Monday, July 22, 2024

ከኮሮና ቫይረስ ሥጋት በስተጀርባ መጤን ያለባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በትረ ሥልጣኑን የተቆናጠጡበት ሁለተኛ ዓመት ሐሙስ መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በለሆሳስ ሲታሰብ፣ በሁለት ዓመታት ውስጥ ካጋጠሙ በርካታ ችግሮች መካከል በጣም ከባዱ ኮሮና ቫይረስ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ምንም እንኳ በሁለቱ ዓመታት በርካታ ተስፋ ሰጪ ጉዳዮች ቢከናወኑም፣ ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት የቀጠፉና ሚሊዮኖችን ከመኖሪያ ቀዬአቸው ያፈናቀሉ ከባድ ክስተቶችም ማጋጠማቸው አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዓለምን ብርክ እያስያዘ ያለው ኮሮና ቫይረስ ኃያላን መንግሥታትን ሳይቀር እየፈተነ ከመሆኑም በላይ፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምን በማድረግ ሥርጭቱን በመግታት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ የሚያስችል መፍትሔ ይኼ ነው ለማለት የሚደፍር ጠፍቷል፡፡ ከቻይና ተነስቶ አሜሪካን፣ ጣሊያንን፣ ስፔንንና ሌሎች በርካታ አገሮችን እያደቀቀ ያለው ኮሮና ቫይረስ፣ ለኢትዮጵያም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከባድ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል ከሚደረገው ጎን ለጎን የወደፊቱንም ፈተና ከወዲሁ መቃኘት ግድ የሚልበት ጊዜ መሆኑን፣ ከበርታ አገሮች ልምድ መቅሰም ያስፈልጋል እየተባለ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን የያዙበትን ሁለተኛ ዓመት አስመልክተው ለሕዝብ ባስተላፉት መልዕክት፣ ‹‹የለውጡን ጉዞ ሁለተኛ ዓመት የምናከብረው በአንድ በኩል ፈተናና ሥጋት በሌላ በኩል የተስፋ ውጋጋን ከፊታችን እየታየን ነው፡፡ አገራችን ባለፉት ሁለት ዓመታት በለውጥ ሒደት ያገኘቻቸውን ተስፋዎች ለማፍካት፣ ያጋጠሟትን ሳንካዎች ደግሞ ለማስተካከል እየጣረች ባለችበት ወሳኝ ወቅት መላው ዓለምን በጥቂት ወራት ውስጥ በቁጥጥሩ ሥር ያዋለው የማይታየው ጠላት የኮሮና ቫይረስ በእኛም አገር አሻራውን አሳርፏል፤›› ብለዋል፡፡ እስካሁን 200 የሚጠጉ አገሮችን ያዳረሰው ይህ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ጎራ ብሎ 29 (እስከ መጋቢት 24 ቀን) ሰዎችን የቫይረሱ ተጠቂ ማድረጉን፣ ነገ ምን ያህል ኢትዮጵያዊያንን እንደሚያጠቃ በእርግጠኝነት ባይታወቅም በርብርብ በዝቅተኛ ጉዳት ማስቆም እንደሚቻል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የኮሮና ቫይረስ እንኳን ኢትዮጵያን ጠንካራ የጤና መሠረተ ልማት የገነቡትን ምዕራብያውያን ምን ያህል እያስጨነቀ እንዳለ፣ በብዙ አገሮች ትምህርት ቤቶች ከተዘጉ መሰነባበታቸውን፣ በድንበሮች አካባቢ ከፍተኛ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን፣ የንግድና የሥራ እንቅስቃሴዎችም በከፊል መቋረጣቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የዶላር ግኝት አለኝታችን የሆነውና ከአገራችን አልፎ የአፍሪካችን የኩራት ምንጭ የሆነው አየር መንገዳችን እንቅስቃሴው በከፊል ተገቷል፡፡ የአበባ ኤክስፖርት ንግዳችን የሚያንሰራራበት ጊዜ በውል ባልታወቀ አጣብቂኝ ውስጥ ተቀርቅሯል፡፡ በኤክስፖርት፣ በማኑፋክቸሪንግና በፋይናንስ ዘርፎቻችን ላይ የተደቀነው ተግዳሮት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ምንም እንኳ እየገጠመን ያለው ችግር ከዚህ በፊት እንዳየናቸው አደጋዎች የማያልፍ ቢመስልም፣ ማለፉ ግን አይቀርም፣ ስለተመኘን ሳይሆን በትብብር ስለምንሠራ ይህ ጊዜ ያልፋል፡፡ ከወዲሁ ዕውቀታቸውን፣ ሀብታቸውን፣ ጊዜና ጉልበታቸውን በመስጠት የትብብር አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ እያሳዩን ያሉ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ምስክር ናቸው፤›› በማለት ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ ተስፋ ግን ብዙ ሥራ እንደሚፈልግ ከዓለም ዙሪያ የሚወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡ በዚህ አሳሳቢ ጊዜ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማሩና ያላቸውን እየለገሱ ቫይረሱን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት የሚደግፉ በርካታ ሰዎች ቢኖሩም፣ በጣም ብዙዎች ግን በፍራቻ ውስጥ ሆነው ግራ ሲጋቡ የዚያኑ ያህል ደግሞ ያልተገቡ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ ተስተውለዋል፡፡ ችላ ባይነት፣ አጋጣሚውን ላልተገባ ትርፍ መጠቀም፣ ዘረፋ መፈጸምና በሕዝብ ደኅንነትና ጤና ላይ አደጋ የሚጋርጡ ድርጊቶች በተለያዩ አገሮች እየታዩ መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡ ብዙዎቹ በቤት ውስጥ መቀመጥን ያወጁ አገሮች ሥራ በማቆማቸው ምክንያት ችግር ለሚገጥማቸው ወገኖች መጠባበቂያ በጀት ባለመመደባቸው፣ ወደፊት ሁከት ሊቀሰቀስባቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ከአሁኑም በአንዳንድ አገሮች ምልክቶች እየታዩ መሆናቸው እየተሰማ ነው፡፡

ሕዝቡ በአብዛኛው ወደ ቤት ክተት በተባለባት አሜሪካ ራስን ለመጠበቅ ይሁን ወይም ወደፊት ችግር ቢያጋጥም ለዘረፋ ለመጠቀም ባለየበት ሁኔታ፣ የጦር መሣሪያ ሸመታ ለመፈጸም በርካቶች ሠልፍ ይዘው ታይተዋል፡፡ በመጋቢት ወር በተከናወነው በዚህ ሪከርድ የሰበረ የጦር መሣሪያ ሸመታ ምክንያት፣ ኤፍቢአይ 3.7 ሚሊዮን የሸማቾች የማንነት ዳራ ፍተሻዎች (Background Checks) ማድረጉ ታውቋል፡፡ ይህም በሃያ ዓመታት ውስጥ ያልታየ ተብሏል፡፡ መሣሪያ ሻጮች ለሚዲያዎች እንደተናገሩት ብዙዎቹ ሸማቾች ለመጀመሪያ ጊዜ መሣሪያ እየታጠቁ ነው፡፡

የመሣሪያ ሸመታው ያሳሰባቸው ደግሞ ኮሮና ቫይረስ አሜሪካን እያሸበረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ መሣሪያ መታጠቅን ምን አመጣው እያሉ ነው፡፡ ከመሣሪያ ጋር ትውውቅ የሌላቸው በገፍ ሸመታ ውስጥ መግባታቸው፣ ወደፊት አጠራጣሪ የሆነ ችግር ሊፈጠር እንደሚችል አመላካች ነው ሲሉም ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሥራቸውን እንዳጡ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከእጥፍ በላይ እያሻቀበ ብዙዎችን የመንግሥት ድጎማ ጠባቂዎች ያደርጋቸዋል ተብሏል፡፡ ሥራ ያጡና የሚበሉት የሌላቸው ደግሞ ወደ ወንጀል ድርጊት ሊያመሩ ይችላሉ የሚለው ግምት አይሏል፡፡

በአፍሪካ አኅጉር ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥር የተመዘገበባት ደቡብ አፍሪካ ዜጎች በቤታቸው ብቻ እንዲወሰኑ መመርያ ካወጣች በኋላ፣ የፀጥታ አስከባሪዎችና መመርያውን ከሚጥሱ ሰዎች ጋር እየተጋጩ ነው፡፡ የዕለት ምግባቸውን ከግሮሰሪዎች ለመግዛት ከሚወጡ ጀምሮ፣ በመንገዶችና በፓርኮች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መብዛታቸው የፀጥታ አስከባሪዎች የፕላስቲክ ጥይቶችን እንዲተኩሱ አስገድዷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ጆሐንስበርግ ውስጥ እንደ አሌክሳንድራን በመሳሰሉ የከተማው ክፍሎች ወስጥ የሚኖሩ ሰዎች፣ በድህነታቸው ምክንያት አንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ በብዛት ተፋፍገው ስለሚኖሩ፣ ቤት ከመቀመጥ ፓርክ ውስጥ መቆየት እንደሚሻላቸው ተናግረዋል፡፡

ለሲቢኤስ ኒውስ ጋዜጠኛ፣ ‹‹ስድስትና ከዚያ በላይ ያሉበት ጠባብ ክፍል ውስጥ መታጎር ያው ከኮሮና የማይተናነስ ስለሆነ ውጭ ለመውጣት ተገድጃለሁ፡፡ ለመሆኑ በእንዲህ ያለው ሁኔታ እስከ መቼ ነው መቆየት የሚቻለው?›› ሲል አንድ ስሙ ያልተገለጸ ሰው ምሬቱን ተኗግሯል፡፡ በሌላ በኩል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ወትሮም የሚታወቀው ወንጀል በዚህ ከባድ ጊዜ ገጽታውን ቀይሮ እንዳይመጣ የሚሠጉ አሉ፡፡ ድህነት ከመጠን በላይ በሚታይባቸው አካባቢዎች ቤት ውስጥ መቀመጥን ብቸኛ አማራጭ ማድረግ፣ ታይቶ ለማይታወቁ ወንጀሎች በር መክፈት ነው ሲሉም ወቀሳዎች ይሰማሉ፡፡ በኬንያ የፀጥታ ኃይሎች የመንግሥት መመርያ አላከበሩም ባሉዋቸው ሰዎች ላይ እየወሰዱዋቸው ያሉ የኃይል ዕርምጃዎች ሰብዓዊ መብትን የሚጋፉ ናቸው ከመባል አልፎ፣ ከዚህ በፊት ታይቶ ለማይታወቅ ሁከትና ቀውስ ምክንያት እንዳይሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የዕለት ጉርሳቸውን ፍለጋ የወጡ ሰዎችን መደገፍ ሲገባ፣ የኃይል ዕርምጃ ውስጥ መግባት የከፋ መዘዝ እንደሚያስከትል እየተሰማ ነው፡፡

በኮሮና ቫይረስ ከተጎዱ አገሮች ግንባር ቀደም በሆነችው ጣሊያን ድህነት የተንሰራፋባቸው ሥፍራዎች፣ ወደፊት አስፈሪ በሆኑ ሁከቶች ከፍተኛ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል ከወዲሁ አመላካቾች እየታዩ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ ዘ ጋርዲያን ሰሞኑን ይዞት በወጣው ዘጋባ ኮሮና ቫይረስ ጣሊያንን ባስጨነቀበት ጊዜ፣ ‹‹ሁሉም ነገር መልካም ይሆናል›› እያሉ ከባልኮኒዎቻቸው ሆነው በጋራ ሲዘምሩ የነበሩ ጣሊያናውያን፣ አሁን መዝሙራቸውን አቁመው ወደ አመፅ እያመሩ ነው፡፡ በተለይ በደቡብ ጣሊያን የሚኖሩ ብዙ ሰዎች ከቫይረሱ ይልቅ ድህነታቸው ስለበረታ፣ ‹‹አሁን ሁሉም ነገር ጥሩ አይደለም›› በማለት ፍርኃትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ የገቡ ብዙ ናቸው ተብሏል፡፡ ‹‹ብዙዎች ሥራ በማቆማቸው ተርበዋል፣ በዚህም ምክንያት በምግብ ባንኮች (ማደያዎች) በር ረጃጅም ሠልፎች አሉ፤›› ሲሉ የናፖሊ ከተማ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ሳልቫቶሬ ሜሉሶ መናገራቸውን በዘገባው ተመልክቷል፡፡

ምንም እንኳ ደቡባዊው የጣሊያን ግዛት ከሰሜኑ አንፃር የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትና ሞት በጣም ዝቅተኛ ነው ቢባልም፣ ወረርሽኙ በሰዎች ኑሮ ላይ ግን ትልቅ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ዘገባው ያስረዳል፡፡ በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች ምግብና ገንዘብ በማጣታቸው በደቡብ ጣሊያን ካምፓሊያ፣ ካላብሪያ፣ ሲሲሊና ፑግሊያ ውጥረት መስፈኑ ተገልጿል፡፡ አነስተኛ ኪዮስኮች ያሉዋቸው ነጋዴዎች ምግብ በነፃ እንዲሰጡ እየተገደዱ መሆናቸውን ሪፖርት መደረጉን፣ በሱፐር ማርኬቶች ፖሊሶች ጥበቃ እያደረጉ መሆናቸውንና ዝርፊያዎች መፈጸማቸውን መሰማቱን ዘ ጋርዲያን ከሮምና ከፓሌርሞ ባጠናቀረው ዘገባ አስነብቧል፡፡

ሁከትና ተስፋ መቁረጥ በስፋት እየታዩ ባለበት ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ መንግሥት 4.3 ቢሊዮን ዩሮ ከሶሊዳሪቲ ፈንድ ለሁሉም ማዘጋጃ ቤቶች ለተለያዩ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ለምግብ አቅርቦት 400 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን ቢያስታውቅም፣ የከተሞች ከንቲባዎች ግን የምግብ በጀቱ በቂ አይደለም በማለት ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ የካታኒያ ከንቲባ ሳልቮ ፖግሊዜ፣ ‹‹እኛ የምንጠብቀው ከዚህ የበለጠ ነው፣ ተስፋ አደርጋለሁ መንግሥት ለዚህ የተሻለ መንገድ ይፈልጋል፤›› ብለው፣ የነዋሪዎች ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ከመሆኑም በላይ ገቢያቸውም ዜሮ ሆኗል ሲሉ ችግሩን ገልጸዋል፡፡ ‹‹በፊት በክብር ይኖሩ የነበሩት አሁን በአስቸጋሩ ሁኔታ ውስጥ ናቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ አጋጣሚውን የተደራጁ ወንጀለኞች ባይጠቀሙበትም፣ በወረርሽኙ ምክንያት ከቤት እንዳይወጣ የተደረገው የጣሊያን ደቡባዊ ክፍል ሕዝብ ግን፣ ያለው የመጨረሻ አማራጭ ዝርፊያና ከቁጥጥር የወጣ አመፅ እንዳይሆን ተሠግቷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተደራጁ ወንጀለኞች ከመጠን በላይ ገንዘብ ስላላቸው የተቸገሩ ሰዎችን ለዓላማቸው ሊመለምሉ እንደሚችሉም ሥጋት አለ፡፡

በኢትዮጵያ ከመንግሥት ሠራተኞች የተወሰኑት በቤታቸው እንዲገደቡ ቢደረግም፣ የአገልግሎት መስጫዎች ሙሉ በሙሉ ባይቋረጡም፣ ብዙዎቹ ክልሎች የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቆም ቢያደርጉም፣ በአብዛኛው አካላዊ ርቀትና ንፅህና መጠበቅ ላይ የሚያተኩሩ መልዕክቶች ቢተላለፉምና ከጊዜ ወደ ጊዜ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት አሳሳቢነት ሥጋት እየጨመረ ቢመጣም፣ ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴን ገድቦ ሰዎችን ቤት እንዲቀመጡ ማድረግ ላይ ግን የተደባለለቁ ስሜቶች ይሰማሉ፡፡ በሕዝብ ትራንስፖርት፣ በገበያዎች፣ በቤተ እምነቶችና በመኖሪያ አካባቢዎች የሚታዩ ቸልተኝነቶችን በተለያዩ አማራጭ ዕርምጃዎች ለመግራት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ በቂ አይደሉም በማለት ሙሉ በሙሉ ቤት ዘግቶ መቀመጥ ተገቢ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የዕለት ጉርሳቸውን ሊያጡ የሚችሉ ሚሊዮኖችን ከቤት እንዳይወጡ ማድረግ አደጋ አለው የሚሉም አሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥት አሁን በያዘው ሁኔታ ከበድ ያሉ የሕግ ማስከበር ዕርምጃዎችን በማከል፣ ሰዎች ሥራቸውን እያከናወኑ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን መግታት እንደሚቻል፣ በተቃራኒው ከሄደ ግን ምግብ ያጡ በርካቶች ወደ ወንጀል እንደሚያመሩ መጠራጠር አይገባም ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሁለተኛውን ዓመት የለውጥ ጉዞ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹እስካሁን ባለው ጉዟችን የአገራችንን ኢኮኖሚ፣ ተቋማቶቿን፣ የፍትሕ ሥርዓቷን፣ ማኅበራዊ ደኅንነቷን፣ የሕግ አስከባሪ አካላትን፣ የጤናና የትምህርት ሥርዓቷን በማጠናከር ፈተናዎችን መቋቋም በሚችሉበት ደረጃ ለማደራጀት ጠንካራ የአቅም መሠረት መጣል ጀምረናል፤›› ካሉ በኋላ፣ አቅም ግንባታ ስትራቴጂካዊ ዕይታን የሚጠይቅ፣ ተከታታይ ሥራን የሚፈልግና ፈጽሞ የማያቋርጥ ረጅም ሒደት መሆኑ ግልጽ እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹ይህም ደግሞ እንደኛ ደሃ በሆኑ አገሮች ብቻ ሳይሆን፣ በኢኮኖሚ ግንባር ቀደም የሆኑትን ጭምር የሚመለከት መሆኑ የሰሞኑ ዓለም አቀፋዊ ፈተና ምስክር ነው፤›› ማለታቸው፣ ኢኮኖሚው አሁንም የማያወላዳ መሆኑን እንደሚያመለክትና እንዲያው በቀላሉ አገሪቱን ሙሉ ለሙሉ ዘግቶ መቀመጥ እንደማይቻልም ማሳያ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሮና ቫይረስንና የህዳሴ ግድቡን አስመልክተው ረቡዕ መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ባስተላለፉት መልዕክት፣ ጊዜያቸውን በሥራ ሲያሳል ለነበሩ ሰዎች ለኮሮና ሲባል ቤት ውስጥ መቀመጥ አስቸጋሪ ነው ብለው ነበር። ‹‹ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሳራዎችን ሊያደርስብንም ይችላል፡፡ ሆኖም በሌላ በኩል ካየነው ይኼንን አጋጣሚ ለመልካም ተግባራት ልናውለው እንችላለን፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው ፍቅር የሚሰጡበት፣ ባለትዳሮች ስለቀጣይ የሕይወታቸው ምዕራፍ በሰፊው የሚያቅዱበት፣ እንዲሁም ማንበብ የሚፈልጉ ሰዎች ጊዜ ወስደው እንዲያነብቡ፣ የሚጽፉ ሰዎች ጊዜ አግኝተው እንዲያሰላስሉ፣ የሚመራመሩ ሰዎች እንዲመራመሩ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡ በዚህ መንገድ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ውጭ ከመውጣት ተቆጥበው ቤታቸው የሚያሳልፉ ዜጎቻችን ራሳቸውንና ሌሎችንም ከክፉው ወረርሽኝ ከማዳን በዘለለ፣ ወረርሽኙ አልፎ ሁሉም ነገር ሲረጋጋ ብዙ መልካም ነገሮችን ማትረፋቸው አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡ ይህ አባባል የትኛውን የማኅበረሰብ ክፍል እንደሚመለከት ግልጽ ነው በማለት፣ የሚሊዮኖች ዕጣ ፈንታ ምን መሆነ አለበት ሲሉ አስተያየት የሰጡም አሉ፡፡

በሌላ በኩል የጂኦ ፖለቲክስ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት የግድ መሆኑን እንደሚያምኑ፣ ወረርሽኙን መከላከል የሚቻልበት ዋናው መንገድ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና እንቅስቃሴን በመገደብ ስለሆነ መንግሥት እዚህ ላይ ማተኮር እንዳለበት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው የዕለት ጉርሱን ለማግኘት የሚማስነውን ብዙኃኑን ሕዝብ ታሳቢ በማድረግ ነው ሲሉም ህንድን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡ የህንድ መንግሥት ዜጎች ከቤታቸው ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ ድንጋጌ ሲያወጣ የዕለት ጉርስ ለሌላቸው ወገኖች 24 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን አስረድተው፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም በተቻለ መጠን ዛሬ በልተው ነገ የሚበሉት ለሌላቸው መፍትሔ መፈለግ አለበት ሲሉ አቶ ልዑልሰገድ አሳስበዋል፡፡

የአቅም ጉዳይ ቢፈታተን እንኳ ያሉትን አማራጮች በሙሉ በማየት ትኩረቱን የሚበሉት የሌላቸው ወገኖች ላይ በማድረግ፣ ሙሉ በሙሉ ቤት የመቀመጥ ድንጋጌ ማውጣት የሚያስችለውን ተግባር በፍጥነት መጀመር አለበት ሲሉም ተናግረዋል፡፡ አቶ ልዕልሰገድ ያነሱት ሌላው ነጥብ ሠርተው በጥረታቸው ካገኙ ጥቂቶች ውጪ በአብዛኛው በዘረፋ በተገኘ ሀብት ምግብና ምግብ ነክ አቅርቦቶችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያከማቹ እንደ አሸን የፈሉ የኢፍትሐዊ ሥርዓት ተጠቃሚዎች ባሉበት አገር ውስጥ ምንም የሌላቸውን ችላ በማለት ሙሉ ለሙሉ መዝጋትም ሆነ፣ ምንም ጉርስ የሌላቸውን ወገኖች ለመርዳት አቅም የለም በማለት ቤት ውስጥ የመቀመጥ ድንጋጌ አለማውጣት መዘዙ የከፋ መሆኑን ነው፡፡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመግታት ከሕይወት የሚቀድም ስለሌለ፣ ማናቸውም የአገር ሀብት ሥራ ላይ ውሎ በቶሎ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት አማራጭ የለውም ሲሉ አክለዋል፡፡ ለዚህም ሲባል መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የሚደረጉ እጅን ቶሎ ቶሎ በውኃና በሳሙና እንዲሁም በሳኒታይዘር ማፅዳት፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና በአንድ ሥፍራ መሰባሰብ እንደማይገባ ማሳሰቢያዎች አሁንም እየተሰጡ ቢሆንም፣ ተግባራዊነታቸው ላይ ለማመን የሚያዳግቱ ክፍተቶች እንዳሉ ብዙዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እያስታወቁ ነው፡፡ ማሳሰቢያዎቹ ተፈጻሚ መሆን ባለመቻላቸው ምክንያት የሚሊዮኖች ሕይወት አደጋ ውስጥ መግባት ስለሌለበት ሙሉ ለሙሉ መዝጋት አስፈላጊ ነው የሚሉ እንዳሉ ሆነው፣ ተከታታይና የማያቋርጥ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ያለመታከት በመስጠት ይህንን ክፉ ጊዜ ማለፍ ያስፈልጋል የሚሉም አሉ፡፡ በብድርና በዕርዳታ ላይ ጥገኛ የሆነ ኢኮኖሚ ያላት አገር ውስጥ ሆኖ ያለ የሌለ ሀብትን ማባከን ዋጋ ያስከፍላልም ይላሉ፡፡ ኮሮና ቫይረስ መፍትሔ አግኝቶ ዓለም ወደነበረበት ሲመለስ፣ ብዙ ባለፀጋ አገሮችና አበዳሪ ተቋማት ሳይቀሩ ደቀው ነው የሚገኙትና ለዕርዳታም ሆነ ለብድር ማንጋጠጥ አይቻልም ሲሉም ያክላሉ፡፡

እነዚህን የሚሞግቱ ወገኖች ግን መጀመሪያ የሚሊዮኖችን ሕይወት ማዳን ይቅደም፣ ከዚያ በኋላ ስለመጪው ጉዳይ ወቅቱ ይፈታዋል ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜም ኢመደበኛ በሚባለውና ለመኖር የዕለት ተዕለት ጥረት በሚባለው ዘርፍ ውስጥ ያሉ በርካቶች፣ ሥራ ባለመኖሩ ምክንያት ለችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም ሲሉ ያሳስባሉ፡፡ ከኢንዱስትሪ ፓርኮችና ከተለያዩ ማምረቻዎችና ማከፋፈያዎች የተቀነሱ፣ የአገር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመቆሙ ሥራቸውን ያጡ፣ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች ገቢ የሌላቸው ሰዎችን በደፈናው ቤት ውስጥ ተቀመጡ ከማለት ባሻገር ወቅቱን የሚመጥን ስትራቴጂ መንደፍ እንደሚያስፈልግ ማሳሰቢያ እየተሰጠ ነው፡፡ ያለበለዚያ ረሃብ ሰዎችን ለከፋ ድርጊት ሊያነሳሳ ይችላል ሲሉም ያስጠነቅቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -