ዓለም አቀፍ የስፖርት ማኅበራት በጊዜ ሒደት ስያሜዎቻቸውን ከወቅቱና ከጊዜው ጋር ተጣጥመው እንዲሄድ ማሻሻያ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ፡፡ ለዚህ በቀድሞ ስያሜው የሚታወቀው የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) በማሳያነት መመልከቱ በቂ ይሆናል፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመናት በላይ ‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ብሔራዊ ተቋም አሁን ላይ የዓለም አቀፉ ተቋም እያሻሻለው ካለው ስያሜ በመነሳት መጠሪያውን ማሻሻል እንዴት እንዳልቻለ የሚጠይቁ አልጠፉም፡፡ ለወትሮ ‹‹የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር›› በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ተቋም አዲሱ መጠሪያ ‹‹የዓለም አትሌቲክስ›› (World Athletics) ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ከአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለዓመታት የዘለቀ ስያሜውን ዓለም አቀፉን ተቋም ተከትሎ “የኢትዮጵያ አትሌቲክስ” ይለው ይሆን?