Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናምርጫ ቦርድ ምርጫው ለምን እንደተላለፈና ለፓርላማ ሪፖርት ያደረገበትን ምክንያት አስታወቀ

ምርጫ ቦርድ ምርጫው ለምን እንደተላለፈና ለፓርላማ ሪፖርት ያደረገበትን ምክንያት አስታወቀ

ቀን:

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጉዳዩ ላይ በሁለት ዙር ተወያይቻለሁ ብሏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማክሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ምርጫው ለምን እንደተላለፈና ለፓርላማም ሪፖርት ያደረገበትን ምክንያት አስታወቀ፡፡ ምርጫውን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ማካሄድ ለምን እንደማይቻልና ከዚህ በኋላ ምን ዓይነት ሥራዎች እንደሚኖሩት በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

ምርጫ ቦርድ መጋቢት 24 ቀን 2012 .ም. መግለጫ ማውጣቱን አስታውሶ፣  በመግለጫው ዋና ዓላማ ምርጫውን ቀድሞ ባቀደው ቀን ማለትም ነሐሴ 23 ቀን 2012 .ም. ማከናወን እንደማይችል ማሳወቅ መሆኑን ገልጿል፡፡ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጥናት ማካሄዱን፣ ተጠሪነቱም ለተወካዮች ምክር ቤት ስለሆነ ውሳኔውንም ለተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁን፣ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት ምርጫውን ማከናወን ካለመቻሉ በስተቀር የተራዘመ ቀን ቆርጦ አለማቅረቡን አመልክቷል፡፡ ማድረግ ያለበትም አለመቻሉን ብቻ ገልጾ ሪፖርት ለሚያደርግለት ለተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቅ ብቻ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት መጋቢት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫውተገለጹትን ዋና ዋና ውሳኔዎቹን  አስታውሷል፡፡ በኮቪድ-19 የተነሳ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ማካሄድ የማይቻለው መሆኑን በመረዳት ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሠረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ፣ ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን ዕቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን እንደሚያስጀምር፣ በኮቪድ 19 የማይስተጓጎሉና የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ መቆየት እንዳለበት፣ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ምክር ቤቱ ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንፃር የሚሰጠው ውሳኔ ቢኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ውሳኔ ላይ መድረሱን፣ እንዲሁም ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍለት እንደነበረ አስረድቷል፡፡

ቦርዱ ውሳኔውን ለተወካዮች ምክር ቤት ያሳወቀበትን ምክንያት ሲያብራራ፣ ተጠሪነቱ ለተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን፣ የአፈጻጸም ሪፖርቶችን የሚያቀርበውም ለምክር ቤቱ እንደሆነና ውሳኔውን ለተወካዮች ምክር ቤት ከማሳወቅ ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው ጠቁሟል፡፡ ቦርዱ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ችግሩን ለተወካዮች ምክር ቤት ከማቅረብና በጥናት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ከማድረግ ውጪ፣ ከሥልጣኑ ክልል በመውጣት የሠራው ወይም ሥልጣኑ ኖሮት ሳይወጣ የቀረው ኃላፊነት አለመኖሩን አክሏል፡፡

ኮቪድ 19 በምርጫው ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር መደረጉን፣ ያደረገው ምክክርም በሁለት ዙር ሆኖ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለያዩ አስተያየቶችን መስጠታቸውን፣ የሰጧቸው አስተያየቶችምችግሩን ዓለም አቀፍነት፣ በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስና በምርጫ ሥራ ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖ እንደሚረዱ መግለጻቸውን አስረድቷል፡፡ ፓርቲዎቹ ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በመመካከር እንዲሠራ መጠየቃቸውን፣ ከዚህም በተጨማሪ ቦርዱ ምክክሩን ማድረጉን አድንቀው መንግሥት ያስቀመጠው 14 ቀናት ክልከላ ታይቶ ቢወሰን የሚል አማራጭም ማቅረባቸውንና ውይይቱ በመግባባት የተጠናቀቀ መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይህንን ዕድል የአገሪቱንለቲካ ለማስተካከልም ሆነ በቂ ዝግጅት ለማድረግ መጠቀም እንደሚገባ፣ ይህ ውሳኔ በቦርዱ መወሰን እንዳለበት፣ ፓርቲዎችን ማማከር ጥሩ ቢሆንም ውሳኔው ከፓርቲዎች በላይ መሆኑን፣ በአገር የመጣ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ለመቋቋምም ሁሉም ፓርቲዎች ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው መናገራቸውን አስረድቷል፡፡ ቦርዱ የተለያዩ ተጨማሪ ምክክሮችን ለማድረግ ያሰበ ቢሆንም፣ የመጀመሪያው ውይይት የተካሄደው የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ በተገኘ በሦስተኛው ቀን በመሆኑ ከዚያ በኋላ ያሉ ክልከላዎች መጠናከራቸውና የተለያዩ ዕርምጃዎች በክልሎችም ጭምር በመወሰዳቸው ክልከላዎችን መጣስ ስለማይቻል፣ እንዲሁም ኮቪድ 19 የደቀነው አደጋ በጣም ግልጽ መሆኑን ፓርቲዎችም እንደሚረዱ በማመኑ ከፓርቲዎች የተገኘው ግብዓት በቂ ሆኖ ለውሳኔው እንደ ግብዓት ስለተጠቀመበትበመግለጫው እንዳሳወቀው ውሳኔውን በሚወስንበት ወቅት የፓርቲዎችን አስተያየት እንደ ግብዓት ከተጠቀመባቸው መረጃዎች አንዱ መሆኑን አብራርቷል፡፡

የቦርዱ ሥራ ከዚህ በኃላ ምን እንደሚሆን ሲያስረዳም፣ ‹‹ቦርዱ በአሁኑ ወቅት አብዛኞቹ ሠራተኞቹ ከቤት ሆነው የቀሩት ደግሞ በፈረቃ ሥራውን በማከናወን ላይ ሲሆኑ፣ መሰብሰብ የማያስፈልጋቸው ሥራዎቻቸው ማኅበራዊ መራራቅን ተግባራዊ በማድረግ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስችል ሁኔታ የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ ይቆያል፤›› ብሏል፡፡ በዚህም መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ዲጂታል ኮሙዩኒኬሽን መረጃ እየሰበሰበ መሆኑን፣ ከፓርቲዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነትም በተቻለ መጠን በዲጂታል ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርግ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...