Monday, April 15, 2024

ከዘጠኙ ክልሎች አራቱ ብቻ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በኢትዮጵያ በፊትም በአንፃራዊነት የተሻለ የጤና አገልግሎት ደረጃ ያላቸው አራቱ ክልሎች ብቻ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ዝግጁ እንደሆኑ፣ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ ያደረገው ግሞገማ አመለከተ።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተቀመጠው ዓለም አቀፍ መመዘኛ መሥፈርቶች መሠረት ከተመዘኑት ዘጠኙ የክልል መንግሥታት መካከል አራቱ ዝቅተኛውን የዝግጅት ደረጃ እንዳሟሉ፣ የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ መገምገሙን ሪፖርተር ያገኘው የሰነድ መረጃ አመልክቷል።

ቢሮው የግምገማውን ውጤት የያዘ ሪፖርት ለባለድርሻ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት፣ በተጠናቀቀው እ.ኤ.አ. ማርች ወር ላይ ማቅረቡን መረጃው ያመለክታል። አገሮች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ የዓለም ጤና ድርጅት ዘጠኝ መሠረታዊ መሥፈርቶችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ በእነዚህ መመዘኛ መሥፈርቶች ድምር ውጤት መሠረት ከ80 በመቶ በላይ ያመጡ ዝግጁ ተብለው እንደሚቆጠሩ ከመረጃው ለመረዳት ተችሏል።

በእነዚህ መመዘኛ መሥፈርቶች ተገምግመው ከ80 በመቶ በላይ ያመጡት ክልሎች ኦሮሚያ፣ አማራ፤ ደቡብና የትግራይ ክልሎች መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል። በዚህም መሠረት ኦሮሚያ 82.7 በመቶ፣ አማራ 80.9 በመቶ፣ ደቡብ 94.5 በመቶና ትግራይ 85.5 በመቶ በማግኘት ወረርሽኙን ለመከላከል ዝግጁ እንደሆኑ ሪፖርት ማድረጋቸውን መረጃው ያመለክታል።

የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ቢሮ የክልል መንግሥታቱ የሚገኙበትን የዝግጅት ደረጃ የገመገመው የክልሎቹ ተቋማት ለእያንዳንዱ የመመዘኛ መሥፈርቶች የሰጡትን ምላሽ መሠረት በማድረግ እንጂ፣ በራሱ ሄዶ በማጣራት ያደረገው  እንዳልሆነ በሰነዱ ተመልክቷል፡፡

ጥቅም ላይ በዋሉት ዘጠኙ መመዘኛ መሥፈርቶች የቫይረሱ ሥርጭትን መከላከልና መቆጣጠር፣ ቅኝት የማድረግ አቅም (ሰርቪላንስ)፣ ለቫይረሱ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመ ቡድን ማዘጋጀት፣ የቫይረሱ ሥርጭት ሥጋትን የማሳወቅ አቅም፣ የቫይረሱ መግቢያ በሮች ላይ የሚደረግ የጥንቃቄ ዝግጅት፣ የመመርመር አቅም፣ የሎጂስቲክስ ዝግጅትና ኬዝ ማኔጅመንት ወይም ለወረርሽኙ ምላሽ የሚሰጥበት የዝግጅት ደረጃ (ማለትም የሰው ኃይል አቅም፣ የመለያ ማዕከል፣ ሕክምና መስጫ ማዕከል)፣ እንዲሁም ተቀናጅቶ የመሥራት ዝግጅት ናቸው።

በእነዚህ መመዘኛዎች ተገምግመው ከ80 በመቶ በላይ አጠቃላይ ውጤት ካመጡት አራት ክልሎች ውጪ፣ የተቀሩት ክልሎች በተለያዩ የዝግጅት ደረጃዎች ላይ መሆናቸውን መረጃው ያመለክታል። በመመዘኛ መሥፈርቱ የዝግጅት ደረጃ አሰጣጥ መሠረት የአጠቃላይ መሥፈርቶቹ ድምር ውጤት ከዜሮ እስከ 49 በመቶ ከሆነ ዝግጁ እንዳልሆኑ የሚቆጠር ሲሆን፣ ከ50 እስከ 79 በመቶ ያስመዘገቡት ደግሞ ውስን የዝግጅት ደረጃ ያላቸው ተብለው ይመደባሉ።

በዚህ መሠረት፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላና ሐረሪ (የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጨምሮ) ክልሎች ውስን የዝግጅት ደረጃ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ክልሎቹ በተገለጹበት ቅደም ተከተል መሠረት 78.2 በመቶ፣ 59.1 በመቶ፣ 51.8 በመቶና 62.7 በመቶ ደረጃ እንደተሰጣቸው መረጃው ያመለክታል።

ከሁሉም በታች በዝቅተኛ የዝግጅት ደረጃ ላይ የሚገኘው የሶማሌ ክልል ሲሆን፣ አጠቃላይ ውጤቱ 27.3 በመቶ በመሆኑ ዝግጁ ያልሆነ ደረጃ ተሰጥቶታል። የምዘና ሪፖርቱ የሶማሌ ክልልና ሌሎቹ በውስን ዝግጅት ደረጃ ላይ የሚገኙ ክልሎች ፈጣን ምላሽ፣ እንዲሁም ዕገዛ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ያሳስባል።

 ነገር ግን ሁሉም ክልሎች የተለያየ የዝግጅት ደረጃ ላይ ይገኙ እንጂ፣ ሁሉም ክልሎች በተናጥል መሥፈርቶቹ ሲመዘኑ በቂ ዝግጅት ላይ አለመሆናቸውን ሰነዱ ይገልጻል። በተለይም ከዘጠኙ መሥፈርቶች ውስጥ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደ ዋነኛ መመዘኛ ከሚያገለግሉት መካከል ኬዝ ማኔጅመንት፣ የቫይረሱ ሥርጭትን መከላከልና መቆጣጠር (IPC)፣ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ቡድን ማቋቋምን ከሚመለከቱት መሥፈርቶች አንፃር ሁሉም ክልሎች በዝቅተኛ የዝግጅት ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው፣ ፈጣን ማስተካከያ ካልተደረገ አሳሳቢ መሆኑ በሰነዱ ተመልክቷል።

የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ሆነው የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት የተመለከተ ግምገማ የተለያዩ የቢሆን መመዘኛዎችን (Scenarios) በመጠቀም፣ ግርድፍ የጉዳት መጠኖችን እንደለዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከእነዚህ ቢሆኖች አንዱ የከፋ ጉዳት ቢሆን (Worst Case Scenario) መመዘኛ ሲሆን፣ ይህም ማለት ምንም ዓይነት የተለየ ዝግጅት ባልተደረገበት፣ በነባሩ የጤና አገልግሎት ዝግጅትና የማኅበረሰብ እንቅስቃሴና የአኗኗር ዘይቤ ሳይቀየር የቫይረሱ ሥርጭት ምን ሊሆን እንደሚችል የተገመገመበት ነው።

በዚህ የሁለቱ ተቋማት ግምገማ መሠረት ለቫይረሱ የመጋለጥ ምጣኔ (ሥርጭት) በገጠርና በከተማ ተለይቶ የተቀመጠ ሲሆን፣ የሁለቱ ድምር በርካታ ሕዝብ ለቫይረሱ ተጋላጭ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

ተጋላጭ ማለት የተጠቀሰውን ያህል ሕዝብ በቫይረሱ ያጠቃል ማለት እንዳልሆነ ዳሰሳው ያመለክታል። ሁሉም የመንግሥት አካላት ፈጣንና ጠንካራ የመከላከልና የመቆጣጠር ዝግጅት ካደረገና ማኅበረሰቡም የሥጋት ደረጃውን ተገንዝቦ የጥንቃቄ ዕርምጃዎችን በአግባቡ የሚተገበር ከሆነ፣ የተጋላጭነት መጠኑም ሆነ በቫይረሱ ሊጠቃ የሚችለውን የሰዎች ብዛት መቀነስ እንደሚቻል በመረጃው ተብራርቷል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -