Friday, December 8, 2023

በወረርሽኙ ምክንያት የተዘጉ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎቻቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ማሳወቅ ጀመሩ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የዓለምን ሕዝቦች በማስጨነቅ ላይ በሚገኘው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከመጋቢት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተዘጉት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ ለውሳኔ ቀጥረዋቸው በነበሩት የፍትሐ ብሔር መዝገቦች ላይ ውሳኔ እየሰጡ በማኅበራዊ ትስስር ገጾችና በማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ በመለጠፍ ማሳወቅ ጀመሩ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ፣ ከፍተኛና የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በየቀኑ በጣም በርካታ ሰዎች ከሚሰበሰቡባቸው ቦታዎች ቅድሚያውን እንደሚይዙና ለወረርሽኙ መስፋፋትና መዛመትም አደገኛ በመሆናቸው ምክንያት፣ ለአሥራ አምስት ቀናት ተዘግተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

የወረርሽኙ ሥርጭት መቀጠሉን በመግለጽ ፍርድ ቤቶች ለተጨማሪ 23 የሥራ ቀናት እስከ ሚያዝያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ተዘግተው እንዲቆዩ ውሳኔ መተላለፉን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳን ወረርሽኙ በ15 ቀናት ውስጥ መሻሻሎችን ባያሳይም፣ የሦስቱም ፍርድ ቤቶች ዳኞች ግን ሥራቸውን ሲያከናውኑ መክረማቸውን የፕሬዚዳንቷ ቃል አቀባይና የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ነዋይ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ዳኞች ለውሳኔ ተቀጥረው የነበሩ 1,500 መዝገቦች ላይ ባለፉት 15 ቀናት ውሳኔ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ዳኞቹ የሠሯቸውን የፍትሐ ብሔር ፍርዶች ባለጉዳዮቹ ማወቅ ስላለባቸው፣ በፍርድ ቤቶቹ ቅጥር ግቢ ውስጥ ባሉ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ የውሳኔው አጭር መግለጫ ማለትም፣ ‹‹ለከሳሽ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ተወስኗል፣ ወይም ውድቅ ተደርጓል›› ተብሎ እንደሚለጠፍ አስረድተዋል፡፡ በትስስር ገጾች ማለትም በፌስቡክና በኤስኤምኤስ (በአጭር ጽሑፍ) እንደሚገለጽ አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

የወንጀል መዝገቦች ለውሳኔ የተቀጠሩ ቢሆንም፣ የራሳቸው የአካሄድ ሥነ ሥርዓት ስላላቸው በዚህ ወቅት ላይ እንደማይታዩም አክለዋል፡፡

የፍትሐ ብሔር ክሶችንም በሚመለከት በከሳሽ ወይም በተከሳሽ በኩል የሚቀርቡ ተጨማሪ ማስረጃዎች ቢኖሩ፣ እንዲሁም ተከሳሽ መከሰሱን ሳይሰማ ቀርቶ በፍርድ እንደተቀጠረ ቢሰማና ማመልከቻ ለማቅረብ ቢፈልግ እንዴት ማድረግ እንደሚቻል የተጠየቁት አቶ ተስፋዬ፣ አንድ መዝገብ ለውሳኔ የሚቀጠረው ብዙ ሒደቶችን አልፎ ነው ብለዋል፡፡ ተከሳሾች ከክሳቸውና ከመልሳቸው ጋር አያይዘው ማስረጃዎቻቸውን ስለሚያቀርቡ ጊዜ ለማጓተትና ለማዘግየት ካልሆነ በስተቀር ያን ያህል ወሳኝ የሆነ ማስረጃ ይቀርባል ተብሎ አይታሰብም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 256 መሠረት ማስረጃው ልዩ ከሆነ ሊቀርብና በተረኛ ችሎት ሊታይ እንደሚችል ገልጸው፣ ዳኛው ለፍትሕ አሰጣጥ ይጠቅማል ብሎ ካመነበት ብቻ ሊቀበለው እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ በክርክር ወቅት የቀረበለት ማስረጃ በቂ መሆኑን ካመነም ላይቀበለው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ አንድ መዝገብ ለውሳኔ የሚቀጠረው ረዥም ክርክር ተደርጎበት፣ ማስረጃዎች ተያይዘውና የማጠቃለያ ሐሳብ ከቀረበበት በኋላ በመሆኑ፣ በልዩ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር ያን ያህል እንደማይሆንና ልዩ ሆኖ ከተገኘም በተረኛ ችሎት ሊታይ እንደሚችል አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ ችሎት የሚሠሩ ቁጥራቸው ሦስትና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ዳኞች ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ  ስለሚያነሱት ሥጋት  የተጠየቁት ቃል አቀባዩ፣ የተባለው ትክክል መሆኑንና ዳኞቹም እየሠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ሌሎችም ዳኞች በቤታቸው ቢሆኑም በሥራ ላይ መሆናቸውን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ውዝፍ መዝገቦችን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ሲገባ ፍርድ ቤቶችን ነፃ ለማድረግ እየተሠራ  መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ፍርድ ቤቶች በሚከፈቱበት ወቅት በርካታ አዳዲስ መዝገቦች ሊከፈቱ ስለሚችሉ፣ የነበሩ መዝገቦችን ጨርሶ ለመግባት ዳኞች በትጋት እየሠሩ  መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

የዳኞችን ሥጋት ለመቅረፍና ወደፊትም አሠራሮችን በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ ዳኞች በጉግል ሀንግ አውት እንዲወያዩ እየተሠራ መሆኑን፣ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ክርክሮች የሚደረጉበትና ውይይቶችም የሚካሄዱበትን አሠራር ለመተግበር እየተሠራ እንደሆነ፣ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆንና ሥጋቶችን መቅረፍ እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -