢሰምር ያለ ጤና ምንም ዋጋ እንደማይኖረው ሲገባኝ፣ እኔም ራሴን መመርመር ጀመርኩ። ‘እያዩት ከማይበሉት ሰዎች ተርታ አያሠልፋችሁ!’ ነው አሉ የሚባለው በዚህ ሰሞን። አይ እኛ መቼም አሉ ስንወድ እኮ! ባሻዬ ባለፈው ከዕድር ስብሰባቸው ሲመለሱ፣ ‹‹አቤት! እግዚኦ አንተ ፈጣሪ!›› እያሉ ሲጓዙ አገኘኋቸው። እጆቻቸውን ወደ ሰማይ አንስተው ረቂቅ ትዝብታቸውን ለአምላካቸው ይኸው ብለው እንደ ንድፍ የሚያሳዩት ይመስላሉ። ‹‹ምነው ባሻዬ?›› ስል እንደ ልማዴ፣ ‹‹እንዲያው ማን ይሆን ጤነኛ ዘንድሮ አንበርብር? ሰው ሁሉ ጉዱን ከኋላው ደብቆ ነው ለካ የሚኖር?!›› ሲሉኝ ምን ሰምተው እንደሆነ አልጠየቅኳቸውም። ጊዜው ብዙ ያናግራልና እኔም በውስጤ ለፈጣሪ አቤት እያልኩ መሆኔ የታወቀኝ ባሻዬ ርቀውኝ ከሄዱ በኋላ ነበር፡፡ ‹‹ሰው ለፈጣሪ ትዕዛዝ ሲገዛ የምድሩንም ገዥ መመርያ ማክበር አለበት፡፡ ለነፍሱ ሲያስብ ሥጋውንም በሥርዓት መምራት ይኖርበታል. . .›› እያለ ንቃተ ህሊናዬን የሚያዳብርልኝ ምሁሩ ልጃቸው፣ ‹‹አንበርብር ፈጣሪ ደስ የሚለው ራስህንም ስትጠብቅ ነው. . .›› ሲለኝ ደግሞ እፅናናለሁ፡፡ መፅናናቱንና ብርታቱን ያድለን!

በስርቆትና በሕገወጥ መንገድ ዘመናችንን በሙሉ ለምን የተደላደለ ነገር ይዘን ለመኖር እንደምንደክም ሳስበው ብቻዬን ገርሞኝ እስቅ ጀመር። ወደው አይስቁ እኮ ነው፡፡ ስለዚህ አመራማሪ ስለሆነ የእኛ የሰው ልጆች ባህሪ ከባሻዬ ጋር ስንጨዋወት፣ ‹‹ይኼ አሁን የምትለኝ ነገር ከጥንትም ከእነ አዳም ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለ አመል ነው። ቀናው እያለ ጠማማውን፣ ፊት ለፊቱ እያለ ጓሮውን፣ ብርሃን እያለ ጨለማውን መሄድ ነው የምንወደው። እንዴት ያለ ባህሪ ነው ግን?›› ብለውኝ ባሻዬ ራሳቸው እጅግ ገርሟቸው ሳቁ። በዚህ መሀል ስለሰው ልጅ በሥልጣኔ መገስገስና መራቀቅ ለማሰብ ሞከርኩ። ጨርሶ የሚዋጥልኝ ነገር አልሆነም። ሰው ሰውን የሚጥልበትን ገደል እየማሰ፣ ለሰውነቱም ለአዕምሮውም ጤና የማይሰጠውን የሕዝብ ገንዘብ እየቀማ፣ የአገሩን ኢኮኖሚ ለማድማት የማይገባበት ሲገባ ስታዩ እውነት 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነን ወይስ የጋርዮሽ ዘመን ላይ ትላላችሁ እኮ፡፡ እርስ በርሱ ለመጠፋፋት የኑክሌር አረሮች አከማችቶ፣ የባዮሎጂካል መሣሪያዎችን ፈብርኮ ቫይረሶችን እየፈለፈለ ሲወራጭ እንዳልነበር፣ አሁን ከአቅሙ በላይ ሆኖበት እጁን እየሰጠ ከማየት የበለጠ ምን አለ? ምንም!

በጠፋ ሥራ ማምሻም ዕድሜ ነውና በአጋጣሚ የሸቃቀልኳትን ቆንጥጬ ይዤ ከፊሉን ለማንጠግቦሽ የቤት ወጪ አድርጌ፣ ከፊሉን ወደ ‹አካውንቴ› ወርውሬ ወደ ሠፈር አዘገምኩ። ስደርስ ድብልቅልቅ ጠበቀኝ። በሐሳቤ ብዙ ነገር ይመላለሳል። ማን ዓይን በዓይን ተከድቶ ወይም የማን ንብረት ተዘርፎ ይሆን እላለሁ። እህ ስል የአንድ ወዳጃችን ታናሽ ወንድም ራሱን ሰቅሎ በገዛ ፈቃዱ ከዚህ ዓለም መሰናበቱን ሰማሁ። ደግሞ በቅርብ አውቀዋለሁ። የአርጋጅ አናጓጁ እንዲያው፣ ‹‹ምናለበት ይህን ክፉ ጊዜ ቢያሳልፍ?›› ሲልም እሰማለሁ። ‹‹አሁን እስኪ ቀኑን መዋል ያቃተውን ሰው ጊዜውን ቢያሳልፍ ብሎ ነገር’ ብዬ ሳስብ፣ ብሸቀት ይይዘኝ ይጀምራል። ዕንባና ትዝብት በህልውናዬ ሰርጥ እሰጥ አገባ ገጥመው መንፈሴ ደቀቀ። ባሻዬ ገና ከቤት መውጣታቸው ነው። ‹‹የት ይደርሳል የተባለው ገና መንገዱን ሳይጀምር እንዲህ ሩብ መንገድ ላይ ሲታጠፍ፣ መንገዱን የጨረሱት ምን ይሉት ይሆን?›› ስል የባሻዬ ልጅ ሰማኝ። ‹‹ሩጫዬን ጨርሻለሁ ነዋ፤›› ብሎ ተኮሳትሮ መለሰልኝ። የምይዝ የምጨብጠው ሲጠፋኝ፣ ማንን ማፅናናት ማንን ማረጋጋት እንዳለብኝ ግራ ሲገባኝ፣ የባሻዬን ልጅ ጎትቼ ወደ ቤት ሄድን።

በሉ እንሰነባበት። እኔና የባሻዬ ልጅ ወግ ጀምረን እያቋረጥን ተዘጋግተን ተቀምጠናል። ያየኛል አየዋለሁ። ቆይቶ ግን፣ ‹‹ስማ እንጂ አንበርብር?›› ብሎ ጀመረኝ። ‹‹ወይ?›› ስለው፣ ‹‹አይገርምም ግን የዚህ ዓለም ነገር?›› ብሎ አፈጠጠብኝ። ‹‹ተገራሚ መሆኔን አምነህ ሳለ መልስ እንዳለው ሰው ምን እኔን ትጠይቀኛለህ?›› አልኩት ዝግ ብዬ፣ ‹‹ተመልከተው እስኪ ሰውን። ይሠራል፣ ይደክማል፣ በውጣ ውረዱ ሁሉ ተስፋውን በሚተማመንበት አምላኩ ላይ አድርጎ ይውላል፣ ያድራል። ግን ይኼው የአንዱ ውልደት ለሌላው የድሎትና የፈንጠዝያ ኑሮ፣ የአንዱ የትግልና የፍልሚያ ኑሮ ለሌላው የውለታ ቢሶች መፈንጫና ማደሪያ ሆኖ ይቀር ነበር። አሁን ግን ሁሉም የከንቱ ከንቱ ሲሆን አይገርምም?›› ሲለኝ ለማለት የፈለገው ቢገባኝም ምንም እንዳልገባው ዝም አልኩ። በበረት ተወልዶ በበረት ከሚሞተው የምስኪኑ ሰው ልጅ ሞት ይልቅ እኔን ያሳስበኝ የነበረው የሕይወት ትርጉም ነበር። ዛሬ ጊዜ ትርጉም አልባ ሕይወት የሚኖረው አላንስ ብሎ ሕይወት ትርጉም እንዳላት የረሳነው በዝተናል። ገንዘብ ዝና መብልና መጠጥ የኑሯችንና የሐሳባችን ጣሪያ የነበሩ ቢመስሉም፣ አሁን ግን ዋጋ አልባ የሎተሪ ቲኬት መስለዋል። ግን ደግሞ በዚህ አበቃ ስትሉት ዞሮ ዞሮ በሌላ ገጽታ ይመጣል። ከልደት አንስተን እስከ ፍፃፈሜያችን የምንሸከመው ዕዳ ላይቀል፣ በገዛ ራሳችን ላይ በቁምም በአካልም ሞት የምንፈርደው በዝተናል። በበኩሌ ያቅልልን ብያለሁ። አንዳንዴ እኮ ከማይጋፈጡት ባላጋራ ጋር ከመታገል ዞር ማለትም ጥበብ ነው፡፡ ጥበቡ ደግሞ መተኪያ የሌለው ጥንቃቄ ነው፡፡ የፈጣሪን ለፈጣሪ፣ የቄሳርን ለቄሳር እንዲሉ ሕግ እናክብር፡፡ የሚያዋጣው ሕግ ማክበር ነው፡፡ አያከስርም! መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት