Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉማኅበራዊ ርቀት ወይስ አካላዊ ርቀት?

ማኅበራዊ ርቀት ወይስ አካላዊ ርቀት?

ቀን:

በሰሎሞን ማርቆስ (ዶ/ር)

የኮሮና ቫይረስ በቅርቡ በዓለማችንና በአገራችን ከተከሰተ ወዲህ፣ የቫይረሱን ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ለመቀነስ አካላዊ ንክኪን ማስቀረት እንደ ዋነኛ መፍትሔ ተቀምጧል። ይሁንና ይህንኑ መልዕክት ለሰዎች ለማስተላለፍ የተለያዩ ቃላትን ማለትም ማኅበራዊ ርቀት፣ አካላዊ ርቀት፣ ማኅበራዊ ፈቀቅታ፣ አካላዊ ፈቀቅታ፣ ማኅበራዊ ጥግግት፣ አካላዊ ጥግግት የሚሉ ቃላትን በተለዋዋጭነት ስንጠቀም ይስተዋላል። የምንጠቀመው ቃል ወጥነት የሌለው መሆኑ ሕዝብን ግራ ሊያጋባና ለተለያዩ ትርጉሞች ተጋላጭ ሊያደርግ ከመቻሉ የተነሳ፣ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራን ውጤታማ እንዳይሆን ሊያደርግ ይችላል።

አንዳንዱ ይህንን ጉዳይ እንደ ቀላልና ተራ የቃላት ስንጠቃ አድርጎ ይመለከታል። ይሁን እንጂ የቃልና ትርጉም ወጥነት በጣም አስፈላጊ ነው። በማኅበራዊ ግንኙነት ተሳስሮ የሚኖር ማኅበረሰብን የማኅበራዊ ርቀት እንዲጠብቅ ከመጠየቅ፣ አካላዊ ርቀት እንዲጠብቅ መጠየቁ የተሻለ ቅቡልነት ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ። ማኅበራዊ ርቀት የሚለው በተለይም ባደጉ አገሮች የተለመደ ቃል ቢሆንም፣ ኮቪድ 19 ወይም ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ ሰዎች ‹‹ማኅበራዊ ርቀትን ጠብቁ›› ሲባሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ ቃሉ ብዙም አዲስ ባልሆነባቸው በአደጉት አገሮችም ጭምር በቀላሉ ሊቀበሉት አልቻሉም።

- Advertisement -

ጋዜጠኛ ላውራ ማርች እ.ኤ.አ. 23 ቀን 2020 ለግሎባል ኒውስ እንደ ዘገበችው፣ ካናዳ ውስጥ ፖለቲከኞችና የጤና ባለሙያዎች ዜጎች ማኅበራዊ ርቀትን እንዲጠብቁና ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ደጋግመው ቢያሳስቡም ሕዝቡ ሊሰማ አልቻለም፡፡ እንግዲህ ይህ እየሆነ ያለው ከእኛ አገር በንፅፅር ግላዊነት ባየለበት ባህል  (Individualistic Culture) ባለው ካናዳ ውስጥ ነው፡፡ አብሮና ተባብሮ የመኖር ባህል (Collectivist Culture) ባለው በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ‹‹ማኅበራዊ ርቀት ጠብቁ›› የሚለው መልዕክት ተቀባይነቱ አናሳ ሊሆን ይችላል። ጋዜጠኛ ላውራ እንደምትለው ከሆነ ለብዙዎቹ ካናዳዊያንማኅበራዊ ርቀትየሚለው ቃል አዲስ ባይሆንም፣አካላዊ ርቀትየሚለው ቃል የተሻለ ተቀባይነት እያገኘና እየተዘወተረ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም አካላዊ ርቀት የሚለው ቃል ሕዝቡ በቀላሉ ሊረዳው የሚችለው እንደሆነ ታምኖበታል፡፡

የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የተላላፊ በሽታዎች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆነው ዶ/ር ጄፍዎንግ እንደሚለው ስለማኅበራዊ ርቀት አስፈላጊነት ሲነገር፣ አብዛኛው ሕዝብ የቃሉን ትክክለኛ ትርጉም ባለመረዳት ቃሉን ከማኅበራዊ ሕይወት እንደ መገለል አድርጎ ወስዶታል፡፡ ስለዚህም አካላዊ ርቀት የሚለውን ቃል መጠቀም የተሻለ አማራጭ ነው ይላል፡፡ ምክንያቱም አሁን በዚህ አስቸጋሪ የኮቪድ 19 በሽታ ወረርሽኝ ወቅት የሚያስፈልገን በአካል በመጠኑ መራራቅ፣ ነገር ግን በማኅበራዊ ሕይወት መተጋገዝና በተለይም የተለያዩ ዘመናዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በማኅበራዊ ኑሮ ተሳስሮ ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፍ ነው፡፡

/ር ሚለር በጣም ተነባቢ በሆነው ሳይኮሎጂ ቱዴይ መጽሔት ላይ እ.ኤ.አ. ማርች 18 ቀን 2020 እንዳሰፈሩት፣ ‹‹እስቲ ከማኅበራዊ ርቀት ይልቅ ወደ አካላዊ ርቀት እናትኩር፡፡ አካላዊ ርቀትን እየጠበቅን ማኅበራዊ ትስስራችንን መቀጠል እየተቻለ፣ ሰዎች ለምን ማኅበራዊ ርቀትን እንዲጠብቁ እየነገርናቸው ተያይዞ ለሚመጣው አላስፈላጊ ጭንቀት፣ ድባቴና ብቸኝነት እናጋልጣቸዋለን?›› በማለት ይከራከራሉ፡፡ በእርግጥ አካላዊ ርቀት የተወሰነ ማኅበራዊ ርቀት መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ቢሆንምአካላዊ ርቀትየሚለውን ቃል መጠቀም የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልገን ማኅበራዊ ርቀት ሳይሆን አካላዊ ርቀት ነው፡፡

አንድን ችግር ለመፍታት የምናመጣው መፍትሔ ሌላ ችግር ማስከተል የለበትም፡፡ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ማኅበራዊ ርቀት የሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጤና ችግር ሊያስከትል ስለሚችል፣ አንዳንድ የሥነ ልቦናና የማኅበረሰብ ሳይንስ ባለሙያዎች ማኅበራዊ ርቀት በሚለው ቃልም ትክክላዊ ርቀት የሚለውን ቃል እንድንጠቀም ይመክራሉ፡፡ አካላዊ ርቀትን ጠብቀን ማኅበራዊ ትስስራችንን ሳናጣ በሥነ ልቦናም ሆነ በአካላዊ ጤንነት መኖር እንችላለን፡፡ በተቻለ መጠን አላስፈላጊ አካላዊ ቅርርብን መገደብ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን መግቻ ዋናው መሣሪያ ነው፡፡

አካላዊ ርቀት መጠበቅ እነዚህን ዕርምጃዎች ያካትታል

ለአስፈላጊ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ከቤት አለመውጣት፣ አለመጨባበጥ፣ አለመሳሳም፣ አለመተቃቀፍ፣ አካላዊ ንክኪን መተው፣ ሰዎች በብዛት ከሚሰበሰቡበት ቦታ መራቅና ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት ከፈለግን ቢያንስ የሁለት ሜትር ርቀት በመካከላችን መኖሩን ማረጋገጥ፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሚመከረው በተለይም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከሰዎች ጋር በስልክ፣ በኢሜይል፣ በቪዲዮ ቻትና በማኅበራዊ ትስስር ሚዲያዎች ከሰዎች ጋር መገናኘቱ ነው፡፡ እነዚህን ምክሮች ስንተገብር አካላዊ ርቀትን እየጠበቅን ማኅበራዊ ትስስራችንን ማጠናከር እንችላለን፡፡ ይህንን ቫይረስ ከተቆጣጠርነው በኋላ ወደ ተለመደው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንመለሳለን፡፡

በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት የዓለም ጤና ድርጅትማኅበራዊ ርቀትከሚለው ቃል ይልቅ፣የአካል ርቀትየሚለውን ቃል እንድንጠቀም ያበረታታል፡፡ እ.ኤ.አ. ማርች 23 ቀን 2020 የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አዳኖም (ዶ/ር) የአካላዊ ርቀትን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እሳቸው እንዳሳሰቡት ሰዎች ቤታቸው እንዲቆዩና አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቁ ማድረግ የቫይረሱን በፍጥነት የመተላለፍ ዕድል ይቀንሳል፡፡

አካላዊ ርቀትን እየጠበቅን ማኅበራዊ ትስስራችንን እንዴት እንፍጠር?

1. መረጃ መቀባበል እውነተኛ መረጃ ከትክክለኛው ምንጭ ማግኘትና ለሌሎች ማሳወቅ፣

2. ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን በቤተሰብም ሆነ በጎረቤት አካባቢ ካሉ ማገዝ፣

3. በተቻለ መጠን ከቤተሰብ፣ ከቅርብ ጓደኞችና ከሥራ ባልደረቦች ጋር በስልክ፣ በኢሜይል፣ ወይም በማኅበራዊ ትስስር ሚዲያዎች መገናኘት፣

4. ከመጠን በላይ በመፍራት ከሚያስፈልገን መጠን በላይ መድኃኒት፣ የምግብ ግብዓቶችን ሌሎች ዕቃዎችን አለመግዛትና አለማከማቸት ምክንያቱም እነዚህን አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎችን ከመጠን በላይ ማከማችት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡

አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚኖሩባቸው አካባቢዎች አካላዊ ርቀትን እንኳን መጠበቅ የማያስችሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የስደተኞች መቆያዎች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች የኑሮ ሁኔታ፣ ወላጅ ያጡ ሕፃናት መኖሪያዎች፣ እንዲሁም አረጋዊያንና የአዕምሮ ሕመምተኞች የሚኖሩባቸው ሥፍራዎች አካላዊ ርቀት እንኳን ለመጠበቅ የማይመቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ለኮሮና ቫይረስ እጅግ ተጋላጭ ናቸው፡፡ ሌሎቻችን ከዚህ በመጠኑም በተሻለ የኑሮ ደረጃ የምንገኝ የማኅበረሰብ ክፍሎች የጤና ባለሙያዎች የሚነግሩንን ሰምተንና አካላዊ ርቀት ጠብቀን፣ ከኮሮና ቫይረስ ራሳችንን ተከላክለን በጤንነት መኖር እንችላለን፡፡

በመጨረሻም በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ማኅበራዊ ትስስር ከፍ ያለ በመሆኑ መጨባበጥን፣ መሳሳምን፣ መተቃቀፍን ለጊዜው ገታ አድርገን በመካከላችን የሁለት ሜትር ያህል አካላዊ ርቀት እየጠበቅን፣ እኛንም ሆነ ሌሎችን ከኮሮና ቫይረስ እየተከላከልን ማኅበራዊ ግንኙነታችንን መቀጠል እንችላለን፡፡ ጽሑፌን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የተከበሩ አቶ ታከለ ኡማ እ.ኤ.አ. ማርች 21 ቀን 2020 በፌስቡክ ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ላጠቃልል (በዚህ አጭር መልዕክት ከላይ ያሰፈርኩት አብዛኛው ሐሳብ በሚገባ የተገለጸ ይመስላል)፡፡ ‹‹በሐሳብ፣ በመንፈስና በፀሎት አንድ ላይ ሆነን፣ በአካል ደግሞ ተገቢውን ርቀት ጠብቀን ይህንን ወቅት በአሸናፊነት እንወጣዋለን።››

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...