‹‹ሥራ በተቀዛቀዘበት ወቅት የዓመት ዕረፍታቸውን እንዲወስዱ ማድረግ ሕግ የሚፃረር አይደለም››
የኢትዮጵያ አየር መንገድ
በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ራሱን ብቸኛ ተጎጂ በማስመሰል በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ሠራተኞቹን ከሥራ ማሰናበቱ ኢፍትሐዊ ድርጊት መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር አስታወቀ፡፡
የሠራተኛ ማኅበሩ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሙሉ ባሠራጨው የተቃውሞ ደብዳቤ፣ በዚህ በወረርሽኝ ወቅት መንግሥት ዜጎቹን ከወረርሽኙ ለመታደግ ሲል ሥራቸውን አቁመው ደመወዛቸው እየተከፈላቸው በቤታቸው ውስጥ እንዲቀመጡ መመርያ በማውጣት ጭምር እየለመነ ባለበት ወቅት፣ አየር መንገዱ ‹‹ያለምንም ደመወዝ ከሥራ ተሰናብታችኋል፤›› ማለቱ የኢትዮጵያዊነትን ባህል የጣሰ ከመሆኑም ሌላ ኢፍትሐዊ ድርጊት መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን የአፍሪካም ኩራት የሆነው አየር መንገዱ ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ መሰናክሎችን በማለፍ ትርፋማ ለመሆን መብቃቱን ያስታወሰው የሠራተኛ ማኅበሩ፣ ይህም የሆነው በሥሩ ባሉ ትጉህና አገር ወዳድ ሠራተኞቹና አመራሮቹ መሆኑንም አስታውሷል፡፡ አየር መንገዱ ችግር ሲገጥመው ሠራተኞቹ የራሳቸውን ጥቅማ ጥቅም እየተው ስኬቱ እንዲቀጥል ማድረጋቸውም የማይታበል የአደባባይ ሀቅ መሆኑን አክሏል፡፡
በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ያወሳው የሠራተኛ ማኅበሩ፣ በአየር መንገዶች ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የግልና የመንግሥት ድርጅቶች ገቢም ላይ መቀዛቀዝ መፍጠሩን አስረድቷል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በወረርሽኙ ምክንያት በዓለም የአቪዬሽን ዘርፍ ላይ በተፈጠረው አሉታዊ ተፅዕኖ ምክንያት የገቢ ምንጩ መቀነሱን በመጠቆም በትርፋማነቱ ላይ የሚያመጣውን ጫና ለመቀነስ የተለያዩ የወጪ ቅነሳ አሠራሮችን ነድፎ ተግባራዊ ማድረጉ ትክክል ቢሆንም፣ የሠራተኛን ወርኃዊ ደመወዝ ግን ጥያቄ ውስጥ በሚከት ደረጃ ላይ አለመሆኑን ማኅበሩ አብራርቷል፡፡ አየር መንገዱ ምንም እንኳን መንገደኞችን ማጓጓዝ ቢቀንስም የጭነት ሥራው ግን መጧጧፉንና ተጨማሪ ገቢ እያገኘ መሆኑንም ማኅበሩ ጠቁሟል፡፡ የጥገና ክፍሉም ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የውጭ አየር መንገዶች አውሮፕላኖችን በመጠገን ላይ እንደሆነና ገቢ እያገኘም መሆኑን አክሏል፡፡
አየር መንገዱ የሕዝብ ንብረት በመሆን ከማንኛውም የግል ድርጅት በተሻለ ሁኔታ ማኅበረሰባዊ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት የገለጸው ማኅበሩ፣ በዚህ ጊዜ ሠራተኞቹን በችኮላ ከደመወዝ ውጭ በማድረግ ማሰናበት ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ትርፍን ዓላማ አድርጎ ይሠራ እንደነበር የሚያሳይ መሆኑ እንዳሳዘነውም ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በርካታ አውሮፕላን አብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች መኖራቸውን የጠቆመው ማኅበሩ፣ በርካታ ቤተሰብ ከጀርባቸው ያላቸውን ኢትዮጵያውያንን ብቻ ለይቶ ከሥራ ማባረር ወይም ያለ ደመወዝ እረፍት ማስወጣት ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ ሌላው ማኅበሩን ግራ ያገባው በአሁኑ ጊዜ የአብራሪዎች የሰው ኃይል ፍላጎት በመቀነሱ ምክንያት፣ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን የዓመት ዕረፍት ላይ ሆነው እያለ በውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ክፍያ የሚፈጸምላቸው በርካታ የውጭ ዜጎች እየሠሩ ያለበት ሁኔታ መሆኑን አብራርቷል፡፡
አየር መንገዱ ለዓመታት ይጠቀምበት የነበረው ሕገወጥ ኮንትራት የሥራ ቅጥር ሠራተኞች ሊኖራቸው የሚችለውን መብት እንዳሳጣቸው ገልጾ፣ ለአብነት ያህል በሺዎች የሚቆጠሩ የበረራ አስተናጋጆች፣ የትኬት ቢሮ ሠራተኞችና ቴክኒሽያኖችን በምሳሌነት አቅርቧል፡፡
ይኼ አሠራር ከሠራተኞች አዋጅ ጋር የሚፃረርና ስህተት ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በዚህ ወረርሽኝ ወቅት የሥራ ውል ማቋረጥ የለየለት ጭካኔ በመሆኑ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲታረም እንዲያደርግ ጠይቋል፡፡ አየር መንገዱ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ወጪው ውስጥ የሠራተኛ ደመወዝ የሚይዘው በጣም አነስተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ ምንም ገቢ የሌላቸውን ሠራተኞች በዚህ ጊዜ ቀንሶ የሚያተርፈው ገንዘብ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑንም አስረድቷል፡፡
ለምሳሌ 50 ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ደመወዛቸውን አቁሞ ከማባረር ይልቅ፣ አንድ የውጭ ዜጋ አብራሪን ዕረፍት ማስወጣት የበለጠ ተጠቃሚ እንደሚያደርገውም ጠቁሟል፡፡ እንደ አገር የሚፈጠረውን ማኅበራዊ ቀውስም በተወሰነ ደረጃ ሊቀንሰው እንደሚችልም አክሏል፡፡
ወረርሽኙ አገራዊ ችግር በሆነበት በዚህ ወቅት አየር መንገዱ መተባበርና መደገፍ ሲገባው ያለ ደመወዝ ከሥራ ማባረሩ፣ ‹‹ማን እንዲቀጥራቸው አስቦ ነው? እንዴትስ እንዲኖሩ ታስቦ ነው? ቤተሰቦቻቸውን እንዴት ሊያስተዳድሩ ነው?›› በማለት የሚጠይቀው መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበሩ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ወረርሽኙ ሊያመጣ የሚችለውን ማኅበራዊ ቀውስ ለመከላከል ሲል ያወጣውን የሥራ ፕሮቶኮል የሚፃረርና እጅግ በጣም ልብ የሚሰብር አካሄድ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ድርጊቱ ኢፍትሐዊና ከኢትዮጵያዊነት ፍፁም ያፈነገጠ ተግባር በመሆኑ የሚመለከተው አካልና መንግሥት ሁኔታውን ተመልክቶ የተወሰደውን ዕርምጃ በማስተካከል፣ ሠራተኞች በደመወዝ በዕረፍት ላይ እንዲቆዩ ወይም በሥራቸው ላይ እንዲገኙ እንዲደረግ ማኅበሩ ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አላግባብ ከሥራቸው ያለ ደመወዝ ተሰናብተዋል ስለተባሉ ሠራተኞቹ ማብራሪያ እንዲሰጥ ሪፖርተር አነጋግሮታል፡፡ አየር መንገዱ በሰጠው ምላሽ ሥራ በቀዘቀዘበት ወቅት ሠራተኞች የዓመት ዕረፍታቸውን እንዲወስዱ ማድረግ፣ የትኛውንም የአገሪቱን የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ የሚፃረር አለመሆኑን አስረድቷል፡፡
ምንም እንኳን በአየር መንገዱ የሚታወቀውና ቀዳማዊ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር አብዛኛውን ሠራተኛ ያቀፈ ማኅበር እንደሆነ የጠቆመው አየር መንገዱ፣ ከማኅበሩ ጋር በጋራ አብሮ እየሠራ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ከቤቱ እንዳይወጣ ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባስከተለው የኢኮኖሚ ቀውስ ብዙ አየር መንገዶች በኪሳራ ውስጥ ስለሆኑ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸውን ከሥራ እያሰናበቱ መሆናቸውን ኤምሬትስ አየር መንገድን በምሳሌነት በመጥቀስ፣ አየር መንገዱ አንድም ቋሚ ሠራተኛ አለመቀነሱን ገልጿል፡፡
ቋሚ ሠራተኞቹን ከእነ ደመወዛቸው የተጠራቀመ የዓመት ዕረፍታቸውን እንዲወስዱ ማድረጉን፣ ይህንንም ያደረገው በርካታ ሠራተኞች ስላሉት ማኅበራዊ ርቀትን (Social Distancing) ለመጠበቅና ለመጠንቀቅ መሆኑን ገልጿል፡፡
በሠራተኛ አቅራቢ (Out Sourcing) ድርጅቶች አማካይነት ተቀጥረው በጊዜያዊነት ሲሠሩ የነበሩ ሠራተኞቹን ግን፣ ለጊዜው በቤታቸው እንዲቆዩ ማድረጉንም አስረድቷል፡፡ በተለያዩ ድረ ገጾች የሚነገረው መረጃና ስለውጭ አገር ሠራተኞች የሚቀርበው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን አየር መንገዱ ገልጿል፡፡
አየር መንገዱ ሙሉ በሙሉ በረራ በሚጀምርበት ጊዜ ኢትዮጵያውያኑም ሆነ የውጭ አገር ሠራተኞችን ስለሚፈልጋቸው የዓመት ዕረፍታቸውን ብቻ እንዲጠቀሙ ማድረጉን በመግለጽ፣ የአየር መንገዱ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ያነሳውን ተቃውሞ አስተባብሏል፡፡ ሁሉም ሠራተኞች የሥራው አስፈላጊነት እየታየ ዕረፍት እንዲወጡ እንደሚደረግና እየተደረገ መሆኑንም አክሏል፡፡