በዓለም በየደቂቃው ስሙ እየተነሳ ያለ ቃል ቢኖር ‹‹ኮሮና ቫይረስ›› ነው፡፡ በዚህ ወቅት በዚህ ርዕስ ከሚነገር ወሬ ሌላ በዓለም ቀድሞ የሚነሳ አጀንዳ አለ ተብሎ አይታሰብም፡፡ ዓለማችን ከገጠሟት ክፉ ወቅቶች አንዱ ይኸው የከፋ ወረሽኝንና እያስከተለ ያለው ጥፋት ነውና አገሮች በዚሁ ጉዳይ ተጠምደዋል፡፡ ወረርሽኙን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ ዕርምጃዎችን ሁሉ እየወሰዱ ነው፡፡ የደነደነ ኢኮኖሚ ያላቸውን አገሮች ጭምር ያብብረከረከው ይህ ወረርሽኝ፣ ኢትዮጵያ ውስጥም መግባቱ በተገለጸ ወር ባልሞላ ጊዜ 35 በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ ይህ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊጨምር ይችላል የሚለው እምነት ብዙዎች የሚስማሙበት ነው፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስን መከላከል ቁጥር አንድ አጀንዳ ሆኗል፡፡ በዚሁ ዕሳቤ ወረርሽኙን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ እንቅስቃሴዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ተጀምረዋል፡፡ ችግሩን ለመቀነስ ይረዳሉ የተባሉ ውሳኔዎችም እየተላለፉ ነው፡፡ የከፋ ነገር ቢገጥም ተብሎ የለይቶ ማቆያና ማከሚያ ጣቢያዎች እየተዘጋጁም ነው፡፡ በጡረታ ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎችና የሕክምና ተማሪዎች ሳይቀሩ ሊደረግላቸው ለሚችል አገራዊ ጥሪ ተዘጋጁ ተብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡም እያደረገ ያለው ድጋፍ በተለያዩ ዓይነቶች እየታየ ነው፡፡ በዋናነት ግን ዜጎች ራሳቸውን እንዲጠብቁና ርቀትን ጠብቀው እንዲንቀሳቀሱ እየተወተወተ ነው፡፡ እንዲህ ያሉና ሌሎች ቫይረሱን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ ዕርምጃዎች በተግባር እየታዩ ያሉ ጥረቶች ግን፣ ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት እንደሚታሰበው ይቀንሱታል ብሎ ለመተንበይ ያስቸግራል የሚል አመለካት ያላቸው ወገኖች ግን አሉ፡፡ እስካሁን ባለው ውሳኔ ዜጎች በቤት እንዲቀመጡ የተላለፈው ውሳኔ በሚገባ እየተተገበረ ባለመሆኑ አደጋ ይኖረዋል በማለት፣ ሐሳባቸውን የሚሰነዝሩና የተሻለ ነው ብለው የራሳቸውን ምክረ ሐሳብ እስከማቅረብ እየደረሱ ነው፡፡ እንዲህ ያለ አመለካከት ካላቸው ዜጎች መካከል የቢዝነስ ባለሙያው ካሳሁን አበሩ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ አሁን ከሁሉም በላይ መተግበር ያለበት በአስገዳጅነት ዜጎች ለ15 ቀናት ከቤት እንዳይወጡ ማድረግ ነው የሚል የጠነከረ አመለካከት አላቸው፡፡ ሌሎች አገሮች ይህንን በመተግበራቸው ውጤት ስላገኙበት ከዚህ የተሻለ መፍትሔ አይኖርም የሚለውን ሐሳብ ከሌሎች ነገሮች ሁሉ ያስቀድማሉ፡፡ መንግሥት ይህንን ለማስፈጸም የተቸገረበት ምክንያት ሊኖረው ቢችልም፣ ኢትዮጵያ ለ15 ቀናት ከቤት መቀመጥን አስገዳጅ አድርጋ መተግበር አለባት ይላሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ እንዴት ይቻላል የሚለው ጥያቄም ሊያሳስብ ቢችልም፣ ለዚህ መፍትሔ መፈለግ እንጂ ፈርቶ መቀመጥ እንደማያዋጣም ካሳሁን (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ስለዚህ በዋናነት የሚነሳው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የዕለት ጉርሱን የሚያገኘው በዕለት ሥራው በመሆኑ፣ እንዴት 15 ቀናት ተቀመጥ ይባላል ለሚለው መፍትሔ ይሆናል ያሉት ሐሳብ አላቸው፡፡ ይህም ያለው የሌለውን ለመመገብ የሚያስችል ሥርዓት በአስቸኳይ መፍጠር ነው፡፡ የትራንስፖርት ዘርፍ ኢኮኖሚስት ሲሆኑ፣ ከሁለት ሸሪኮቻቸው ጋርም አካካስ የተባለ የሎጂስቲክስ ኩባንያ በማቋቋም የሎጂስቲክስ ዘርፉን በሥራ አስኪያጅነት ይመራሉ፡፡ በሥጋ ማቀነባበር ሥራ የተሰማራ ፕራይም ሚት የተባለ የአግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ባለቤት ናቸው፡፡ ካሳሁን (ዶ/ር) ሊተገበር ይገባል ባሉትና እንደ መፍትሔ ይዘው በቀረቡት ጉዳይ ላይ ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ የተለያዩ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ እርስዎ ግን ይህ ዘላቂ መፍትሔ አይደለም ይላሉ፡፡ መፍትሔው መንግሥት ለ15 ቀናት ከቤት መቀመጥን በአስገዳጅነት ማስፈጸም አለበት ይላሉ፡፡ ወደዚህ ድምዳሜ የደረሱበት ዋነኛ ምክንያት ምንድነው?
ዶ/ር ካሳሁን፡– አሁን መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎች መራራቅ፣ እጅ መታጠብ፣ ቤት መቀመጥ፣ ሠራተኞችን በተቻለ መጠን መቀነስና በመሳሰሉት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ሆስፒታሎችን ለተሻለ አገልግሎት እንዲዘጋጁ ማድረግና አቋማቸውን እንዲያጎለብቱ እየተሠራ ነው፡፡ ሌሎች ብዙ ነገሮች እየተደረጉ ነው፡፡ በመጨረሻ ግን ሁሉም አገሮች እያደረጉ ያሉትና የማይቀረው ቤታችሁ ቁጭ በሉ የሚለው ነው፡፡ እዚህም ቤታችሁ ቁጭ በሉ የሚለው ነገር አይቀርም፡፡ የእኔ አንኳር ነጥብ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ቤታችሁ ቁጭ በሉ ከሚለው ጀርባ ግልጽ የሆነ ዕቅድ የለም፡፡ መንግሥትም ፈርቷል ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡– የመንግሥት ፍራቻ ሲባል እንዴት?
ዶ/ር ካሳሁን፡– መንግሥት ፈራ የምለው ቤታችሁ ቁጭ በሉ ብል ምን ይፈጠራል የሚለው ሥጋት ስላሳደረበት ነው፡፡ ምክንያቱም ሥራ አጡ ብዙ ነው፡፡ ደካሞች አሉ፡፡ በፋይናንስ ደረጃም በሚገባ ያልተዘጋጀበትና የጠነከረ አይደለም፡፡ መቶ በመቶ ቤታችሁ ቁጭ በሉ ቢል ከበሽታው ውጪ ያሉ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም ያለው፡፡ ሁኔታዎችን ለመቆጣጠር የሚችልበት ደረጃ ላይ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡– ለምሳሌ ?
ዶ/ር ካሳሁን፡– ለምሳሌ ሥራ የሌላቸው ሰዎች ቤታችሁ ቁጭ በሉ ቢላቸው በረሃብ ያልቃሉ፡፡ አሁን ለእነሱ የሚሆን ጥርት ያለ ዕቅድ አለው ብዬ አላምንም፡፡ አዛውንቶች አቅመ ደካሞች፣ እንዲሁም ምንም ነገር የሌላቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በተለያዩ ወገኖችና በቤተሰብ የሚደገፉ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ የኅብረሰብ ክፍሎችን ከቤት አትውጡ ሲባል አደጋው ይከፋል፡፡ ለምሳሌ ሥራ መሥራት እየቻሉ ነገር ግን ሰው ቤቱ እንዲቀመጥ ከተደረገ ሥራ የመሥራት ዕድሉ አይኖርም፡፡ ይኼ ከሁለት አንፃር አስፈሪ ነው ብዬ ነው የምገምተው፡፡ አንዱ እነዚህ ሰዎች መብላትና መጠጣት አለባቸው፡፡ እንደሚታወቀው በተለይ አዲስ አበባ ውስጥ የቀን ሠራተኞች መሥራት እየቻሉ ቤታችሁ ቁጭ በሉ ቢባሉ፣ ቀን የሆስፒታል ማታ ደግሞ የዘረፋ ጉዳይ ነው የሚሆነው፡፡ ነገሩ የደኅንነት ሥጋት አለው፡፡ ነገር መፍትሔ መስጠት ያለብን ከሁሉም አንፃር ነው፡፡ መንግሥት እንደ ሌሎች አገሮች 15 ቀናት ከቤታችሁ አትውጡ ያላለበት ዋነኛ ምክንያት፣ እነዚህ የሥጋት ምንጭ ስለሚሆኑ ነው፡፡ ሰሞኑን በዚሁ ጉዳይ ወረዳዎችን አነጋግሬያለሁ፡፡ በአብዛኛው በወረዳ ላይ ያሉ ሰዎች ብዙ እየሠሩ ነው፡፡ በሸማቾች ማኅበር በኩል መከናወን ያለበትን እየሠሩ ነው፡፡ ተያያዥ ሥራዎችንም ይሞክራሉ፡፡ ስለቫይረሱ ትምህርት ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን የማይቀረው ቤት የመቀመጥ ውሳኔ ካለ ይህንን ሁሉ ሰው ምንድነው የምናደርገው የሚለው ጉዳይ ጥርት ያለ ራዕይ ሊኖረው ይገባል፡፡ እኔም ይዤ የተነሳሁት ሐሳብ ከዚህ የሚነሳ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– እርስዎ የ15 ቀናት የቤት ውሎ መቅረት የለበትምና ተፈርቷል ላሉት ጉዳይ መፍትሔ ለመስጠት አለኝ ያሉት ሐሳብዎ እንዴት ይገለጻል? ለ15 ቀናት ያለው የሌለውን በመደገፍ እንዴት መከናወን እንዳለበትና በጉዳዩ ላይ ከሚኖሩበት ወረዳ ኃላፊዎች ጋር የተነጋገሩበት ነገር ምንድነው? ቀደም ብለው እንደገለጹትም ካለው ችግር አንፃር መፍትሔው ምንድነው?
ዶ/ር ካሳሁን፡– አሁን ለዚህ የሚሆን መፍትሔ ነው እየሞከርኩ ያለሁት፡፡ እኔ በቦሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው የምኖረው፡፡ ቦሌን በአምስት እከፍለዋለሁ፡፡ የሌሎችንም ክፍላተ ከተሞች ነዋሪዎች በአምስት ከፍሎ ለመሥራት የታሰበ ነው፡፡ ይህም ሲብራራ አንዱ ምንም ነገር የሌላቸው አዛውንቶችና አቅመ ደካሞች ያሉበት ምድብ ነው፡፡ ከእነዚህ ኑሮ በመጠኑ ሻል ያለው ሁለተኛው ክፍል ደግሞ መሥራት የሚችሉ ሆነው፣ ከመሸከም ጀምሮ፣ የተለያዩ የቀን ሥራዎችን እየሠሩ በጉልበታቸው ከሚያገኙ የቀን ገቢ የየዕለቱን ኑሮ የሚገፉ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ምድብ ውስጥ የሚቀመጡት ደግሞ ነገ በራችሁን ዝጉ ቢባል ለሌላ ሰው ሊተርፍ የሚችል ነገር የሌላቸው፣ ነገር ግን ለ15 ቀናት ራሳቸውን ችለው መቀጥ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ብዛት ያለው ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ ከዚህ ክፍል የሚመደብ ነው የሚል ግምት አለኝ፡፡ ስለዚህ ይህ መሀል ላይ ያለ የኅብረተሰብ ክፍል ለ15 ቀናት ራሱን ችሎ ቤት መቆየት የሚችል ነው፡፡ በአራተኛ ደረጃ የማስቀምጠው ምድብ ራሱን ችሎ በተወሰነ ደረጃ ለሌሎች አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል አቅም አለው ተብሎ የሚታመን ነው፡፡ አምስተኛው ምድብ ደግሞ ራሱን መቻል ብቻ ሳይሆን፣ ጥሩ ኑሮ የሚኖርና ጥሩ አቅም አለው የሚባል የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ እነዚህ በአምስት ምድቦች ሊኖሩ የሚችሉትን መረጃዎች ደግሞ በቀላሉ ከወረዳዎችና ከቀበሌዎች ማግኘት ይችለል፡፡ ስለዚህ ይህንን ጥርት አድርጎ ለማስቀመጥ በክፍለ ከተማ ደረጃ የመንግሥት አመራሮች መሥራት የሚኖርባቸው፣ ጠንካራ የመረጃ ስብሰባና ዳና ማጠናቀር ነው፡፡ በዚህም በአምስቱ ምድቦች ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲያስታውቁ ማድረግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ይህ ከባድ ሊሆን ስለሚችል እነዚህ አካላት መረጃውን እንዴት በቀላሉ ሊያጠናቅሩ ይችላሉ?
ዶ/ር ካሳሁን፡– ክፍላተ ከተሞች በሥራቸው ያሉትን ወረዳዎች፣ ቀበሌዎችና ነዋሪዎቻቸውን ያውቃሉ፡፡ 85 በመቶ የሚሆኑ ነዋሪዎችን ያውቃሉ፡፡ መረጃም አላቸው፡፡ ምናልባት 15 በመቶ የሚሆኑት መታወቂያ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለማንኛውም ሁሉም ቀበሌ ነዋሪዎችን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ወዲያው ቀደም ብዬ በአምስት ምድቦች በከፋፈልኩት መሠረት መረጃውን እንዲያቀርቡ ማድረግ ነው፡፡ ይህም በቶሎ መሠራት አለበት፡፡ ቤታችሁን ዝጉና ለ15 ቀናት ቁጭ በሉ ከመባሉ በፊት ይህ መረጃ መጠናቀር አለበት የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ ማን በምን ሁኔታ ላይ ነው? ማን ረጂ ማን ተረጂ ነው? የሚለውን በቤት ቁጥርና በቤተሰብ ብዛት ለይቶ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ ዳታው የሚመሠረተው በአምስት ምድቦች በመክፈልና መረጃውን ማደራጀት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ከፍተኛ ወጪ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ግን በዘመቻ መልክ መሥራት ነው፡፡ ምክንያቱም ቀበሌዎች በእዚህ ላይ ተመሥርተው መሥራት አለባቸው፡፡ እነ ማን የትኛው ክፍል ላይ ይመደባሉ ለሚለው ይህንን ዳታ መሥራት አለባቸው፡፡ ይህንን ማድረግ የችግሩን ግማሽ አካል መቅረፍ ማለት ነው፡፡ መንግሥት ዳር ዳር እያለ እጅ ታጠቡ በማለት ላይ ላዩን ያለ ይላል እንጂ፣ የመፍትሔ መሠረቱ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- እንዲህ ላለ ፈጥኖ ተግባራዊ መሆን ለሚገባው አጣዳፊ ችግር ዳታ መሰብሰብ ጊዜ አይወስድም?
ዶ/ር ካሳሁን፡- እስከ ክፍለ ከተማ ያለው ነገር በአንድ ሳምንት መሠራት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ በእጃቸው ላይ መረጃው አለ፡፡ ያንን ማጠናቀር ነው፡፡ በአንድ ሳምንት መሠራት ያለበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይኼ ከሆነ በኋላ የመጨረሻዎቹ ታች ያሉ ምድቦችና ላይ ያሉት ሁለት ምድቦች አብዛኛውን ቁጥር ይይዛሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ላይ ያሉት በአብዛኛው በርህን ዝጋ ብትላቸው መኖር ይችላሉ፡፡ ከታች ያሉት መሥራት እየቻሉ ግን በራቸው የተዘጋባቸውን እየመገብክ አስፈላጊዎቹን 15 ቀናት ማጠናቀቅ ይቻላል፡፡ በዚህ ዕሳቤ በከፋፈልኩት ምድብ መሠረት ላይ ያለው ሁለት ምድብ ታች ያለውን ሁለት ምድብ የመንከባከብ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ከተለዩ በኋላ ምንም ችግር የለም፡፡ መሀል ያለው በሸማቾች ማኅበር በኩልም ሆነ በሌላ መንገድ 15 ቀናት መኖር ይችላል፡፡ ከዚያ በኋላ መካከለኛ ገቢ ያለው የምንለው ክፍል ራሱንም ችሎ የሚተርፈው ነገር አለው፡፡ ከላይ ያለው ደግሞ ተለይቶ በትልቁ ብዙ ሰዎች መርዳት የሚችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ ይህንን አውቀን ከለየን ላይ ያሉት ታች ያሉትን ይረዳሉ፡፡ ይህንን ማድረግ ግዴታቸውም ነው፡፡ አገር ከሌለ ላይ ያለውም አይኖርም፡፡ ታች ሠርቶ መብላት የሚችለውን ሰው ምግብ ሰጥተን ለ15 ቀናት ቤቱ እንዲቀመጥ ካላደረግን፣ በአገር ደኅንነት ብዙ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባለው አስተሳሰብ በመስማማት ሁሉም በየድርሻቸው የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን አለባቸው፡፡ ይኼ የሞራል ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ብቻ አይዳለም፡፡ የደኅንነት ጉዳይ ነው፡፡ የሰብዓዊነትም ጉዳይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ይህ እርስዎ ያነሱት ሐሳብ ተቀባይነት ካገኘ ወደ መሬት ለማውረድ አይከብድም? መረጃው ተሰብስቦ ረጂና ተረጂ ከተለዩ በኋላ ቀጣይ ዕርምጃው እንዴት ተግባራዊ ይሆናል?
ዶ/ር ካሳሁን፡– አሁን ገንዘብ ተዋጥቶ በቀበሌዎቹ ወይም በወረዳዎቹ በኩል እነዚህ ሰዎች ይረዱ ቢባል አንድ ቢሮክራሲው ከፍተኛ ነው፡፡ ሁለተኛ ለሥራ ማስኬጃ የሚወጣው ታች ሥራ ላይ ሊውል ከሚገባው ገንዘብ በእጅጉ ይበልጣል፡፡ ይኼ በልምድም ለዘመናት ያየነው ጉዳይ ነው፡፡ በተደራጀ መንገድ በቀበሌ በኩል ለማድረግ ችግር ይኖረናል፡፡ ለምሳሌ ለቆሼ ተጎጂዎች በተዋጣው ገንዘብና ለተረጂዎቹ በደረሰው ገንዘብ መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ ሰምተናል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከልምዳችን እንደምናውቀው ምንም ዓይነት ዕርዳታ 20 እስከ 25 በመቶ የሚሆነው ታች ለተጠቃሚው ከደረሰ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ደርሶ አያውቅም፡፡ ከረድኤት ድርጅቶችና ከሚሰጡ አገሮች ጀምሮ ገንዘቡን መውሰድ ይጀመራል፡፡ አስተዳደራዊ ወጪና የተለያዩ ወጪዎች እየተባለ ገንዘቡ ይወሰዳል፡፡ ይህንንም ነገር ወደ ወረዳ ብናወርደው ጥቅም የለውም፡፡ በመካከል የሚባክነው ገንዘብ ከፍተኛ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይህ መንገድ አያዋጣም ማለት ነው፡፡ እስካሁን ግልጽ ያደረግኩት ነገር ቢኖር፣ በተለይ እንደ ቦሌ ያለ ክፍለ ከተማን እንውሰድ፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ ያሉትን ድሆች ለሁለት ሳምንት ሳይሆን ለአንድ ወር መመገብ ይቻላል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡– ዕርዳታው እንዴት ይሰጣል የሚለውን በመልሱልኝ?
ዶ/ር ካሳሁን፡– ሰውን ገንዘብ አምጣ እኛ እናከፋፍላለን ቢባል በወረዳ ደረጃ የማይሆን ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ወረዳውን እንደ መንግሥት እንውሰድና እሱ ማትሪክሱን በሰፊው ሠርቶና ለይቶ እነዚህ እነዚህ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል ማለት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ ማለትም ያለበት ይህንን ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የላይኛው ደረጃ ላሉ ሰዎች መረጃ ማቅረብ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ቤት በመምጣት አንተ ጥሩ ኑሮ ነው የምትኖረው፣ ይኼ የአንተም የእኛም የሁላችንም የአገርም ጉዳይ ነው፣ አገር የምትቀጥለው አንተ ቢያንስ አሥርና አሥራ አምስት ቤተሰብ ስትይዝ ነው ይባላል፡፡ እኔም እንዲህ ከተባልኩኝ ይሆናል፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው ያለው፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመርዳት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ተረጂዎች ተለይተው እኔ አሥር ቤተሰብ እችላለሁ ብልና በጀት ባወጣ ምናልባት 1,500 ብር ለአንድ ቤተሰብ በወር 15 ሺሕ ብር ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ እንዲህ ያደርጋል፡፡ ይህ ትልቅ ሥራ ነው፡፡ ብዙ ነገር ይቀይራል፡፡
ሪፖርተር፡– ይህ የእርስዎ ዕቅድ እንዴት ሊተገበር ይችላል የሚለው አያሳስብም? እንዴትስ ይመራል? ማንስ ነው የሚሠራው?
ዶ/ር ካሳሁን፡– አንደኛ ሥራው ‹ማቺንግ› ነው፡፡ እከሌ እከሌን ያግባ ዓይነት ነገር ነው፡፡ ይኼ በሮተሪ ክለብ ተሠርቶበታል፡፡ ለረዥም ዘመን ተሠርቶበታል፡፡ ‹ማቺንግ ግራንት› ይባላል፡፡ ዕርዳታው በገንዘብም ሆነ በእህል መልክ በመንግሥት ሰዎች በኩል ካለፈ ወጪው ብዙ ነው የሚሆነው፣ አይቻልም፡፡ ነገር ግን እኔ አሥር ቤተሰብ ቢሰጠኝና የአንተ ናቸው ከተባልኩ በኋላ እንዴት ይደረግ የሚለው በፈቃደኝነት ላይ የሚመሠረት ነው፡፡ ልክ እንደ ሽያጭ መቅረብ አለበት፡፡ በዚህ ድጋፍ አሰጣጥ አንደኛ የዕለት ጉርሳቸውን በጉልበታቸው ሠርተው የሚሸፍኑ ሰዎች መለየት አለባቸው፡፡ ሁለተኛ በየቦታው ያሉ አሮጊቶች፣ ሽማግሌዎች፣ ለሥራ ያልደረሱ ትንንሽ ልጆችን የያዙ ምንም ገቢ የሌላቸው ሰዎችን የመለየቱ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ የወረዳውና የመንግሥት ሥራ ነው፡፡ መለየት ነው፡፡ ይህ ከታወቀ ግማሹን ችግራችንን እንደ ተሻገርነው ይቆጠራል፡፡ ሰዎች የተወሰኑ ቤተሰቦችን ይዘው የመሻገር ግዴታ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል መሻገር ያለባቸውን ሰዎች ዳታ መንግሥት ሰብስቧል፡፡ ይህንን ማዛመድ አለብን፡፡ የማዛመድ ሥራው ላይ ወረዳዎቹ ተሳታፊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ገንዘብ እስካላንቀሳቀሱ ድረስ ይህንን መሥራት ይችላሉ፡፡ ሁለተኛ ሥራው በበጎ ፈቃደኞች መከናወን ይችላል፡፡ በጎ ፈቃደኞችን ማስተባበር አለባቸው፡፡ እዚህ ቤት ያሉ ሰዎች ምንም ነገር የሌላቸው ናቸው ብለው ማቅረብ አለባቸው፡፡
ሪፖርተር፡– እርስዎ ቦሌ ክፍለ ከተማን ነው እንደ ምሳሌ ያቀረቡት፡፡ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ውጪ ባሉት ክፍላተ ከተሞች የአብዛኞቹ የኑሮ ደረጃ ዝቅተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ ሥራውን በክፍለ ከተማ ብቻ መገደብ እንዴት ይቻላል?
ዶ/ር ካሳሁን፡– የቦሌዎች ይችላሉ፡፡ ወደ አሮጌ አውሮፕላን ማረፊያ ያሉ ይችላሉ፡፡ ሌሎች የተሻለ ኑሮ የማታይባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ ቂርቆስ አካባቢ አይችሉም፡፡ ቂርቆስ 70 በመቶውን ወይም 60 በመቶ ይችላል፡፡ በዚህ መንገድ መረጃውን ከያዝክ ሌላው ቀላል ነው፡፡ የመንግሥትን ሥራ ያቀላል፡፡
ሪፖርተር፡- በእርስዎ ዕቅድ መሠረት በክፍላተ ከተሞች መካከል የማይጣጣም ነገር ካለ፣ አንዱ ክፍለ ከተማ ላይ የታየን የተሻለ አሠራር ወደ ሌላው ክፍል ክፍለ ከተማ ማሻገር የሚቻልበት አሠራር ይኖራል?
ዶ/ር ካሳሁን፡- በቦሌ ክፍለ ከተማ ያለው የበለጠ መስጠት ይችላል፡፡ ቦሌ የበለጠ መስጠት ከቻለ ደግሞ ለሌላው መስጠት መቻል አለበት፡፡ በአጠቃላይ ሥራውን በክፍለ ከተማ እንዲሆን የፈለግሁበት ምክንያት፣ መንግሥትም በክፍለ ከተማ ስለሚያውቀን ነው፡፡ ነገር ግን በበጀት ላይ ድጎማ የሚባል ነገር አለ፡፡ በአንድ በኩል በጀቱ ከፍ ብሎ በአንድ በኩል ዝቅ ካለ፣ በዚያ በኩል የለውን ወደዚህ ማንሸራሸር ይቻላል፡፡ በእኔ ዕቅድ መሠረት ከሄደ የአዲስ አበባ ሕዝብ ምናልባት ከአሥሩ ክፍላተ ከተሞች ስድስት ሰባቱ ራሳቸውን እንዲችሉ ታደርጋለህ፡፡ 1,500 ብር አልኩህ እንጂ አንድ ሺሕ ብርም ሊበቃ ይችላል፡፡ ስለዚህ የበለጠ ሰው መድረስ ትችላለህ፡፡ ቀሪውን ግን መንግሥትም ይደጉማል፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ብዙ ነገር ላይ ግራ ተጋብቶ ነው ያለው፡፡ ለባንኮች ይህንን ያህል አድርጌያለሁ ብሏል፡፡ ነገር ግን ግልጽና ጥርት ያለ ራዕይ ስለሌለ ገንዘብም ቢኖረው፣ አሁን ስመለከተው ገንዘቡን ወዴት እንደሚያደርገው የቸገረው ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ነው ቶሎ ብሎ ቤታችሁ ተቀመጡ ያላለው፡፡ ነገር ግን ስድስትና ሰባት ክፍላተ ከተሞች ራሳቸውን ቢችሉለት ሌሎቹን ግማሽ በግማሽ ራሱ መርዳት መቻል አለበት፡፡
ሪፖርተር፡– ይህ እንዲህ 15 ቀናት ተቀመጡ ሲባል ሊሆን የሚችል ሐሳብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ መንገዶች ዕርዳታዎች እየተሰበሰቡ ነው፡፡ ዕርዳታዎቹ እንዴት መዳረስ አለባቸው ይላሉ?
ዶ/ር ካሳሁን፡– በሌሎች አገሮች ለምሳሌ ቻይናን ብትወስድ ውጤታማ የሆኑት 15 ቀን ከቤት አትውጡ አላቸው፡፡ ከ15 ቀናት በኋላ ሽታው ይጠፋል የሚል መንፈስ ስላለ ነው፡፡ የታመሙት እየታከሙ አዲስ ሰው ግን አይታመምም፡፡ በእነዚህ 15 ቀናት ጥሩ ልምድ ይኖረናል፡፡ ወደ የሚቀጥሉት 15 ቀናት የመሄድ ጉዳያችን ቀላል ይሆንልናል ማለት ነው፡፡ እኔ አሁን መናገር በፈለግኩት ግልጽ ራዕይና የሐሳብ መነሻ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ይህንን በዚህ ብንጨምርበት የሚል ነገር ይኖራል፡፡ በእኔ እምነት ቦሌ ብቻ ይቻል ማለት ሳይሆን፣ ቦሌን ችሎ ቢያንስ የሌላውን ክፍለ ከተማ ሸክም ማቅለል ይቻላል፡፡ ሲስተም ይኑረን እንጂ አሠራሩ ከተቀመጠ ከዚያ በኋላ ወደ የሚቀጥለው ምዕራፍ መሄድ ቀላል ነው፡፡ አሁን ዕርዳታ እየተሰበሰበ ነው፡፡ ነገር ግን ዕርዳታውን ወደ የሚፈለግበት ቦታ ለማድረስ እኔ የጠቀስኩልህ ዳታ ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብሎ ላይ ላዩን መጋለብ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ታች ያሉት አነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙት በቶሎ መድረስ ስለሚያስፈልግ፡፡ ትልቁ ችግር እሱ ስለሚሆን እነሱን በአግባቡ የመታደግ ሥራ ነው መከናወን ያለበት፡፡ ስለዚህ አሁንም ደጋግሜ የምለው ማን ራሱን ይችላል፣ ማን አይችልም፣ የሚለው መለየት አለበት፡፡ ማን መስጠት አለበት የሚለውም መለየት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡– በእርግጥ መቶ በመቶ ከቤት ተቀመጡ የሚለው አስገዳጅ ሊሆን ይችላል?
ዶ/ር ካሳሁን፡– የማይቀር ነው፡፡ አሁን መንግሥት በሕክምናው በኩል ውስጥ ውስጡን በጣም እየተዘጋጀ ነው፡፡ ሚሊኒየም አዳራሽን ጭምር እያዘጋጀ ነው፡፡ የግል የሕክምና ተቋማትንም እንዲሁ ዝግጁ እንዲሆኑና በተለይ አይሲዩን አሰፉ እያለ ነው፡፡ ሕንፃ ሳይቀር ግለሰቦች እየሰጡ ነው፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ከቻይና ዕርዳታ መጥቷል፡፡ ታጠቡ፣ ተራራቁ የሚለውም መልዕክት ሁሉ ጥሩ ነው፡፡ ያቺ የምትቀጥለዋ ዕርምጃ የማትቀር ነች፡፡ ሌሎች ብሶት እንዳይስፋፋ ማድረግ የቻሉት ሰዎች በየቤታቸው እንዲቀመጡ በማድረግ ነው፡፡ የታመመው ታሟል፣ ያልታመመው አልታመመም፡፡ እ.ኤ.አ. በ1918 በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንፉሉዌንዛ ገብቶ ነበር፡፡ በጊዜው የተባለው ግን ታይፈስ ነው፡፡ በዚያ ኢንፉሉዌንዛ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፡፡ አራት የውጭ አገር ሐኪሞች ሞተዋል፡፡ ያኔ የተፈጠረው ከፍተኛ ዝርፊያ ነበር፡፡ አንድ ቤቱ ተቆልፎበት ቤቱ በረሃብ ይሞታል፡፡ ቀውስ እንዳይፈጠር ግን መፍትሔው ይኼ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህም እንደ የሰውነት አካል ተባብረን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡ ጭንቅላት ከእግር ከራቀ ጥሩ እንደማይሆነው ሁሉ፣ ያለው ከሌለው መራቅ የለበትም፡፡ ይህንን ከባድ ጊዜ ለመሻገር ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ሰው መንቀሳቀስ አለብን፡፡
ሪፖርተር፡– ይህንን ሐሳብዎን ለሚመለከተው አካል አቅርበዋል?
ዶ/ር ካሳሁን፡– ለወረዳ አቅርቤ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡– ከወረዳ ከፍ ባለ ደረጃስ?
ዶ/ር ካሳሁን፡– ከፍ ባለ ደረጃ ማቅረብ አልቻልኩም፡፡ ወደ ላይ ለመንገር ጥረት ቢደረግ አንድ ወር ሊፈጅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ሐሳቤ በቶሎ እንዲፈጸም እንዲህ አቀርባለሁ፡፡