Sunday, October 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሮና ቫይረስ በሚፈጥረው የኢኮኖሚ ቀውስ እስከ 1.5 ሚሊዮን  ሠራተኞች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢኮኖሚ ቀውሱን ለመቋቋም መንግሥት 90 ቢሊዮን ብር መበጀት እንዳለበትም ጠቁሟል

በኢትዮጵያ ኮሮና ቫይረስ ሊፈጥረው በሚችለው የኢኮኖሚ ቀውስ፣ ከ750,000 እስከ 1.5 ሚሊዮን በሚደርሱ ሠራተኞች ላይ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ።

መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው ሲፈስ (CEPHUS) የተባለ የማክሮ ኢኮኖሚ ጥናትና ትንተና ላይ የሚሠራ ድርጅት፣ ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት የተመለከተ ባለ 21 ገጽ መረጃዎችን መሠረት ያደረገ የማክሮ ኢኮኖሚ ትንታኔ ይፋ አድርጓል።

ተቋሙ የማክሮ ኢኮኖሚ ትንታኔውን ያቀረበው መንግሥት በአገሪቱ ያለውን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት አስመልክቶ በሚሰጠው መረጃ ላይ በመንተራስ ሲሆን፣ አሁን ባለው ሁኔታ የቫይረሱ የሥርጭት መጠን የተወሰነ በመሆኑ በኮንስትራክሽንና በግብርና ዘርፎች ላይ የሚያደርሰው የኢኮኖሚ ጉዳት መጠነኛ መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑም ትንታኔው የተገለጹትን የኢኮኖሚ ዘርፎች በመተው አሁን ባለው የቫይረሱ ሥርጭት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውንና እየደረሰባቸው ባሉት የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ በማተኮር፣ ይህ ሁኔታ ባለበት ለመጪዎቹ ስድስት ወራት ቢቀጥል የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በ2.5 በመቶ እንደሚቀንስ ገልጿል።

በመሆኑም የቫይረሱ ሥርጭት ወደ ከፋ ደረጃ ካልተሸጋገረ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት በ2.5 በመቶ ቀንሶም ቢሆን፣ አምስት በመቶ ዕድገት ሊያስመዘግብ እንደሚችል ተንብይዋል።

አሁን ያለው የቫይረሱ ሥርጭት የከፋ ጉዳት የሚያደርስባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች፣ የሆስፒታሊቲ (የሆቴል፣ የቱሪዝምና የመስተንግዶ)፣ የኤክስፖርት  (በዋናነትም የአበባና የጨርቃ ጨርቅ ኤክስፖርት)፣ እንዲሁም የተወሰኑ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ባንኮች መሆናቸውን ገልጿል።

አሁን ባለው የቫይረሱ ሥርጭት ሁኔታና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ መንገደኞች መገደብ ጋር ተያይዞ የሆቴል፣ የመጠጥና የምግብ አቅርቦት የሚሰጡ የንግድ ተቋማት ደንበኞችን ማግኘት እንዳልቻሉ፣ በተለይ ሆቴሎች ባዷቸውን በመቅረታቸው አንዳንዶቹ በክፍያ አንዳንዶቹ ደግሞ ያለ ክፍያ ሠራተኞቻቸውን አስገዳጅ እረፍት በማስወጣት ላይ መሆናቸውን ጥናቱ ጠቁሟል።

የአበባና የሆርቲከልቸር ዘርፉ በቫይረሱ ምክንያት በአውሮፓ ገበያ ማጣቱን የሚገልጸው ጥናቱ፣ መንግሥት በዚህ ዘርፍ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በማለት ጥሎት የነበረውን አስገዳጅ ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ በቅርቡ ቢያነሳም ትርጉም ያለው ለውጥ እንደማይኖረው ጠቁሟል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ 1,200 ሆቴሎች በትንሹ በአማካይ 50 ሺሕ ሠራተኞች እንዳሏቸው፣ የአበባና የሆርቲከልቸር ዘርፉ 150 ሺሕ ሠራተኞችን እንደሚቀጥር፣ በአዳስ አበባ ከተማ የሚገኙ 20 ሺሕ የትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የፈጠሩትን የሥራ ዕድል፣ እንዲሁም በአጠቃላይ የቫይረሱ ሥርጭት በአነስተኛ የንግድ ተቋማት ላይ የሚያደርሰው ከፍተኛ የንግድ መቀዛቀዝን ከግምት ያስገባል።

ተቋሙ በራሱ ጥናት የለየውን ጉዳት በሚደርስባቸው ዘርፎች የተቀጠሩ ሠራተኞችን አኃዝና የማዕከላዊ የስታትስቲክስ ኤጀንሲ በተጠቀሱት ዘርፎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችን ብዛት አስመልክቶ ያወጣውን መረጃ በመጠቀም፣ የቫይረሱ ሥርጭት በሚያደርሰው የኢኮኖሚ ጫና ከ750 ሺሕ እስከ 1.5 ሚሊዮን ሠራተኞች ላይ ጉዳትና ከሥራ መቀነስን ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁሟል።

መንግሥት በተጠቀሱት ዘርፎች ጉዳት ለሚደርስባቸውና እየደረሰባቸው ላሉት ሠራተኞች እስካሁን ያስቀመጠው የጉዳት መቋቋሚያ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ አለመኖሩን ያስታወሰው የማክሮ ኢኮኖሚ ጉዳት ትንታኔው፣ ሠራተኞቹ ጉዳቱን ተቋቁመው ማለፍ እንዲችሉ በወር 1,500 ብር መሠረታዊ የደመወዝ ክፍያ ለተወሰኑ ወራት ለመክፈል መንግሥት ማቀድና በጀት መመደብ እንዳለበት ገልጿል። ለዚህም ከ13 እስከ 17 ቢሊዮን ብር መመደብ እንዳለበት አሳስቧል።

በተመሳሳይ ጉዳት የሚደርስባቸው ዘርፎች ተቋቁመው ማለፍ እንዲችሉም መንግሥት ከታክስ ዕፎይታ ጀምሮ፣ የብድር ዋስትና የመስጠት፣ የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው የማድረግ፣ የንግድ ቦታ ኪራይ ክፍያ ዕፎይታ እንዲያገኙ ማድረግን በምክረ ሐሳብነት አቅርቧል። ይህንንም ለመወጣት በአጠቃላይ 90 ቢሊዮን ብር የአስቸኳይ ጊዜ በጀት ሊመድብ እንደሚገባ በምክረ ሐሳብነት አቅርቧል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች