የኮሮና ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ እያሳረፈ የሚገኘው ተፅዕኖ በሰፊው እየታየ ነው፡፡ የጉዳቱ መጠን ቢለያይም፣ ችግሩ ጎልቶ ከታየባቸው ዘርፎች አንዱ የአበባ የወጪ ንግድ ነው፡፡ የዘርፉ ባህርይ ለየት ማለቱ ጉዳቱን ከፍ አድርጎታል፡፡ በአበባ ዘርፍ ከታየው ችግር አኳያ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል እየተደረገ ካለው እንቅስቃሴና በመሰል ጉዳዮች ዙሪያ በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ላይ በመሳተፍ ስማቸው ጎልቶ የሚጠቀሱትን፣ ዘርፉን የሚወክለውን የአምራቾና ላኪዎች ማኅበር በሊቀመንበርነት ያገለገሉትንና በዚሁ ዘርፍ አሁንም እየተሳተፉ የሚገኙትን አቶ ፀጋዬ አበበን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኮሮና ቫይረስ በመከሰቱና አሁን በሚታይበት ከፍተኛ ሥርጭት ሳቢያ የተፈጠረው ቀውስ እንደሚያመጣ አስበውት ነበር? ይህ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖስ እንዴት ይታያል?
አቶ ፀጋዬ፡- የቫይረሱ ሥርጭት መጀመርያ ቻይና ከዚያም ወደ አውሮፓ እያለ ዓለምን አዳርሷል፡፡ በተለይ ቻይና በወረርሽኙ መጠቃቷ በሚነገርበት ወቅት ሌላው ዓለም ግንዛቤው አልነበረም፡፡ በአውሮፓ በተለይም በጣልያን ላይ የደረሰው ጉዳት ሲታይ ነው ብዙ ሰው ስለሁኔታው በትኩረት መረዳት የጀመረው፡፡ እኔም ከኢኮኖሚ አንፃር ሊያደርስ የሚችለው ተፅዕኖ እየገባኝ የመጣው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ እያስከተለ ያለው ኢኮኖሚያዊ ጉዳት አደጉ የሚባሉ አገሮችን ጭምር እየፈተነ እንደሚገኝ ተገንዝበናል፡፡
ይኼ ነገር አገራችን ሲገባ፣ ምን ልንሆን ነው? የሚለው ጥያቄ አሳስቦኛል፡፡ እውነቴን ነው ኢኮኖሚው ላይ እንዲህ ተቻኩሎ ተፅዕኖ ያሳድራል ብዬ አልገመትኩም ነበር፡፡ የወጪ ንግዱ ላይ በፍጥነት ችግር ያስከትላል ብዬም አልጠረጠርኩ፡፡ በሆላንድ፣ በሳዑዲ ዓረቢያና በጃፓን የሚገኙ ደንበኞቻችንም ይህንን ያህል ፍራቻ አልነበራቸውም፡፡ ከመቅጽበት ወደየአገሮቹ ሲዛመት ግን ሁላችንም ይኼ በሽታ በአገራችን፣ በሕዝባችንና በኢኮኖሚያችን ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ተገንዝበን መነጋገር ጀመርን፡፡ በኤክስፖርቱ መስክ የምንንቀሳቀሰው ሰዎች በሁኔታው ላይ ስንነጋገር፣ በተወሰኑ የኤክስፖርት ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል ዓይተናል፡፡ በተለይ እኔ ባለሁበት ዘርፍ አጠቃላይ የወጪና ገቢ ንግዱን በተመለከተ መረጃ ተሰባስቦ ሲታይ፣ ነገሩ ከፍተኛ አደጋ እንዳመጣ ተገነዘብኩ፡፡ ዕለት ተዕለት ካለው እንቅስቃሴ አንፃር ላኪዎችም ለመላክ አስመጪዎችም ለማስመጣት ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬም ሆነ በሌላው ዘርፍ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተፈጠረው አጠቃላይ ችግር እንዴት ይገለጻል?
አቶ ፀጋዬ፡- በጣም የሚገርመው፣ በውጭ አገር የቫይረሱ መሠራጨት ሪፖርት የተደረገባቸው አገሮች ብቻ ሳይሆኑ የሁሉንም የዓለም አገሮች ኢኮኖሚ በአንዴ መጉዳቱ ነው፡፡ ላኪና ተቀባይ አገሮች በተመሳሳይ ወቅት ኢኮኖሚያቸው ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳቱ ዓለም ልክ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ እንዳለች ያሳየና እያንዳንዱ ቢዝነስ ከእያንዳንዱ አገር ጋር እንደተያያዘ ያሳየ አደጋ ነው የተከሰተው፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ተያይዞ የቆመ መሆኑን የተገነዘብንበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የእኛ ኢኮኖሚ በማደግ ላይ ያለ ኢኮኖሚ እንደመሆኑ መጠን፣ የቫይረሱ ተፅዕኖ ወዲያውኑ ነው የታየው፡፡ ሳይታሰብ ዱብ ያለብን ነገር ሆኗል፡፡ የቢዝነስ መቀዛቀዝ፣ የወጪ ንግድ መዳከም ታይቷል፡፡
በእኛም ዘርፍ ችግሮች ጎልተው ታይተዋል፡፡ የዓለም አንድ አካል እንደመሆናችን በብዙ መንገድ ነካክተናል፡፡ በኢኮኖሚ አንቱ የተባሉትን ሁሉ ነካክቷል፡፡ ከእኛ አገር አንፃር ሲታይ ግን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ካለብን ችግር አንፃር የበሽታውን ሥርጭት መቼ ይቃለል ይሆን? ብለህ ብታስብ እንኳ በዚህ ጊዜ ብለህ መገመት የማትችልበት ክስተት ሆኗል፡፡ ደንበኞቻችንም ችግሩ መቼ ሊፈታ እንደሚችል ስንጠይቃቸው መገመት እንኳ አልቻሉም፡፡ አያውቁም፡፡ በተለይ በአውሮፓ ችግሩ በርትቷል፡፡ ሰንጠረዡ ወደ ላይ እየወጣ ነው፡፡ አንድ ቦታ ይቆማል ወይም ይወርዳል የሚል እምነት ቢኖራቸውም መቼ? ለሚለው ጥያቄ ማናቸውም መልስ የላቸውም፡፡ እኛም አናውቅም፡፡
ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ እንደተገለጸው የአበባ እርሻ ላይ የተዘራውን ማቆየት አይቻልም፡፡ አበባው ባይሸጥ እንኳ ማሳውን እየተንከባከቡ ማቆየት ግድ እንደሆነ እየታየ ነው፡፡ በርካታ ሠራተኞች የሚያስተዳድር ዘርፍ እንደመሆኑ፣ የተፈጠረው ችግርም መቼ ይስተካከላል የሚለውም ምላሽ ከሌለው፣ ኢንቨስትመንቱን እንዴት ማቆየት ትችላላችሁ?
አቶ ፀጋዬ፡- በአበባው ዘርፍ ችግሩ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ ከአፍሪካ እኛና ኬንያ ነን አበባ በመላክ የምንፎካከረው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በኬንያ ከ90 እስከ 95 በመቶ የአበባ ንግድ ሥራ ቆሟል፡፡ በኢትዮጵያም አንዳንድ የሽያጭ ስምምነቶችና ለሱፐር ማርኬቶች የሚውል ጥቂት ሽያጭ ካልሆነ በቀር፣ ከ80 በመቶ በላይ የወጪ ንግዱ ቆሟል፡፡ በአውሮፓ ብዙዎቹ የአበባ ንግድ ስምምነቶች ተሰርዘዋል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በተለይ ዱባይ ላይ የሁሉም አገሮች ድንበሮች ስለተዘጉ ገበያ የለም፡፡ ምናልባት በሳምንት ይላክ ከነበረው ሁለት ሦስት በመቶ ብቻ ሊላክ ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን ዋጋው እዚህ ግባ በማይባል ሒሳብ ነው፡፡ ለዚህ ነው መንግሥት ችግሩን አውቆት ከዚህ ቀደም ዝቅተኛ የአበባ መሸጫ ዋጋ ለጊዜው እንዲነሳ የወሰነው፡፡ ይህ ምናልባት የአውሮፕላንና የማሸጊያ ወጪዎችን የሚሸፍን ገቢ ቢመጣ ተብሎ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም 300 ሚሊዮን ዶላር ቢያስገኝም፣ ከዚህ በኋላ ምናልባት 50 ወይም 60 ሚሊዮን ዶላር ካስገኘ ተብሎ ነው፡፡ የአገር ጉዳይ ሆኖ እንጂ ሥራው አዋጭ ሆኖ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ያልጠቀሱት ጉዳይ አለ፡፡ የአበባ ገበያ ባይኖርም እርሻው እየለማና እያመረተ መቀጠል አለበት የሚባለውን ያብራሩልኝ፡፡ ገበያው ከሌለ አበባ እያለሙ መጣል ለምን እንዳስፈለገ ቢገልጹልኝ?
አቶ ፀጋዬ፡- አበባ ሲመረት 365 ቀናት ሙሉ አበባ ትቀጥፋለህ፡፡ ከዚህ ውስጥ ከሐምሌ እስከ መስከረም አራት ወራት ምርቱ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ምርቱ ዓመቱን ሙሉ አይቀንስም፡፡ በነገራችን ላይ ችግሩ የመጣብን በዋና የገበያ ወቅት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ የአበባ ምርት አይቆምም፡፡ ዛሬ ትቀጥፍና ከ45 ቀናት በኋላ ሌላ ምርት ያብባል፡፡ ይደርሳል፡፡ ነገር ግን ከአንድ ሔክታር በዓመት ሁለት ሚሊዮን ዘንግ አበባ የምታመርት ከሆነ፣ በቀን ሁለት ጊዜ ከማሳ ትለቅማለህ፡፡ በገበያ ዕጦት ምክንያት ግን በቀን ሁለቴ እየለቀምን ሁለቴም እየጣልን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አበባውን ከመጣል ይልቅ ለሌላ አገልግሎት የሚውልበት ዕድል የለም?
አቶ ፀጋዬ፡- ለምንም አይሆንም፡፡ ማሽን ያለን አምራቾች እየፈጨን ብስባሽ እንሠራበታለን፡፡ ማሽን የሌለው ግን ይጥለዋል፡፡ ወይም ለማገዶነት ሊጠቀምበት የአካባቢ ሰው ይወስደዋል፡፡
ሪፖርተር፡- አበባውን ሳትለቅሙት ቢቆይ ምን ይሆናል? አንድ ሁለት ወር ባለበት ቢቆይስ?
አቶ ፀጋዬ፡- እንቡጥ አበባ ነው የምትለቅመው፡፡ ለገበያ የሚቀርበውም እንቡጡን ነው፡፡ አንድ ቀን ሳትለቅም ብታቆየው ይፈካል፡፡ ጠዋት መልቀም ያለብህን ለከሰዓት ብታቆየው ይፈካል፡፡ ተበላሸ ማለት ነው፡፡ የተበላሸው ደግሞ ሌላው አበባ ላይ ተፅዕኖ ያመጣል፡፡ ስለዚህ በጊዜው በቀጠፍከው ቁጥር አሥር ሌላ አዲስ አበባ ያወጣል፡፡ የአበባ ትልቁ ኢንቨስትመንቱ ችግኞቹ ናቸው፡፡ አንድ የጽጌሬዳ ችግኝ እስከ አንድ ዩሮ ዋጋ አላት፡፡ የአንድ ችግኝ ዋጋ ከ35 ብር በላይ ማለት ነው፡፡ በአንድ ሔክታር ውስጥ ወደ 75 ሺሕ ችግኝ አለ፡፡ ብዙዎቹ የእኛ አልሚዎች ከ15 እስከ 500 ሔክታር ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ 15 ሔክታር ያለው አልሚ፣ የችግኝ ኢንቨስትመንቱ ብቻ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ የችግኝ ወጪ ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ገበያው ነገ ተመልሶ ቢመጣ የሚሆነው ስለማይታወቅ ተንከባክበን ማቆየት አለብን፡፡ ማዳበሪያ መስጠት አለብን፡፡ ውኃ ማጠጣት አለብን፡፡ የተባይ መከላከያ መርጨትና መንከባከብ አለብን፡፡ ዝም ካልከው ግን በአንድ ጊዜ ተባይና በሽታ ይወረዋል፡፡ ለችግኝ ያወጣኸው ያ ሁሉ ገንዘብ ዜሮ ይገባል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው የአበባ እንክብካቤ ሊቋረጥ የማይችለው፡፡
ሪፖርተር፡- አበባ በርካታ ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ነው፡፡ ከ50 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን ይዟል፡፡ በሽታው ያመጣው ችግር ከቀጠለና ገበያው ከጠፋ የሠራተኞች ህልውና እንዴት ይሆናል? በምን አግባብ ይዛችሁ ትቀጥላላችሁ? ከመንግሥት ጋር በምን ተስማማችሁ?
አቶ ፀጋዬ፡- በመጀመርያ ሠራተኛው የእኛ አካል ነው፡፡ ቤተሰብህ ነው፡፡ ዛሬ ችግር ስለመጣ በአንድ ጊዜ ዕርምጃ የምትወስድበት፣ ነገ ጥሩ ጊዜ ሲመጣ የምትሰበስበው አይደለም፡፡ ችግሩንም መልካሙንም ነገር ይዘን በጋራ እዚህ ደርሰናል፡፡ ስለዚህ ችግሩ ሲከሰት መቋቋም እስከምንችለው ድረስ አብረን እንዘልቃለን፡፡ ለሠራተኞቻችን ቃል የገባነው ይህንን ነው፡፡ ዋናው ማነጣጠሪ ሠራተኞቻችን መሆን የለባቸውም፡፡ መንግሥትን የምንጠይቀው ገንዘብ እንዲሰጠን አይደለም፡፡ ድሃ ነን፡፡ መንግሥታችን የሠራተኞቻችንን ወጪ ይሸፍን የምንልበት አቅም የለውም፡፡ ስለዚህ እኛው እስከቻልነው ድረስ ሠራተኞቻችንን ማቆየት አለብን፡፡ ይህ የሚሆነው እስከመቼ ነው የሚለው ግን አይታወቅም፡፡ ሦስት፣ አራት ወይም አምስት ወራት ድረስ ልንሄድ እንችላለን፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ገበያው መፍትሔ ካላመጣ፣ ከመንግሥትም ከሠራተኞችም ጋር መመካከር ይኖርብናል፡፡ ሠራተኛው የንብረቱ አካል ነው፡፡ እነሱ ከሚሸማቀቁ እኛ ባለን አቅም እስከመጨረሻው ተፍጨርጭረን መሸጋገር አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- የኮሮና ቫይረስን ለመቀነስ የመንግሥት ዝግጅት በእርስዎ ዕይታ እንዴት ይታያል?
አቶ ፀጋዬ፡- መንግሥትና ሕዝባችን ወረርሽኙ ተስፋፍቶ ጉዳት እንዳያደርስ እያደረጉት ያለው ጥረት ከጠበቅነው በላይ ነው፡፡ በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ይታያል፡፡ አቅሙ ካላቸው ባለሀብቶች እየተደረገ ያለው ድጋፍም በጣም ጥሩ ነው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ግን ሁለት ነገሮች አያለሁ፡፡ ኮሮና ሕዝባችንን ችግር ውስጥ እንዳይጥለው ማናችንም የአቅማችንን በማድረግ የሚያበረታታ ጥረት ይታያል፡፡ የሚቀረው ነገር ቢኖርም ሚዲያው ብዙ እየሠራ ነው፡፡ በአንፃሩ በከተማም ከከተማም ውጭ ያለውን አዝማሚያ ስታየው ግን የኅብረተሰቡ ግንዛቤ የችግሩ አሳሳቢነት ምን ያህል እንደሆነ የተመለከተው አይመስልም፡፡ ሦስትና አራት እየሆነ ተቧደኖ ሲሄድ ታያለህ፡፡ በአንዳንድ የእምነት ቦታዎች ሰዎች ተሰብስበው ታያለህ፡፡ ሰዎች መደዳውን ተቀምጠው ያወራሉ፡፡ ይህ በብዙ ቦታ ይታያል፡፡ ይህን ስታይ ትሠጋለህ፡፡ 110 ሚሊዮን ሕዝብ ባላት አገር ውስጥ እንዲህ ያለውን ያልተገባ ነገር በፖሊስ መቆጣጠር አትችልም፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት እያደረጋቸው ያሉት መልካም እንቅስቃሴዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ማዕከላዊ በሆነ መንገድ ሰንሰለቱን ይዞ መስማማትና መደማመጡ ላይ የሚቀረው ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ምን እንደሚቀር በምሳሌ ቢያስረዱኝ?
አቶ ፀጋዬ፡- ለምሳሌ ኢትዮጵያ ልክ ኬንያ የወሰደችውን ዓይነት ዕርምጃ ላትወስድ ትችላለች፡፡ ኢትዮጵያ ኮሮናን መቆጣጠር ያለባት ከተጨባጭ ሁኔታዋ አንፃር ነው፡፡ ከመንግሥት ወደ ክልል ሲወርዱ የምናያቸው ነገሮች፣ ከማዕከል ወደ ታች ሲኬድ ተመሳሳይ አካሄድና አተገባበር አይታይም፡፡ የፌዴራል መንግሥትና ክልሎች መናበብ አለባቸው፡፡ በፌዴራል የሚወጡ ሕጎች እንደ የክልሉ ፀባይ፣ እንደ የክልሉ የገቢ ምንጮች መሠረት ተጣጥመው ሕጎች ሊወጡ ይችላሉ፡፡ ገንዘብ መሰብሰብ ላይ፣ ትምህርት ላይ፣ የዝውውር ወይም እንቅስቃሴና ሌሎች ነገሮች ላይ ከማዕከል ወጥተው በተመሳሳይ መንገድ በሁሉም ወገን በወጥነት መተግበር አለባቸው፡፡ የገጠመንን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ የሚወሰነው ውሳኔም ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ለምሳሌ ከነገ ጀምሮ የሕዝብ ማመላለሻዎች እንቅስቃሴ ያቁሙ ከማለትህ በፊት በቂ መረጃ መስጠትና ዝግጅት ማድረግ አለብህ፡፡ እንዲሁ በችኮላ ከመወሰን በእንቅስቃሴ መንገድ ላይ የሚገኘውን ሰው ማሰብ አለብህ፡፡ ጊዜ ሰጠኸው በቶሎ ወደ መኖሪያ ቀዬው እንዲሄድ ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ መጉላላቱ ይቀንሳል፡፡ ድንገት ከዛሬ ጀምሮ ተወስኗል ስትል ግን ችግር ማባባስ ስለሚሆን ተናቦ መሥራቱ መልካም ነው፡፡ ስለዚህ አንዳንድ ውሳኔዎች ከመተላለፋቸው በፊት ታስቦባቸው ቢወጡ ስህተቶች ይቀነሳሉ፡፡ ሕዝቡን ድንገት ተነስተህ ለ15 ቀናት ከቤትህ አትውጣ ብትለው፣ የዕለት ጉርሱን በየዕለቱ ሠርቶ በሚያገኛት የሚተዳደረው ሰው፣ አንድ ቀን ቀርቶ 15 ቀናት ሠርቶም ለአንድ ቀን የሚሆን ነገር አይተርፈውም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ሰዎች ጉዳይ መጀመርያ መፍትሔ ማግኘት አለበት፡፡ መንግሥት በምግብ፣ በጤናና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ አስቦ መወሰን አለበት፡፡ ይህ ከሁሉም ጋር በመተባበር የሚሠራበት ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችን እንደ መመገቢያ ማዕከልነት መጠቀም ይቻላል፡፡ ሌላም ዘዴ ሊፈልግ ይችላልና ወደ መፍትሔው ለመሄድ በማዕከላዊነት የሚንቀሳቀስ አሠራር ሊኖረን ይገባል፡፡ ጉዳዩ ስናወራው ቀላል ሊመስል ይችላል፡፡ ውስብስብ ነው፡፡ ቢሆንም መፍትሔ ይኖረዋል፡፡ አደጋውን ለመቀነስ ለምሳሌ አትክልት ተራን ወደ ጃንሜዳ መውሰድ የተቻለው ታስቦበት ነው፡፡ ሌላውንም እንዲህ ባለመንገድ አስቦ መሥራት ይገባል፡፡ ይህንን ማድረጉ በብዙ ይጠቅማል፡፡ ችግሩን ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል ባይባልም መዝጋቱ ጥሩ ዕርምጃ ነው፡፡ የገበያ ሥርዓታችን ዘመናዊ ስላልሆነ ጭንቅንቅ አለ፡፡ ስለዚህ ሌሎች ሥጋት ሊፈጥሩ የሚችሉትን እንዲህ ባለው መንገድ እያዩ ሥጋትን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢኮኖሚውን የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስበት ምን መደረግ አለበት? ማኅበራዊ ቀውሱ እንዳይከፋ ምን ማድረግ ያሻል? የዜጎች ኃላፊነትስ ምንድን ነው?
አቶ ፀጋዬ፡- የኢኮኖሚው አንቀሳቃሳሽ ዘርፍ የሚባሉትን ከለየን በኋላ ኢኮኖሚው የበለጠ እንዳይጎዳ በጋራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የበኩሉን ማድረግ አለበት፡፡ አሠሪው፣ ሠራተኛና መንግሥት መስማማት አለባቸው፡፡ ከሰሞኑም እነዚህ አካላት በጋራ የወሰኑበት ዓይነቱ አሠራር ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ የወረርሽኙ ሁኔታ እየታየ ተመካክሮ በመሥራት ጉዳቱን መቀነስ ያስፈልጋል፡፡ መተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ በመንግሥት በኩል ኮሮናን ለመከላከል ዕርዳታ የሚያሰባስብ አካል አለ፡፡ በአገር ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ እንዴት ነው የተፅዕኖ ግምገማ ሠርቶ ከሚመለከታቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችና የኢኮኖሚ ተዋናዮችና ከሠራተኛው ተወካዮች ጋር ውይይት በማድረግ ይህንን ችግር የምናልፈው? የሚለውን ካየን፣ ተንደላቀን ሳይሆን፣ ዳቦና ሻይ በልተንና ጠጥተንም ቢሆን ችግሩን ለማለፍ መጣር የእያንዳንዳችን ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደረጉት ጥረቶች ውጤት የሚያመጡት ወረርሽኙን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ ምክረ ሐሳቦችን ሕዝቡ ተቀብሎ ሲተገብራቸው ነውና ከዚህ አንፃር አስተያየትዎት ምንድን ነው?
አቶ ፀጋዬ፡- ኅብረተሰቡ ከመንግሥትና ከጤና ባለሙያዎች የሚተላለፉ መመርያዎችን በማክበር ራሱን መጠበቅ አለበት፡፡ ሌላውን ለመርዳት መጀመርያ አንተ መኖር አለብህ፡፡ አንድ ሰው ተነስቶ ለስድስት ወራት የምትሆን ገንዘብ አለኝ ቢልና ሌላው ወገናችን ለአንድ ቀን እንኳ የሚያቆየው አቅም ከሌለው፣ ይህ ዜጋ አቅም አጥቶ በበሽታ ሲጠቃ ማየት አይቻልም፡፡ ያለው ሰው የሌለውን መርዳት አለበት፡፡ ሁላችንም መተባበር አለብን፡፡ ችግሩ የመንግሥትና የተወሰነ አካል ጉዳይ አይደለም፡፡ የሁላችንንም ርብርብ ይፈልጋል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ እንዳንያዝ የግል ጥረታችን ወሳኝ ነው፡፡ ዕርዳታው ማዕከላዊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከቀበሌና ከወረዳ ዕርዳታ የሚሰበስቡ ሰዎች ሦስት አራት ጊዜ ይመጣሉ፡፡ ይህ አይመችም፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የተዋቀረ አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ ዕርዳታው በአንድ ቋጥ መሰባሰብ ወይም መሠራጨት መቻል አለበት፡፡ አንድ ሰው አሥር ጊዜ ይጠየቃል፡፡ ካለው 100 ጊዜም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ነገር ግን በተደራጀና መዋቅር ባለው መልኩ ቢሆን የተሻለ ውጤት ያመጣል አለበት፡፡ ኮሮናን ያህል ጠላት መጥቶብን፣ ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ሒደት ውስጥ ስህተቶችን በተቻለ መጠን መቀነስ አለብን፡፡ በትራንስፖርት መታገድ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች ቢታዩ ጥሩ ነው፡፡ ጉዞዎች እንዴት ይስተናገዱ፣ የሰዎች እንቅስቃሴ በምን አግባብ ይገደቡ የሚለው መታየት አለበት፡፡ ምንም ዓይነት የመሠረታዊ ዕቃዎችና የእህል እጥረት እንዳይኖር መንግሥት መሥራት አለበት፡፡ ገበያውን የሚረብሽ ነገር እንዳይኖር በርትቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ትኩረት የተደረገው ዋጋ ጭማሪ ያደረጉትን መቆጣጠሩ ላይ ነው፡፡ በቂ ምርት ወደ ማዕከል ገበያዎች መምጣት መቻል አለበት፡፡ ስለዚህ እጥረት እንዳይኖር መሠራት አለበት፡፡ በተለይ የታችኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረገ አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የተፈጠረው ችግር ብዙ ነገር የምንማርበት አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡ ለወደፊቱ ልምድ የምንወስደበትን ምልክት አሳይቶናል፡፡
ሪፖርተር፡- ምንድን ነው ያሳየን?
አቶ ፀጋዬ፡- አንደኛው ለወደፊቱ አንድ አደጋ በሌላ አገር ውስጥ ሲከሰት መንግሥት በቶሎ መዘጋጀትና መንሳቀስ እንዳለበት ትምህርት ሰጥቷል፡፡ ኅብረተሰቡም እንዲህ ዓይነት ነገር ቢከሰት ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት የተማረ ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ ጉዳይ ላይ መንግሥት በየትኛው ጉዳይ ላይ ዝግ ማለት እንዳለበትና፣ ችግር ቢከሰት ለመጠባበቂያ ምን ሊኖረኝ ይገባል? የሚለው ላይ ለወደፊቱ ያሳብብበታል፡፡ በየትኛውም መንገድ ችግር ቢመጣ፣ በዚህ መልኩ እወጣዋለሁ የሚለውን እንዲያሰብ አድርጎታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሰሞኑ እንዳየነው በዘመናዊ መንገድ ስብሰባዎችን ማካሄድ በስካይፕና በመሳሰሉት መንገዶች በመጠቀም መነጋገር እንደሚቻል ታይቷል፡፡ ወደፊትም በዚህ አግባብ ቢቀጥል የሚያስብል ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡
ሪፖርተር፡- ብዙውን ጊዜ አደጋ ሲከሰት ለመከላከል የዕርዳታ ጥሪ ይደረጋል፡፡ እዚህም እዚያ ይሮጣል፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አገር አቀፍ ቋት አያስፈልገንም?
አቶ ፀጋዬ፡- አዎን አስፈላጊ ነው፡፡ የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያና ዝግጁነት ሥርዓት ምንጊዜም መኖር አለበት፡፡ መንግሥት ብሔራዊ የእህል መጠባበቂያ አለው፡፡ ልክ እንደዚህ ያለ ለአደጋ ጊዜ የሚሆን የመጠባበቂያ ፈንድ ሊኖረው ይገባል፡፡ ችግር ሲፈጠር ለአደጋ ተብሎ የሚጠራቀም ገንዘብ ወጪ ተደርጎ ይሠራበታል ማለት ነው፡፡ ለዚህ የሚሆነውን ገንዘብ በተለያየ መልክ እንዲጠራቀም ማድረግ ነው፡፡ ዜጎች እንዲያዋጡ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ የሚሆነውን ድጋፍ በቋሚነት ማሰባሰብ ተገቢ ነው፡፡ የቀውስ ወይም የአደጋ ጊዜ ተቀማጭ ገንዘብ አስቀድሞ ማሰባሰብና ለዚሁ ለይቶ ማስቀመጥ ጠቃሚ ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ ለዚህ ፈንድ የተወሰነ እንዲያዋጣ ማድረግ ይቻላል፡፡ መንግሥትም ከሚያገኘው ገቢ አንድ ወይም ሁለት በመቶ ለዚህ ተግባር ቢያውል ብዙ ችግሮቻችንን በቶሎ ለመቅረፍ ያስችለናልና ይህ መተግበር አለበት፡፡ ይህ ገንዘብ እንዲንቀሳቀስ ማድረግም መጠኑ ከፍ እንዲል ለማድረግ ያስቻላልና እንዲህ ያሉ ነገሮች መታሰብ አለባቸው፡፡