Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት ሥራቸውን እያጡ ያሉ ሰዎች ችግር ላይ እየወደቅን ነው አሉ

በኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት ሥራቸውን እያጡ ያሉ ሰዎች ችግር ላይ እየወደቅን ነው አሉ

ቀን:

በኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት ቀስ በቀስ እየተዘጉ ባሉ ሥራዎች ሳቢያ፣ በዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጉዳት እየደረሰበት መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሥራዎች የተሰማሩ ዜጎች፣ እንቅስቃሴዎች እየተቀዛቀዙ በመምጣታቸው ችግር ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወትሮ በሰዎች የሚሞሉ አነስተኛ ምግብ ቤቶች፣ ካፌዎችና የፔርሙዝ ሻይና ብስኩት የሚሸጡ ሰዎች የነዋሪዎች እንቅስቃሴዎች በጣም በመገደባቸው መቸገራቸውን እየተናገሩ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ አምስት መውጫና መግቢያ በሮች አንዱ ‹ሰሜን መውጫ› እየተባለ የሚጠራው ላም በረት አካባቢ ያለ መናኸሪያ ሲሆን፣ ከ63 እስከ 14 መቀመጫ ያላቸው የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ በቀን ከ200 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ይስተናገዱበት ነበር፡፡ ከመናኸሪያው አልፎ አካባቢው ከሌሊቱ አሥር ሰዓት ጀምሮ በሾፌሮች፣ በረዳቶች፣ በተራ አስከባሪዎች፣ በተሳፋሪዎች፣ በሸኝና ተቀባዮች፣ በአልጋ አከራዮች፣ በደላሎች፣ በምግብ አቅራቢዎች፣ በነጋዴዎችና በተለያዩ በርካታ ሰዎች እስከ ምሽት ሁለት ሰዓት የሚርመሰመሱበት አካባቢ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን፣ ሪፖርተር በሥፍራው ያነጋገራቸው ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ብዙዎችም በዚህ ምክንያት የዕለት ጉርሳቸውን ማጣታቸውን ያስረዳሉ፡፡

አካባቢው ፀጥ እረጭ ከማለቱም በላይ ክርችም ብለው ከተዘጉት ሦስቱም የመናኸሪያው መግቢያ በሮች ሥር በአንደኛው፣ በሁለት ቡድን ሰብሰብ ብለው እንደ ቤተሰብ የሚጫወቱ ሰዎች ይታያሉ፡፡ ታዳጊ ልጆችም ይዘዋል፡፡ የደሴ፣ የወልዲያና የሸዋ ሮቢት መንገደኞች መሆናቸውን ሻንጣዎቻቸውን እያሳዩ ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ዕድሜያቸው ወደ ሃምሳዎቹ የሚጠጋ ጎልማሳ የአንድ ቀን የሕክምና ቀጠሮአቸው ጨርሰው ለመመለስ ነበር በመናኸሪያው የተገኙት፡፡ መናኸሪያው ሲደርሱ ግን ተዘግቷል፡፡ ‹‹በኮሮና ምክንያት ላልታወቀ ጊዜ የትራንስፖርት አገልግሎት ቆሞ መናኸሪያው መዘጋቱን ነገሩኝ፡፡ እዚህ ምንም የማውቀው ዘመድም መጠጊያም  የለኝም፣ በቂ ገንዘብም የለኝም፡፡ ከገጠር ገንዘብ እስኪመጣልኝ ከመሰሎቼ ጋር ቀን ዳቦና ሻይ በመመገብ፣ ሲመሽም በአካባቢው የተሠሩት የሸራ ሱቆች በመጠለል እየዋልኩና እያደርኩ ነው፤›› ሲሉ በእንባ ታጅበው ችግራቸውን ተናግረዋል፡፡ አብረዋቸውም ያሉት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡና እንደማይተዋወቁ፣ የተፈጠረው ችግር ግን ለጊዜው ቤተሰብ እንዳደረጋቸው ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ከመናኸሪያው በስተጀርባ በፕላስቲክ የተሠሩ ሱቆች ያሉት ፍቅር የገበያ ማዕከል አለ፡፡ ከ140 በላይ በመደብ የተሠሩ የአልባሳት፣ የመጫሚያዎችና የጌጣ ጌጦች መሸጫ ሱቆች፣ እንዲሁም ምግብ ቤቶች አሉት፡፡ እንደ ቀድሞው ሻጮችና ገዥዎች የሚርመሰመሱባቸው አይደሉም፡፡ በተቃራኒው መደቦቹ ተገልብጠው በቀይና በሰማያዊ ፕላስቲኮች በተተበተበ ገመድ ጥፍንግ ተደርገው ታስረው ቁጭ ቁጭ ብለው ይታያሉ፡፡ ገሚሶችም ሙሉ በሙሉ ሸራ ለብሰው የኮሮና ቫይረስን መጨረሻ የሚጠብቁ ይመስላሉ፡፡ ባለቤቶቻቸውም ሥራ ፈት ሆነው ቁጭ ብለዋል፡፡ ቤት ከምንውል በማለት የመጡ ሁለት ግለሰቦች ካሁኑ ችግር እየፈተናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የኮሮና ወረርሽኝ ሥጋት በርካታ  ከሥራ ውጪ ያደረጋቸው ሾፌሮችና ረዳቶች ውር ውር ይላሉ፡፡ ሰብሰብ ሰብሰብ ብለው የሚታዩም አሉ፡፡ የመናኸሪያው ግቢ ወፍ ዝር አይልበትም፡፡ መናኸሪያውን ታከው ይሠሩ የነበሩ በመቶ የሚቆጠሩ በዕለት ገቢ የሚተዳደሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የት እንደሄዱና ምን እየሠሩ እንደሆነ ባይታወቅም፣ በቦታው አይታዩም፡፡ በአካባቢው ያሉትም ገቢ ማጣታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

በአዲስ አበባ በኮሮና ሥጋት ምክንያት ቀስ በቀስ በሚዘጉ ምግብ ቤቶች፣ ሱቆች፣ ካፊቴሪያዎችና በመሳሰሉት ከሥራ ውጪ እየሆኑ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጉዳቱ ከአሁኑ መታየት እንደ ጀመረ እየተናገሩ ነው፡፡ በተለይ ከዕለት ገቢ ውጪ ምንም የሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ችግሩ እየባሰ መሆኑን፣ በብዙ ሥፍራዎች ማየት ተችሏል፡፡

ገርጂ መብራት ኃይል የካቲት ወረቀት ፋብሪካ ጀርባ ካሉት ከ40 በላይ የኮንቴይነር ምግብ ቤቶች ውስጥ አንዱን ተከራይታ የምትሠራው ወጣት፣ ‹‹በዚህ አካባቢ በቀን ከሦስት ሺሕ በላይ በቀን ሥራ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ቁርስ፣ ምሳና ራት ይመገባሉ፤›› በማለት ገልጻ፣ በችግሩ ምክንያት ሰዎች ገቢ በማጣታቸው እሷን ጨምሮ በርካቶች እየተጎዱ መሆናቸውን ተናግራለች፡፡ አብረዋት የሚሠሩት ጭምር ከሥራ ውጪ መሆናቸውን ገርበብ አድርጋ ከከፈተው በሯ ላይ ሆና ገልጻለች፡፡

ሌላው ከፍተኛ የሥራ ቁጥር የሚይዘው የአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት ወረርሽኙ በፈጠረው ሥጋት፣ ከቀን ወደ ቀን ሥራው እየቀዘቀዘና ረዳቶችም እየተቀነሱ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደበፊቱ ብዙ ተሳፋሪዎች ስለሌሉ ሾፌሮች የረዳቶችን ሥራ ደርበው እየሠሩ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ከኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ከተለያዩ የንግድ ድርጅቶችና ማምረቻዎች በርካታ ሰዎች በብዛት ከሥራ እየተቀነሱ በመሆናቸው ችግር እየገጠማቸው መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...