በአበጀ ብርሃኑ (ዶ/ር)
በዚህ አጭር መጻሕፍት ውስጥ በህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ አንዳንድ ነገሮችን ለማለት አሰብኩ፡፡ በመጀመርያ ግን ስለርዕሱ ትንሽ የምለው አለኝ፡፡ የእንግሊዝኛው አባባል ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን የድርድር ሁኔታ በተሻለ ይገልጸው ይሆናል በሚል የተቀመጠ እንጂ የአማርኛ ትርጉሙ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለዲፕሎማሲ አዲስ አይደለችም፤›› ብዬ አምናለሁ፡፡
ወደተነሳሁበት ሐሳብ ስመጣ አንድ ቁምነገር ላንሳ፡፡ ሁሉም የዓለም መንግሥታት የሚተዳደሩበት ሰው ሠራሽ ሕግ እ.ኤ.አ. በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀደቀው ነው፡፡ ይህም ሕግ የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ በሚል የሚታወቅ ሲሆን፣ አባል አገሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ተቀብለውና በሕገ መንግሥታቸው አካተው፣ ለሕዝባቸውና ለዜጎቻቸው መተዳደሪያ ካደረጉት ይኼው ከሰባ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ የዚህ ሕግ ዋና መነሻ ሰዎች በተፈጥሮ ያላቸው መብቶች ማለትም ሐሳብን በነፃ የመግለጽ፣ እምነታቸውን በነፃ የማራመድ፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር፣ ለኑሯቸው የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች የማግኘት ወዘተ. መብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ናቸው ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ መሠረት የሆኑት፡፡
ከዚህ ስንነሳ አገሮችም እንደ ግለሰብ ለተፈጥሮ ሕግ የመገዛት ግዴታም ሆነ መብት ይኖራቸዋል፡፡ አንድ አገር ሉዓላዊ ናት ሲባል በግዛቷ ውስጥ ያለውንና ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ማንኛውንም ሀብት ተጠቅማ፣ የዜጎቿን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ይጠበቅባታል፡፡ ይህም ሲባል ምድሪቱንና አፈሩን አቅፈውና ደግፈው የያዙትን ወንዞችና ማዕድናት የመጠቀም ኃላፊነትና ግዴታ ያካትታል፡፡ በተፈጥሮ ያገኙትን ሀብት አለመጠቀም የዋህነት ወይም ጅልነት ሊባል ይችላል፡፡ ዓባይ የሚገኘው በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ነው፡፡ ይህን የተፈጥሮ ሀብት ዜጎችን በሚጠቅም ሁኔታ መጠቀም የተፈጥሮ ሕግ ያስገድዳል፡፡ ይልቁንም አለመጠቀም የተፈጥሮን ሕግ መፃረር ነው፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ጫና እየተደረገባት ያለው በተፈጥሮ ያገኘችውን መብት ለመጠቀም ስምምነት ውስጥ ግቢ የሚል ነው፡፡ ሲጀመር አንድ አገር ስምምነት ውስጥ የምትገባው የራሷን ጥቅም ለማስከበር እንጂ፣ ለሌላ ተደራዳሪ ወገን አሳልፎ ለመስጠት ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ መርህ ለኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ይሰወራል ብሎ ማሰብ፣ በግብፆች በኩል ዓይን ያወጣ ብልጣ ብልጥነታቸውን ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከግብፅ ጋር ስምምነት እንድትገባ የሚወተውቱ አደራዳሪዎች ስምምነቱ ለኢትዮጵያ ምን ጥቅም ያስገኝላታል የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለባቸው፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎችና በኢትዮጵያ ተደራዳሪ ባለሥልጣናት ገለጻ መሠረት፣ በአሜሪካ አደራዳሪነት (ሞጋችነት ብንለው ይሻላል) የተረቀቀው ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ የተለያዩ (Obligations) ሲጥል፣ ለግብፅ ግን ይህ ነው የሚባል ኃላፊነት አይሰጥም፡፡ የግብፅ ኃላፊነት ስምምነቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚጥለውን ግዴታ በአግባቡ መወጣቷን ከመከታተልና ከመቆጣጠር ያለፈ አይደለም፡፡
ልብ በሉ በአንድ ስምምነት ውስጥ ለሚገባ ተደራዳሪ ይህ ነው የሚባል ግዴታ ካልተጣለበት፣ እንዴት ነው ስምምነቱ ፍትሐዊ ነው ሊባልና ሊፀና የሚችለው? የዲፕሎማሲ መርሆችም የሚያስተምሩን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተገቢና ተግባራዊ የሚሆኑት፣ በሁሉም ተደራዳሪ ወገኖች ላይ ተመጣጣኝ የሆነ (Obligations) ግዴታ ሲጥሉ ነው፡፡ ለአንዱ ወገን ግዴታን ጥሎ ለሌላው ወገን መብት (ያውም ተፈጥሮ የማይደግፈው) ብቻ አደላድሎ መስጠት አድልኦነት በግልጽ የሚታይበት፣ ግዴታ የገባውን ወገን ሆን ብሎ ለመጉዳት የሚደረግ አካሄድ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ለዲፕሎማሲ አዲስ አይደለችም፡፡ ስለዚህ የራሷን ጥቅም የማያስከብር ስምምነት ልትዋዋል ቀርቶ ልታስበው አይቻላትም፡፡ በግልጽ እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ከግብፅ ጋር ውል መግባት ላያስፈልጋት ይችላል፡፡
ልብ በሉ በግዛቷ ውስጥ የሚመነጨውንና የሚፈሰውን ወንዝ ለልማት ለመጠቀም፣ እንዴት ነው ለሌላ አገር ያውም ጎረቤት ካልሆነ ጋር ስምምነት ውስጥ የመግባት ግዴታ ያለባት? ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሰቻት ዓባይን የመጠቀም መብት አላት፡፡ ይህንን መብት ለሌላ ወገን አሳልፋ መስጠት የለባትም፡፡ ግድ የለም ኢትዮጵያ ለሰላምና ለአኅጉሩ መረጋጋት ካላት ፅኑ ፍላጎት አንፃር ጥቅሟን በማይጎዳ ሁኔታ ስምምነት ትግባ ከተባለ፣ ስምምነቱ በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ነጥቦችን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ የመጀመርያው ነጥብ ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ በፍትሐዊነት ለመጠቀም ፍላጎት አላት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡
ይህም ለግብፅ ሲባል ካልሆነ በስተቀር ለኢትዮጵያ የሚያስገኘው ጥቅም እምብዛም ነው፡፡ ኢትዮጵያ የተለያዩ እምነቶች ተከታይ ሕዝቦች ስብስብ በመሆኗ፣ እነዚህ ሕዝቦች በሌላው ሕዝብ ላይ ሆን ብለው ጉዳት እንዲደርስ ስለማይሹና ኢትዮጵያ የሕዝቦችን እምነቶች አክባሪ አገር ስለሆነች፣ አሁንም ሆነ ወደ ፊት ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ በምታከናውናቸው ልማቶች ሆን ብላ የግብፅን ሕዝብ የሚጎዳ ሥራ አትሠራም፡፡
ልብ በሉ ይህም ውል ቢሆን የሚጠቅመው ግብፅን እንጂ፣ ለኢትዮጵያ ቅንጣት የምላጭ ስባሪ የሚያህል ጥቅም አያስገኝም፡፡ ይሁን እንጂ ለአፍሪካዊ ወንድሞቻችን ለግብፅ ሕዝብ መልካም በማሰብ ኢትዮጵያ የምትከፍለው መስዋዕትነት ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ግን የኢትዮጵያን ጥቅም እስካልጎዳ ድረስ መሆን አለበት፡፡
በግብፅ በኩል ቢያንስ ሦስት ሐሳቦችን የያዙ ኃላፊነቶን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይገባል፡፡ አንደኛ ግብፅ የዓባይ ወንዝ ዘላቂ ተጠቃሚ የምትሆነው የተፋሰስ እንክብካቤ በቋሚነት ሲሠራ መሆኑን ተገንዝባ፣ ኢትዮጵያ ለተፋሰሱ እንክብካቤ ለምታደርገው ሥራ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ስታደርግ መሆኑን በፅኑ መረዳት፡፡ ሁለተኛ የዓባይን ወንዝ በፍትሐዊነት ለመጠቀም መስማማት፡፡ ሦስተኛ መታሰብ ያለበት ግብፅ ወደ ግዛቷ የገባውን ውኃ በአግባቡና ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ ለመጠቀም ቁርጠኝነት ማሳየት አለባት፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያና የግብፅ ድርድር መቀጠል ካለበት ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ያላት ተፈጥሮን መሠረት ያደረገ የመጠቀም መብቷ በግልጽ ቋንቋ መታወቅ አለበት፡፡ ይህም በታሪክ ከተገኘው መብት እንደሚቀድም በግልጽ መታወቅ አለበት፡፡
በተጨማሪም ግብፅ ለዓባይ ወንዝ እንክብካቤ አስተዋጽኦ ለማድረግ መስማማትና የውሉ አካል ተደርጎ መግባት ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያን ብቻ ግዴታ ውስጥ ያስገባና ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ኪሳራ ዓባይን የመጠቀም መብት የሚሰጥ ውል፣ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ቦታ የለውም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘጠኝ ዓመታት ሙሉ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሲገነባ የከረመው ተጨማሪ ሃያ ዓመት ፈጅቶ ግድቡን ውኃ በመሙላት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አመንጭቼ ተጠቃሚ እሆናለሁ በሚል ዕሳቤ አይደለም፡፡ ከጨለማ የሚያወጣው አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ እሱም ግድቡን ቶሎ መሙላትና ኃይል ማመንጨት ነው እንጂ፣ ተጨማሪ ሃያ ዓመታት መጠበቅ አይደለም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡