Friday, September 22, 2023

ለኮሮና ቫይረስ ሕክምና መስጫ ቬንቲሌተሮችንና ሌሎች መሣሪያዎችን እንዲያሰባስቡ ለሁሉም ኤምባሲዎች መመርያ ተላለፈ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውጭ የሚገኙ ሁሉም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ለኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቬንቲሌተሮችን ጨምሮ የሕክምና መስጫ መሣሪያዎችን፣ ከሚገኙባቸው አገሮች በዕርዳታ አሰባስበው እንዲልኩ መመርያ አስተላለፈ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የጻፉት ደብዳቤ ለሁሉም በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የተላከ ሲሆን፣ የደረሱበትን ውጤትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሚከታተሏቸው የውጭ ጉዳይ ዳይሬክቶሬቶች እንዲያሳውቁ ያዛል።

ሪፖርተር ያገኘው በሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተፈርሞ የተላከ ደብዳቤ  ኤምባሲዎቹ የሕክምና መስጫ መሣሪያዎችን ከሚገኙባቸው አገሮች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት፣ እንዲሁም በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በዕርዳታ ለማሰባሰብ ትኩረት እንዲያደርጉ ይጠይቃል።

ኤምባሲዎቹ ይኼንን ኃላፊነት መወጣት እንዲቻላቸው ለማድረግም ለኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ሕክምና ለመስጠት በኢትዮጵያ የሕክምና ተቋማት በእጅጉ የሚፈለጉ የሕክምና መስጫ መሣሪያዎችን ዝርዝር፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስUሩ ከደብዳቤያቸው ጋር በአባሪነት አካተው መላካቸው ታውቋል፡፡ የተላከው አባሪ ሰነድ 21 የሕክምና መሣሪያዎች ዝርዝር ያካተተ ሲሆን፣ በግንባር ቀደምትነት የተጠቀሰው በተለይ በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ከፍተኛ የሕክምና ክትትል ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች መተንፈስ እንዲችሉ የሚያግዘው ቬንቲሌተር ይገኝበታል።

በዚህም መሠረት ኤምባሲዎቹ ለአዋቂዎች ሕክምና የሚያገለግሉ 1,000 ሜካኒካል ቬንቲሌተሮችን ከእነ ሙሉ ተጓዳኝ መሣሪያዎች፣ እንዲሁም ለሕፃናት ሕክምና መስጫ የሚያገለግሉ 500 ተመሳሳይ ቬንቲሌተሮች አፈላልገው እንዲልኩ በአባሪ ሰነዱ ተገልጾላቸዋል።

በኮሮና ቫይረስ ለተጠቁ በእጅጉ የሚያስፈልገው ይህ የሕክምና መከታተያ መሣሪያ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እጥረት የታየበትና የአንዱ የመሸጫ ዋጋውም በከፍተኛ ደረጃ መናሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአሜሪካ የዚህ የሕክምና መከታተያ መሣሪያ እጥረት ከፍተኛ በመሆኑ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አስገዳጅ የሆነውን የብሔራዊ አደጋ አዋጅ (ዲፌንስ አክት) በመጠቀም፣ ጄኔራል ሞተርስ (GM) የተባለው የአሜሪካ መኪና አምራች ኩባንያ ሙሉ ትኩረቱን ቬንቲሌተሮችን በማምረት ላይ እንዲያደርግና ምርቶቹንም በአስቸኳይ እንዲያቀርብ ታዟል።

ሌሎች የአሜሪካ ኩባንያዎችም ተመሳሳይ አስገዳጅ ትዕዛዝ ደርሷቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቬንቲሌተርና ሌሎች የሕክምና መሣሪያዎችን እጥረት ለመቅረፍ፣ አሜሪካ ከቻይናው የአሊባባ ባለቤት ጃክ ማ ጋር እየተነጋገረች ነው፡፡ የደቡብ ኮሪያ መንግሥትንም ዕርዳታ ጠይቃለች።

የዚህ መሣሪያ እጥረት ከአሜሪካ በተጨማሪ በእንግሊዝና በሌሎች ባለፀጋ የአውሮፓ አገሮች የተከሰተ መሆኑን፣ የአንድ ቬንትሌተር ዋጋም እስከ 25,000 ዶላር እንደሚያወጣ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሕክምና ተቋማት ውስጥ የሚገኘው የዚህ መሣሪያ ብዛት ከአራት መቶ እንደማይበልጥ ይታወቃል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት አንፃር፣ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ይህንን መሣሪያ በተጠየቀው ብዛት በዕርዳታ ማግኘት ይችላሉ የሚለው አጠራጣሪ ሆኗል።

ከዚህ የሕክምና መከታተያ መሣሪያ በተጨማሪ 1,300 የተለያዩ የኮሮና ቫይረስ መመርመርያ ኬሚካሎች፣ ሰርጂካል ማስክ የያዙ ሁለት ሚሊዮን ሳጥኖች (ለቀዶ ሕክምና የሚያገለግል ፊት መሸፈኛ)፣ አንድ ሺሕ ኦክሲጅን ኮንሰንትሬት፣ አምስት ሺሕ የኦክስጂን መስጫ የፊት መሸፈኛዎች በዝርዝሩ ከተካተቱት መካከከል ጥቂቶቹ ናቸው።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -