በቻይና የተቀዛቀዘው የኮሮና ትኩሳት ለሰሊጥ ገበያ ተስፋ ተጥሎበታል
በስምንት ወራት ውስጥ ከወጪ ንግድ ዘርፍ 1.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ቢመዘገብም፣ ታቅዶ ከነበረው የ2.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አኳያ በ500 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ የታየበት ውጤት መገኘቱን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃ አመላክቷል።
በዓመቱ የሚጠበቀው የወጪ ንግድ ገቢ 3.3 ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ በስምንት ወራት ከታየው አፈጻጸም አኳያ በቀሩት ወራት ውስጥ የዓመቱን የገቢ ዕቅድ ማሳካት አዳጋች እንደሚሆን ይታመናል። ይህም ሆኖ በስምንት ወራቱ አፈጻጸም ቡና የ467 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲያስገኝ፣ በኮሮና ቫይረስ ችግር ውስጥ ከሚገኙ ምርቶች የባሰ ቀውስ የገጠመው አበባ ከ334 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ቡናን ይከተላል።
የቅባት እህሎች 188 ሚሊዮን ዶላር ሲያስገኙ ትልቁን ድርሻ የያዘው ሰሊጥ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የነበረውን ዓይነት ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። የ40 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ የተመዘገበበት ይህ ንዑስ ዘርፍ፣ የገቢ ዕቅዱን የ18 በመቶ ብቻ ውጤት እንዳስመዘገበ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሰሊጥ ምርት ከቅባት እህሎች ሁሉ ትልቁን የወጪ ንግድ ድርሻ ቢይዝም፣ በቻይና የተዛመተው የኮሮና ቫይረስ ሥርጭቱ እስከተገታበት ጊዜ ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ማዳረሱ አስቸጋሪ ሆኖ ቢቆይም፣ በአሁኑ ወቅት በታየው የበሽታው ሥርጭት መገታትና የእንቅስቃሴ ማንሰራራት ሳቢያ የሰሊጥ ዋጋ በቶን ከ70 እስከ 80 ዶላር የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቅሷል፡፡ ቡናም በተመሳሳይ ደረጃ በበርካታ አገሮች ዘንድ የፍላጎት ጭማሪ በማሳየቱ የዋጋ መሻሻል እየታየበት መጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ ከዓለም ሕዝብ ግማሹ በቤቱ በግዳጅ እንዲቀመጥ በመደረጉ ሳቢያ፣ ድንበሮች መዘጋታቸው፣ ካርጎን ጨምሮ የአየር ትራንስፖርት መቋረጡ በተፈጠረው የዋጋ ለውጥ ለመጠቀም የሚያስቸለውን አጋጣሚ ጠባብ አድርጎታል፡፡
ጥራ ጥሬ እህሎች የ134 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ቢያስገኙም በገቢም በመጠንም ቅናሽ ካሳዩ የወጪ ንግድ ምርቶች ተርታ ተሠልፈዋል፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንዳስታወቁት፣ በጥራ ጥሬ ምርቶች ላይ የተንሰራፋ የሕገወጥና የኮንትሮባንድ ንግድ መደበኛውን የንግድ እንቅስቃሴ እያወከ ይገኛል፡፡ በአንፃሩ ለውጭ ገበያ የቀረበ 3.670 ቶን ጫት፣ ከ230 ሚሊዮን ዶላር በላይ አስገኝቷል፡፡ በመጠንም በዋጋም ጭማሪ ታይቶበታል፡፡
በሌላ በኩል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የምርት እጥረት የተፈጠረ በማስመሰል ዋጋ አንረዋል፣ ምርት ሸሽገዋል የተባሉትን ጨምሮ የምግብ ሸቀጦችንና የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን ከባዕድ ነገሮች ጋር በማደባለቅ ሲሸጡ የተደረሰባቸው ከ15 ሺሕ በላይ መደብሮች ሲታሸጉ፣ ከ448 ያላነሱ በወንጀል የተጠረጠሩ ነጋዴዎችም መታሰራቸውን አቶ ወንድሙ አስታውሰዋል፡፡
ይህ ይባል እንጂ በጅምላ እያሸጉ በጅምላ መክፈት ለበርካታ ሕግ ተላላፊ ነጋዴዎች የልብ ልብ እየሰጣቸው እንደሚገኝ፣ ይባስ ብሎም የጠቆመባቸውን አካል ማስፈራራትና ‹‹ለመንግሥት ተናግረህ (አቃጥረህ) ምን የምታመጣ መሰለህ› የሚሉ አጉራ ዘለሎች እንደገጠሟቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው ሸማቾች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ስላለው ጉዳይ የተጠየቁት አቶ ወንድሙ የመንግሥት አካሄድ ምክርና ተግሳጽን በማስቀደም ወንጀለኞችን በማሰር እየቀጣ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ይህ የማይመልሳቸውን እንደማይታገሱ አስታውቀዋል፡፡
የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በየወሩ ከ640 ሺሕ ኩንታል በላይ ስንዴ እየቀረበ እንደሚገኝ፣ ይሁን እንጂ የዚህ ያህል አቅርቦት ሳይቋረጥ ለዱቄት ፋብሪካዎች ለማቅረብ እንዲቻል ከውጭ የተገዛ ስንዴ እስኪገባ ድረስም ከብሔራዊ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በብድር የተወሰደ የ1.5 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በመጠባበቂያነት ከመያዙም ባሻገር ተጨማሪ የ1.5 ሚሊዮን ኩንታል በቆሎም በመጠባበቂያነት መያዙን አቶ ወንድሙ ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 45 ሺሕ ኩንታል ጤፍም ለአዲስ አበባ እየቀረበ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡
የ8.9 ሚሊዮን ኩንታል አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የንጽፅና መጠበቂያ ፈሳሽ ምርቶች በተለይም ሳኒታይዘር ምርት ለሚያመርቱ አካላት የግብዓት እጥረትን በመቅረፍ በጠቅላላው ከ150 ሚሊዮን ሊትር ማምረት ለሚችሉ አካላት ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡