424 ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር ሲውሉ የ1‚559 ተጠርጣሪዎች ክስ ተቋረጠ
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወይም አገርን አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚተላለፉ መመርያዎችንና ውሳኔዎችን ተላልፎ መገኘት፣ ከቀላል እስራት እስከ ዕድሜ ልክ እስራት እንደሚያስቀጣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡
መጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ወዲህ 4,011 ተጠርጣሪ ተከሳሾችና ታራሚዎች፣ መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ደግሞ 1‚559 ተጠርጣሪዎች ከእስር መለቀቃቸውን ይፋ ያደረጉት ዋና ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ ስለሚተላለፉ መመርያዎችንና ውሳኔዎችን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
‹‹የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ዓለምን እያዳረሰ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል የሚቻለው ርቀትን በመጠበቅ፣ ለቫይረሱ ከሚያጋልጡ ነገሮች በመራቅ፣ በመንግሥት አካላት የሚተላለፉ መመርያዎችን በማክበርና በመተግበር፣ ከውጭ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ በኋላ በመመርያው መሠረት አስገዳጅ የለይቶ ማቆያን ጊዜ አክብሮ በመቆየት፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን ባለማስተላለፍና በአቋራጭ መንገድ ለማትረፍ ምርትን ባለመደበቅና ከዋጋ በላይ ባለመሸጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ጥሶ የተገኘ ማንኛውም አካል ከቀላል እስራት እስከ ዕድሜ ልክ እንደሚቀጣ አስታውቀዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአደጋ ጊዜ የሚወጡ መመርያዎችና የሚተላለፉ ውሳኔዎች መከበር ያለባቸው ሕጎች በመሆናቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ወ/ሮ አዳነች ይህንን የተናገሩት ለሁለተኛ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ፣ 559 እስረኞችን በይቅርታ መፈታታቸውን በገለጹበት ወቅት ነው፡፡ የተለቀቁት እስረኞች በፖሊስ ጣቢያ በምርመራ ላይ የነበሩ፣ በማረሚያ ቤት የቆዩና ማስረጃ ያልቀረበባቸው ታራሚዎች የነበሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ከእስር እንዲፈቱ የተወሰነላቸው 1‚511 ወንዶችና 48 ሴቶች መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ እስረኞቹ ይቅርታ የተደረገላቸው ለይቅርታ ቦርድ የቀረበ ማስረጃ ተመርምሮና ተጣርቶ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቀርቦ፣ የይቅርታው ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ከ15 ሺሕ በላይ የንግድ ተቋማት አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው፣ 424 ነጋዴዎችም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም. በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ እንደተገለጸው፣ ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባልና ለፖለቲካ ምኅዳሩ ስፋት›› ሲባል 63 ተከሳሾችና ታራሚዎች መፈታታቸው ከተገለጸ በኋላ፣ ወ/ሮ አዳነች ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ደግሞ 4‚011 እስረኞች መጋቢት 15 ቀን፣ እንዲሁም 1‚559 እስረኞች መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በይቅርታ እንዲፈቱ ተደርጓል፡፡