Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት በሚያከማቹ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ ከተወሰደ ለቀጣዮቹ አራት ወራት የምግብ እጥረት እንደማያጋጥም ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መጋቢትና ሚያዝያ አርሶ አደሮች ምርት በብዛት የሚያገኙበትና ወደ ገበያ የሚያወጡበት በመሆናቸው፣ በመጪዎቹ ሦስትና አራት ወራት የእህል አቅርቦት ችግር እንደማይኖር፣ ምርት በሚያከማቹ ላይ የማያዳግም ዕርምጃ ከተወሰደም የምግብ እጥረት እንደማይኖር፣ በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ ገለጹ፡፡

ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ የእህል አቅርቦት እንዳይስተጓጎል፣ እህል በሚያከማቹና የዋጋ ንረት በፈጠሩ ነጋዴዎችና ግለሰቦች ላይ መንግሥት የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡

የቫይረሱ ሥርጭት፣ አርሶ አደሩ ደርሶ የእርሻ ሥራው እንዳይቋረጥ በጤና ቢሮዎች ከሚሠራው በተጨማሪ፣ ሚኒስቴሩ የግብርና ጣቢያ ልማት ሠራተኞችንና አርሶ አደሩን በተለያዩ ቋንቋዎች በኤፍኤምና በሌሎች የድምፅና የኅትመት መልዕክቶች ለማስተማር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለቀጣዩ እርሻ የሚያገለግሉ ማዳበሪያዎችንና ዘሮችን ቀድሞ ለማቅረብም ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በምርቶቹ ላይ አሁን የታየው እጥረትና የዋጋ ውድነት የተፈጠረው ሰው ሠራሽ በሆነ መንገድ መሆኑን፣ አርሶ አደሩ በወረርሽኙ እንዳይያዝ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ከተደረገ የቀጣዩ እርሻ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ሊኖር ይችላል ተብሎ የሚገመተውን ተፅዕኖ መቆጣጠር እንደሚቻልም አቶ ኢሳያስ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በየትኞቹ ወራት የምርት አቅርቦት እንደሚጨምርና ዋጋ እንደሚቀንስ፣ በየትኞቹ ደግሞ እጥረት እንደሚኖርና ዋጋ እንደሚጨምር እንደሚታወቅ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹አሁን ያለንበት ወቅት ደግሞ የእህል እጥረት እንደሌለበትና የአቅርቦት እጥረት ገጥሟል ከተባለም ሆን ተብሎ የተፈጠረ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአብዛኛው ሸማች ገዝቶ የማከማቸት አቅም ከአንድና ከሁለት ወር እንደማያዘልቅ፣ አብዛኛው ደመወዝተኛም አንድ ኩንታል ጤፍ ቢገዛ ሌሎች ፍላጎቶችንና ግብአቶችን ለማሟላት እንደሚቸገር፣ አሁን የገጠመው እጥረትና የዋጋ ንረት የተፈጠረውም ክምችት በመያዝ እንደሆነ አክለዋል፡፡

ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ በመግባቱ ከሚፈጥረው ጫና ይልቅ፣ ነጋዴውና ሸማቹ የፈጠሩት ችግር እንደሚጎላ መታዘባቸውን አቶ ኢሳያስ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ችግሩን በሚያባብሱ ላይ የጀመረውን ዕርምጃ ከዚህ ቀደም ከተለመደው በተለየ ጠንካራ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አገሪቱ ውስጥ የኢኮኖሚ ቀውስ ሲፈጠር፣ ግጭት ሲያጋጥምና የፖለቲካ ቀውስ ሲኖር በተደጋጋሚ የሚታየው ሥርዓት አልባ የንግድ ልውውጥ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አሁን ላይ መቋጨት እንዳለበት፣ ንግዱን ሥርዓት ለማስያዝ የተቀመጡ ሕጎችን ለመተግበርና ለማስቀጠል ያለውን አጋጣሚ መጠቀም ይገባልም ብለዋል፡፡

‹‹ወደፊት ሊገጥመን ይችላል ተብሎ የሚፈራው የምግብ እጥረት መንግሥት እንደሚወስደው ዕርምጃ ይወስዳል፤›› ያሉት አቶ ኢሳያስ ምግብ በሚያከማቹ፣ ዋጋ በሚያንሩና ትራንስፖርት በሚያስተጓጉሉ ላይ መንግሥት ጥብቅ ዕርምጃ ከወሰደ ችግሩን መሻገር እንደሚቻል፣ ይህ ካልሆነ ግን ረሃቡ ይፈጥናል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ድንበሮች በመዘጋታቸው የተመረተው ምርት በየትም ሊወጣ እንደማይችል፣ ነገር ግን ይህንን ለመተላለፍ የሚሞክሩ ካሉ ድርጊታቸው በአገር ህልውናና በኢትዮጵያውያን ሕይወት ላይ ስለሚሆን፣ መንግሥት እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራ ጠቁመዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር በኩል የግብርና ልማት ጣቢያ ሠራተኞች ከንክኪ ነፃ በሆነ መንገድ አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርሱ፣ የነበረው ግብርና እንዲቀጥል ከክልሎች ጋር እየተሠራ መሆኑንና በሌሎች አገሮች እንደታየው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭት ቢጨምርና ጉልህ ተፅዕኖ ቢፈጥር፣ ተግባራዊ መደረግ በሚችሉ አማራጮች ላይ የማካካሻ ዕቅድ መጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች