Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮና ወረርሽኝ 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳጣ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሠራተኞች አልቀነስኩም ብሏል

ሦስት የበረራ አስተናጋጆች በበሽታው ተይዘዋል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኮሮና ወረርሽኝ በፈጠረው ቀውስ ምክንያት 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም ከሌሎች የአየር መንገዱ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላትና የሠራተኛ ማኅበር ተወካዮች ጋር ማክሰኞ መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተሉን ገልጸው የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ቀዳሚ ተጠቂ እንደሆነ አኃዞችን በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የዓለም ሕዝብ 1/3ኛ ከቤቱ እንዳይወጣ እንደተገደደና ዓለም አቀፍ የንግድ፣ የሆቴልና የቱሪዝም ዘርፎች ክፉኛ መጎዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማኅበርን ዋቢ በማድረግ የመጀመርያው ገፈት ቀማሽ የሆነው ዓለም አቀፍ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ፣ 252 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጣ እንደተነበየ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የአፍሪካ አየር መንገዶች 4.2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጡ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ በመሆኑ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከጥር ወር ጀምሮ 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳጣና ትልቅ የገንዘብና የኦፕሬሽን ቀውስ ውስጥ እንደገባ አቶ ተወልደ ተናግረዋል፡፡ 110 የመንገደኛና 17 የጭነት በድምሩ 127 መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 91 መዳረሻዎች እንደተዘጉ፣ 19 የመንገደኞች መዳረሻዎች ብቻ እንደቀሩት ገልጸዋል፡፡ በየቀኑ 350 በረራዎች የነበሩት አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት በቀን በአገር ውስጥ 14፣ በዓለም አቀፍ አሥርና ከዚያ በታች በረራ በማከናወን ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ከገበያ አቅርቦት አንፃር ሲታይ የአየር መንገዱ እንቅስቃሴ 90 በመቶ ቀንሶ፣ በአሥር በመቶ ብቻ አቅም እየበረረ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

አየር መንገዱ ካሉት 120 አውሮፕላኖች 91 ያህሉ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እንዲቆሙ መደረጋቸውን፣ ይህም የቦታ ጥበት እንደፈጠረ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ ስለአየር መንገዱ የተለያዩ የተዛቡ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያና በመደበኛ ሚዲያዎች በመውጣት ላይ እንደሆነ የገለጹት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵየ አየር መንገድ በመብረር ላይ ያለ ብቸኛ አየር መንገድ እንደሆነ የሚነገረው ስህተት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ኤምሬትስ፣ ሉፍታንዛ፣ ኳታር ኤርዌይስ፣ ታይ ኤርዌይስ፣ ብሪትሽ ኤርዌይስ፣ ኤር ፍራንስና የጃፓን አየር መንገዶች በመብረር ላይ እንደሆኑ ጠቁመው  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኮሮና ወረርሽኝ ቀውስ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ቢሆንም በጭነት በረራዎች፣ በቻርተር በረራዎች፣ በአውሮፕላን ጥገና ጥሩ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የካርጎ ዘርፍ ከአየር መንገዱ አጠቃላይ ገቢ ያለው ድርሻ 15 በመቶ፣ የአውሮፕላን ጥገና ከዚያ ያነሰ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ የሕክምና መሣሪያዎችና መድኃኒቶች ፍላጎት በመናሩና ከፍተኛ የጭነት በረራ ፍላጎት በመፈጠሩ፣ የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጂስቲክስ ክፍል ጥሩ በመሥራት ላይ ቢሆንም አየር መንገዱ ያጣውን ገቢ እንደማያካክስ አስረድተዋል፡፡

አየር መንገዱ በሚሰጠው የካርጎና የቻርተር በረራዎች አገልግሎቶች የነፍስ አድን አገልግሎትና የተቆራረጡ ቤተሰቦችን በአብዛኛው ከአፍሪካ ወደ አሜሪካና እስያ በማገናኘቱ፣ ከተለያዩ አገሮች ምሥጋና እንደጎረፈለት ተናግረዋል፡፡ በተለይ የአሊባባ ኩባንያ ሊቀመንበር ጃክ ማ ለአፍሪካ አገሮች የለገሱዋቸው የሕክምና ዕቃዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለ51 አገሮች በማዳረሱ ከፍተኛ ምሥጋና እንዳገኘ ጠቁመዋል፡፡

አየር መንገዱ በረራዎቹን በሚያከናውንበት ወቅት ስለሚያደርጋቸው ጥንቃቄዎች ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ተወልደ የመንገደኞች ተርሚናል፣ የጥገና ሃንጋር፣ የቢሮ ሕንፃዎች በቀን እስከ ሦስት ጊዜ ፀረ ተዋስያን ኬሚካል እንደሚረጩ ገልጸዋል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅትና የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ባወጧቸው መሥፈርቶች መሠረት፣ ለመንገደኞችና ለድርጅቱ ሠራተኞች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ለበረራ ሠራተኞች (ለአብራሪዎችና የበረራ አስተናጋጆች) በተመሰከረላቸው የጤና ባለሙያዎች መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ማብራሪያ እንደሚሰጥ፣ የፊት ጭምብልና ጓንት በበረራና በምድር ላይ ላሉ ሠራተኞች እንደሚታደል ገልጸዋል፡፡

የበረራ አስተናጋጆች የፊት ጭምብልና የእጅ ጓንት እንዳያደርጉ እንደሚከለከሉ የሚገልጹ መረጃዎች እንደወጡ የተጠየቁት አቶ ተወልደ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የፈጠራ ወሬ ነው፡፡ የበረራ አስተናጋጆቻችን የፊት ጭምብልና የእጅ ጓንት እንዲጠቀሙ መመርያችን ያስገድዳል፤›› ብለዋል፡፡

የደንበኞች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሚካኤል ያሬድ ከእያንዳንዱ በረራ በፊት ለአብራሪዎች በበረራ መግለጫ የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች ማብራሪያ እንደሚሰጥ፣ ለበረራ አስተናጋጆች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መከናወኑን፣ በእያንዳንዱ በረራ 100 ያህል የፊት ጭምብልና የእጅ ጓንት እንደሚጫን ተናግረዋል፡፡ ኮሮና ከመምጣቱም በፊት በአውሮፕላን ውስጥ የሚፈጠረው ስለማይታወቅ የእጅ ጓንት ይቀመጥ እንደነበር አቶ ሚካኤል አክለዋል፡፡

ለመንገደኞችና ለአውሮፕላኑ ሠራተኞች ከፍተኛ ጥንቃቄ ቢደረግም፣ ሦስት የበረራ አስተናጋጆች በኮሮና በሽታ መያዛቸው ተገልጿል፡፡ ‹‹ሦስት የበረራ አስተናጋጆች በተደረገላቸው ምርመራ ፖዘቲቭ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡ በየቀኑ ሁኔታቸውን እንከታተላለን፣ እናነጋግራቸዋለን፣ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፤›› ብለዋል፡፡

የበረራ ሠራተኞች በየትኛውም አገር ለይቶ ማቆያ እንደማይገቡ የገለጹት አቶ ተወልደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚበርባቸው አሜሪካ፣ አውሮፓና እስያ የበረራ ሠራተኞች ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ እንደማይገደዱ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ ዓለም አቀፍ አሠራር ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ ወደ ኢትዮጵያም ሲመጡ ለይቶ ማቆያ እንደማይገቡ፣ ነገር ግን ጥርጣሬ ካደረባቸው አየር መንገዱ በቅጥር ግቢው ባዘጋጀው ለይቶ ማቆያ እንደሚገቡ አስረድተዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር አባል አገሮች የበረራ ሠራተኞችን በለይቶ ማቆያ እንዳያስገቡ በየጊዜው በሚያወጣው መግለጫዎች በመወትወት ላይ ነው፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው ቀውስ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ግዙፍ አየር መንገዶች የመንግሥታትን ድጋፍ እየጠየቁ ነው፡፡ አሜሪካ ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃት ከመደበችው ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ገንዘብ 58 ቢሊዮን ለአየር መንገዶች፣ 60 ቢሊዮን ዶላር ለቦይንግ ኩባንያ ልትሰጥ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ የአውሮፓና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች አየር መንገዶቻቸውን በመታደግ ላይ ናቸው፡፡

‹‹አልኢታሊያ በዚህ ሳምንት 540 ሚሊዮን ዶላር የመንግሥት ድጋፍ አግኝቷል፡፡ ኤምሬትስና ኳታር አየር መንገዶችም መጠኑ አይገለጽ እንጂ የመንግሥት ድጋፍ እያገኙ ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ የገጠመው ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ አንገብጋቢ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ያሉበት በመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከመንግሥት ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ እንዳልጠየቀ አረጋግጠዋል፡፡

‹‹ወጪያችንን በመቀነስ ማኔጅመንቱና ሠራተኛው ተባብሮ ጠንክሮ ሳምንቱን በሙሉ በእልህ በመሥራት፣ ከመንግሥት ዕርዳታ ላለመጠየቅ እየታገልን ነው፡፡ ብዙ ችግሮችን ያለፈ የ73 ዓመት ልምድ ያለው አየር መንገድ በመሆኑ፣ ይህንንም ችግር እንደምንሻገረው እርግጠኛ ነኝ፤›› ብለዋል፡፡ የሠራተኞችን ቅነሳ በተመለከተ ድርጅቱ የተጋረጡበትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ሠራተኞቹን ይዞ ለመቀጠል እንዳቀደ ተናግረዋል፡፡

‹‹አየር መንገዱ ሠራተኞች ቀንሷል የሚል የተሳሳተ መረጃ በመውጣት ላይ ነው፤›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ ማኔጅመንቱ ሠራተኛ የመቀነስ ዕቅድ እንደሌለው ገልጸው ሥራው በመቀዛቀዙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቋሚና ኮንትራት ሠራተኞች ከእነ ደመወዛቸው ዕረፍት እንዲወጡ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ይህ በሥራ ቦታና በሠራተኞች ሰርቪስ ውስጥ ማኅበራዊ ፈቀቅታን ለመተግበር እንዲረዳ በማሰብ ጭምር ነው ዕርምጃው የተወሰደው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ተወልደ የተቀነሱ የአየር መንገዱ ሠራተኞች እንደሌሉ የገለጹ ቢሆንም፣ በጡረታ ተገልለው በኮንትራት ሲሠሩ የነበሩ ጊዜያዊ ሠራተኞች ቤታቸው እንዲያርፉ መደረጉን አልሸሸጉም፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዴሚ በራሳቸው ወጪ በበረራ አስተናጋጅነት ሠልጥነው በሥራ ላይ ልምምድ ላይ የነበሩ 596 የበረራ አስተናጋጆች ፈቃድ እንዲወጡ መደረጉን አረጋግጠዋል፡፡

‹‹የ2019 ፈቃዳቸውን ወስደዋል፡፡ የመጀመርያው ባች ፈቃዳቸውን የሚጨርሱት ኤፕሪል 22 ነው፡፡ ሲጨርሱ የ2020 ፈቃድ እንሰጣቸዋለን ወይም ያለ ክፍያ ዕረፍት ይወጣሉ፡፡ ይህ ገና አልተወሰነም፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳሚ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ተሊላ ደሬሳ 58 ዓመታት ያስቆጠረው ማኅበሩ በርካታ ሥራዎች ማከናወኑን ገልጸው፣ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት ተከትሎ በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከማኅበራዊ ፈቀቅታ፣ ከእጅ መታጠብና ከሳኒታይዘር አጠቃቀም ጀምሮ ሠራተኛው ሊያደርጋቸው ስለሚገባው ጥንቃቄ በመቀስቀስ ከማኔጅመንቱ ጋር ተባብሮ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ተሊላ፣ ማኅበሩ ለሠራተኞች ድርጅቱ ከቀረበው የፊት ጭምብልና ሳኒታይዘር በተጨማሪ ለቤተሰቦቻቸው እየሸጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከበሽታው መከሰት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም ማኅበሩ 15 ሚሊዮን ብር ብድር ከወለድ ነፃ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ የሠራተኞችን ዕረፍት መውጣት በተመለከተ ማኔጅመንቱ ከማኅበሩ ጋር በመመካከር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ አየር መንገዱ ያቋቋመው የኮሮና ወረርሽኝ ግብረ ኃይል አባል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የሠራተኛ ማኅበር የሚቋቋመው የሠራተኛውን መብት፣ ጥቅምና የኢንዱስትሪ ሰላም ለማስከበር ነው፡፡ ችግር ካለ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃለን፡፡ ነገር ግን አሁን የጥቅም ጥያቄ የምናቀርብበት ወቅት አይደለም፡፡ የሠራተኛው ህልውና የሚረጋገጠው መጀመርያ አየር መንገዱ ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ጠንክረን ከማኔጅመንቱ ጋር ተባብረን ሠርተን እንዴት ይህን ክፉ ጊዜ እናሻግረው ብለን እየታገልን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሠረታዊ ሠራተኛ ማኅበር ሠራተኞች ያላግባብ እንደተቀነሱ ገልጾ፣ ከፍተኛ ደመወዝ የሚያገኙ የውጭ ዜጎች የሆኑ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ለምን አይቀነሱም የሚል ጥያቄ አንስቷል፡፡

ስለጉዳዩ የተጠየቁት አቶ ተወልደ የዲሲፒሊን ዕርምጃ የተወሰባቸው ጥቂት ሠራተኞች መኖራቸውን፣ የእነሱ ጉዳይ ከኮሮና ቀውስ ጋር እንደማይገናኝ ተናግረዋል፡፡  የውጭ ዜጎች የሆኑ የአየር መንገዱን ሠራተኞች አስመልክቶ፣ ኩባንያው የውጭ ዜጎች ባለሙያዎች የቀጠረው ሙያቸው ተፈልጎ  እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይህ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ አየር መንገዱ ነው፡፡ ጃፓን እንበራለን፣ ጃፓን ውስጥ ጃፓናውያን ሠራተኞች አሉን፡፡ ቻይና እንበራለን፣ ቻይናውያን ሠራተኞች አሉን፡፡ በየጣቢያው የሚሠሩ የአገሩ ዜጎች አሉን፡፡ የውጭ ዜጎች አብራሪዎች አሉን፡፡ ምዕራብ አፍሪካ አገሮች በብዛት ስለምንበር ምዕራብ አፍሪካውያን የበረራ አስተናጋጆች አሉን፡፡ እንግሊዝኛ የማይናገሩ ደንበኞቻችን በቋንቋቸው እንዲስተናገዱ ለማድረግ  የውጭ ዜግነት ያላቸው የበረራ አስተናጋጆች ይቀጠራሉ፡፡ አፍሪካዊ አየር መንገድ ነው እያልን አፍሪካውያንን አንይ የምንል ከሆነ ይህ አብሮ አይሄድም፡፡ ሙያቸውን ፈልገን ከቀጠርናቸው ለምንድነው የምናባርራቸው?›› ያሉት አቶ ተወልደ፣ አየር መንገዱ አሁን ወደ ቅነሳ እንደማይገባ ወደፊት በሁኔታዎች አስገዳጅነት ወደ ቅነሳ ከገባ ግን ቅነሳው ዜግነት መሠረት አድርጎ እንደማይከናወን አስረድተዋል፡፡

አየር መንገዱ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያህል ለአውሮፕላን ግዥና ለመሠረተ ልማት ግንባታዎች መበደሩን ጠቅሰው፣ በተገቢው መንገድ ብድሩን በመክፈል ላይ እንደሆነ፣ እስካሁን የብድር ማራዘሚያ ጥያቄ እንዳላቀረበ፣ ነገር ግን በኪራይ የመጡ አውሮፕላኖች ክፍያ ለተወሰነ ጊዜ እንዲተላለፍ አከራይ ኩባንያዎችን መጠየቁን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች