ኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚደረገው ድጋፍና ዕገዛ እንደቀጠለ ነው፡፡
ስፖርት ኮሚሽን፣ መንግሥት ያቀረበውን የድጋፍ ማሰባሰብ ጥሪ በመቀበል አገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራትና የአትሌቶች ማኅበርን በማስተባበር ያሰባሰበውን ሦስት ሚሊዮን ብር መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ለብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመገኘት አስረክቧል፡፡
የገንዘብ ድጋፉን ለብሔራዊ ድጋፍ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ምስጋናው አረጋ ያስረከቡት የስፖርት ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ቀደም ሲል ሌሎችም የስፖርት ማኅበራትና በተለይም ለአዲስ አበባ ስታዲየም ድምቀት ሆነው ለዓመታት የሚታወቁት የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ያሰባሰቡትን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማበርከታቸው ታውቋል፡፡
የክለቦቹ ደጋፊዎች ድጋፍ ያደረጉት በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠብቁ የሚረዳ የተለያዩ አልባሳትን የሚያካትት መሆኑ ታውቋል፡፡ በተጨማሪም በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ከተጨዋችነት እስከ አሠልጣኝነት እንዲሁም ካለፈው ዓመት ጀምሮ የባህር ዳር እግር ኳስ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ሆኖ እያገለገለ የሚገኘው ፋሲል ተካልኝና ኢንተርናሽናል አልቢትር ቴዎድሮስ ምትኩ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የሚያስችሉ ድጋፎችን ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
ከክልል ክለቦችና አመራሮች የመቐለ 70 እንደርታ ክለብና አባላት ግማሽ ሚሊዮን ብር፣ የድሬዳዋ እግር ኳስ ክለብ ተጨዋቾችና አመራሮች እንዲሁም የሐዋሳ ከተማ እግር ኳስ ክለብና አመራሮች በተመሳሳይ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየበኩላቸው የገንዘብና የአልባሳት ድጋፍ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
በግለሰብ ደረጃ የዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም መብርሃቱና የሉሲዎቹ ዋና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው፣ የአሠልጣኞች ማኅበርና የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማኅበር የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸው ታውቋል፡፡