የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት የሚደረገው ዘመቻ ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ስትራቴጂካዊ አመራር ያስፈልጋል፡፡ ወሳኝ በተባሉ የጥንቃቄ ዕርምጃዎች በመታገዝና ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች በማማከል ውጤታማ መሆን የሚቻለው፣ በዕውቀት ላይ በተመሠረተና በተቋም በተደገፈ አሠራር ኃላፊነትን በመወጣት ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ የከፋ ችግር አጋጥሞ ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው እንዲታቀቡ አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠር፣ ቢያንስ በተጣለው የጊዜ ገደብ ውስጥ የምግብና የሌሎች አቅርቦቶች ዋስትና ሊኖራቸው የሚችለው ስትራቴጂካዊ አመራር ሲኖር ነው፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎች በጠንካራ ክትትል ተግባራዊ እንዲደረጉ፣ የተጣሉ ገደቦች እንዲከበሩና የሕግ ማስከበር ሥርዓቱ በብቃት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ በሀብት ማሰባሰብ ዘመቻው የተገኙ እንደ ገንዘብ፣ ምግብ፣ የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችና የመሳሰሉት ችግር ላለባቸው ወገኖች ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲዳረሱ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ለምርመራ፣ ለመለየትና ለማከም የሚደረገው እንቅስቃሴ ቀልጣፋና አስተማማኝ እንዲሆን ተቋማዊ የሆነ ስትራቴጂካዊ አመራር ግዴታ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አመራር ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበትና ከሕዝቡም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ከተሰማሩ ባለሙያዎች ጋር ጠንካራ ቁርኝት ይኖረዋል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ጥላ ሥር ሆኖ ስለሚመራ፣ ለሰብዓዊ መብት ጥሰትም ሆነ አላስፈላጊ ለሆኑ ድርጊቶች አይጋለጥም፡፡ መረጃዎችን በፍጥነት እየለቀቀ ለሕዝቡ ተደራሽ ስለሚያደርግ፣ መሠረተ ቢስ ወሬዎችና አሉባልታዎች ውዥንብር አይፈጥሩም፡፡ ከሌሎች አገሮች ልምድ በመቅሰም የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ዕድሉን ማግኘት ስለሚችል፣ የፀረ ኮሮና ቫይረስ ዘመቻው ውጤታማ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ ወቅቱ የሚፈልገውም ይህንን የመሰለ ብርቱና ብቁ ተቋማዊ አመራር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሚኒስትሮች ብሔራዊ ኮሚቴ መጪው ጊዜ ከበድ ሊል እንደሚችል በመገንዘብ፣ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚደረጉ ተግባራት ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን በመረዳትና ካሁን በኋላ የሚኖሩ ሥራዎች በርካታ ልምዶችንና ዕውቀቶችን ማካተት እንደሚኖርባቸው በማመን መዘጋጀት አለባቸው፡፡ በመደበኛው ደካማ ቢሮክራሲና መዋቅር የትም መድረስ ስለማይቻል፣ በተለይ ብሔራዊ ኮሚቴው በርካታ ባለሙያዎችን በአማካሪነትና በአመራር ሰጪነት ማሳተፍ ይጠበቅበታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢጋድም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የቀጣናውንና የአኅጉሩን ትብብር ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር የማስተሳሰርና ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራውን በወሳኝነት እየመሩ፣ የሎጂስቲክስና የሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን በየደረጃው ብቃት ላላቸው ሰዎች አደራውን በመስጠት ተቋማዊ አቅም መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የስትራቴጂካዊ አመራር ዋነኛ ግብ ውጤታማ መሆን ሲሆን፣ ውጤቱ የሚለካው ደግሞ በተቀመጠለት መርሐ ግብር መሠረት ተቋማዊ ሆኖ እየሠራ መሆኑ ሲያስተማምን ነው፡፡ ይህም የበርካታ አመራር ሰጪዎች ድምር ውጤት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኃላፊነትን ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ የልምድና የዕውቀት ባለቤት የሆኑ በርካታ ልጆች ስላሏት፣ አጋጣሚውን ተቋማዊ አሠራር ለመፍጠር መጠቀም ይገባል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ጠቃሚ ምክርና ማሳሰቢያ ያላቸውንም ወገኖች መስማት አንዱ የአመራር ጥራት ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጓት የኮሮና ቫይረስ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዴት መግታት እንደሚቻል አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዜጎች እንጂ፣ ውኃ ለምን ቀጠነ እያሉ ሁሉንም ነገር ለወቀሳና ለትችት የሚያውሉ ቀልበ ቢሶችን አይደለም፡፡ ወረርሽኙ ዓለምን እያተራመሰና ኃያላንን ሳይቀር ግራ እያጋባ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የተለመደውን የፖለቲካ ሽኩቻ አዝሎ መዞር የጤንነት አይደለም፡፡ በወረርሽኙ ሥጋት እንቅስቃሴው የተገደበ የፖለቲካ ፓርቲ ለምን ምርጫ ተላለፈ ብሎ ሲወራጭ፣ ዓላማው ምን እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን አመራሩ በእነ ማን ነው የተያዘው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከለከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የበኩልን ሚና ለመወጣት መዘጋጀት ሲገባ፣ ምንም ነገር ያልተፈጠረ ይመስል መንጎማለል ከሕዝብ ጋር ያራርቃል፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ ከሕዝብ ልብ ውስጥ መውጣት የሚያስከፍለው ዋጋ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች አሁን ሙሉ ኃይላቸውን ማዋል ያለባቸው፣ ብሔራዊ ጥረቱ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ተቋማዊ ሆኖ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ ትብብር ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ሌላው ነገር ፋይዳ ቢስ መሆኑን መገንዘብ የግድ ይላል፡፡ ይህ ማሳሰቢያ የሚመለከተው አገር የሚያስተዳድረውን ብልፅግና ፓርቲ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችንና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ማናቸውንም ወገኖች ነው፡፡ ወቅቱ አገርንና ሕዝብን መታደጊያ በመሆኑ ግላዊና ቡድናዊ ጉዳዮችን ወደ ጎን ማለት ይገባል፡፡ ወቅቱም የሚጠይቀው እንዲህ ያለውን የተቀደሰ ተግባር ብቻ ነው፡፡
በዓለም ዙሪያ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው 60 ሺሕ ያህል ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ220 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ማገገማቸው ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የቫይረሱ ሥርጭት አሁን ካለው መጠን በጣም ሊጨምር ይችላል ተብሎ ስለሚታሰብ፣ የሰዎችን ሕይወት የመታደግ ተግባራት በተለያዩ መንገዶች መከናወን አለባቸው፡፡ በአንድ በኩል የቫይረሱን ሥርጭት የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መመርያ መሠረት የጥንቃቄ ተግባራትን በፅናት በማከናወን ሕይወት ማዳን ሲሆን፣ የተለያዩ የሥራ ዘርፎች በመዘጋታቸውና የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች በመቆማቸው ምክንያት ለምግብ ችግር የሚጋለጡ ወገኖችን ሕይወት መታደግ የግድ ይሆናል፡፡ ይህንን ሥራ በብቃት ለማከናወን መንግሥት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጎ ፈቃደኞችን በመመልመልና በሎጂስቲክስ ዘርፍ የሥራ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በማሰባሰብ፣ የመደበውን በጀትና ከሕዝብ ያሰባሰበውን ሀብት በተቀላጠፈ መንገድ ለተቸገሩ ለማድረስ የተደራጀ ተቋማዊ ሥርዓት መፍጠር አለበት፡፡ ገና ከአሁኑ ለችግር መጋለጥ የጀመሩ ወገኖች በየቦታው እየተስተዋሉ ስለሆነ መፍጠን ይገባል፡፡ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆኑ ለስትራቴጂካዊ አመራር መዘጋጀት የግድ ይሆናል፡፡ ጊዜው አጣዳፊና ተለዋዋጭ ክስተቶች የሚታዩበት ስለሆነና አንዴ ከእጅ ካመለጠ ዕድል ስለማይኖር፣ ዕርምጃን በተጠና መንገድ ተቋማዊ ሆኖ ማከናወን የስትራቴጂካዊ አመራር ኃላፊነት ነው፡፡
መንግሥት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተገናኘ በርካታ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡለት የታወቀ ነው፣ የሚጠበቅም ነው፡፡ ስትራቴጂካዊ አመራር ሲኖረው ግን ለዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አይቸገርም፡፡ ክፍተቶችን እግር በእግር እየተከታተለ ለመድፈን እንቅፋት አይገጥመውም፡፡ የጤና ተቋማትን ለማጠናከር በጣም አስፈላጊ ግብዓቶችን ማሰባሰብ፣ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎችን የሚያመርቱ ድርጅቶችን ማበረታታት፣ የብሔራዊ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽንን አቅም የበለጠ በማጠናከር ዝግጁ ማድረግ፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች በሙሉ አቅማቸው የጤና፣ የምግብና የምግብ ነክ ምርቶችን፣ እንዲሁም አስፈላጊ ግብዓቶችን እንዲያመርቱ ማነሳሳትና የመሳሰሉት ዕርምጃዎችን ማጠናከር ይገባል፡፡ በመንግሥት ከተመደበው 15 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ ጠቀም ያለ በጀት እንደገና በማፅደቅ በምግብ ዕጦት የሚቸገሩ ወገኖች ዘንድ መድረስ የግድ ይሆናል፡፡ ከከተማ ነዋሪዎች በተጨማሪ የአርሶ አደሮችና የአርብቶ አደሮች ጉዳይም የስትራቴጂካዊ አመራር አካል መሆን ይኖርበታል፡፡ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት ልዩ ትኩረት በመስጠት ተግባራዊ ዕርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝቡም ለዘመናት ሲሸጋገሩ እዚህ የደረሱ የጋራ እሴቶቹንና መስተጋብሮቹን ተጠቅሞ፣ በክፉ ጊዜ የመረዳዳት ባህሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ማስተባበር የግድ ይላል፡፡ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ማለት ማኅበራዊ ቁርኝትን መበጠስ እንዳልሆነ በተግባር ማረጋገጥ የግድ ስለሚል፣ መንግሥት ሕዝቡን ለፀረ ኮሮና ዘመቻ በአንድ ልብ ማንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ ስትራቴጂካዊ አመራር የሚያስፈልገው በተቋማዊ አሠራር ውጤታማ ሆኖ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ድል ለመንሳት ነው!