Saturday, December 2, 2023

አብሮነት የምርጫውን መራዘም እንደሚደግፍ አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት ሕዝቡ ትኩረቱ ሳይከፋፈል የሚጠበቅበትን ርብርብ በወረርሽኙ ላይ እንዲያደርግ፣ የምርጫው አለመካሄድ የማይተካ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መሠረት ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲካሄድ ቀን ተቆርጦለት የነበረው አጠቃላይ ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መካሄድ እንደማይችል ማሳወቁ ይታወቃል፡፡ አብሮነትም ይህን ውሳኔ እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

አብሮነት ውሳኔውን የሚደግፈው በሁለት ምክንያቶች መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት የመጀመርያው ኅብረተሰቡ ትኩረቱንና አቅሙን በሙሉ ወረርሽኙ ላይ እንዲያደርግ የሚያስችል መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ‹‹በአሁኑ ወቅት በሁለንተናዊ መልኩ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ ያልሆነችው አገራችን በቂ ጊዜ አግኝታ የተሟላ ዝግጅት እንድታደርግ የምርጫው መራዘም ዕድል ይፈጥራል፤›› ከሚል ዕሳቤ እንደሆነ አስታውቋል፡፡

አብሮነት ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያት የምርጫው ጊዜ እንዲራዘምና የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ሲወተውት መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት አንገብጋቢውና ቀዳሚው የአገሪቱ ችግር የኮሮና ቫይረስን መከላከልና መቆጣጠር መሆን ስለሚገባው፣ ‹‹የፖለቲካውን ጉዳይ ለጊዜው ወደ ጎን አስቀምጠን፣ ሙሉ ትኩረታችንን ወረርሽኙን በመከላከልና በመቆጣጠር ሥራ ላይ ማድረግ አለብን፤›› ሲል አቋሙን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ለረዥም ጊዜ ሲያራምደው የቆየውን የሽግግር መንግሥት መመሥረትና አገራዊ ምክክር የማካሄድ አጀንዳን፣ ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ መተግበር እንዳለበት አሳስቧል፡፡

‹‹ወረርሽኙን በብቃት መከላከላችንን እርግጠኞች ከሆንን በኋላ ግን በፍጥነት ሁሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር ሒደት መጀመርና አገራችንን ወደፊት ሊገጥማት ከሚችል ከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አደጋ መታደግ የምንችልበት ሁኔታ ይመቻች፤›› በማለት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

አብሮነት እንዲቋቋም የጠየቀው አገራዊ የምክክር መድረክ ደግሞ፣ ‹‹ምን ዓይነት የሽግግር መንግሥት ይቋቋም? የሽግግር መንግሥቱ እንዴትና በማን ሊቋቋም ይችላል? የሽግግር መንግሥቱ ዋና ኃላፊነትና ተግባርስ ምን ይሆናል? ዕድሜውስ ምን ያህል ጊዜ መሆን ይገባዋል?›› የሚሉትን ጥያቄዎች ሊመልስ እንደሚገባም አስታውቋል፡፡

አብሮነት በኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ በኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኅብር ኢትዮጵያ) እና በኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሃን) አማካይነት አገራዊ ህልውናን ማስጠበቅ የሚል አጀንዳ ለማራመድ የተቋቋመ የትብብር ስብስብ መሆኑ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -